18/04/2024
ጆ ባይደን በቻይና የብረት ምርቶች ላይ የሚጣለው ቀረጥ ከፍ እንዲል ጠየቁ
ሚያዝያ 10፣ 2016 (አራዳ ኤፍ ኤም) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ወደ አሜሪካ በሚገቡ የቻይና የተወሰኑ ምርቶች ላይ የሚጣለው ቀረጥ ከፍ እንዲል ጥሪ አቀረቡ።
ባይደን በቻይና የተወሰኑ የብረት እና አሉሚኒየም ምርቶች ላይ የሚጣለው ቀረጥ በሦስት እጥፍ ከፍ እንዲል ጥሪ አቅርበዋል።
ባይደን ቻይና የብረትና አሉሚኒየም ምርቶቿን ወደ አሜሪካ ገበያ በርካሽ ዋጋ በገፍ ታስገባለች የሚል እምነት አላቸው።
ይህ መሆኑ ደግሞ የዋሺንግተንን አምራች ኩባንያዎች ገበያና የሥራ እድል ፈጠራን በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳ ነው በሚል በተደጋጋሚ ትችት ሲያቀርቡ ይስተዋላል።
ለዚህም አስፈላጊው ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል በሚል የቀረጥ ጭማሪ ምክረ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።
ኋይት ሃውስጥ በፕሬዚዳንት ባይደን የቀረበው ሃሳብ የአሜሪካን ገበያ እና የሥራ እድል ፈጠራ ከአላስፈላጊ የገበያ ውድድር ለመጠበቅ ያለመ መሆኑን ገልጿል።
በፔንሲልቫኒያ ለብረት ኢንዱስትሪ ማህበር ሰራተኞች ባደረጉት ንግግርም፥ ቻይና ምርቶቿን የምታቀርብበት ዋጋ “ባልተገባ መልኩ በጣም ዝቅተኛ” ነው ሲሉ ኮንነዋል።
መንግስታቸው ትርፍን ሳያስብ የብረት ኢንዱስትሪውን ቢደጉምም ቻይና ተገቢ ባልሆነ የገበያ ፉክክር ጉዳት እያስከተለች ነው ሲሉም ኮንነዋል።
በገበያው “እነርሱ መርህን አያከብሩም” ያሉት ባይደን “ጥፋቱንም እዚሁ በአሜሪካ እያየነው ነው” ሰሉ በምሬት ገልጸዋል።
በፈረንጆቹ 2000 መጀመሪያ ላይም የቻይና የብረት ምርቶች ወደ አሜሪካ በብዛት መግባታቸውን ተከትሎ በኢንዱስትሪው በመቶ ሺህዎች ሥራ መፍታታቸውን አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ይህ በድጋሚ እንዲሆን አንፈቅድም ብለዋል ባይደን በንግግራቸው።
ቻይና በበኩሏ በአሜሪካ የሚቀርብባትን ውንጀላ በተደጋጋሚ ስታስተባብል ቆይታለች።
በዋሺንግተን የቻይና ኤምባሲም በባይደን የቀረበውን ምክር ሃሳብ ተቃውሞታል።
የኤምባሲው ቃል አቀባይ ሊዩ ፔንግዩ ይህን መሰሉ እርምጃ የሃገራቱን ግንኙነት ብሎም ዓለም አቀፉን ኢኮኖሚ የሚጎዳ ነው በሚል ሃሳቡን ተቃውመዋል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም መሰል ውጥረቶች የዓለም ኢኮኖሚን የሚጎዳና የዋጋ ግሽበትን ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ የሚወስድ አደገኛ አካሄድ ነው ሲል አስጠንቅቋል።
አራዳ ኤፍኤም 95.1 ፤ ውለው የሚያመሹበት!
Telegram:https://t.me/Arada_Fm
Website:https://aradafm.com/
Facebook: https://www.facebook.com/aradafm95.1/
Youtube:https://www.youtube.com/.1
Tiktok:https://www.tiktok.com/.1