23/08/2023
በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመታት ጡረታ ያልተከፈላቸው አረጋውያን በምግብ እጥረት እየሞቱ መሆኑ ተሰማ
በትግራይ ክልል ከሁለት ዓመታት በላይ የጡረታ ደመወዝ ያልተከፈላቸው አረጋውያን በምግብ እጥረት ለሕልፈተ ሕይወት እየተዳረጉ መሆኑን የክልሉ አረጋውያን ማኅበር ገልጿል፡፡
ከዓመታት በፊት ጡረታ የወጡ አረጋውያን ብዛት 75 ሺሕ ሲሆን፤ አሁን ላይ ቁጥራቸው ወደ 100 ሺሕ የሚጠጉ መሆናቸውን የክልሉ አረጋውያን ማኅበር ያሳወቀ ሲሆን፤ ከሁለት ዓመታት በላይ የጡረታ ደመወዝ ያልተከፈላቸው አረጋውያንም በምግብ እጥረት እየሞቱ መሆኑን የማኅበሩ ሊቀመንብር አቶ አርዓያ ገሠሠ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የሰባት ወር የሚሆን ተብሎ የጡረታ ደመወዝ ቢለቀቅላቸውም፤ የተወሰኑ ሰዎች ሲያገኙ አብዛኛዎቹ ገና በመጠባበቅ ላይ እንዳሉም ሊቀመንበሩ አክለዋል፡፡
አቶ አርዓያ ለሁለት ዓመታት የጡረታ ደመወዝ አልተከፈላቸውም ከተባሉት አረጋውያን መካከል በምግብ እጥረት የሞቱት ምን ያህል እንደሆኑ አለመታወቁን ጠቅሰው፤ የፌዴራሉ መንግሥት ይህን ችግር እንዲቀርፍ ጠይቀዋል፡፡
ከጥር ወር 2015 ዓ.ም. ወዲህ በክልሉ ከ1 ሺህ 3 መቶ በላይ ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን፣ የክልሉ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን፣ ለፌዴራልና ለዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድርጅቶች ዓርብ ሐምሌ 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ባቀረበው ሪፖርት አስታውቆ ነበር፡፡
በስርቆት ምክንያት የዕርዳታ ድጋፍ ካቆመ ጊዜ ወዲህ ግን ሕይወታቸው በጥር ወር አልፏል ከተባለው ቁጥር በላይ ከፍ ማለቱን፣ የክልሉ አደጋ ሥጋት ኮሚሽን ለተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ይፋ አድርጎ ነበር፡፡
ኮሚሽኑ የሟቾቹን ቁጥር ይፋ ያደረገው፣ በማዕከላዊ ዞን 22 ወረዳዎች፣ በደቡብ ትግራይ ዞን በስድስት ወረዳዎች፣ እንዲሁም በምዕራብ ትግራይ መሆኑም ተነግሯል፡