10/07/2023
ለሃገረ መንግስቱ፣ ለኦሮሚያ ክልል፣ ለደቡብ ክልል፣ ለመላው ጉራጌና ሶዶ ክስታኔ ህዝብ ተወካዮች!
አርሶ-አደሩ...እርፍ ይጨብጥ መድፍ?
***
ሃገር የሰው ውጤት ነው። ቤተሰብ፤ ማህበረሰብ...እያለ ''ሃገር'' የሚባለውን ትልቅ ስዕል የሚሰጠን ሰው ነው።
ሰው ደግሞ ሁሉም እኩል ነው። በሌላ ነገር ቢበላለጥ እንኳ ''ነፍስ'' በምትባል ፍፁም ስስ ነገር እኩል ነው! ነገርዬው ይህ ሁሉ ማብራሪያ የሚፈልግ ባይሆንም ለመዘርዘር ግን እየተገደድን ነው።
''ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ሞት እጅግ እየተባባሰ ነው'' ሲባል መንግሥትም የሚያስተባብልበት ሞራል ላይ እንዳልሆነ እራሱ ያውቀዋል ባይ ነን። መንግሥት ግን አሁንም ''መገዳደል ምንም ጥቅም የለውም'' የሚል ምንም ጥያቄ የማያሻው ''የሞኝ ንግግር'' ላይ ነው። ገዳዩን እንዲያስቆሙለት፤ ሞቱን እንዲያስቀሩለት እንጂ የሚያውቀውን ነገር እንዲደግሙለት የሚፈልግ ማንም የለም።
በህዝብ የተመረጠ መንግሥት ሌላው ነገር ቢቀር ሰላም የማስፈን ግዴታ አለበት። ከማንም ጋር ተስማምቶም ይሁን ተጣልቶ! ታዲያ እዚህ ጋ ''መች?'' መባሉ አይቀርም። ''አሁን እና አሁን ብቻ'' ነው መልሱ!
አንድም ሰው አላማው በግልፅ ያልታወቀ የታጠቀ ቡድን ጥቃት ሰለባ ሳይሆን! ''ሰውም ነፍስም እኩል ነው'' ብለን የለ? አሁንስ? የብዙ ሰው ህይወት አልፏል። በርካቶች ተደብድበው ሀብት ንብረታቸውን ተቀምተዋል። የቀሩትም ስጋት በወለደው ቆፈን ላይ ናቸው! ይህ እጅግ አደገኛ እና ሃገርን የባሰ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል አደጋ ያዘለ በእንጭጩ ያልተቀጨ ችግር ነው።
ገዳዩን አካል ''ማንም አሉት ማን'' ዋናው ነገር ሞትና እንግልትን ማስቆሙ ላይ ነው። የመንግሥት መንግሥትነት ያለውም እዚህ ላይ ነው። ችግሩ በመላ ሃገሪቱ የተንሰራፋ ቢሆኖም ከቅርብ ወራት ወዲህ ግን በ #ጉራጌ በተለይም በ ህዝብ ላይ የተደቀነው አደጋ የህልውና ሆኗል! ችግሩ እንደተጠቀሰው የሃገር ቢሆንም ሞት ግን የሚጀምረው ከሃገር ሳይሆን ከግለሰብ፣ ከቤት፣ ከቤተሰብ፣ ከሰፈር-መንደርና አካባቢ እያለ ነው።
ስለሆነም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስቶ ባለባችሁ የበዛ ሃላፊነት ልክ መንቀሳቀስ ሲገባችሁ የበዛ ዝምታን የመረጣችሁ የህዝብ ተወካዮች #ህጋዊ እስከመምሰል የደረሰውን ግድያ አስቁሙልን! ምድራዊው ሀይል ያለው በናንተና እናንተ በምትመሩት ስርአት እጅ ነው። ህዝብ ምናልባት ለጊዜው መረጃ ሰጪ ቢሆን ነው። መረጃ ደግሞ የላችሁም አንልም።
አርሶ-አደሩ ለዛውም በዚህ ወርቃማ የአዝመራ ጊዜው ሲሞት፣ ሲገረፍና ሲዘረፍ ማየት እንደምን ዝምታን ያስመጣል? የሃገሬ ሰው ''ቀልደኛ ገበሬ በሰኔ ይሞታል'' ያለው ቢቻለው ተፈጥሯዊውን ሞት ጭምር መሞት የለበትም ለማለት ነው። ሲቀጥል ከእጅ ወደአፍ ህይወት የሚኖር አርሶ-አደር ስለምን ይገደላል? ስለምንስ ይዘረፋል? በሃገር ኢኮኖሚ ላይ የተቀጣጠለ እሳት አጥፊ እንጂ የፖለቲካ ብልሽት ማብረጃ ነው እንዴ አርሶ-አደር? በቀዬው እንዴት ይታፈናል? እንዴት በልጆቹ ፊት ይገረፋል? ከብቶቹን አሰማርቶ ወጥቶ የሚገባበት ታዛው ጦርሜዳ ነው እንዴ? እና አርሶ-አደሩን መሳሪያ በገፍ ከታጠቀ ገዳይ እና ከማንም የ የሚታደገው ማነው? በዚህ አስቸጋሪ ወቅትስ እንዴት ወጥቶ ይግባ? የሰአት እላፊ ገደቡ በርግጥስ አርሶ-አደሩን ተጠቃሚ አድርጓል ወይስ...? በጥቅሉ አርሶ-አደሩ እርፍ ይጨብጥ መድፍ?
እናም ተጠሪ እና ተወካዮቻችን ሆይ እባካችሁ አካባቢውን መልከት አድርጉት? የፌዴራል የፀጥታ ሀይላት ልዩ ትኩረት በሚያሻቸው የገጠር ቀበሌ ማዕከላትና አቅራቢያ ከተሞች እንዲሰፍሩ ቢደረጉ። ሌላው እዛው አርሶ-አደር ጉያ ተወሽቀው መረጃ በማቀባበልና በማቀሳሰር ከመቺው በላይ አስመቺ #ሆድ-አደሮችን እንኳ የዘረጉትን የሴራ ኔትወርክ በመበጠስ አርሶ-አደሩ ''አዎ መንግሥት አለ'' እንዲል ምክንያት ሁኑት። ታጣቂ ቡድኑን በተመሳሳይ የትጥቅ አፀፋም ሆነ በሌላ ሃገር በቀል የሰላም መንገድ በማነጋገር ሂደቱን መምራት ያለበትም እራሱ መንግስት ነው። ከነዚህ ሁለቱ መፍትሔዎች አንዱም ባለመደረጉ ግን በሚስኪን አርሶ-አደሮች ላይ የሚደርሰው ግፍ አሁንም ሞልቶ እየፈሰሰ ነው።
ከዞን እስከ ወረዳ እና ቀበሌ ባለው የመንግሥት መዋቅር እጃቸው በንፁሃን ገንዘብና ደም የቆሸሸ አመራር አሉ። እየሆነ ያለው ነገር ''መንግሥትም የጥቃቱ ደጋፊ ወይም አካል ነው'' የሚያስብል ነው። ጨለም ሲል በየአቅጣጫው የሚፈነዳው ግጭት አርሶ-አደሮች የሚቋቋሙት አይደለም። አንዳንዶቹ አካባቢዎች ላይ የአርሶ-አደሩን በግና ፍየል እያሳረዱ በግድ አብሮ እስከመኖር ደርሷል።
ሃገሪቱ በግልፅ ታውቀው የነበረው የሰላም ችግር የፌደራሉ መንግሥት ገብቶበት የነበረው ጦርነት ነው። እሱ ይሻላል። መንግሥትም ሆነ የህዝብ ተወካዮች አሁን በአርሶ-አደሩ ላይ ስለሚፈፀመው ኢ-መደበኛ ጥቃት ምንም ሲሉ እየተሰሙ አይደለም። እንደድሮው ልዩ ሀይል እንኳ በሌለበት ክልልና ዞን ይህንን የሚያክል አውዳሚ ሀይል በአካባቢ ፖሊስና በገበሬ ትከሻ መቋቋም የማይታሰብ ነው።
አርሶ-አደር እኮ ''ሰለጠንኩ'' ያለው የከተሜው ነዋሪ፣ አሻጥረኛ ነጋዴና ፖለቲከኞች የፈጠሩትን የኑሮ ውድነት ያለጥፋቱ እየተጋፈጠ የሚገኝ #አፈር-ገፊ ነው። ነገር ግን የአፈር ማዳበሪያ እንኳ በቅጡ እንዳይደርሰው ተደርጎ የሚያርስበትን በሬ ከቀንበሩ ፈትቶ፤ የሚታለብ ላሙን ከጥጃው ነጥሎ እስከመሸጥ በደረሰ ዘግናኝ ዋጋ ገበያ ወጥቶ ለመግዛት ሲገደድ ዝም ብሎ ማየት እንዴት ያለ ጭካኔ ነው? እሺ ይሁን፤ እሱን ገዝቶ ወደቀየው ሲገባ እንዴት ይገደላል? ቢያንስ በሰብአዊነት እንተዛዘን እንጂ!