03/04/2024
ይኸውልህ ወዳጄ ልቤ፣ ከተማ የሚታደሰው እንዲህ ነው
Zekeriya Mohammed
(መጀመሪያ በFeb. 26, 2021 የተለጠፈ።)
(ፒያሳ ግድም እንዲህ ታድሰው የከተማው ውበትና የቱሪስት መስህብ ሊኾኑ ስንት የድንጋይና የጣውላ ሕንጻዎች ያለ ርኅራኄ ተደርምሰው ይኾን?!😢)
የከተማይቱን ቅርስና ውበት ሳታጠፋ፣ ትናንትን ከዛሬ እና ከመጪው ዘመን ጋር የሚያገናኙ ድልድዮችን ሳታፈርስ፣ ሕዝብ ከመኖሪያ ቀዬው ጋር ያዳበረውን ስነ ልቡናዊ ቁርኝት ሳትንድ፣ የስነ ሕንጻ ቅርስ አሻራዎችን ሳታበላሽ፣ እንዲህ ከተማን ብታድስ ትውልዶች ያከብሩሃል።
ለዚህም ነው በአዲስ አበባ፣ አራዳ ጊወርጊስ ቤተስኪያን አቅራቢያ የሚገኘው የቢትወድድ ኃ/ጊዮርጊስ ወ/ሚካኤል ሕንፃ፣ "ጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል" ተሰኝቶ ኅያውነቱ ሊቀጥል መሆኑን ብንሰማ ጊዜ ደስ ያለን።
ከ117 ዓመት በፊት እንደተገነባ የሚነገረውና የመጀመሪያው ማዘጋጃ ቤት፣ በጣሊያን ወረራ ዋዜማ በኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገር ፍቅር ማኅበር የሕዝብ ማነቃቂያ ዲስኩር ይካሄድበት የነበረና ሌሎችም አገልግሎቶች ሲሰጡበት የቆየው ይህ ውብ ሕንፃ፣ እርጅና ተጫጭኖት ሊፈርስ መቃረቡ በግልጥ ይታይ ነበር።
ይህ ታሪካዊ ሕንጻ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሆኖ ሲያገለግል፣ ስንት አሠርት ዓመታት ተቆጥረዋል። አሁን ግን ታድሶ፣ ገጽታውን ለሚመጥን አገልግሎት እንዲውል ተወስኗል።
በዕቴጌ ጣይቱ ብጡል ስም የተሰየመ የባህል እና የትምህርት ማዕከል ሆኖ ያገለግል ዘንድ፣ ለዕድሳቱ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል ብለዋል የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ አንጋፋዋ አርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆ።
አርቲስት ዓለምፀሐይ፣ መጋቢት 4 ቀን 2013 የትውውቅና የገቢ ማሰባሰብ ሥራ በታሪካዊው ግቢ ውስጥ ስለማከናውን፣ ጉዳዩን ጉዳዬ ያላችሁ ወገኖች መጥታችሁ በጨረታውም፣ በገንዘብ ድጋፉም፣ በትውውቁም ተሳተፉልኝ ብላለች።
ድጋፋችሁ ካልተለየኝ፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ሕንፃውን አድሼ ለትውልድ የሚተርፉ ሥራዎችን ለመሥራት አስቤያለሁና እገዛችሁ አይለየኝም ብላለች። አርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆ የመሠረተችው ጣይቱ የባህል ማዕከል፣ ለሀያ ዓመታት የተለያዩ የጥበብ ሥራዎችን በሀገረ አሜሪካ ሲያሰናዳ የቆየ ተቋም ነው።