13/04/2023
የረመዳን 20ኛ ቀን ዋነኛ ትዉስታ ‹‹ፈትህ መካ›› የተባለዉ ታሪካዊ ድል ነዉ፡፡ በስምንተኛዉ ዓመተ ሂጅራ (ጃንዋሪ/630) በነብያችን (ሶ.ዐ.ወ) የተመራዉ የሙስሊሞች ሀይል የመካ ከተማን የተቆጣጠረበት ዕለት ሲሆን በዐረብያ ምድር የጣኦት አምልኮ ዋነኛ ምሽግ ተደርምሶ እስልምና በቀጠናዉ የበላይነቱን ያረጋገጠበት ክስተት ነዉ፡፡ በዘመቻዉ 10 ሺ ያህል ሙስሊሞች ተሳትፈዋል፡፡ መካን ለመቆጣጠር ባደረጉት በዚህ እንቅስቃሴ ከተቃራኒ ወገን ይህ ነዉ የሚባል ተቃዉሞ አልገጠማቸዉም፡፡ የዘመቻዉ ምክንያት ቁረይሾች ‹‹ሁደይቢያ›› የተሰኘዉን በጦርነት ያለመፈላለግ ዉል ማፍረሳቸዉ ነበር፡፡ ድሉን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ጣኦታዉያን እስልምናን ተቀላቅለዋል፡፡ ሀይማኖቱ በፍጥነት ተስፋፍቷል፡፡ ከዐረብያ ምድር ዉጭ የሚያደርገዉን ግስጋሴ ፍጥነቱን ጨምሮለታል፡፡ በዕለቱ ከታዩ ትኩረት ሳቢ ክስተቶች መሀል፡-
አሸናፊዉ የሙስሊሞች ሠራዊት ወደመካ የገባዉ እንደድል አድራጊ ሀይል እየፎከረና እየሸለለ ሳይሆን ልክ እንደተሸናፊ አንገቱን ደፍቶ፣እያለቀሰና አምላኩን እያመሰገነ በከፍተኛ ዲሲፕሊን ነበር፡፡ ይህ ድርጊቱ የሺዎችን መካዉያን ልብ ማረከ፡፡ ብዙም ሳይቆዩ ‹‹አፍዋጀን›› ወደአላህ ዲን ጎረፉ፡፡
‹‹ወለላዬ›› (ሶ.ዐ.ወ) ለዓመታት ያሳደዷቸዉን፣የወጓቸዉን፣የበደሏቸዉን የመካ ባላባቶች በሙሉ ይቅር በማለት አስደደናቂ የምህረት ጀብዱ ፈጸሙ፡፡ ‹‹ረህመተን ሊልዐለሚን›› የተሰኘዉ ዋነኛ ገጽታ ከነሙሉ ዉበቱና ግዝፈቱ ተገለጠ፡፡
ሰይድ ቢላል እብን ረባህ ከካዕባ አናት ላይ ወጥተዉ አዛን እንዲያሰሙ የተደረገበት ሁነት የሰብአዊ እኩልነትን ዕሴት ያጸና እጅግ ማራኪ ትእይንት ነበር፡፡ ሀበሻ የዚህ ትዕይንት ዋነኛ ባለቤት ሆና በታሪክ ተመዝግባለች፡፡ ያበሻ አካል መሆናችንን ለምንቀበልና በዚህም ለምንኮራ ሁሉ ክስተቱ ልባችንን በሀሴት የሚሞላ፣ በኢትዮጵያዊነት ኩራት የሚያንጎማልል ነዉ፡፡
ዉዳችን (ሶ.ዐ.ወ) ወደካዕባ በማምራት ከዉስጡ የነበሩ ጣኦታትን ሰባበሩ፡፡ በነብዩ ኢብራሂምና በልጃቸዉ በኢስማዔል ለ‹‹ተዉሂድ›› ዓላማ ዳግም የታነጸዉ ካዕባ ከጣኦታት ጉድፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጸዳ፡፡ የሰዉ ልጅ ከአምላክ የተቸረዉን ክብርና ማዕረግ ትቶ ለእንጨት፣ ለዲንጋና ለተፈጥሮ ክስተቶች ሲሰግድ የመባጀቱ ነገር ሲያስቡት የሚደንቅ ነዉ፡፡
‹‹ዘይኑል ዉጁድ›› (ሶ.ዐ.ወ) የዚህን ሀይማኖት መሠረታዊ ዕሴቶች ያሰመረ መሳጭ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
በዕለቱ በርካታ ታዋቂ ሰዎች የሰለሙ ቢሆንም ‹‹ያልቃሻዉ ዛሂዱ›› የሰይድ አቡበክር ሲዲቅ አባት አቡቁሀፋ መስለማቸዉ ለኔ የተለየ ስሜት ይሰጠኛል፡፡ ሰይድ አቡበክር በእጅጉ ሲጓጉለት የነበረ ጉዳይ ስለሆነ የርሳቸዉ ደስታ ከሰይዲ ደስታ ቀጥሎ ሊገመት የማይችል ዋጋ አለዉ፡፡
በአካልም ባይሆን በዕምነትና በስሜት የዚህ ድንቅ ትዕይንት አካልና የመልካም ዉጤቱም ተቋዳሽ መሆን፣ የተቀደሰ ሀይማኖቱን መሸለም መታደል ነዉ፡፡ ለኛ ለሀበሾች ደግሞ ከዚህ በተጓዳኝ ከካዕባ አናት ላይ የመዉጣት የኢትዮጵያዊነት ክብርና ሞገስ ስላጎናጸፈን ዕለቱ የተለየ ትርጉም አለዉ፡፡ ስለሀገራችን ያለንን አተያይ ከተሰጣት ክብርና ሞገስ አኳያ በመፈተሸ እንድናስተካክልም ዓመታዊ ማስታወሻ ነዉ፡፡ ሀበሻ ለሶሀቦች ስደት መመረጧ፣ በታላቁ ነብይ፡ ‹‹የዕዉነት ምድር›› መባሏ፣ ‹‹የጀነት ወንዝ›› የተሰኘዉ የአባይ (የጊዮን) መፍለቂያ መሆኗ፣በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ከኛ ጋር የሚገናኙ ከ20 በላይ የቁርአን አንቀጾችና ከ30 በላይ ሀዲሶች መነገራቸዉ ያጋጣሚ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡
እናማ የዚህ ሁሉ ታሪክ ቋትና ባለቤት ስለሆነችዉ ሀገራችን ሠላምና አንድነት እንትጋ፤ ለህልዉናዋ ስጋት የሆነንና የህዝቧን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥልን ማንኛዉም አካል በፅናት እንፋለም፤ ክብሯን የሚመጥን የመንግስት ሥርዓት ዕዉን እንዲሆን ያለመታከት እንታገል፡፡ ‹‹ፈትህ መካ››ን ዕዉን ያደረገ አምላክ ለሙስሊሙ ዓለም ዘመኑን የዋጀ ሌላ ‹‹ፈትህ›› እንዲለግስ፣ እንዲሁም በሀገራች የሚስተዋሉ ያልተገቡ ነገሮችን አስወግዶ፣ ጀርባዋን ያደቀቀውን የመከራ ሸክም አንስቶ፣አድማሷን የሸፈነዉን ጽልመት ገፎ ‹‹ሀገራዊ ፈትህ›› እንዲያጎናጽፋት ዱዐ እናድርግ፡፡