22/03/2024
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተፈጠረው ክስተት ባንኩ በሞባይል ሲስተሙ ላይ ባደረገው የማሻሻያ ስራ የተከሰተ እንጂ፤ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ሀገር የተሰነዘረ የሳይበር ጥቃት አለመሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ፡፡
===========================================
መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ያጋጠመው ችግር ከሲስተም ማሻሻያ ትግበራ ጋር የተያያዘ እንጂ የሳይበር ጥቃት አለመሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቀ። የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ በሰጡት መግለጫ ተቋሙ ባደረገው ምርመራ ባንኩ ለሚቃጡበት የሳይበር ጥቃቶች አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል አቅም እንዳለው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
ችግሩ የተፈጠረው ባንኩ የሲስተም ማሻሻያ በሚያደርግበት ወቅት፤ ቀደም ብሎ የተጫነው ኮር ባንኪንግ ሲስተም ጥቅም ላይ የዋለ የስሌት ሞጁል በመውሰድ በሞባይል ባንኪንግ ሲስተሙ ላይ በቀጥታ ለመተግበር በተደረገ ሙከራ መሆኑን ባደረግነው ምርምርና ትንተና ደርሰንበታል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሯ።
በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ባንኩ የሳይበር ጥቃት እንደደረሰበት የሚናፈሱ መረጃዎች ከእውነት የራቁ መሆናቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በሀገሪቱ የሳይበር ደህንነትን እና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በሳምንት ሰባት ቀናት ለ24 ሰዓት እየሰራ የሚገኝ ጠንካራ ተቋም መሆኑም ተገልጿል።