15/10/2023
15 October 2023
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ የምታደርገውን የምድር ላይ ጥቃት ከመጀመሯ በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን ከሰሜን ጋዛ እየሸሹ ይገኛሉ።
በሰሜን ጋዛ ያሉ ሰላማዊ ሰዎች በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከጥዋቱ አንድ ሰዓት እስከ አራት ሰዓት ድረስ ወጥተው ወደ ደቡባዊ ጋዛ ማምራት እንዳለባቸው የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አዲስ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ነዋሪዎች ከቤይት ሃኑን ወደ ክሃን ዩንስ የሚወስደውን መስመር ብቻ መጠቀም እንዳለባቸው ጠቅሶ በእነዚያ ሰዓታት ውስጥ መንገዱ ከኢላማ ውጭም እንደሚሆንም አስፍሯል።
እስራኤል በሰሜን ጋዛ ለሚኖሩ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች በ24 ሰዓታት ውስጥ ወደ ደቡባዊ ጋዛ እንዲሄዱ ማስጠንቀቂያ ሰጥታ የነበረ ሲሆን በዚህ ወቅትም ሁለት መንገዶችን መጠቀም አለባቸው ብላ ነበር።
በሰሜን ጋዛ ያሉ ሆስፒታሎችም አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ተነግሯቸዋል። የዓለም ጤና ድርጅት የእስራኤልን ውጡ ማስጠንቀቂያ በሆስፒታል ያሉ ህሙማንን አስገድዶ ማስወጣት "የሞት ፍርድ ነው" ሲል አውግዞታል