18/01/2023
እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! አደረሰን!- አቶ ዮሐንስ በየነ
የጥምቀት በዓል በማይዳሰስ ቅርስነት ከተመዘገቡ ድንቅ የኢትዮጵዊነት ማሳያ፣ውድ ሃብታችን፣ ድምቀታችንና የሀገራዊ ኩራት ምንጭ ከሆኑ በዓሎቻችን አንዱ ነው፡፡
ሁሉን ቻይ፤ ሁሉን አድራጊ፤ ሁሉን ፈጣሪና ሁሉን ወሳኝ የሆነው አምላክ በውኃ መካከል ተገኘ። በዮሐንስ እጅ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ። ይህም ለሰው ልጆች ትህትናን ለማስተማር ራሱን ዝቅ አድርጓል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ ከመጠመቁ በፊት የሰው ልጅ ውኃን የሚያውቀው በመዓትነቱና በዕንቅፋትነቱ ነበር። በኖኅ ዘመን የሰው ልጅ የጠፋው በውኃ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በማዕከለ ዮርዳኖስ ሲቆም ግን ለመዓት የነበረው ውኃ ለበረከት ሆነ። ይሄው ዛሬም በየዓመቱ ወደ ውኃ ወርደን የጥምቀት በዓልን እናከብራለን።
ክርስቶስ ከውልደቱ እስከ ጥምቀትና ስቅለቱ፣ ትንሳኤና እርገቱ ያለው ሂደት ተስፋውን ሲጠባበቁ ለነበሩ ሁሉ፥ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ውስጥ ክርስቶስ የፈጸማቸው ተግባራት፥ የአዳምን ዘር የመዳን ተስፋ ያለመለሙና ጠላት ዲያቢሎስን ያሸነፈበት በመሆናቸው ለሰዎች ልጆች ሁሉ ትልቅ ብስራት ናቸው፡፡ ታላቅ ደስታም አስገኝተዋል፡፡
የሥራ ባህላችንን በማሻሻል በሁሉም የልማት መስኮች ተሠማርተን ለማሸነፍ በቁጭት መስራትና መትጋት አለብን። የኋላቀርነት ቅርፊቶችን ከኋላችን ጥለን ድህነታችንን በየቀኑ የምናባብልና ስለድህነት ሠርክ የምናለቅስ ሳንሆን በተስፋና በእልህ ወደ ብልጽግና የምንገሰግስ መሆን ይገባል፡፡
በኢኮኖሚውም፣ በማህበራዊውም፣ በፖለቲካውም መስክ የበለጸገችና በሁሉም ረገድ ስልጡን ህዝብ የሚኖርባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ሁላችንም የወንድማማችነትን እሴት ተላብሰን ለአንድ ዓላማ መቆም አለብን፡፡
ከሚያለያዩን ጉዳዮች ይልቅ በጋራ ያለፍናቸው እና ወደፊትም የምናልፋቸው የአብሮነትና የወንድማማችነት መንገድ ለመከተል ጠባብ እይታችን በአድማስ ማስፋት ያስፈልጋል፡፡
እሳት ምግብ ለማብሰያም ለጥፋትም ይውላል። ወሳኙ ተጠቃሚው ሰው ነው። እሳትን ለጥቅም ለማዋል እሳቱን ወደ ውኃነት መቀየር አያስፈልግም፤ የእሳቱን አጠቃቀም መቀየር እንጂ።
በማህበራዊ ሚዲያ የምናሰራጫቸው መረጃዎች ከአሉባልታ ይልቅ ጀግንነታችንን፣ ልማታችንን፣ የሀገራችንን ሉአላዊነት፣ የህዝባችንን አንድነትና ብሩህ ተስፋችንን የሚያጎሉ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በአመጽና ጥላቻ ንግግር የሚመጣ ልማት ትላናትም፣ ዛሬም፣ ነገም አይኖርምና፡፡
እንደ ጥምቀት ያሉ ታላላቅ ክብረ በዓላትን እንደ አንድነታችን ማጠናከሪያ መሣሪያ ይዘን በአጭርና በረዥም ጊዜ የያዝነውን የብልፅግና ጉዟችንን ለማደናቀፍ የሚሯሯጡ ሁሉንም ጥሰን በማለፍ የያዝነውን ራእይ ለማሳካት በአንድነት እንድንሠራ በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች የክልል አደረጃጀት ህዝበ ውሳኔ ጥር 29 በሚካሄዳው ሁሉም ህብረተሰብ ክፍሎች ድምጽ በመስጠት የዜግነት ግዴታችሁን እንዲትወጡ እያሳሰብኩ የድምጽ አሰጣጡ ሂደት ፍጽም ሠላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታችሁን በተግባር እንዲታረጋግጡ አሳስባለሁ፡፡
ጥምቀት ልዩ ገፅታን የሚያላብስ ከአይን ማረፍያ በአሎቻችን አንዱ በመሆኑ በዓሉ በድምቀት እንዲከበር፣ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ አስተዋዩ፣ ጨዋዉና ሰላም ወዳዱ የዞናችን ህዝብ ወትሮም እንደምናደርገው ሁሉ በትብብርና በአብሮነት አካባቢያችንን በንቃት በመጠበቅ፤ ከፀጥታ ሃይሎቻችን ጋር በትብብር በመስራት፤ እንድናሳልፍ ዘንድ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ!!
ጥምቀቱን ስናከብር ቅንነትን ተላብሰን፣ በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች የተጎዱ ወገኖቻችንን በቸርነት ዓይናችን እያየን፣ የተቸገሩትን በድጋፍ እጃችን እየጎበኘን መሆን እንደሚገባ ላሳስባችሁ እወዳለሁ፡፡
በድጋሚ፣ መልካም የከተራና የጥምቀት በዓል እንዲሆን እመኛለሁ።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ዮሐንስ በየነ
የወላይታ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ