Deacon Gebrê Medhn

Deacon Gebrê Medhn Christian affairs

+ ተራ የማይደርሰው ተጠማቂ + ✍️Henok Haile 🙏🏽💒"ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ...
12/03/2023

+ ተራ የማይደርሰው ተጠማቂ +
✍️Henok Haile 🙏🏽💒
"ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ፦ ልትድን ትወዳለህን? አለው ሰውዬውም፦ ጌታ ሆይ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል፡ ብሎ መለሰለት" ዮሐ.5:5-7

ይህንን ጥያቄና መልስ ሳይ በሽተኛውን ማናገር ያምረኝና እንዲህ በል ይለኛል :-

አንተ በሽተኛ ግድ የለህም የተጠየቅከውን መልስ:: እመነኝ ጠያቂህ ተራ ጠያቂ አይደለም::
የሚጠይቅህ ሲያደርቁህ እንደኖሩት አሰልቺ ጠያቂዎች አይደለም:: ጥያቄውም የሌሎችን ሰዎች ዓይነት ጥያቄ አይደለም:: ከፊትህ የቆመው የመጠመቂያውን ውኃ ብቻ ሳይሆን በዓለም የሞላውን ውኃ የፈጠረ ነው::

"ወደ መጠመቂያው የሚያኖረኝ ሰው የለኝም" አልክን? የተጠየቅከውን መልስ እንጂ!
ወደ መጠመቂያው መግባት ትወድዳለህን? ብሎ ማን ጠየቀህ? ተው እንጂ! የጠየቀህ ማን እንደሆነ ባታውቅ እንኩዋን ጥያቄውን በደንብ ስማ::

ሰው የለኝም አትበለው : ስለመጠመቂያው ወረፋ አትንገረው : ስንት ሰው ቀድሞህ እንደዳነ አትቁጠርለት:: የጠየቀህ ግልፅ ጥያቄ ነው::
ልትድን ትወዳለህን?

እግዚአብሔር ፊት ስለ ችግርህ ክብደት ለምን ታወራለህ? ምን እንደሌለህማ እሱም ያውቃል:: አዎን እድን ዘንድ በለው:: ችግርህን ትተህ የምትፈልገውን ንገረው:: የችግርህ መወሳሰብና ሥር መስደድ ለእሱ የሚከብድ አይደለምና መዳን እንደምትሻ ብቻ በእምነት ንገረው የሚል ተግሣፅ በበሽተኛው በኩል ወደ እኛ ደረሰ::

🛌🛌🛌🛌🛌🛌🛌🛌🛌

መጻጉዕ (በሽተኛው) ቤተ ሳይዳ ከመጣ 38 ዓመት ሆነው:: ዳዊትና ሰሎሞን 40 40 ዓመት ነግሠው እንኳን ብዙ የምሬት ቅኔ ተቀኝተዋል:: ይህ ሰው አልጋ ላይ ሆኖ አርባ ዓመት ሊሞላው ሲል ምንኛ ተንገሽግሾ ይሆን?

ልብ በሉ ጌታችን በቤተልሔም ሲወለድ ይህ በሽተኛ በአልጋው ላይ ነበረ:: እረኞች ከብዙ መላእክት ጋር ሲዘምሩ እሱ የአንድን መልአክ መውረድና ውኃውን ማናወጥ እየጠበቀ ስድስተኛ ዓመቱን ደፍኖ ነበር:: ጌታችን የሠላሳ ሁለት ዓመት ዕድሜ ላይ ደርሶ ወደ መጠመቂያው ሥፍራ ሲመጣም ይህ ሰው አልጋው ላይ ነው:: መጠመቂያዋን 38 ዓመት በተስፋ ሲጠብቅ ቆይቶ ሳይጠመቅባት ቀረ::

ጌታ ሆይ የማይደርሰኝን ወረፋ ከመጠበቅ አድነኝ:: እንድፈወስበት ባልፈቀድክበት ሥፍራ ዕድሜዬን እንዳልጨርስ ጠብቀኝ::

ወደ ሐዲስ ኪዳንዋ ቤተ ሳይዳ ወደ ቤተክርስቲያን ከመጣሁ ብዙ ዘመን አስቆጠርኩኝ:: ግን እስካሁንም ድረስ ከኃጢአት አልጋ ላይ አልወረድሁም:: መነሣት እፈልጋለሁ ግን አቃተኝ:: ልቤ እንጂ እግሬ ጸንቶ መቆም አልቻለም::

ፈረቃ የሌለብህን የሕይወት ውኃ አንተን ሊጠጡ ሲመጡ በዓይኔ እየተቀበልኩ ብዙዎች ጠጥተውህ ሲድኑ በዓይኔ እየሸኘሁ አልጋዬ ላይ ቀረሁ::

እኔ እንደተኛሁ ስንቱ ቀድሞኝ እንደዳነ ባየህልኝ:: ከእኔ በኁዋላ መጥተውስ ከእኔ በፊት ስንቶች ዳኑ?
ስንቱ ከኃጢአት አልጋ በንስሓ ተነሥቶ ያንተን ሥጋና ደም ተቀብሎ ተፈወሰ?

የቤተ ሳይዳው ሐኪም ሆይ ወደ አንጋፋው በሽተኛህ ወደ ጽኑዕ ሕመምተኛህ ወደ እኔ የምትመጣው መቼ ይሆን? ያን ሕመምተኛ "ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደነበረ" አውቀህ ያናገርከው ሆይ እኔን የምታናግረኝ መቼ ይሆን? እኔስ ብዙ ዘመን እንደሆነኝ አታውቅምን? ሰው የለኝም : ልብ የለኝም : ኃይል የለኝም : አቅም የለኝም ብዬ ብሶቴን የምነግርህ መቼ ይሆን?

"ኢየሱስ፦ ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፡ አለው። ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ" ዮሐ.5:8-9

አንተ ተነሥ ብለኸው የማይነሣ ማን ነው? እንኳንስ ከአልጋ ከመቃብርም ተነሥ ያልከው ይነሣ የለምን?
ግዴለህም እኔንም ተነሥ በለኝ:: ተነሥ ኃይልን ልበስ ያልከኝ እንደሆነ እንኳንስ "ሸክሜም ቀሊል ነው" ያልከው አንተ ያዘዝከኝ የራሴን ሸክም ቀርቶ የወንድሜን ሸክምም ተሸክሜ የአንተን ሕግ እፈጽማለሁ:: (ገላ. 6:2)

🛌🛌🛌🛌🛌🛌🛌🛌

"ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ። ... ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመቅደስ አገኘውና፦ እነሆ፥ ድነሃል፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ፡ አለው" ይላል::

በሽተኛው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ እንደሔደ ሳነብ አንድ ነገር ልቤን አስጨነቀው:: ይህ ሰውዬ 38 ዓመት ሙሉ የኖረው በቤተ ሳይዳ ነው:: ክርስቶስ ድንገት ፈውሶት ሒድ ሲለው እሺ ብሎ ከዚያ መጠመቂያ ሥፍራ ከወጣ በኁዋላ ወዴት ሔደ?

የሠላሳ ስምንት ዓመት ሕመምተኛው ሆይ እውነት ወዴት ሔድህ? ከመጠመቂያው መውጣትህን ሰምተን አድንቀናል:: ከዚያስ ወዴት ሔድክ? ዙሪያ ገባው አልተለወጠብህም? መንገድስ አልጠፋብህም?
ወደ ዘመዶች ቤት ሔድክ እንዳልል "ሰው የለኝም" ስትል ሰምቼሃለሁ::

አልጋህንስ የት አደረስካት? መቼም ሰባብረህ እንደማትጥላት የታወቀ ነው:: አልጋ ለታመመ ብቻ ሳይሆን ለጤነኛም ያስፈልጋልና አራት እግር እያላት ጥላህ ያልሔደችውን ዘመድህን መቼም በክብር ማስቀመጥህ አይቀርም::

ለማንኛውም እዚያው ምዕራፍ ላይ ኢየሱስ ይህንን በሽተኛ ዳግም በመቅደስ አገኘው ይላል:: ዮሐ. 5:14 ጌታ ከመጠመቂያ ቦታ አድኖ ያስነሣውን ሰው በመቅደስ ቆሞ አገኘው:: ይህ በሽተኛ እግሩ ሲጸናለት የሔደው ወደ ፈጣሪ ደጅ መሆኑ ያስመሰግነዋል::

ጌታ በመጠጥ ቤት ቢያገኘው ኖሮ ያሳዝን ነበር:: እግርህን ያጸናሁልህ ለዚህ ነው ወይ ብሎ ባዘነበት ነበር:: አሁን ግን ያዳነው ጌታ በመቅደስ አግኝቶት "እነሆ ድነሀል ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ" አለው::

ይህንን የምታነብ ወንድሜ ሆይ ክርስቶስ አንተንስ አላዳነህም? "ኸረ እኔ ሽባ ሆኜ አላውቅም:: ማንም እኔን ከአልጋ አላስነሣኝም ትለኝ እንደሆን እመነኝ ክርስቶስ እንደ አንተ ያዳነውስ የለም:: እርሱ እኔና አንተን ተነሡ ብሎ ያስነሣን ከ38 ሳይሆን ከዘላለም የሲኦልና የኃጢአት አልጋ ነው::

እኛን የፈወሰን አልጋችንን አሸክሞ ሳይሆን እሱ ራሱ እኛን ከነአልጋችን ተሸክሞን ነው:: ካላመንከኝ ነቢዩ ኢሳይያስን ጠይቀው "እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ" ሲልህ ትሰማዋለህ:: ኢሳ. 53:12 የእኛን በደል ተሸክሞ ጀርባው ምን ያህል እንደ ቆሰለ ባየህ:: ይህንስ ጀርባዬን ታያለህ የተባለውን ሙሴን ብትጠይቀው ሳይሻል አይቀርም::

ያዳነህ አምላክ አንተንስ የት ነው የሚያገኝህ? እንደዚህ ሰውዬ መቅደስ ያገኝህ ይሆን?

የትም ቢያገኝህ ግን ቃሉ አንድ ነው "እነሆ ድነሀል ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ" ከሠላሳ ስምንት ዓመት የአልጋ ቁራኝነት የሚብስ ምን ሊመጣ ነው? ካልክስ እሱን ከማየት ይሠውረኝ ብትል ይሻልሃል::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
መጋቢት 10 2014 ዓ.ም.
ባሕር ዳር ኢትዮጵያ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ!
በኮሜንት መስጫው ሥር "ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ዋጋን በምድር የሚያስቀር ውዳሴም ሆነ ሌላ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ" (ኤፌ 4:29)

25/12/2022

Address

Addis Ababa

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Deacon Gebrê Medhn posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share



You may also like