03/02/2024
የሰርፀ ፍሬስብሃት መልዕክት
| ስለ ዳዊት ጽጌ የተዋጣለት ድምፃዊነት ዛሬ ምን ዐዲስ ነገር መናገር ይቻላል? ኹሉ የመሠከረለት ዜማ የሚኩል እና ሸምኖ የሚቋጭ አዚያሚ ነው። በሙያም በግብረ ገብም ማንነቱን ያስመሠከረ የዘመን አርአያ ነው።
ወደ ኋለኛው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘመን መለስ ብሎ፥ "ወትረ ኅልው" (classic) የምንላቸውን ዜማዎች ተጫውቶ አዳመጥኳቸው። እጅግ በሚገርም ብቃት እና ዘመን አሻጋሪ በኾነ መንፈስ ውብ አድርጎ ነው ያዜማቸው። የተመረጡት ሙዚቃዎችም በተሠጡት ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ እንደተወሳው፣ ከዘወትር ድምጫችን የራቁ እና በቀላሉ የማናገኛቸው ሥራዎች ናቸው።
አበጋዙ ክብረወርቅ ሺዎታ፥ በተለመደ የሙያ አክብሮት እና ጥንቃቄው፣ የቀደሙ አቀናባሪዎችን አሻራ እንዳይለቅ አድርጎ በዘመን Expression የተጌጠ Adaptation እና Re-Arrangement የተዋሐዱበት ፕሮዳክሽን አስደምጦናል። የጥላሁን ገሠሠን፣ የማሕሙድ አሕመድን፣ የዓለማየሁ እሸቴን፣ የምኒልክ ወስናቸውን፣ የአስቴር ዐወቀን፣ የተፈራ ካሣን (በግርማ ተፈራ) ሥራዎች፤ በልዩ ጥራት እና ከፍታ (ራሳቸውን ድምፃውያኑን ባሳመነ ብቃት) ፕሮዲውስ ማድረጉ ይታወቃልና፣ እንዲህ ያለውን ፕሮዳክሽን እንዴት re-arrange ሊያደርገው እንደሚችል መገመት አይሳነንም ።
የሙዚቃ መሣሪያዎቹ formation እና የሙዚቀኞቹ የየግል ብቃት ብዙ የሚያስጽፍ፣ ምሁራን ሙዚቀኞችን ያገናኘ አስደናቂ መሰባሰብ ነው። እንደ አንድ ኦርኬስትራ ወይም ባንድ አብረው ብናያቸው ኹሌም የምመኛቸውን ሙዚቀኞች ይህ ፕሮዳክሽን ማገናኘት ችሏልና በጣም ደስ ይላል።
እያንዳንዱ ሥራ የራሱ ፈተና ስላለው፥ ይሄኛውም ለሙዚቀኞቹ ፈተና ይኖረዋል። ግን የተሳካለት ስሜት ሰጪ ፕሮዳክሽን መሠራቱን መመስከር ይቻላል።