27/06/2024
ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊና ውጤታማ የውይይት መድረክ አካሂደናል:- አቶ ተሾመ አናሞ
በአዲስ መልክ ተግባራዊ የሚደረገውን ስትራቴጂክ ፕላንን በማስመልከት ከባለድርሻ አካላት ጋር የተደርገው የውይይት መድረክ ውጤታማና አስፈላጊ ሃሳቦች የተገኙበት ነው ሲሉ የሀዲያ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ አናሞ ገለፁ።
ህብረተሰብ ያልተሳተፈበት የከተማ ፕላን ብዙ ጉድለት እንዳለው የገለጹት አቶ ተሾመ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያደረግነው ሰፊ ውይይት ብዙ ግብዓት ያገኘንበት ነው ብለዋል።
አዲሱን የአስር ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን በማስመልከት በዋና ዋና ችግሮች ዙሪያ ከተሳታፊዎች የተነሱትን ሰፋፊ ሀሳቦች በሚገባ ይዘናል ያሉት አቶ ተሾመ:-
ለፕላን ትግበራ አስፈላጊ ናቸው የተባሉ ግብዓቶችን በማሰባሰብ ፕላኑን እየተሰራ ባለው አግባብ በአጭር ጊዜ ሰርተን ይፋ እናደርጋለን ብለዋል።
የሾኔ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበራ በዶሬ እንደገለጹት ፕላኑ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲደረግ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በቁርጠኝነት ትብብሩን እንዲገልጽ በማሳሰብ:-
በባለሙያ ስህተት ምክንያት የሚፈጠረውን የፕላን ስህተት እና ጥሰት ለመከላከል እንዲሁም በህግና ስርዓት አስይዞ ከመምራት አኳያ ህግ እየተከበረ እንደሚሄድ ተናግረው:-
ሾኔ ውብ፣ጽዱ፣ለነዋሪዋ ምቹ ከተማ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልፀዋል።
ለፕላን ያስፈልጋሉ የተባሉ የሶሺዮ ኢኮኖሚ፣የሰርቬይ ስራዎች፣የመሬት አጠቃቀም መረጃ፣የፍልድ ስራዎች ሁሉ ከሞላ ጎደል በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተማ ፕላን እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ከፍተኛ ፕላነር የሆኑት አቶ ተስፋዬ ፊጦራ አብራርተዋል።
በሀዲያ ዞን ሾኔ ከተማ አስተዳደር ከዚህ ቀደም ሲሰራበት የቆየው መዋቅራዊ ፕላን ጊዜው እንዳበቃም ተገልጿል።
በቀጣይ አስር አመታትን የሚዘልቅ አዲስ ስትራቴጂክ ፕላንም በዝግጅት ሂደት ላይ ይገኛል።
ፕላኑ በክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ፣በሃዲያ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያና በከተማ አስተዳደሩ የጋራ ትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
በሀዲያ ዞን ሾኔ ከተማ አስተዳደር በቀጣይ በሚተገበረው የአስር ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን ዝግጅት እና ችግሮች ልየታ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተደረገው ሰፊ ውይይት ለፕላኑ አተገባበር የተሻለ ሀሳብ ተሰጥቶበት በታላቅ መግባባት ተጠናቋል ሲል የሾኔ ከተማ አስተዳደር የመንግስት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው የዘገበው።