25/04/2024
ሁለንተናዊ ብልጽግና ማለት ምን ማለት ነዉ?
ብልጽግና ምሉዕ የሆነ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የሀገር ደህንነትና ውጭ ግንኙነት ልህቀት ውጤት ነው፡፡ ከፖለቲካው አንጻር ብልጽግና መካከለኛና አካታች የፖለቲካ እይታን ይከተላል፡፡
ከዚህ አንጻር ሲታይ ብልጽግና በቀኝና በግራ ዋልታዎች መካከል ሚዛን በመበጠበቅ በመደመር እሳቤ የተቃኘ የተረጋጋ የፖለቲካ ሀይሎች አሰላለፍና መስተጋብር የሰፈነበት ምህዳር የበለጸገ ፖለቲካ ማሳያ ነው፡፡ ሁሉም ማንነቶችና ፍላጎቶች እውቅናና ክብር አግኝተው የሚደመጡበት፣ ህግና ስርዓት የሰፈነበት አውድ ነው።
ቅቡልነት የተጎናፀፈ ሀገረ መንግሥት የተረጋገጠበት ነው። ፍትህና ርትህ እውን የሆነበት፤ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት የሰፈነበት ነው፡፡
በሌላ በኩል ሁለንተናዊ ብልፅግና የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ እውን የሆነበት ነው፡፡ ሁለንተናዊ የግብርናና ኢንዱስትሪ ልማትና ዕድገት የተሰናሰለበት ነው፡፡ ገቢ ምርቶች በብዛትና በጥራት የተተኩበት፣ የኤክስፖርት ምርቶችም በዚያው ልክ በብዛትና በጥራት የተመረቱበትና የውጭ ምንዛሬን ማሳደግ የተቻለበት፣ ለሰፊ የተማረ የሰው ኃይል ዘላቂና አስተማማኝ የስራ ዕድል መፍጠር የተቻለበት ነው፡፡
ብልጽግና ፓርቲ የኢኮኖሚ ሽግግርን ለማፋጠን የግብርናና ኢንዱስትሪ ዘርፉን ትስስር የሚያጠናክርና ሀገራችንን በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ቀዳሚ ማዕከል እንድትሆን የሚያስችሉ ስራዎችን በስፋት እየሰራ የሚገኘውም ከዚሁ እሳቤ በመነሳት ነው፡፡