03/12/2023
• አረጀች አገሬ፣ አበቀለች አረም!!!
• ለም አፈሯን በልቶ፣ ውሃዋን ጠጥቶ የገነገነ አረም፣
• ለምለሚቱ ሀገሬን፣ ለም አፈሯን በልቶ፣ ሊያጠፋት አይደለም፣
• ሥር ሰዶ ጠንክሮ፣ እንዲህ እንደ ዋዛ ሚነቀል አልሆነም፣
• ህዝብ ሆ ! ብሎ ወጦ፣ በህብረት በጋራ ይነቀል ይህ አረም፣
• ህዝብ አንድ ከሆነ፣ ህዝብ ከተባበረ፣ ማይነቀል የለም።
• ሕዝብን አለያይቶ፣ የተገነባዉ ግንብ፣ የበርሊን ግንብ ፈርሶ፣
• ዓለም ተደስቶ፣ ሕዝብ ተገናኝቶ፣ እየተላቀሰ የደስታ እለቅሶ፣
• የዓለም ህዝብ በመላ፣ በጣም ተደስቶ፣ ተቃቅፎ ተላቅሶ፣
• የነበረዉ ሰላም፣ የሕዝብ አንድነት፣ ጀርመን ተመልሶ፣
• ጥንት አባቶቻችን፣ በደም የገነቡት፣ የሕዝብ አንድነት፣ የእኛዉ በግድ ፈርሶ፣
• በህዝብ አንድነት፣ ተከብሮ የኖረው፣ ወሰኑ ተጥሶ፣
• ሀገር ተረብሾ፣ ህዝብ ተበጥብጦ፣ ተሞልቶ በለቅሶ፣
• ያሳለፈው ስቃይ፣ ግፍና መከራ፣ ዳግም ተመልሶ።
• በቋንቋ በጎሳ፣ ድንበር ተበጅቶ፣
• ሕዝብ ተከልሎ፣ አገር ተመስርቶ፣
• በሃሰት ትርክት፣ ጥላቻ ተስፋፍቶ፣
• በቂም በጥላቻ፣ ህዝብ ሰላሙን አጥቶ፣
• ፍቅሩ አብሮነቱ፣ አንድነቱ ጠፍቶ።
• የነበረዉ ፈርሶ፣ ሕዝብ በክልል ታጥሮ፣
• በጎጥ ተለያይቶ፣ በዘር ተወጥሮ፣
• በነግድ በጎሳ፣ አንዱ አንዱን ጠርጥሮ፣
• የእኔ ያላለዉን እያፈናቀለ፣ ሲያስወጣ ዘር ቆጥሮ፣
• በግፍ በመከራ፣ ሲያስወጣዉ መንጥሮ፣
• ሰዉ ሰዉን ሲጠላ፣ ሰዉ ሁኖ ተፈጥሮ፣
• ሰው ሰውን ሲበድል፣ ሰው ሁኖ ተፈጥሮ፣
• ሰዉ ሰዉን ሲገድል፣ ሰዉ ሁኖ ተፈጥሮ።
• እንዴት ሰው ይኖራል፣ ይሄን ኑሮ ብሎ፣
• በዚህ መጥፎ ጊዜ፣ የታሪክ ጎደሎ።
• ጥዋትና ማታ፣ ይሄን እየሰማን፣ ይሄን እያየነ፣
• ሰዉ መሆን አስከፋን፣ ሰዉ መሆን ጠላነ፣
• በመከራው በግፉ፣ ሕዝባችን አዘነ
• በሃዘን በለቅሶ፣ ጊዜአችን ባከነ፣
• እስከመቼ እንኑር፣ ይሄን እያየነ፣
• በግፍ በመከራ፣ በሃዘን በንዴት እየተቃጠልነ።
• ከሃጢያት የነፃ፣ ደም ያልተቃባ፣ ደም ያልተነካካ፣ ሰው እንፈልጋለን፣
• ለሰላም የቂመ፣ ሰላምን የሚወድ፣ እርቅን የሚያመጣ ሰዉ እንፈልጋለን፣
• ቂም በቀል የሌለው፣ ለሰላም የተጋ፣ ፈራእግዚአብሔር ያለው ሰው እንፈልጋለን
• በደላችንን አይቶ፣ እለቅሷችንን ሰምቶ፣ እግዚአብሔር ካደለን፣
• የሰላም ሻፒዮን፣ የፍቅር ሻፒዮን፣ ለሰላም ያደረ፣ ለፍቅር ያደረ፣ ፍቅር እንዲሰጠን፣
• ከጥል ከጥላቻ፣ ከቂም፣ ከበቀል፣ ከጦርነት አውጥቶ፣ ሰላም የሚሰጠን።
• እስኪ ሰዉ ፈልጉ፣ ከሃሰት የራቀ፣
• እስኪ ሰው ፈልጉ፣ ከቅጥፈት የራቀ፣
• በህዝብ የተከበረ፣ በህዝብ የተፈቀረ፣ በህዝብ የታወቀ፣
• ህዝብን ያከበረ፣ ህዝብን ያፈቀረ፣ ህዝብን ያልናቀ።
• ጥላቻን ሚያጠፋ፣ ጦርነትን ሚያስቆም፣ እርቅ ሰላም ሚያመጣ፣
• ለሰላም የቆመ፣ ፈራእግዚአብሔር ያለዉ፣ ቅን ሰዉ የት ይምጣ፣
• አረመኔ ሥራት፣ ሕዝብ እያጋደለ፣ የሕዝብ ደም አይጠጣ፣
• ማንንም አይጠቅም፣ በቃን ይሄ ሥራት፣ ከአገራችን ይዉጣ።
• አረጀች መሰለኝ፣ አረጀች ኢትዮጵያ፣ አበቀለች አረም፣
• አረጀች አገሬ፣ የሚበቅለው ሁሉ፣ እንደ ድሮ አይደለም፣
• ለም አፈሯን በልቶ፣ ደንድኖ ሥር ሰዶ፣ ወፈረባት አረም፣
• አረሙ ወድሎ፣ እንዱህ በተናጠል፣ ሊነቀል አልቻለም፣
• እንድ ሁነህ ሆ ! ብለህ በደቦ ንቀለው፣ ያለዚያ አይቻልም፣
• ወይ ቆራርጠህ ጣለው፣ ቆፍረህ ንቀለዉ፣ ሌላ ዘዴ የለም።
• ቆራርጠህ አድርቀህ፣ ከምረህ አቃጥለው፣ ይሄንን መጥፎ አረም።
ጌታቸው ሙላቱ