የጉራጌ ዞን ፍትህ መምሪያ

የጉራጌ ዞን ፍትህ መምሪያ Alerting the community with legal issues and its update

15/03/2024

62.2K likes, 2897 comments. ““What is happening in Gaza now is funded with US taxpayer dollars. These are our bombs.” Senator speaks about the US being directly complicit in the war on Gaza through the military aid it provides to Israel.”

13/10/2022
02/11/2021

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽመው “የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ዕዝ” ነው ተብሏል

22/10/2021

የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የሁለት ዳኞችን ያለመከሰስ መብት አነሳ፡፡
›››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››››
የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የሁለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞችን ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ውሳኔ አሳለፈ፡፡
የኢፌዲሪ ፍትህ ሚኒስቴር ሁለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች በወንጀል መጠርጠራቸውን በመጥቀስ ምርመራ ለማድረግ ያስችል ዘንድ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ መጠየቁን ተከትሎ የፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጥቅምት 12 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በቀረበው ጥያቄ ላይ በሰፊው ተወያይቶ በአዋጅ ቁጥር 1233/13 አንቀጽ 34(2) መሰረት የሁለቱንም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ወስኗል፡፡

11/07/2021

ደሀ ደንብ/ዳኝነት ሳይከፈል፣ በነፃ መዝገብ ማስከፈት/
ክስ ለማቅረብ የፈለገ ወገን ከፍርዱ ለሚያገኘው የዳኝነት አገልግሎት መክፈል የሚገባውን የዳኝነት ገንዘብ ለመክፈል የሚያስችል የገንዘብ አቅም የሌለው ከሆነ ክሱን ያለዳኝነት ገንዘብ በደሀ ደንብ መሠረት የማቅረብ መብት እንዳለው በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 215 ተደንግጓል፡፡ ክሱን የሚያቀርበው ወገን ድሀ በመሆኑ ምክንያት የዳኝነት ገንዘብ ሳይከፍል ክሱን አቅርቦ እንዲያሰማ ሊፈቅድለት ይገባል? የሚለው ጉዳይ ሊለይ የሚችልበት ዝርዝር አፈፃፀም ደንቡም ፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 467 እና ተከታዩ ድንጋጌዎች ተመልክቷል፡፡ እነዚህ ደንቦች ተፈፃሚነታቸው ክስ ለማቅረብ በፈለገ የተፈጥሮ ሰውም ሆነ በሕግ ሰውነት ያላቸው ወገኖችም ጭምር ነው፡፡
በዚህም መሠረት ድሀ ነኝ፤ መብቴን ለማስከበር ያለኝ ፍላጐቴ በዳኝነት ገንዘብ እንቅፋት ምክንያት ሊሰናከል አይገባም፡፡ ስለሆነም በድሀ ደንብ መሠረት ክሱን በነፃ እንዳሰማ ይፈቀድልኝ የሚል ማናቸውም ከሳሽ ድሀ መሆኑን ሊያመለክት የሚችል የሚገኝበትን የገንዘብ አቋም ማረጋገጥ ይገባዋል፡፡ ይህም ከሳሹ የሚገኝበት የገንዘብ አቋም ከተረጋገጠ በኋላ ለክሱ ሊከፈል የሚገባው የዳኝነት ገንዘብ መጠን ከሳሹ ከሚገኝበት የገንዘብ አቋም አኳያ ተገናዝቦ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 467 መሠረት ድሀ የመሆኑና ያለመሆኑ ጉዳይ ሊለይ ይገባል፡፡
ሰ/መ/ቁ. 79555 ቅጽ 14፣ ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 215፣ 467
አንድ ሰው በፍርድ ሊያልቅ የሚገባው ጉዳይን ፍርድ ቤት ይዞ ሲቀርብ የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ መክፈል ያለበት መሆኑን የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 215፣ ከ467 እስከ 479 ድረስ የተደነገጉት ድንጋጌዎች ያሳያሉ፡፡ የዳኝነት አገልግሎት መክፈል የማይችል ሰው ክስ ለማቅረብ የሚችልበት አግባብ ስለመኖሩም ተጠቃሽ ድንጋጌዎች ያስገነዝባሉ፡፡ አንድ የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ ለመክፈል የማይችል ሰው በደሃ ደንብ ክስ ለማቅረብ የሚችል ሲሆን ለመክፈል አቅም እያለው ክስ ያቀረበ መሆኑ ከተረጋገጠ ግን መዝገቡ እንደሚዘጋ፣ የተዘጋ መዝገብ ደግሞ የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ /ገንዘቡን/ ለመክፈል ዝግጁ እስከሆነ ድረስ የሚንቀሳቀስለት መሆኑን የሥነ ሥርዓት ሕጉ ድንጋጌዎች መንፈስና ይዘት ያስገነዝባሉ፡፡
ሰ/መ/ቁ. 52942 ቅጽ 12፣ ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 215፣ 467-479
ይግባኝ ዳኝነት ሳይከፈል በነፃ ለመክሰስ እንዲፈቀድ በቀረበ ጥያቄ ላይ ሊሰጥ የሚችለው ትእዛዝ እንደነገሩ ሁኔታ ሁለት ዓይነት ነው፡፡ አንደኛው ከሣሽ የዳኝነት ገንዘብ ለመክፈል የሚያስችለው የገንዘብ አቅም የሌለው ስለሆነ እንደ ጥያቄው የዳኝነት ገንዘብ ሳይከፍል በነፃ ፋይል ከፍቶ ክሱን ለማቅረብ ይችላል የሚለው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከሣሹ ድሃ ያለመሆኑ ስለተረጋገጠ ተገቢውን የዳኝነት ገንዘብ ካልከፈለ በቀር በነፃ ፋይል ከፍቶ ክሱን ለማቅረብ አይችልም የሚለው ነው፡፡
በመጀመሪያው አኳኋን ትእዛዝ በተሰጠ ጊዜ በዚህ ትእዛዝ መሠረት ፋይሉ ተከፍቶ ክርክሩ የሚቀጥል ነው፡፡ የክርክሩ ውጤት የሚታወቀው ግራ ቀኙ በሚያቀርቡት የፍሬ ነገርና የሕግ ክርክር ማስረጃ መሠረት ነው፡፡ በመጨረሻው የክርክር ውጤት ተከሣሹ ባይስማማ ክርክሩ ከመጀመሩ በፊት ክሱ ዳኝነት ሳይከፈልበት በነፃ እንዲከፈት መደረጉ የሕግ ድጋፍ አልነበረውም የሚለውን እንደ አንድ የይግባኝ ምክንያት በማድረግ በውሣኔው ላይ ካለው ቅሬታ ጋር አዳምሮ ማቅረብ ይኖርበታል እንጂ ከሥረ-ነገሩ ፍርድ በፊት የይግባኝ አቤቱታ የማቅረብ መብት አይኖረውም፡፡ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ. 320/3/ የተመለከተው ድንጋጌም በዚህ አኳኋን በሚቀርበው የይግባኝ አቤቱታ ላይ ክልከላ ለማድረግ ነው፡፡
በሌላ በኩል ድሀ ያለመሆንህ ተረጋግጧል፡፡ የዳኝነት ገንዘብ ካልከፈልክ በቀር ፋይል አይከፈትም ለተባለው ከሣሽ ግን ይህ ዓይነቱ ትእዛዝ የመጨረሻ ነው፡፡ ሌላ የሚጠበቅ የሥረ-ነገር ፍርድ የለውም፡፡ ስለሆነም የዳኝት ገንዘብ ለመክፈል አቅም ሳይኖረኝ ክርክሬና ማስረጃዬ በአግባቡ ሳይታይ አቅም እንዳለኝ ተቆጥሮ የዳኝነት ገንዘብ ክፈል መባሌ ተገቢ አይደለም የሚል ከሆነ የተሰጠው ትእዛዝ የመጨረሻ እንደመሆኑ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 320/1/ መሠረት የይግባኝ አቤትታ የማቅረብ መብት አለው፡፡
ሰ/መ/ቁ. 23744 ቅጽ 6፣ ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 320

19/02/2021

የተለያዩ አዋጆችና ደንቦች እንዲሁም አዳዲስ መረጃዎች ከዚህ በታች ያለውን የቴሌግራም ቻናል ሊንኩን https://t.me/GurageZoneAttorneyDepartment በመጫን subscribe /join በማድረግ በቀላሉ ያገኛሉ እንዲሁም ይጠቀማሉ። መልካም...

25/08/2020

የንግድ እቃን ማከማቸት፣ መደበቅ፣ ዋጋ ጨምሮ መሸጥ እና የኮረና ወረርሽኝ ከኢትዮጵያ
ሕግ አንፃር
=======================
መግቢያ
በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወረርሽኝ ሲከሰት የሰዎች ህይወትን ከመቅሰፉ
በተጨማሪ የንግድ እንቅስቃሴዎችንም አደጋ ላይ ይጥላል። ንግድ የተሳለጠ እና ለሁሉ
ተደራሽ የሚሆነው የተረጋጋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ሲኖር ብቻ ነው።
በንግድ ዓለም ውስጥ የነጋዴዎች ዋነኛ ግብ ተደርጎ የሚወሰደው በአጭር ጊዜ ወይም
በረጅም ጊዜ ውስጥ ትርፋማ መሆን ነው። ነገር ግን ይህ ትርፋመነታቸውን የሚያሳኩት
ሕግ እና ሥርዓትን በአከበረ መንገድ በሚደረግ እንቅስቃሴ ሊሆን ይገባል። ከሕግ እና
ሥርዓት ውጭ ትርፍ ለማጋበስ የሚንቀሳቀስ ነጋዴ የተመሰረተበት አላማ ማትረፍ ስለሆነ
በሚል ተልካሻ ምክንያት ዝም ተብሎ ሊታለፍ አይገባም። ይህንም መሰረት ለማስያዝ ሕግ
እና ሥርዓት አስፈፃሚ አካላት ትልቅ ድርሻ አላቸው። ትርፍ ለማግኘት ከሚደረጉ ጥረቶች
ጎን ለጎን ማህበራዊ ሀላፊነትን መወጣትንም መዘንጋት አይገባም። የነጋዴዎች ትርፍን
ለማሳደግ የሚያርጉት እሩጫ ሕግ እና ሥርዓትን ለማስከበር ከተቋቋመ አካል ጋር በጥብቅ
ከሚካረሩባቸው ወቅቶች አንዱ ወረርሺኝ የሚከሰትበት ወቅት ነው። ወረርሽኝ በሚከሰትበት
ወቅት ሁሉም ከወረርሽኙ ለመዳን በሚያደርገው እሩጫ ወቅቱ የሚፈልጋቸው እቃዎች እና
አገልግሎቶች እጥረት ሊከሰት ይችላል። በዚህ ጊዜ ማህበራዊ ሀላፊነትታቸውን
ለመወጣት ደፋ ቀና የሚሉ ነጋዴዎች የሚኖሩትን ያክል አጋጣሚውን ተጠቅመው ሀብት
ለማካበት እና ከችግር ለማትረፍ የሚሯሯጡም አሉ። እነዚህ ከችግር ለማትረፍ የሚሯሯጡ
ነጋዴዎች ከሚተገብሯቸው ነገሮች መካከል እጥረት ያለበትን እቃ ማከማቸት እና በተፈላጊ
እቃዎች ላይ አለአግባብ ዋጋ መጨመር ይገኙበታል። እነዚህ ተግባራት በሸማቹ
ማህበረሰብ ላይ ከቀላል እስከ ከባድ አደጋዎችን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ይህንንም ታሳቢ
በማድረግ ሀገራት የሸመቾች ጥበቃ ሕግን በማውጣት ሸማቹን ማህበረሰብ ከእንደዚህ
አይነት ችግር ለመጠበቅ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል። ሀገራችን ኢትዮጵያም ከ2002
ዓ.ም ጀምሮ ለሸማቾች መብት ጥበቃ ልዩ ትኩረትን የሰጠች ሲሆን በመካከልም ሁለት
ህጎችን አርቅቃለች። አሁን ላይ በስራ ላይ ያለው የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ
አዋጅ ቁጥር 813/2006 ትኩረት ከሰጣቸው ነገሮች መካከል እጥረት ያለባቸውን እቃዎች
ማከማቸት እና ተፈላጊ እቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች
ይገኙበታል። በሀገራችን ዓለም አቀፍ የሆነው የኮረና ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ ከወረርሽኙ
እኩል በሚባል ደረጃ የመገናኛ ብዙሀንን ትኩረት የሳበው ጉዳይ የነጋዴዎች እጥረት
ያለባቸውን እቃዎች ማከማቸት ተግባር እና የተፈላጊ እቃዎችን ዋጋ ጨምሮ መሸጥ
ይገኙበታል። የዚች አጭር ፅሁፍ አላማም እነዚህን የነጋዴው ማህበረሰብ ተግባራት
ከኢትዮጵያ የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ አንፃር መተንተን እና መወሰድ ያለባቸውን ተግባራት
መጠቆም ነው።
የኮረና ወረርሽኝ እና እጥረት የተከሰተባቸው እቃዎች
የኮረና ወረርሽኝን ለመከላከል ከሚደረጉ ጥረቶች መካከል የህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት
የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። የዓለም ጤና ድርጅት በሰጠው መመሪያ መሰረት ሀገራት
ሊከተሏቸው ከሚገቡ የመከላከያ መንገዶች አካላዊ እርቀት፣ ማስክ መጠቀም
፣አለመጨባበጥ እና እጅን በተደጋጋሚ መታጠብ ዋነኞቹ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ
ማስክ መጠቀም የማስክ አቅርቦትን እንዲሁም እጅን በተደጋጋሚ መታጠብ ደግሞ
የሳሙና እና የሳኒታይዘር አቅርቦትን ይጠይቃሉ። በአሁኑ ሰዓት በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም
አቀፍ ደረጃ እነዚህ በሽታውን ለመከላከል የሚረዱ እቃዎች እጥረት የመንግስታት እና
የህዝብ ጭንቀት ከሆኑ ውሎ አድሯል። ከዚህ በተጨማሪ እነዚህን እጥረት ያለባቸውን
ቁሳቁስ በአገኙት አጋጣሚ የሚሰበስቡ እና በውድ ለመሸጥ የሚያከማቹ ነጋዴዎች
እንዲሁም ከእራሳቸው እና ከቤተሰባቸው ፍጆታ በላይ የሚገዙ ግለሰቦች መበራከት ሌላ
ትልቅ የእራስ ምታት ሆኗል። ከህክምና ቁሳቁሶች በተጨመሪ ለእለት ፍጆታ የሚውሉ
እቃዎችም ለዚሁ ችግር ሰለባ ሆነዋል። መንግስት የሚያወጣውን መመሪያ ተከትሎ ዜጎች
እቤት ውስጥ ለመቀመጥ ከሚገዙት ከመጠን ያለፈ የምግብ እቃዎች በተጨማሪ ወደፊት
የዋጋ ጭማሪ ሊከሰት እንደሚችል በመተንበይ ዜጎች ሊገዙ የሚፈልጉአቸውን እቃዎች
አከማችቶ የለም iማለት ወይም አላግባብ ዋጋ በመጨመር የሸማቹን የመግዛት አቅም
የመቀነስ ተግባር በነጋዴው ማህበረሰብ ዘንድ ይስተዋላል። እነዚህ ተግባራት በወቅቱ
ተገቢ የሆነ ህጋዊ እርምጃ ካልተወሰደባቸው በጊዜ ሂደት የሚያስከትሉት አደጋ በጣም
ከባድ ይሆናል። የህክምና ቁሳቁሶች ላይም ሆነ የእለት ፍጆታ እቃዎች ላይ የሚደረገው
የማከማት እና ሰው ሰራሽ የእቃ እጥረት ችግር ሸማቹን ማህብረሰብ ለርሀብ ብሎም
ለሞት የሚዳርግ ችግር ውስጥ ሊከተው ይችላል። ወረርሽኙን ለመከላከል የሚረዱ
እቃዎች በአግባቡ እንዲሰራጩ ከአልተደረገ ከእለት ወደ እለት ወረርሽኙ እየተስፋፋ
ከሚያስከትለው ሰብዓዊ ኪሳራ በተጨማሪ የእለት ከእለት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ
እንቅስቃሴዎችን በመገደብ ሀገርን ከባድ የማትወጣው አዘቅት ውስጥ ሊከት ይችላል።
የእለት ፍጆታ አቅርቦቶችን መገደብም በእራሱ ዜጎችን ለርሀበ እና ሲቃይ በመዳረግ
ወረርሽኙ ሊያስከትል ከሚችለው አደጋ የበለጠ ችግር ሊያመጣ ይችላል። እነዚህን ከባድ
ችግሮች መቋቋም የሚቻለው ሕግን መሰረት አድርጎ በእንደዚህ አይነት ተግባራት ላይ
የተሰማሩ አካላትን ማስተካከል እና አስፈላጊ እርምጃዎች ሲወሰዱ ብቻ ነው።
የንግድ እቃን ማከማቸት እና ሰው ሰራሽ እጥረት መፍጠር በኢትዮጵያ ሕግ
እቃን ማከማቸት እና ሰው ሰራሽ እጥረት መፍጠር የገቢያ አለመረጋጋት እና የዋጋ ንረትን
ከሚያስከትሉ ተግባራት መካከል የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ
ግለሰቦች የእቃውን በገቢያ ላይ ያለውን ተፈላጊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የአቅርቦት
ችግር በሌለበት ሁኔታ የአቅርቦት ችግር ያለ በማስመሰል በግለሰብ ወይም በቡድን ደረጃ
ሊያከማቹ እና ሰው ሰራሽ እጥረት ፈጥረው በትልቅ ዋጋ የመሸጥ ተግባር ሊፈፅሙ
ይችላሉ። ነጋዴዎች እቃውን አከማችተው የሚያስቀጡበት ዋነኛ አላማቸው ጊዜውን
ጠብቆ ከተገቢው በላይ ትርፍን ለማጋበስ ነው። ከነጋዴው ማህበረሰብ በተጨማሪ የሸማቹ
ማህበረሰብም በእንደዚህ አይነት ተግባራት ተሰማርቶ ሊገኝ ይችላል። የሸማቹ
ማህበረሰብ በዋነኝነት እንደዚህ አይነት ተግባር ውስጥ የሚሰማራው እቃው ከገቢያ ላይ
ይጠፋል የሚል ፍራቻ ሲያድርበት ነው። ይህ የንግዱ ማህበረሰብም ሆነ የሸማቹ
የማከማቸት ተግባር በዜጎች ላይ ወይም እንደ አጠቃላይ በሀገር ላይ የሚያደርሰው ኪሳራ
በጣም ከባድ የሆነ ነው። ይህንም ተግባር ለመከላከል ይረዳ ዘንድ የኢትዮጵያ ንግድ
ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 እቃን ስለማከማቸት እና ሰው
ሰራሽ እጥረት መፍጠርን አስመልክቶ ድንጋጌዎችን የአካተተ ሲሆን የማስፈፀም
ሀላፊነቱንም ለንግድ ሚኒስትር፤ ለንግድ ዉድድር እና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን እና
ለንግድ ቢሮዎች ሰጥቷል።
በአዋጁ አንቀፅ 24 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት አንድ ነጋዴ ከመደበኛ የግብይት ስርዐት ውጭ
ወይም ነጋዴ ያልሆነ ሰው ለግል ወይም ለቤተሰብ ፍጆታ ከሚውል መጠን በላይ በንግድ
እና ኢንደስትሪ ሚኒስተር በገቢያ ላይ እጥረት ያለበት መሆኑ በሚኒስተሩ በወጣ የህዝብ
ማስታወቂያ የተገለፀ የንግድ እቃን ማከማቸት ወይም መደበቅ ክልክል ነው። እዚህ ላይ
በመጀመሪያ ደረጃ የንግድ ሚኒስተር እጥረት ያለበትን እቃ በዝርዝር በህዝብ ማስታወቂያ
የማሳወቅ ሀላፊነት ያለበት ሲሆን ይህንም ተከትሎ ነጋዴዎች እና ለግል ወይም የቤተሰብ
ፍጆታ የሚሸምቱ ግለሰቦች ከመደበኛ መጠን ያለፈ እቃን ማከማቸት ወይም መደበቅ
አይችሉም። ነጋዴውን ማህበረሰብ ወይም ሌሎችን ግለሰቦች ከእነዚህ ተግባሮች
እንዲቆጠቡ ለማድረግ ሚኒስተሩ በመጀመሪያ የራሱን ሀላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ
መገንዘብ ይገባል። የህዝብ ማስታወቂያዎች ለህዝቡ ተደራሽ በሆኑ የብሮድካስት ወይም
የህትመት ሚዲያዎች እንዲሁም የህዝብ ማስታወቂያ መለጠፊያ ቦርዶችን እንደአግባብነቱ
በመጠቀም ሊገለፅ ይችላል። በተመሳሳይ አንቀጽ ላይ አዋጁ የአስፈፃሚ አካላት ሕግን
የማስከበር ስራ በሚሰሩበት ወቅት ችግር እንዳይፈጠር እንዲሁም የትርጉም ክፍተቶችን
በመቀነስ የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ለማስቻል በንዑስ
አንቀፅ ሁለት ላይ ከመደበኛ የግብይት አሰራር ውጭ እቃ ተከማችቷል ወይም ተደብቋል
የሚያስብሉ መስፈርቶችን አስቀምጧል። መጀመሪያ ላይ የሰፈረው ነጋዴውን ማህበረሰብ
የተመለከተ ሲሆን አንድ ነጋዴ ግምቱ ከነጋዴው ካፒታል 25% የማያንስ እቃ ከውጭ የመጣ
ሲሆን አስመጭው ራሱ ለቀጣይ የምርት ሂደት በጥሬ እቃነት ወይም በግብይት
የሚጠቀምበት ካልሆነ በስተቀር የጉምሩክ ፎርማሊቲ ከተጠናቀቀለት በኋላ በሶስት ወራት
ውስጥ፤ በሀገር ውስጥ የተመረተ የንግድ እቃ ሲሆን በተመሳሳይ አምራቹ ለእራሱ የምርት
ግብዐት ካልተጠቀመበት በሁለት ወራት ውስጥ ወይም በጅምላ ሻጭ እና በችርቻሮ ሻጭ
የተገዛ እቃ ሲሆን ከተገዛበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ ለሽያጭ ካልቀረበ ነጋዴው
እጥረት ያለበትን እቃ የማከማቸት እና የመደበቅ ክልከላን እንደጣሰ ይቆጠራል። እነዚህ
መስፈርቶች ባይሟሉም እንኳ በማንኛቸውም መጓጓዣ ከተፈቀደው የስርጭት መስመር
ውጭ ሲጓጓዝ የተገኘ እቃ እንደ ተከማቸ እና አንደተደበቀ ይቆጠራል። ይህ ድንጋጌ
ለነጋዴው ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ከንግድ ውጭ ላሉ ማህበረሰቦች ተፈፃሚነት አለው።
እንደፃፊው አረዳድ የተፈቀደ የጉዞ መስመር የሚለውን ሀረግ የሚያመላክተው የጉምሩክ
መመሪያን መሰረት የአደረገ እንቅስቃሴን አለመከተል ወይም የእቃ እጥረት ማጋጠሚን
ተከትሎ በመንግስት የሚወጡ የጉዞ መስመር መመሪያዎችን የተመለከተ ሊሆን ይችላል።
ከነጋዴ ማህበረሰቦች ውጭ ያሉትን ግለሰቦች በተመለከተ ተቀባይነት ያለውን የግል ወይም
የቤተሰብ ፍጆታ ሁኔታዎችን ታሳቢ አድርጎ እንዲወስን ለንግድ ሚኒስትር በአዋጁ ስልጣን
ተሰጦታል። የማከማቸት እንዲሁም የመደበቅ ተግባራት ላይ የሚሳተፉ ግለሰቦችን
በተመለከተ የአዋጁ አንቀፅ 43 ንዑስ አንቀፅ 4 እና 5 ላይ የተቀመጡ ድንጋጋጌዎች
የተከማቸውን እቃ እንዲሁም ማጎጓዣን መውረስን ጨምሮ እስከ አምስት አመት የሚደርስ
ፅኑ እስራትን እና የገንዘብ ቅጣቶችን አስቀምጠዋል። የንግድ ውድድር እና ሸማቾች
ባለስልጣን በአንቀፅ 36 ንዑስ አንቀፅ 1(ለ) መሰረት በአዲስአበባ እና በድሬደዋ ከተማ
የሚፈጠሩ እቃ የማከማቸት ወይም የመደበቅ ወንጀሎችን የመመርመር እና ክስ የማቅረብ
ስልጣን የተሰጠው ሲሆን በክልልሎች የሚፈጠሩ ችግሮችን በተመለከተ በአንቀፅ 23(5)
መሰረት ለክልል የንግድ ቢሮዎች ስልጣን ተሰጠዋል። ከዚህ በተጨማሪም በአንቀፅ
23(5) መሰረት አስተዳደራዊ እርምጃዎችን በተመለከተ ለባለስልጣኑ አዋጁ በግልፅ
ስልጣን ስላልሰጠው የእቃ ማከማቸት እና መደበቅን በተመለከተ የሚያስፈልጉ
አስተዳደራዊ እርምጃዎችን የመውሰድ ስልጣንም በንግድ ሚኒስተር እና ቢሮዎች ስር
የሚወድቅ ይሆናል።
ይህ የንግድ እቃን ማከማቸት እና መደበቅን የተመለከተ ድንጋጌ በተወሰነ ጊዜ ወይም ሁኔታ
የተገደበ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስተር የእቃ እጥረት
መከሰቱን ሲረዳ ሊከተለው እና ሊያስፈፅመው የሚገባ ድንጋጌ ነው። በማንኛውም ጊዜ
አስፈላጊ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ሀገር ለከባድ የተፈጥሮ ወይም ሰው ሰራሽ አደጋ(በሽታ
ወረርሽኝን ጨምሮ) ስትጋለጥ አስፈላጊነቱ ከምንም በላይ ይሆናል። በዚህ ወቅትም ዓለም
በኮረና ወረርሽኝ አደጋ በተጨነቀችበት ወቅት የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማቃለል iA´Xu}
ከምንጠቀምባቸው ህጎች መካከል የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ላይ
የተቀመጠው ይህ የንግድ እቃወችን ማከማቸት እና መደበቅን መቆጣጠሪያ ድንጋጌ አንዱ
እና ዋነኛው ነው። ይህንንም ለማድረግ የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ እጥረት
የተከሰተባቸውን የእቃ አይነቶች የንግድ ሚኒስትር በተከታታይ ይፋ ሊያደርግ እና
የተቀመጡ ሂደቶችን ተከትሎ ሊቆጣጠር ይገባል። ሌሎች በአዋጁ ሀላፊነት የተሰጣቸው
የክልል እና የፌደራል መስሪያቤቶችም ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል። አሁን
ከተከሰተው የኮረና ወረርሽ አደጋ አንፃር የአዋጁን ድንጋጌዎች ከአየናቸው ግን አንዳንድ
ክፍተቶችን መገንዘብ እንችላለን። በአዋጁ አንቀፅ 24 ላይ እንደተመለከተው ከተፈቀደ
መስመር ውጭ ሲጓጓዙ የተያዙ እና በግለሰቦች እጅ የተከማቹ እቃዎች ውጭ ያሉ ሁሉም
የማከማቸት እና የመደበቅ ድርጊቶች በየደረጃው ከአንድ ወር እስከ ሶስት ወር የሚደርስ
የእፎይታ ጊዜን ተሰጦአቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ የንግድ እቃዎችን በተመለከተ አንድ ነጋዴ
እስከ 25% ካፒታሉ ድረስ የማከማቸት ስልጣን መሰጠቱን ከወቅቱ የኮረና ወረርሽኝ
አጣዳፊነት አንፃር ስንመለከተው አዋጁ ታሳቢ ያደረገው በመደበኛ ጊዜ የሚፈጠር እጥረትን
ብቻ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። እስከ 3 ወር የሚደርስ እፎይታን እና አስከ 25% ካፒታሉ
የሚደርስ እቃን የማከማቸት መብት ለነጋዴው የምንሰጥ ከሆነ እቃው በተሎ ለገቢያ
መድረስ እየቻለ የህጉን ክፍተት ተጠቅሞ እንዲያከማች ለነጋዴው እድል እየሰጠነው እና
በመካከል ብዙ የሰብዓዊ ኪሳራ እንዲያጋጥም እያደረግን ነው። ስለዚህ ይህ ክፍተት
ወቅቱን ታሳቢ አድርጎ የሚሞላበትን አቅጣጫ መጠቆም አስፈላጊ ይሆናል። በፀሃፊው
አረዳድ ይህን ክፍተት መሙላት የሚቻለው በህገመንግስቱ መንግስት መደበኛውን የሕግ
አሰራር ወደ ጎን በመተው ነገሮችን እንዲያስተካክል የሚፈቅድለትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ
የማወጅ ስልጣን መጠቀም ነው። በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 93(4) መሰረት
በሀገር ደረጃ ወይም በክልልሎች የወረርሽኝ በሽታ በሚከሰትበት ወቅት የፌደራል
መንግስት ወይም የክልል መንግስታት እንደተዋረዱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማውጣት
በመደበኛ የሕግ ስርዐቱ ማስፈፀም ያልቻሉአቸውን ጉዳዮች እንዲያስፈፅሙ እና ዜጎችን
ከመጣው ወረርሽኝ እንዲከላከሉ ስልጣን ሰጧቸውአል። ይህንንም ተከትሎ የኮረና ቫይረስ
ወርሽኝ የሚያመጣቸውን ችግሮች ከመደበኛው የሕግ ሥርዓት በተለየ መልኩ ተንቀሳቅሶ
በሚገባ ለመመከት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 3/2012ን አወጥቷል። ከላይ
እንደገለፅኩት በትክክለኛው የሕግ አሰራር የኮረና ወረርሽኝን ተከትሎ መንግስት
ሊያስፈፅማቸው ከማይችላቸው ነገሮች መካከል እስከ 25% ካፒታላቸው ያከማቹ
ነጋዴዎችን ምርታቸውን ወደ ገቢያ እንዲያወጡ ማድረግ እና ከአንድ ወር እስከ ሶስት ወር
የሚደርሱ በየደረጃው የተሰጡ የእፎይታ ጊዜዎችን በመጣስ ነጋዴዎች ያላቸውን ምርት
ለገቢያ እንዲያቀርቡ ማስገደድ ይገኙበታል። እነዚህ ደግሞ በአንፃሩ የነጋዴውን
ማህበረሰብ የማከማቸት እና የመደበቅ ተግባር የሚያግዙ እና የመንግስትን ወረርሽኙን
የመመከት እንቅስቃሴ የሚጎዱ የሕግ ክፍተቶች ናቸው። ስለሆነም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን
ክልከላዎችን እንዲያስፈፅም ስልጣን የተሰጠው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሽታውን
ለመቆጣጠር ያግዘው ዘንድ እነዚህን የንግድ ውድድር እና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ የሕግ
ክፍተቶች የሚሞላ ድንጋጌን ቢያወጣ የተሻለ አፈፃፀም ይኖረዋል።
ማጠቃለያ
በሀገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወረርሽኝ አደጋ ሲከሰት በሀገራት ማህበራዊ እና
ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚያደርሰው ጫና ቀላል የሚባል አይደለም። አሁን ላይ
አለማችን ያጋጠማት እና በሀገራችን መከሰቱ የተረጋገጠው የኮረና ወረርሽኝም ኢትዮጵያን
ጨምሮ በዓለም ሀገራት ላይ እያደረሰው ያለው ሰብዓዊ እና ማህበራዊ ኪሳራም በጣም
ከፍተኛ ነው። እንደዚህ አይነት አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት በጣም ፈታኝ እና እልህ
አስጨራሽ ከሚሆኑ ህገወጥ ተግባራት መካከል የነጋዴዎች ከአደጋ የማትረፍ እሩጫ
ትልቁን ድርሻ ይይዛል። ይህ የነጋዴው ማህበረሰብ ኢሞራላዊ እና ህገወጥ እንቅስቃሴ
በሀገር ላይ በተለይ ደሞ በሸማቹ ማህበረሰብ ላይ የሚያደርሰው ሰብዓዊ እና ማህበራዊ
ቀውስ በጣም ከባድ ነው። ይህንን ቀውስ ለመከላከል ወይም ለመቀነስ በሚደረጉ
እንቅስቃሴዎች ውስጥ ጠንካራ የሕግ ሥርዓት መዘርጋት ትልቁን ድርሻ ይወስደዋል።
ሀገራት እንደዚህ አይነት ችግሮችን ለመቀነስ የሸማቾች ጥበቃ ሕግን በብዛት ሲጠቀሙ
ይስተዋላል። ኢትዮጵያም ለሸማቾች ጥበቃ ልዪ ትኩረት መስጠት ከጀመረችበት 2002
ዓ.ም ጀምሮ ሁለት የሸማቾች ጥበቃን የሚመለከቱ ህጎችን ያወጣች ሲሆን አሁን በስራ
ላይ ያለው የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ከአካተታቸው ድንጋጌዎች መካከል
የንግድ እቃዎችን ማከማቸት እና መደበቅን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ይገኙበታል። የአዋጁ
አንቀፅ 24 ለነጋዴዎች በገቢያ ላይ ከተለመደው መጠን ውጭ እንዲሁም ነጋዴ ላልሆኑ
ግለሰቦች ለግል ወይም የቤተሰብ ፍጆታ ከሚያስፈልግ በላይ በንግድ እና ኢንዱስትሪ
ሚኒስተር እጥረት እንዳለበት የተገለፀን እቃ ይዞ መገኘት የተከለከለ መሆኑን ይደነግጋል።
ነጋዴዎችን በተመለከተ አዋጁ የመጠን እና የጊዜ መስፈርት የአስቀመጠ ሲሆን ከነጋዴ
ውጭ የሆኑ ግለሰቦችን በተመለከተ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የመወሰን ስልጣን
ተሰጦታል። ከተፈቀደ መስመር ውጭ ሲጓጓዝ የተገኘ እቃም ምንም እንኳ መስፈርቶችን
ባያሟላም እንደ ተከማቸ እቃ እንደሚቆጠር አዋጁ ያስቀምጣል። የአዋጁን ድንጋጌዎች
ጥሶ እቃ አከማችቶ የተገኘ ነጋዴም እቃ የመወረስ፣የገንዘብ እና የስር ቅጣቶች
ይጠብቁታል። አሁን በዓለም ላይ እንዲሁም በሀገራችን የተከሰተውን ኮረና ወረርሽኝ አደጋን
ተከትሎ እየተስተዋሉ ያሉ የነጋዴዎች እንቅስቃሴን ከመግታት አንፃር የዚህን ሕግ ጥንካሬ
ስንገመግም በተለይ የተቀመጡት የመጠን መነሻ መስፈርቶች እና የእፎይታ ጊዜዎች
የነጋዴውን ማህበረሰብ የአልተገባ እንቅስቃሴ የሚደግፉ እና ህዝብን ለከባድ ችግር
የሚያጋልጡ ስለሆኑ ማስተካከያ ሊደረግባቸው እና ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በሚያስችል
መንገድ ሊቃኙ ይገባል። ይህንም ለማድረግ ወረርሽኙን ለመከላከል የፌደራል መንግስቱ
የአወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 3/2012 መሰረት አድርጎ እነዚህን ገደቦች
የሚያነሳ መመሪያ ማውጣት ያስፈልጋል።

ከታች ባለው ሊንክ በመጠቀም የቴሌግራም ቻናላችንን በመቀላቀል ፈጣንና አዳዲስ መረጃዎችን ያግኙ https://telegram.me/GurageZoneAttorneyDepartment
01/08/2020

ከታች ባለው ሊንክ በመጠቀም የቴሌግራም ቻናላችንን በመቀላቀል ፈጣንና አዳዲስ መረጃዎችን ያግኙ https://telegram.me/GurageZoneAttorneyDepartment

የዚህ ግሩፕ ዓላማ ከመደበኛ ስራ ጋር በተያያዘ መረጃ ለመለዋወጥ ብቻ ነው:: This group is created Only for exchanging information and documents relating to office work

24/06/2020

የማታለል ወንጀል ከእምንት ማጉደል ወንጀል በምን ይለያል? በድንጋጌዎቹ የወንጀል ክስ
ለማቅረብ በመሠረታዊነት መሟላት ያለባቸው የማስረጃ ዓይነቶችስ ምንድናቸው?
=======================
በስራ ሂደት ያጋጠሙ አጋጣሚዎችን መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ ጽሑፍ
መግቢያ
በወንጀል የሚጠረጠሩ ሰዎችን በፍርድ ቤት በመክሰስ ለማስቀጣት በቂና አሳማኝ በሆነ
መልኩ ማስረጃ አቅርቦ ማስረዳት በዐ/ህግ በኩል ይጠበቃል፡፡ የተለያየ አይነት ማስረጃን
የመመዘን መርህ በወንጀል ክስ ለመክሰስና ጥፋተኛ ለማለት በስራ ላይ የሚውል ቢሆንም
በጥቅሉ ሶስት አይነት የማስረጃ አመዛዘን መርህ በስፋት ይታያል፡፡ የመጀመሪያው
የማስረጃ አመዛዘን መርህ ዐቃቤ ህግ የሚያቀርበው ማስረጃ በይዘቱ የተፈፀመውን ወንጀል
ከምክንያታዊ ጥርጣሬ በፀዳ መልኩ ማስረዳት የሚጠበቅበት መሆኑን የሚያስገድድ ሲሆን
በዚህ የማስረጃ አመዛዘን መርህ አግባብ የዐ/ህግ የማስረዳት ግዴታ ከፍ ባለ መልኩ
ተከሳሽ ወንጀሉን ስለመፈፀሙ ከምክንያታዊ ጥርጣሬ በፀዳ መልኩ ማስረዳትን ይጠብቃል
[1]፡፡ ሁለተኛው የማስረጃ ምዘና መርህ ተከሳሹ ላይ የሚቀርበው የማስረጃ አይነት
ተከሳሹ ወንጀሉን ስለመስራቱ በቂና አሳማኝ በሆነ መልኩ ማስረዳትን የሚጠብቅ ነው፡፡
ይህ አይነቱ መመዘኛ መንገድ ከአንደኛው መመዘኛ አነስ ያለ ግዴታ በዐ/ህግ ላይ
የሚጥል ሲሆን ተከሳሹ ወንጀሉን ስለመስራቱ ምንም አይነት ጥርጣሬ የሚጥል ማስረጃ
ከማቅረብ ባነሰ አጠራጣሪ ነገር ቢኖርም እንኳ ያለው ማስረጃ ተከሳሹ ወንጀሉን ሰርቷል
ለማለት በቂና አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብን እንደግዴታ የሚጥል ነው፡፡[2] ሶስተኛው
የማስረጃ ምዘና መርህ ተመጣጣኝ የማስረጃ መርህ የሚባለው ሲሆን ይህ መመዘኛ
መንገድ ከላይ ከተመለከቱት በላላ መልኩ የሚቀርበው ማስረጃ የሁለቱ ወገኖችን ማስረጃ
በንፅፅር ሲታይ የተሻለ ያስረዳውን መቅጣት ወይም ነፃ መልቀቅን መሠረት የሚያደርግ
ነው፡፡ [3]
ተከሳሽ በፍርድ ቤት ቅጣት ጥፋተኛ ተብሎ እስኪወሰንበት ጊዜ ድረስ ንፁህ ሆኖ የሚገመት
እንደመሆኑ በክስ መክሰስ ሂደት ተከሳሹ ወንጀሉን ስለመፈፀሙ በቂና አሳማኝ ማስረጃ
የመስበስብና የመክሰስ ግዴታ በዐ/ህግ ላይ የሚያርፍ ይሆናል፡፡ ለእያንዳንዱ ወንጀል ምን
አይነት ማስረጃ ሊቀርብ ይገባል የሚለው እንደወንጀሉ አይነት፣ እንደ ተጠርጣሪው ተግባር
የሚለያይ ቢሆንም በስፋት በሚያጋጥሙ የወንጀል ተግባራት ላይ ምን አይነት ማስረጃ
ቢቀርብ በቂና አሳማኝ ነው የሚለውን መነሻዊ ምልከታ ማድረግና ጠንካራ የውይይት
ሀሳቦችን ማንሳት ጥራት ያለው ምርመራ ለማድረግ፣ በክስ ሂደት የሚያጋጥሙ በቂ
ማስረጃ የማይቀርብባቸውን ክሶች ለማስቀረት ፣ የተሻለ ጥራት ያለው ክስ ለመመስረት
የሚረዳ ይሆናል፡፡ ይህ ጽሑፍም መሠረት የሚያደርገው በተግባር በስፋት ችግር እየገጠመ
ካሉ ወንጀሎች መሀከል የተወሰኑትን በመለየት ሰፊ ውይይት ለማድረግ በሚል ሲሆን በዚህ
ጽሑፍ ከማታለልና ከእምነት ማጉደል ጋር በተያያዙ እየተነሱ ያሉ ችግሮችን በወፍ በረር
ቅኝት ለመዳሰስ የሚሞከር ይሆናል፡፡
1.በንብረት ላይ የሚፈፀም ወንጀል በጠቅላላው
የማታለልም ሆነ የእምነት ማጉደል ወንጀሎች በወንጀል ህጉ በመፀሀፍ ስድስት ውስጥ
በንብረት ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎች ውስጥ ተካተው ይገኛል፡፡ መፀሀፉ በሁለት ትላልቅ
ርዕሶች ስር ስድስት ምዕራፎችን ይዞ የተዋቀረ ነው፡፡ በመጀመሪያው ርዕስ ውስጥ ካሉት
ሦስት ምዕራፎች ውስጥ በሁለተኛው ምዕራፍ በሆነው በንብረት ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎች
በክፍል አንድ በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ በሚፈፀም ወንጀል ክፍል ውስጥ 19 የተለያዩ
ወንጀሎች የሚገኙ ሲሆን በዚህ ክፍል ውስጥ የእምነት ማጉደል ወንጀልም ተካቶ ይገኛል፡፡
[4]
በምዕራፍ ሶስት ከተመለከቱ በንብረት መብቶች ላይ በሚፈፀመው ወንጀሎች በክፍል አንድ
ላይ ማታለልን የተመለከቱ ድንጋጌዎች የተሸፈኑ ሲሆን ክፍሉ በውስጡ 13 አንቀፆችን
ይዟል፡፡ ከነዚህ አንቀፆች ውስጥ ለዚህ ጽሑፍ አላማ ሲባል በተደጋጋሚ በስራ ላይ
የሚያጋጥሙን ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ምልከታ ይደረጋል፡፡
1.1.አንቀፅ 692፡- አታላይነት
አንቀፅ 692 ላይ የተመለከተው የማታለል ወንጀል በስፋት በአዲስ አበባ የሚፈፀም ወንጀል
ሲሆን በድንጋጌው መሠረት ክስ ለመመስረት ህጉ በመስፈርትነት ስላስቀመጣቸው
ማቋቋሚያዎች፣ ለእያንዳንዱ በህጉ ለተቀመጡ ማቋቋሚያዎች ስለሚቀርቡ ማስረጃዎች
ማሳያ የሚሆኑ የክስና የምርመራ መዛግብትን በማመላከት ምልከታ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በአንቀፁ የአታላይነት ወንጀልን ለማቋቋም አራት መሰረታዊ ማቋቋሚያዎች ያሉ ሲሆን[5]
1ኛ) ተከሳሽ ሆን ብሎ የማይገባ ብልፅግና ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው
ለማስገኘት በማሰብ አሳሳች የሆኑ ነገሮችን በመናገር ፣ የራሱን ማንነት ወይም ሁኔታ
በመሰወር ወይም መግለፅ የሚገባውን ነገር በመደበቅ ወይም የሌላውን ሰው የተሳሳተ
እምነት ወይም ግምት በመጠቀም ፣ በማድረግም ሆነ ባለማድረግ የመግለፅ ተግባር
ከፈፀመ
2ኛ) በዚህ ድርጊት የተነሳ ተበዳዩ ከተታለለ ወይም በአጥፊው የተገለፀውን አምኖ
ሊቀበል ይገባዋል፡፡
3ኛ) በሀሰት የተገለፀውን በማመን የፈፀመው ተግባር መኖር አለበት
4ኛ) እንደዚሁም ተበዳዩ በመታለሉ የተነሳ የራሱ ወይም ሶስተኛ ወገን ያጣው የገንዘብ
ጥቅም መኖር መቻል አለበት፡፡
እነዚህ በህጉ በመስፈርትነት የተመለከቱት የህግ ማቋቋሚያዎች ስለመከሰታቸው
በማስረጃ በበቂና በአሳማኝ በሆነ ሁኔታ ከተረጋገጠ ተጠርጣሪው ላይ ከስ ማቅረብ
ይገባል፡፡ በተራ ቁጥር አንድ ላይ የተመለከተውን መስፈርት ለማስረዳት በተለይም አሳሳች
የሆኑ ንግግሮች ከሆኑ ከግል ተበዳይ ባለፈ ሌሎች ሰዎች ንግግሩን መስማት የሚገባቸው
ሲሆን ንግግሩ አሳሳች ስለመሆን አለመሆኑ እንደሁኔታው በአመዛዛኝ ሰው እይታ እየታዩ
ወይም ከግል ተበዳዩ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የሚመዘኑ ይሆናል[6]፣ አሳሳች ንግግር
የተናገረው ተጠርጣሪ የራሱን ስም፣ የስራ ሁኔታና መሰል ማንነትን በመቀየር የተገለፀ ከሆነ
እነዚህን ኩነቶች ሊያስረዱ የሚችሉ የሰነድ ወይም የሰው ማስረጃ ሊቀርብ ይገባል፡፡
ሌሎች በህጉ የተመለከቱ ሁኔታዎችንም ቢሆን እንደሁኔታው በሰውና በሰነድ ማስረጃ
ሊረጋገጡ የሚገባቸው ናቸው፡፡ በሁለተኛነት የተመለከተው የተበዳይ መታለል ወይም
ተከሳሹ የተናገረውን የማታለያ ተግባራትን አምኖ ተቀብሏል ለማለት በተራ ቁጥር ሶስትና
አራት ላይ የተመለከቱትን ተግባራት ከፈፀመ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ከተታለለ በመታለሉ
የተነሳ በንብረት ጥቅሙ ላይ ጉዳት የሚያደርስ ተግባር ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ለተግባራቱ
ከሚቀርቡ ማስረጃዎች መሀከል በመታለሉ የተነሳ በንብረት ጥቅሙ ላይ ጉዳት የሚያደርስ
ተግባር መፈፀሙን የተመለከቱ ሰዎች ወይም ከባንክ የሚመጡ የሰነድ ማስረጃዎችና
ሌሎች ማስረጃዎች ሊቀርቡ የሚችሉበት ዕድል አለ፡፡ የሚቀርቡ ማስረጃዎች ከጉዳይ
ጉዳይ የሚለያይ በመሆኑ ቁርጥ ባለ ሁኔታ ለመግለፅ አዳጋች ይሆናል፡፡ በተግባር
ከሚያጋጥሙ ጉዳዮች መሀከል፡፡
ሀ.በከሳሽ ዐቃቤ ህግና በተከሳሽ አየለ (ለዚህ ጽሑፍ አላማ ሲባል ስሙ የተቀየረ ተከሳሽ)
በነበረው የክስ ክርክር
ተከሳሹ አደረገ የተባለው ኮንትራክተር ሳይሆን ኮንትራክተር ነኝ በሚል አሁኑኑ ገንዘብ
አመጣለሁ በሚል ከግል ተበዳይ የሱቅ መደበር በመሄድ መጠኑ ስልሳ ኩንታል የሆነ
ሲምንቶ በመውሰድ የተሰወረ ስለሆነ በሚል በማታለል ወንጀል ተከሰሰ፡፡ በክሱ ላይ
የተመለከተውን የወንጀል ተግባር ለማስረዳት
• በተራ ቁጥር አንድ ላይ በተመለከተው መስፈርት መሠረት ተበዳዩ ወደ ውል ግንኙነቱ
ውስጥ ሊገባ ያስቻለው ተከሳሽ ኮንትራክተር ነኝ በማለት የተናገረው ንግግር ከሆነ ይህ
ንግግርም ሀሰተኛ ነው ለማለት እውነትም ተከሳሹ ኮንትራክተር ስለመሆን አለመሆኑ
ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ማረጋገጥ የሚገባ ሲሆን እነዚህ ተቋማት ተከሳሹ
በስሙ ምንም አይነት ፍቃድ ያላወጣ መሆኑን ካረጋገጡ ተከሳሽ የራሱን ማንነት
ኮንትራክተር ሳይሆን ኮንትራክተር ነኝ በሚል በመሰወር አሳሳች ቃል ተናግሯል ሊባል
ይችላል፡፡ የተከሳሽ ድርጊት በንግግር የሚፈፀም እንደመሆኑ መጠን ግን ከግል ተበዳይ
ውጭ ሌሎች ሰዎችም ንግግሩን መስማት ሊኖርባቸው ይገባል፡፡ ሌሎች ሰዎች እንኳን
ባይሰሙ ተከሳሹ በህገመንገስቱና በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ሰርአት ህጉ አግባብ ለፓሊስ
ወይም ለፍርድ ቤቱ እንደክሱ አቀራረብ በአማራጭነት ወንጀሉን ስለመፈፀሙ ሊያምን
ይገባዋል፡፡ በዚህ መሠረት ተከሳሽ ድርጊቱን በንግግሩ ስለመፈፀሙ ከግል ተበዳይ ውጭ
የሰሙ ምስክሮች፣ በክሱ ላይ የተገለፀውን መጠን ያህል ሲሚንቶንም ሰጥቶ በንብረት
መብቱ ላይ ጉዳት የደረሰበት ስለመሆኑ ፣ አሳሳች ነገር የፈፀመው ማንነቱን በመቀየር
እንደመሆኑ መጠን በትክክልም የኮንትራክተር ማንነት የሌለው ስለመሆኑ በቂና አሳማኝ
ማስረጃ ሊቀርብ ይገባል፡፡
• በዚህ የክስ መዝገብ ላይ አከራካሪ የነበረው በሁለቱ ወገኖች መሀከል የነበረው ግንኙነት
የውል እንደመሆኑ መጠን ድርጊቱ በማታላል ሳይሆን በውል ህጉ መሠረት ሊገዛ ይገባዋል
የሚል ነው፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ ምንም እንኳን የውል ግንኙነት አለ እንኳ ቢባል ወደ
ውል ግንኙነት የተገባው አሳሳች በሆኑ የተከሳሽ አድራጎት ከሆነና በዚያም የተነሳ ውሉ
ሊፈፀም የማይቻል ሲሆን ተከሳሹ ላደረገው ተግባር በማታለል አይጠየቅም ማለት ነው ?
በውል መሠረት ላልተፈፀመ ግዴታው መጠየቅ በወንጀል ህጉ መሠረት በማታለል
ለመጠየቅ ያግዳል ወይ የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳትና መጠየቅ ያሻል?
ለ.በከሳሽ የፌደራል ዐቃቤ ህግና በተከሳሽ አቶ ጌታሁን መሀከል ባለው የክስ ክርክር
ተከሳሽ በቀን 13/2/2012 ዓ.ም ከቀን 30/2/2012 ዓ.ም ጀምሮ የሚመነዘር ገንዘብ
የያዘ ቼክ ከተበዳዩ በብድር ለወሰዱት ዕቃ ክፍያ በሚል በስማቸው በመፃፍ ፈርመው
የሰጡ ሲሆን የግል ተበዳዩ ቼኩ ለክፍያ በሚያቀርብበት ጊዜ ቼኩ በቀን 11/12/2011
ዓ.ም በተደጋጋሚ ተከሳሹ በቂ ስንቅ የሌለው ቼክ በማቅረባቸው ወይም ለረጅም ጊዜ
ባለመንቀሳቀሱ የተነሳ ተዘግቷል በሚል ምላሽ በመስጠቱ የተነሳ በማታለል ወንጀል ክስ
ቀርቦባቸዋል፡፡ ክሱን ለማስረዳት የቀረቡ ማስረጃዎች
• የግል ተበዳይና ሌላ አንድ የሰው ምስክር
• ተከሳሹ የሰጠው ቼክና የባንኩ መግለጫ
• ቼኩን ተከሳሹ ራሱ ባወጣው አካውንት ወይም የወንጀል ድርጊቱ በሚፈፀም ጊዜ ላይ
በውክልና የሚያስተዳድረው ስለመሆኑ ከባንክ ህጋዊ የውክልና ማስረጃ
• ቼኩ ለክፍያ በሚደርስበት ወይም ለክፍያ በቀረበበት ጊዜ በቂ ስንቅ የሌለው ስለመሆኑ
የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነበር፡፡
ሆኖም ግን የምርመራ መዝገቡ ላይ በተግባር ያጋጠመው ችግር ምንም እንኳን ተከሳሹን
በማታለል ወንጀል መክሰስ የሚቻል ቢሆንም ተከሳሹ ባደረገው ድርጊት ተከሳሹ የማታለል
ሀሳብ አለው ለማለትና የግል ተበዳይን ቼኩ ገንዘብ አለው ወይም ወደ ባንክ ብወስደው
ገንዘብ በባንኩ ይሰጠኛል የሚለውን እምነት በማታለል ተግባር አታሏል ለማለት ቼኩ
የሚንቀሳቀስበት አካውንት ስለመዘጋቱ ባንኩ ለተከሳሹ ስለማሳወቁ አለመረጋገጡ ነበር፡፡
ባንኩ መዘጋቱን ለተከሳሹ ካሳወቀው የተከሳሹ ተግባር በድርጊት ማድረግ የሌለበትን
ክልከላ የተበዳዩን የተሳሳተ እምነት በመጠቀም የማታለል ተግባር ፈፅሟል ለማለት
ይቻለል፡፡ ከዚህ አንፃር ተከሳሹ ስለመዘጋቱ የሚያውቅ ነበር የሚያስብል ማስረጃ ሊቀርብ
ይገባል፡፡ በዚህ ተግባሩ የተነሳ ተበዳዩ ስለመታለሉ ደግሞ በንብረት ጥቅሙ ላይ በቼኩ
መሰጠት የተነሳ የሚጎዳ ተግባር እንደፈፀመ በሰውና በሰነድ ማስረጃ ማስረዳት ይቻላል፡፡
በተለይ መሰል ተግባራት በማታለል የወንጀል ተግባር ውስጥ የሚያርፉ ቢሆንም ነገር ግን
በቼክ የማታለል ወንጀል ውስጥም(በአንቀፅ 693) ሊያርፍ የሚችልበት ዕድል አለ፡፡ ይህም
የሚሆነው በተለይም ቼኩ ለክፍያ በሚደርስበት ወይም ለክፍያ በሚቀርብበት ጊዜ በቂ
ገንዘብ ስላለመኖሩ በባንክ የተረጋገጠ ከሆነ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ግን የራሱ ውስንነት
አለበት እርሱም ቼኩ የተዘጋ ከሆነ ከመነሻው አካውንት ውስጥ ስላለው ገንዘብ ማጣራት
አስፈላጊ አይደለም የሚለው ነው፡፡ ይህ አጠራጣሪ ሁኔታ የሚያጋጥም ሲሆን በስነ ስርአት
ህጉ አንቀፅ 113 መሠረት ዋና ክሱን በቼክ በማታለል ወንጀል በመከሰስ በአማራጭ
በማታላል ቢከሰስ አግባብ ይመስላል፡፡
ሐ.ከሳሽ የፌደራል ዐቃቤ ህግ እና ወ/ሮ አልማዝ (ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ስማቸው የተቀየረ)
በዚህ የክስ መዝገብ ከሳሽ የፌደራል ዐቃቤ ህግ ለክሱ መነሻ ያደረገው ተከሳሽ ከአምስት
አመት በፊት የተሰጣትን ውክልና የግል ተበዳይ ከሻረችባቸው በኋላና ስለመሻረሙም
በሶስት ምስክሮች ፊት መሻሪያውን ካነበብላቸው በኋላ ተከሳሽ በውክልና ሲያስተዳድሩት
የነበረውን ንበረት ለሶስተኛ ወገን ሸጠዋል በሚል በማታለል ወንጀል ነው፡፡ የውክልናው
ማስረጃ የተሻረው በውጭ ሀገር ሆኖ ምንም እንኳን በሚመለከተው በሀገር ውስጥ
በሚገኘው የውልና ማስረጃ ተቋም ባይመዘገብም ተከሳሽ ግን ስለመሻሩ ታውቅ ነበር፡፡
በማስረጃ ዝርዝር ውስጥ በክሱ አግባብ የሰውና የሰነድ ማስረጃ የቀረበ ቢሆንም በክስ
ክርክሩ አከራካሪ የነበረው የተከሳሽ ድርጊት ንብረቱን የገዙትን ሰዎች አላሳሰትም የሚል
ነበር ምክንያቱም ንብረቱን የገዙት ሰዎች ቤቱን ሲገዙ በውልና ማስረጃ የተከሳሽ ውክልና
(ተከሳሽ ሌላ ሰው የወኩለበት የውክልና ውክልናም) አልተሻረም የሚል ነው፡፡
በድርጊት ደረጃ ተከሳሽ ውክልናው መሻሩን እያወቀች ሌላ ውክልና በንብረቱ ላይ ሰጥታ
ንብረቱ እንዲሸጥ ማድረጓ መግለፅ የሚገባትን ነገር በመደበቅ በመስፈርት አንድ ላይ
የተመለከተውን ተግባር አሟልታለች ቢባልም በዚህ ጊዜ ግን ንብረቱን የገዙት ሰዎች
በራሳቸው ባረጋገጡት መሠረት ውክልና ስለመሻሩ በሚመለከተው የመንግስት አካል
ባለመመዝገቡ የተነሳ አልተታሉም የሚል ክርክር ይነሳል፡፡ ከዚያም ባለፈ ገንዘባቸውንና
ቤታቸውን ለማግኘት በህግ ጥረት እያደረጉ ስለሆነ ያጡት የገንዘብ ጥቅም የለም የሚባል
ክርክር እየተነሳበት ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በተከሳሽዋ ተግባርና በገዢዎች መግዛት
ውክልናውን ያነሳች የግል ተበዳይ የሆነችው ሶስተኛ ወገን ጥቅሟ ስለተጎዳባት ተከሳሽ
በማታለል ልትጠየቅ ይገባል የሚል ሀሳብ ይነሳል፡፡
1.2.እምነት ማጉደል
የእምነት ማጉደል ወንጀል ከማታለል የሚለይበት መሰረታዊ ነገር
1.በእምነት ማጉደል ወንጀል ተከሳሽ(ተጠርጣሪ) ንብረቱን እንዲሰጠው ተበዳዩን
የሚናገረው ወይም የሚያደርገው ተግባር የለም፡፡ ንብረቱ ወደ ተከሳሹ እጅ እንዲገባ
ተበዳዩ ዋናው ምክንያት ነው፡፡ በማታለል ጊዜ በተበዳይ የንበረት መብት ጥቅም ላይ
የመነሻ ድርጊት የሚመጣው ከተከሳሽ በተለያየ መልኩ በሚገለፅ የማታለል ተግባር ነው፡፡
በውስን ሁኔታዎች በእምነት ማጉደል በሚፈፀሙ ወንጀሎች ተጠርጣሪዎች በሚያደርጓቸው
ተግባራት ተበዳይ የንብረት መበት ጥቅማቸው ላይ ጉዳት የሚያርሱበት ሁኔታ ቢኖርም ይህ
ሊያጋጥም የሚችለው ግን በተበዳይና በተጠርጣሪ መሀከል ጥብቅ የሆነ ግንኙነት ሲኖር
ነው፡፡ ለምሳሌ ሁለት ጓደኛሞች በጣም ለረጅም ጊዜ በጓደኝነት በሚያሳልፉበት ሁኔታ
አንደኛው ጓደኛ ንብረት ጠይቆት በሌላኛው ጓደኛ ቢሰጠው ንብረቱን የሰጠው ሰው ተታሎ
ሳይሆን ካላቸው የእርስ በእርስ መተማመን ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ በዚህ ጊዜ ከማታለል
ይልቅ የእምነት ማጉደል ተግባራቶች ተፈፅመዋል ሊባል ይችላል፡፡
2.በማታለል ጊዜ ተበዳዩ በመታለሉ የተነሳ ነው የንብረት ጥቅሙ ላይ ጉዳት የሚደርሰው፡፡
በእምነት ማጉደል ወቅት ግን የንብረት ጥቅም ላይ ጉዳት የሚደርሰው ተበዳዩ ንብረቱን
በአደራ ወይም ለአንድ አግልግሎት በራሱ ተነሳሽነት ሰጥቶ ተከሳሽ አደራውን በማጉደሉ
የተነሳ የሚኖር የንብረት ላይ ጉዳት መድረስ ነው፡፡ ተከሳሽ አንድ ጊዜ አስደውለኝ በሚል
ከተከሳሽ ላይ ስልክ ቢወስድና ስልኩን ይዞ ቢሰወር ተበዳዩ ስልኩን የሰጠው በተከሳሹ
ንግግር የተነሳ ይመልስልኛል በሚል እምነት ተታልሎ ነው እንጂ በአደራ መልክ
እንዲጠብቅለት ወይም ለአንድ ለተወሰነ አገልግሎት በራሱ አነሳሽነት የሰጠው ባለመሆኑ
በእምነት ማጉደል ሊከሰስ የሚገባው አይሆንም፡፡ (ውይይት ሊደርገበት ይችላል)
የእምነት ማጉደል ወንጀል በመሰረታዊነት ለማቋቋም በወንጀል ህጉ አንቀፅ 675 ላይ
የተመለከተው መስፈርት
1.ተከሳሹ ተገቢ ያልሆነ ብልፅግና ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በሚል
1.1.የሌላ ሰው የሆነውንና ለአንድ ለተወሰነ አገልግሎት ወይም በአደራ የተሰጠን ዋጋ
ያለውን ተንቀሳቃሽ ነገር ወይም ጥሬ ገንዘብ በሙሉ ወይም በከፊል ለራሱ ወይም ለሌላ
ሰው ያደረገ ወይም የወሰደ፣ ያስወሰደ፣ የሰወረ ለአንድ የተወሰነ አገልግሎት የተሰጠውን
ዕቃ ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው አገልግሎት ያዋለ
1.2.ተከሳሹ ላልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲባል አደራውን አጉዱሏል ለማለት በተለየ ሁኔታ
በአደራ የተሰጠውን እቃ ወይም ጥሬ ገነዘብ ሲጠየቅ ለመክፈል ወይም ለመመለስ፣ ዕቃው
ያለበትን ቦታ ለማሳየት ወይም ለተገቢው አገልግሎት ስለማዋሉ ለማስረዳት ካልቻለ ብቻ
ነው ላልተገባ ጥቅም ሲባል እምነት አጎደለ የሚባለው፡፡ ተከሳሹ ሲጠየቅ እከፍላለሁ
ወይም እመልሳለሁ ካለ በእምነት ማጉደል የማንጠይቀው ሲሆን ዕቃውን ለተገቢው
አገልግሎት አውየዋለሁ የሚልም ከሆነ የግድ ማጣራትና መመርመር ይገባል፡፡
1.3.በአደራ የተረከብኩት ንብረት ጠፍቶብኝ ነው ፣ ተሰርቆብኝ ነው የሚባሉ ምላሾች
ተከሳሹን ነፃ ለማውጣት መስፈርት አይሆንም፡፡
1.4.ለአንድ አገልግሎት የተሰጠን ዕቃ ላልተገባ አገልግሎት ለራሱ ወይም ለሶስተኛ ወገን
መጠቀሙ የተረጋገጠበት ሰው በ675(3) ስር የተመለከተውን መከላከያ ተጠቅሞ
ለማጣራት መሞከር ከግምት የሚገባ አይሆንም፡፡ (ህጉ በአደራ የወሰደውን እቃ ወይም
ጥሬ ገንዘብ በሚል አመለከተ እንጂ ለአንድ ለተወሰነ አገልግሎት የተሰጠን ዕቃ ወይም
ገንዘብ አለማለቱ ታሳቢ ተደርጓል)
1.5.በጥገና ውል፣ በመጓጓዝ ውል፣ በኪራይ ውል፣ በብድር የሚወሰድ ገንዘብ፣ በዕቃው
ስራ በመስራት ገንዘብ ለማስገባት በሚል ከአሰሪ ሰራተኛ ቅጥር ውጭ ባለ የውል ግንኙነት
የሚወሰዱ ዕቃዎች ውልን መሠረት ተደርገው የተወሰዱ ገንዘቦች ወይም እቃዎች አደራ
ላይ መሠረት ተደርገው ወይም ያለውል ለአንድ ለተወሰነ አገልግሎት ያልተሰጡ
በመሆናቸው የተነሳ በእምነት ማጉደል ወንጀል ሊያስጠይቁ የሚችሉ አይሆንም፡፡
1.6.ነገር ግን በውክልና ውል ግንኙነት ተወካይ ፣ በስራ ምክንያት ሰራተኛ ምንም እንኳን
የአሰሪ ሰራተኛ የውል ግንኙነት ቢኖርም፣ የህግ ወይም የገንዘብ አማካሪ (ጠበቃ፣ የንብረት
አስተዳዳሪ ፣ ሂሳብ አጣሪ )አገልግሎት ለመስጠት በሚል የአገልግሎት የውል ግንኙነት
ቢኖራቸውም በዚህ ግንኙነት የተነሳ የተረከባቸው ንብረቶች፣ ገንዘብ ወይም ለአንድ
ለተወሰነ አገልግሎት ተብሎ የተሰጠውን ዕቃ ለራስ ማድረግና መሰል በህጉ የተከለከሉ
ተግባትን መፈፀም በወንጀል የሚያስጠይቅ ይሆናል፡፡ (የወንጀል ህጉ አንቀፅ 676 ላይ
በተመለከተው መሠረት)
አንቀፁን ከመተግበር አንፃር በተግባር የሚያጋጥሙ ችግሮች
1.ተከሳሾ በፓሊስ ጣቢያ ሲጠየቁ በተለይም ለአንድ ለተወሰነ አግልግሎት የተሰጣቸውን
ገንዘብ ለተባለው አገልግሎት እንዳዋሉት ጠቅሰው ሳለና ይህንንም የሚያስረዳ የሰውና
የሰነድ ማስረጃ እንዳላቸው እየጠቆሙ ለማጣራት ያለመሞከር፡፡ የእምነት ማጉደል ወንጀል
ልዩ ባህሪይ በተለይም ተከሳሾች በአደራ ስለተሰጣቸው ዕቃዎች ወይም ጥሬ ገንዘብ የግድ
መጠየቅ ያለባቸው ሲሆን ከሚሰጡት ምላሽ በመነሳት ዕቃውን ለመመለስ ወይም
ለመክፈል የሚስማሙ ከሆነ ወይም በአደራ የተሰጣቸውን ዕቃ ለተባለው አገልግሎት
ማዋላቸውን ከተናገሩ ማጣራትና ማስረጃቸውን በዝርዝር በመመልከት አስቀድሞ
በማጥራት ውሳኔ ሊሰጥ ይገባል፡፡ ተከሳሾች የሰጡትን ቃል ባለማጣራት የተነሳ ለፓሊስ
የእምነት ቃል ሲሰጡ በአደራ የወሰዱትን ዕቃ ለተገቢው አለማ አውለናል በሚል
ያመለከቷቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ በፍርድ ቤት በማቅረብ ተገቢውን ፍትህ ማግኘት
ቢችሉም ነገር ግን አስፈፃሚው አካል አስቀድሞ በማጣራት የተከሳሾችን መጉላላት
መቀነስ ይቻላል፡፡
2.በህጉ የተመለከተውን ‹‹ተከሳሾች ሲጠየቁ›› የሚለው አገላለፅ አንዳንድ ጊዜ
ለመተርጎም አስቸጋሪ መሆን፡፡ በፓሊስ ጣቢያ ሲጠየቅ በቂ ምክንያት ሳያቀርብ ቀርቶ ክስ
ከተመሰረተ በኋላ ፍርድ ቤቱ ሲጠይቀው እከፍላለሁ ወይም ሌላ ነገር ቢል መዝገቡ
ሊቋረጥለት ወይም ፍርድ ቤቱ ክሱን ሊያቋረጥው ይገባል ወይ የሚለው አከራካሪ ሲሆን
ይስተዋላል፡፡ ሲጠየቅ የሚለው በየትኛው ደረጃ ነው የሚለው በግልፅ ያልተመለከተ
መሆን፡፡ በዚህ ፀሀፊ እምነት ተጠርጣሪው/ተከሳሹ ሲጠየቅ የሚለው የህጉ አነጋገር
ለመተርጎም ከመነሻው ተጠርጣሪው የት እና በማን፣ በምን ሁኔታ ነው ሊጠየቅ የሚችለው
የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ተጠርጣሪው በሶስት ሁኔታዎች በአደራ ስለተረከበው ወይም
ለአንድ አገልግሎት ስለተሰጠው ዕቃ ወይም ገንዘብ በሶስት ሁኔታዎች ሊጠየቅ ይችላል፡፡
አንደኛ አደራ የሰጠው ሰው የሚጠይቅበት ሁኔታ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በፓሊስ ጣቢያና
በፍርድ ቤት በምርመራ ወቅት እንዲሁም በስተመጨረሻ በፍርድ ቤት በክርክር ወቅት
የእምነት ክህደት ቃል በሚጠየቅበት ጊዜ ነው፡፡ በተበዳይ የሚቀርብ ጥያቄ ትልቁ ምክንያት
ተጠርጣሪ አደራውን በልቷል ወይስ አልበላም የሚለውን በግል ግንኙነታቸው መሠረት
ለማጣራት ሲሆን በዚህ ወቅት ተጠርጣሪው አደራውን አለመብላቱን ካሳወቀና ካስረዳው
ከመነሻው እምነት አጎደለ ሊባል አይችልም፡፡ በምርመራ ወቅት የሚቀርብ ጥያቄ አላማው
ተጠርጣሪ የሆኑ ሰዎች ወንጀሉን ፈፅመዋል ወይም አልፈፀሙም የሚለውን እውነታ
ለማጣራት ሲሆን በዚህ ወቅት ተጠርጣሪው እምነቱን እንዳላጎደለ በተለያየ መልኩ ካስረዳ
ከምርመራ አላማ አንፃር ተጠርጣሪው ወንጀሉን አልፈፀመም ፡፡ ስለዚህም በህጉ
የተመለከተው ‹‹ሲጠየቅ›› የሚለው ትርጉም እስከዚህ ደረጃ ያሉ መጠየቆችን በማካተት
ተጠርጣሪን ነፃ ማድረግ ይቻላል፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው ሶስተኛው መጠየቅ ግን ተከሳሹ
ጥፋተኛ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለመወሰን የሚደረግ ጥያቄ በመሆኑ የተነሳ ምንም
እንኳን ተከሳሹ መልሻለሁ ፣ ለተገቢው አገልግሎት አውያለሁ ቢልም መዝገቡ ሊቋረጥለት
የሚገባ አይሆንም፡፡ በፍሬ ነገር ደረጃ ምርመራ እስከሚደረግ ባለው መጠየቅ በአደራ
የተሰጠውን እቃ ወይም ንበረት መመለሱን ወይም ለመክፈል ወይም ለተገቢው አለማ
ስለማዋሉ ካስረዳ ከመጠየቅ ነፃ ከሚሆን በስተቀር በፍርድ ደረጃ ያሉ መመለሶች ወይም
ያንን እንደሚያደርግ መግለፁ ነፃ ሊያደርገው አይገባም፡፡ በዚህ ደረጃ ያሉ ራስን
ለመከላከል የሚገለፁ ሁኔታዎች አደራን ካለመፍራት ሳይሆን ፍርድ ቤት የሚጥልበትን
ቅጣት እንዳይጣልበት ከማድረግ የሚመጬ ይመስላል፡፡
3.በስተመጨረሻም ምንም እንኳን ሁለቱም ወንጀሎች በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ
በሚፈፀሙ የወንጀል ምዕራፍ ውስጥ የሚገኙ ቢሆንም ከአተገባበር አንፃር የሚያጋጥሙ
ወጣ ገባዎችን በአፅኖት በመመልከትና ችግሮችን በመፍታት ወደ ወጥነት የቀረበ ውሳኔ
መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ማድረግ የወንጀል ፍትህ ስርአቱን ከውሳኔ አሰጣጥ አንፃር
ተገማች እንዲሆን ለማድረግ የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ አለው፡፡
የግርጌ ማስታወሻ
[1] .በተከሳሹ በኩል ከክሱ ነፃ ለመውጣት የሚያስፈልገው ምክንያታዊ የሆነ ጥርጣሬን
ሊፈጥር የሚችል ማስረጃ ማቅረብ ብቻ ነው፡፡
[2] .በሀገራችን የወንጀል ህግን የያዙ ድንጋጌዎች በርካታ መሆናቸው የተጠበቀ ሆኖ
የወንጀል ስነስርአትን የሚገዙ ህጎች ከወንጀል ስነስርአት ውጭ በሌሎች ህጎችም
ተደንግገው ይገኛል፡፡በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ ከተመለከቱት አንቀፅ
141፣142፣149 በመነሳት የስነስርአት ህጉ ከማስረጃ መመዘኛ መርሆች ውስጥ በቂና
አሳማኝ የሚለውን የማስረጃ ማቅረብና አመዛዘን መርህን የተከተለ ይመስላል፡፡ነገር ግን
ይህ እይታ በተለይም በህገ መንግስቱ አንፅ 20(3) ማንም ሰው በፍርድ ቤት ጥፋተኛ
እስኪባል ንፁህ ሆኖ ይገመታል ከሚለው እሳቤ አንፃር የመጀመሪያው የማስረጃ ምዘና
መርህ ነው በሀገራችን የስነ ስርአት ህግ የተደነገገው የሚል ምልከታም ይታያል፡፡በነዚህ
መርሆች መሰረት ለእያንዳንዱ ወንጀል ምን አይነት ማስረጃ ነው መቅረብ ያለበት የሚለውን
ለመለየት አስቸጋሪ ቢሆንም ነገር ግን ከሚቀርበው ማስረጃ አይነትና ከአመዛዘን ጥብቅነት
አንፃር የመመዘኛ መርህዎቹ ልዩነት ያለቸው ስለመሆኑ ግን መረዳት ይቻላል፡፡
[3] .ይህ መንገድ ብዙ ጊዜ በፍትሐብሔር ክርክር ወቅት የሚሰራ የማስረጃ ምዘናና
ማቅረቢያ መንገድ ነው የሚል እሳቤ ይታያል፡፡
[4] .የወንጀል ህጉ አንቀፅ 666 (የሀይል ስርቆት) በአዋጅ ቁጥር 810/2006 በሆነው
ስለኢነርጂ በወጣ አዋጅ አንቀፅ 28 የኤሌትሪክ ሀይል መስረቅ የተሻረ ሲሆን፣ አንቀፅ 684
በአዋጅ ቁጥር 798/10 የተተካ ድንጋጌ ነው፡፡
[5] .የሰበር መዝገብ ቁጥር 104923፣ (ቅፅ 19) በገፅ 242 ላይ ይመልከቱ

23/06/2020

ያ ለመያዝ እና ያለመታሰር መብት
===========================
“የነፃነት መብት” መርህ ሲሆን “መያዝና መታሰር” ልዩ ሁኔታ ነው!”
መግብያ
መያዝ እና መታሰር በህግ ተለይተው በተቀመጡ ምክንያቶች እና በግልጽ በተዘረጋው
ስርአት መሰረት በጥንቃቄ የሚከናወን ልዩ ሁኔታ ሲሆን ነፃነት መርህ ነው! የነፃነት መብት
በተለያዩ አለምአቀፍ የሰብአዊ መብቶች ህግጋት፣ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች
ሰምምነቶችና ሰነዶች መደንገጋቸውን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በኢፌድሪ ህገ መንግስት ምእራፍ
ሶስት “መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች” በሚል ርእስ በአንቀጽ 17 ስር ተደንግጎ የሚገኝና
“የሰው ልጅ” ሰው በመሆኑ ብቻ በተፈጥሮ ከተሰጡት ሰብኣዊ መብቶች አንዱ ነው፡፡
የነጻነት መብት በዚሁ ህገ-መንግስት እና ሌሎች ህጎች ላይ የተደነገገው እንደ
መንግስታዊ ስጦታ እንዲቆጠር ታስቦ ሳይሆን ሰዎች በተፈጥሮ ያገኙዋቸውን ሰብኣዊ
መብቶች መንግስት እንዲያከብርና እንዲያስከብር ግዴታ ለማስገባት ነው፡፡ ምክንያቱም
መንግስት ሰብኣዊ መብቶችን መስጠት ሆነ መንጠቅ አይችልም፤እውቅና
መስጠት፣ማክበርና ማስከበር ግን አለበት፡፡ይህ ማለት ግን የነጻነት መብት ፍጹም እና
በህግ ሊገደብ የማይችል ነው ማለት አይደለም፡፡
በዚህ አጭር ጽሁፍም የነጻነት መብት አጠቃላይ መርህ እና የነፃነት መብት የሚገደብበት
ልዩ ሁኔታዎችን መሰረት ባደረገ መልኩ ያለመያዝ እና ያለመታሰር መብት ከህግ አንጻር
የሚተረጎምበት አግባብ በተለይም ደግሞ በወንጀል ተግባር ተጠርጥረው በህግ የሚፈለጉ
ተጠርጣሪዎችን ስለሚያዙበትና የሚታሰሩበት ህጋዊ ምክንያቶችን እና ስነስርአታዊ
አካሄዶችን ከአለምአቀፍ ህጎችና ልምዶች እንዲሁም ከኢትዮጵያ ህጎች አንጻር በመቃኘት
አጭር ዳሰሳ ለማድረግ እሞክራለሁኝ፡፡
ማንኛውም የሰው ልጅ ፍጡር በየትኛውም ግዜ፣ቦታ እና አካል ሊገሰስ ሆነ ሊገፈፍ ወይም
ሊደፈር የማይችል በተፈጥሮ የታደለውን የነፃነት እና የአካል ደህንነት መብት አለው ፡፡
ሁሉም ሰብአዊ መብቶች እርስ በእርሳቸው ፍጹም የማይበላለጡና የማይነጣጠሉ ፣እኩል
እና የሚደጋገፉ መሆናቸውን እንደተጠበቀ ሆኖ የነፃነትና የደህንነት መብቶችን ግን በሂወት
ከመኖር መብት ቀጥለው ቁልፍና መሰረታዊ የግለሰቦች መብት ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
ምክንያቱም የነጻነት እና የደህንነት መብቶች ሳይከበሩ ሌሎች መሰረታዊ የሰው ልጅ
መብቶች ይከበራሉ ማለት ዘበት ነው፡፡ በመርህ ደረጃ ሁሉም ሰብኣዊ መብቶች እርስ
በእርሳቸው የተሳሰሩ፣የሚደጋገፉ እና ፍፁም ሊነጣጠሉ የማይችሉ በመሆናቸው የአንድ
ሰብኣዊ መብት ጥሰት ለሌሎች ሰብኣዊ መብቶችን መከበር አደጋ ላይ የሚጥል እና
በውጤት ደረጃ ሁሉንም ሰብኣዊ መብቶችን የሚበክል እንደ ወረርሽኝ በሽታ በቀላሉ
የሚሰራጭ ነው፡፡ ወረርሽኝ በሽታ ነው ያልኩበት ዋና ምክንያት፡- አንድ የመብት ጥሰት
ከተጀመረ በሌሎች መብቶች ላይ የሚበተነው መርዝ በቀላሉ የማይቆም በጅምላ የሰብኣዊ
መብቶች ጥሰት ስለሚያስከትል በመሆኑ ሲሆን በተለይ ደግሞ መንግስት መሰረታዊ
መብቶችንና ነጻነቶችን የማክበርና የማስከበር ሃላፊነቱን በአግባቡ ከመወጣት ይልቅ
ለሰብኣዊ መብት ጥሰቶች ራሱ መሪ ተዋናይ በሚሆንባቸው ጉዳዮች ላይ ጉዳቱ ከፍተኛና
አደገኛ ነው፡፡
ጉዳዩ ግልጽ ለማድረግ ያህል፤ የጤና መብት ያልተከበረለት፣የምግብ ዋስትና
ያልተረጋገጠለት፣የመኖርያ/ የመጠልያ መብት ያልተመቻቸለት ግለሰብ በሂወት የመኖር
መብቱንም እንደሚነካ የሚያከራክር ጉዳይ አይሆንም፤ በተጨማሪ የደህንነት መብቱን
ያልተረጋገጠለት ወይም ሙሉ ዋስትና ያልተሰጠው ግለሰብ በሂወት የመኖር መብቱንም
አደጋ ላይ መውደቁ የማይቀር ነው፡፡በተመሳሳይ መልኩ ከህግ ውጭ ነጻነቱን የታፈነ
ግለሰብ አያሌ መሰረታዊ መብቶቹ ሊነጠቅ ይችላል፤ለምሳሌ በተገቢው ጊዜ ፍርድቤት
ያለመቅረብ በደል፣ የህግ አማካሪ የማግኘት መብትን መንፈግ ፣በቅርብ ቤተሰቡ እና
ጓደኞቹ እንዳይጎበኝ ማድረግ እንዲሁም ሌሎች ግፎች ፣ድብደባዎች፣ግርፋቶች፣ ኢ-
ሰብኣዊ እና ክብሩን የሚያዋርዱ አያያዞች ሊደርስበት ይችላል፡፡ምክንያቱም ከጅምሩ ከህግ
ውጭ የተያዘ እና የታሰረ ሰው ከዚህ ቀጥለው ለሚደርሱበት የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን
ህግ በመሀል ጣልቃ ገብቶ ያስቆማል ወይም ዋስትና ይሰጣል ብሎ ለመከራከር
እምብዛም የሚያስተማምን አይሆንም፡፡ በሌላ አገላለጽ ከመጀመርያ ጀምሮ ከህግ ውጭ
የተከናወነ የመያዝ እና የማሰር ተግባር ሆኖ እያለ ቀጥሎ የሚከናወነው ሂደት እና ውጤት
ህጋዊ ሊሆን ይችላል ብሎ መናገር ምኞት ከመሆን አይዘልም፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ የሰብኣዊ መብቶች ተማጓች አካላት በሚያቀርቡት የተለያዩ ጥናቶች
መሰረት በአለም ሃገራት ካለምንም በቂ ምክንያት ለእስር እና ለሌሎች የሰብአዊ መብት
ጥሰቶች የሚጋለጡ ሰዎች ቁጥራቸው እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ ከህግ ውጭ
ከተያዙ እና ለእስር ከተዳረጉ በኃላም ቢሆን አካላቸውን ነጻ ስለሚወጣበት እና በህግ
መሰረት መብታቸውን የሚያስከብሩበት እድል እንደማይሰጣቸው ይጠቁማሉ፡፡ለመሆኑ
ከህግ ውጭ መያዝ እና ማሰር ምንድን ነው?የህጋዊነት መርህስ ምን ማለት ነው? የሚሉ
መሰረታዊ ጥያቄዎችን እንደሚከተለው ይዳሰሳሉ፡፡
1) የህጋዊነት እና የኢ-ህጋዊነት (lawfulness and arbitrariness) ፅንሰ-ሀሳባዊ
እና ህጋዊ ትርጉም
1.1) ህጋዊነት (Lawfulness)
ማንኛውም ግለሰብ ነፃነቱ ሊገፈፍ ወይም ሊጣስ የሚችለው በግልጽ ተለይተው
በተቀመጡ የህግ ማእቀፎች እና ህግን በተከተለ መንገድ በሀገሪቷ በተዘረጋው ስርአት ብቻ
በማከናወን ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ከህግ ውጭ ነጻነቱን ሊገፈፍ ከቶ አይቻልም፣በህግ
ባልተከለከለ ጉዳይ ሰዎችን ማሰር ፍጹም የተከለከለና ህገ-ወጥ ተግባር ነው፡፡ ስለሆነም
የህጋዊነት መርህ ማለት አንድ ተግባር ወንጀልነቱ እና አስቀጭነቱ በግልጽ በህግ
የተደነገገ መሆን እንዳለበት የሚያስገነዝብ የወንጀል ህግ አጠቃላይ መርህ ነው፡፡ ይህን
የህጋዊነት መርህ ወደ ጎን በመተው ማለትም በህግ መሰረት ወንጀልነቱን እና አስቀጭነቱን
ባለተደነገገ ጉዳይ ሰዎችን የመያዝ እና የማሰር ተግባር ከተከናወነ ውጤቱ ኢ-ህጋዊነት
ብቻ ሳይሆን መሰረታዊ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰትም ነው፡፡ ሀገራት የህጋዊነት መርህን
ባልተከተለ መልኩ በግለሰቦች ላይ የመያዝና የማሰር ተግባር ያከናወኑ እንደሆነ በአለም
አቀፍ ህጎች መሰረት ተጠያቂ ናቸው፡፡
ከህግ ውጭ መያዝ እና ማሰር ምንነትና ይዘት፤ ዋና ዋና አንጓዎች(መገለጫዎች)እን
ዲሁም እንዲህ አይነት ህገ ወጥ ተግባራትን የምንከላከልበት የመፍትሄ አቅጣጫዎች
ተገቢነት ካላቸው የተለያዩ ህጎች ጋር በማገናዘብ እንደሚከተለው ሰፋ አድርጌ ለማቅረብ
እሞክራለሁኝ፡፡
1.2) ከህግ ውጭ ማሰር (Arbitrariness)
ከህግ ውጭ ማሰር ማለት የህግ የበላይነትን በመጣስ ወይም ህግን እና ስርአትን
ባልተከተለ መልኩ ሰዎችን መያዝ እና ማሰር ማለት ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት
የሰብአዊ መብት ኮሚቴ ደግሞ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች አለምአቀፍ መግለጫ
በአንቀጽ 9(1) ላይ የተደነገገውን ይዘት ሰፋ ባለ መልኩ እንደሚከተለው ያብራራዋል፡፡
“Arbitrariness is not to be equated with against the law; but must be
interpreted more broadly to include elements of inappropriateness,
injustice, lack of predictability and the due process of law.”
ይህ የእንግሊዘኛ አነጋገር ወደ አማርኛ ሲመለስ “ከህግ ውጭ ማሰር ማለት በህግ
የተደነገገውን ክልከላ በመተላለፍ ወይም ህግን በጣሰ መልኩ ሰዎችን ማሰር ብቻ ሳይሆን
አግባብነት በሌለው ፣ፍትሃዊነት በጎደለው ፣ሊተነበይ ወይም ሊገመት በማይችል ምክንያት
ሰውን መያዝ እንዲሁም ህግን ባልተከተለ አሰራር ማሰርን” በሚያካትት መልኩ በሰፊው
መተርጎም እንዳለበት ገልል (ትርጉም የራሴ)፡፡
በተጨማሪም አንድ ሰው በህግ አግባብ የተያዘ ቢሆንም የተያዘበትን ጉዳይ በህግ መሰረት
የዋስትና መብት የማያስነፍግ ሆኖ እያለ ፖሊስ ምክንያታዊነት በጎደለው እና አስፈላጊነቱን
ወይም ወቅታዊነቱን ሳያገናዝብ ተጠርጣሪው በፍርድቤት እያስቀረበ ተጨማሪ የቀጠሮ
ጊዜ በመጠየቅ በእስር እንዲቆይ ማድረግ ከህግ ውጭ ማሰር ነው ሲል ኮሚቴው
ይገልጻል፡፡ሆኖም ግን ተጠርጣሪው ከህግ ተጠያቂነት እንዳይሸሽ ለመከላከል የሚደረግ
የእስር ተግባር ህገ-ወጥ የእስር ተግባር ልንለው አንችልም፡፡ ለምሳሌ፡- ተጠርጣሪው
ከሃገር ለመውጣት ሙከራ ሲያደርግ ከተነቃበት፤መረጃ እና ማስረጃ እንደሚያጠፋ
አመላካች ሁኔታዎች ስለመኖራቸው ከተረጋገጠበት ወይም ሀገራት በራሳቸው የወንጀል
ስነስርአት ህጎች መሰረት ዋስትናን የሚያስከለክሉ ጉዳዮች ናቸው ተብለው የተዘረዘሩትን
ሁኔታዎች ተሟልተው ስለመገኘታቸውን ፍርድቤቱ በማስረጃ አረጋግጦ ተጠርጣሪውን
በእስር እንዲቆይ ከታዘዘ ከህግ ውጭ መያዝ እና ማሰር ነው ሊባል አይችልም፡፡
ከህግ ውጭ መያዝ እና ማሰር መጠኑ ይብዛም ይነስም በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ መኖሩ
የማይቀር ነው፤ በተለያዩ ሁኔታዎች እና ዘዴዎችም ሊከናወን ይችላል፡፡ለምሳሌ የተጣሰ
የወንጀል ህግ ሳይኖር፣ የህጋዊነት መርህን ችላ በማለት ሰውን መያዝ እና
ማሰር፣ምክንያታዊነት እና አግባብነት የሌለው የእስር ተግባር ማከናወን እንዲሁም
በአድልዎ እና በገደብ አልባ እስር ሰዎችን ካለ ፍርድቤት ትእዛዝ እና የቅጣት ውሳኔ
ለረዥም ጊዜ ማሰርን ሊያካትት ይችላል፡፡እነዚህን ከህግ ውጭ የመያዝ እና የማሰር
መገለጫዎች አንድ በአንድ እንደሚከተለው ይብራራሉ፡፡
1.2.1) ኢ- ህጋዊነት (Unlawful Detention)
ሀገራት በህጎቻቸው ላይ በግልጽ ባላካተቱት ምክንያት ሰዎችን የሚያስሩ እና የሚያግቱ
ከሆነ ይህ ተግባር የህጋዊነትን መርህን የሚጥስ የአምባገነን መንግሰት ባህርያዊ
መገለጫ ነው፡፡ ፖሊስ ወይም ሌላ የህግ አስከባሪ አካል አንድን ግለሰብ ሲያስር እና
በቁጥጥር ስር ሥያውል በግለሰቡ የተፈጸመው ድርጊት አስቀድሞ በወንጀል
እንደሚያስጠይቅ በህግ ተደንግጎ መሆን አለበት፡፡በህግ በግልጽ ያልተከለከለን
“ተግባር”(”ግድፈት”) ሰውን ለመያዝ ሆነ ለማሰር ምክንያት ሊሆን አይችልም ፤ፖሊስ
ወይም ሌላ አካል ወንጀል ስለመሆኑ በህግ ባልተደነገገ ጉዳይ አይነ ውሃው ስላልወደደው
ወይም ከተለያዩ ምክንያቶች ከሚመነጩ የጥላቻ መነሻዎች መሰረት በማድረግ ብቻ
ሰዎችን የሚይዝ ከሆነ ከህግ ውጭ የእስር ተግባር ተከናውኗል ማለት ይቻላል፡፡ ይህ
ደግሞ ከላይ ለመግለጽ እንደሞኮርኩት “ኢ-ህጋዊነት” ይባላል፡፡
• ኢ-ምክንያታዊነት(Unreasonable Detention)
በህግ የሚያስጠይቁ ተግባራት ተፈፅመው ሲገኙም መያዝ እና ማሰር ግዴታ ላይሆን
ይችላል፡፡በተጨማሪም በአንድ ወይም በተለያዩ የወንጀል ተግባራት ተጠርጥሮ የተያዘ
ሰውን በግዜ ቀጠሮ ፍርድቤት ማቅረብ ኢ-ህጋዊ ባይሆንም ምክንያታዊ ላይሆን ግን
ይችላል፡፡ለምሳሌ አንድ ተጠርጣሪ የእጅ እልፊት ወይም የስድብ እና ማዋረድ ወንጀል
መፈጸሙን በተጎጂው አማካኝነት የግል አቤቱታ ቀርቦበት በፖሊስ ከተያዘ በኃላ ወደ ፍርድ
ቤት “ጊዜ ቀጠሮ” ማቅረብ አግባብነት አይኖሮውም፤ጠቃሚም ምክንያታዊም አይሆንም፡፡
በመርህ ደረጃ አንድ ተጠርጣሪን ጊዜ ቀጠሮ በማቅረብ እና በዳኛ ፈቃድ በእስር በማቆየት
ምርመራን ለማከናወን (Remand in Custody) ፍርድቤትን መጠየቅ የሚያስፈልገው
ለመካከለኛ እና ከባድ ወንጀሎች ብቻ ነው፡፡ይህ እንዲሆን የተፈለገበት ዋና ምክንያትም
ፖሊስ በከባድ እና በመካከለኛ ወንጀሎች የተጠረጠረን ግለሰብ በዋስትና እንዲለቅ
የሚፈቅድለት ህግ ባለመኖሩ እንጂ ሁሉም ተጠርጣሪ ዋስትና ይከለከላል ማለት
አይደለም፡፡በህግ መሰረት ዋስትና በሚያስከለክሉ ወንጀሎች ተጠርጥሮ በችሎት የቀረበ
ተጠርጣሪን ፍርድቤቱም በህግ መሰረት ብቻ መከልከል ይኖርበታል፡፡የተፈጸመ ወንጀል
ስለመኖሩ አጠራጣሪ ከሆነ ወይም ወንጀሉን በተጠርጣሪ ስለመፈጸሙ ፖሊስ መነሻ
ማስረጃዎች ማቅረብ ካልቻለም ዋስትናን መፍቀድ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም
ተጠርጣሪው የተያዘበት ጉዳይ በህግ መሰረት ዋስትና እንደሚያስከለክል ባይደነገግም
የተያዘው ሰው ከሃገር እንዳይወጣ ለመጠበቅ፤ በፍትህ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ የተጠርጣሪው
ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር ለመከላከል እና ማስረጃዎች ተጠብቀው እንዲቆዩ ለማደረግ
እንዲሁም በሌላ አስፈላጊ እና ህጋዊ ምክንያት ተጠርጣሪውን በእስር ለማቆየት ጠቃሚ
እና ምክንያታዊ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ዋስትናን ለማስከልከል(ሊፈቀድለትም ላይፈቀድለትም
ይችላል) ፍርድቤት ማቅረብ አስፈላጊ ነው፡፡ስለሆነም ጊዜ ቀጠሮን መሰረት በማድረግ
የሚከናወን የእስር ተግባር በህግ ምክንያት የሚከናወን መሆኑን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን
ምክንያታዊ፣ጠቃሚ እና አግባብነት ያለው ሊሆን ይገባል፡፡በሌላ አገላለጽ አንድ ግለሰብ
በቀላል ወንጀል ተጠርጥሮ ከተያዘ ወይም የተጠረጠረበት የወንጀል ተግባር ቀላል ባይሆንም
እንኳን አንድ የወንጀል ተግባር ስለመፈጸሙ እንዲሁም በተጠርጣሪው ስለመፈጸሙ
አማላካች መረጃ ከሌለ ግለሰቡን በመያዝ እና በማሰር እንዲሁም በስመ “ጊዜ ቀጠሮ”
ወደ ፍርድቤት በማመላለስ እና በማንገላታት የነፃነት መብት ጥያቄ ውስጥ መክተት ትክክል
ስለማይሆን መርማሪ ፖሊስ በራሱ መንገድ ህጋዊ መፍትሄ መስጠት ይጠበቅበታል ፡፡
• አድልዎዊነት (Discriminatory Detention)
ከህግ ውጭ ማሰር የተፈፀመውን የወንጀል ተግባር መሰረት በማድረግ ብቻ ሳይሆን ይህ
ተግባር እንደ ሽፋን በመጠቀም በአንጻሩ ሌሎች የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን መሰረት
በማድረግ በአድልዎ ሰዎችን ማሰር ሊያካትት ይችላል፡፡ለምሳሌ ሁለት ግለሰቦች ተመሳሳይ
የወንጀል ተግባር መፈጸማቸው በበቂ ማስረጃ ተረጋግጦ እያለ አንዱን በማሰር እና ነጻነቱን
እንዲያጣ በማድረግ ሌላኛውን ግን በተለያዩ ምክንያቶች ሳይታሰር ከህብረተሰቡ ጋር
ተቀላቅሎ በነፃነት እንደፈለገ መኖር የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡”አድልዎ”
በየትኛውም የአለም ክፍል ማስቀረት የማይቻል የሰዎች “አመለካከታዊ በሽታ” ነው፡፡
ሰዎች በዘራቸው/ በብሄራቸው፣በቋንቋቸው፣በፖሊቲካዊ አቋማቸው፣ በሀይማኖታዊ
እምነታቸው እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን መድልዎ ሊደርስባቸው ይችላል፡፡ እንዲህ
አይነት ተግባር የእኩልነት መርህን ጥሰት የሚያስከትል፣መሰረታዊ መብቶችን እና ነጻነቶችን
አደጋ ላይ የሚጥል ህግን የሚቃረን አሰራር ነው፡፡ለምሳሌ፡- በኢፌድሪ ህገ-መንግስት
አንቀጽ 25 ላይ የተደነገገውን የእኩልነት መብትን በመጣስ የሚከናወን ማንኛውም
የመያዝና የማሰር ተግባር አድልዎ መሰረት በማድረግ የተከናወነ ከህግ ውጭ እስር ነው
ልንለው እንችላለን፡፡ማንኛውም ግለሰብ በህግ ክልከላ ያልተደረገበትን ተግባር(ግድፈት)
በወንጀል ተጠርጥረኃል በሚል ሽፋን በዘሩ፣ በብሄሩ፣ በቀለሙ፣ በጾታው፣ በቋንቋው፣
በሃይማኖቱ፣ በማህበራዊ አመጣጡ፣ በድህነቱ/በሃብቱ፣በትውልድ ቦታው ፣በፖለቲካዊ
አመለካከቱ ወይም በሌላ ግላዊ አቋሙ ምክንያት ብቻ ሊያዝ ወይም ሊታሰር አይገባም፡፡
• ገደብ አልባ እስር (Indefinite Detention)
ካለምንም የፍርድ ቤት ውሳኔ በውል ተለይቶ ላልታወቀ ጊዜ ሰዎችን መያዝ እና ማሰር
ከህግ ውጭ የማሰር ተግባሮች አንዱ ገፅታ ነው ፡፡ከዚህ በተጨማሪም ክስ ሳይቀርብ
ወይም በዋስትና ጉዳይ ፍርድቤቱ ውሳኔ እንዲሰጥ ሳይደረግ በፖሊስ ወይም በሌላ
ባለስልጣን ትእዛዝ ብቻ ለረዥም ጊዜ ሰውን ማሰር(Detaining people with out the
possibility of Charge and Bail) ገደብ አልባ እስር ሊባል ይችላል፡፡ ፍርድቤቱ ከህግ
ውጭ የታሰረን ግለሰብ ከእስር እንዲለቀቅ ትእዛዝ የሰጠ ቢሆንም ላልታወቀ ጊዜ የእስር
ሂደቱ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ይህ ማለት በመንግስት ባለስልጣናት የሚፈጸሙ የእስር
ተግባራት ብዙ ጊዜ ከፍርድቤት ትእዛዝ እና የቅጣት ውሳኔ ውጪ ስለሚከናወኑ ታሳሪዎች
ከእስር የሚፈቱበት ጊዜ ሊያውቁ አይችሉም ፤ምክንያቱም ሁሉም ነገር በአንድ ባለስልጣን
(ፖሊስ፣አቃቤ ህግ፡የፖለቲካ ሹመኛ ወዘተ…) ፈላጭ ቆራጭነት እና አምባገነናዊ ትእዛዝ
ብቻ ስለሚከናወን ነው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በአንድ ወቅት በሀገረ ሩዋንዳ “በዘራቸው ምክንያት ኢ-ሰብአዊ አያያዝና
ስቅያትን የሚያስከትል የድብደባ ወንጀል (Torture) የተፈጸመባቸው ዜጎች(በቱሲ እና
በሁቱ መካካል በነበረው የእርስበርስ ጦርነት ምክንያት ቱሲዎች የደረሰባቸውን በደል
በማስመልከት) መንግሰትን በመቃወማቸው ምክንያት ካለምንም የፍርድቤት ውሳኔ
በሀገሪቷ መንግስት ትእዛዝ ለረዢም ጊዜ መታሰራቸው የአፍሪካ የሰዎች እና የህዝቦች
መብቶች ቻርተር አንቀጽ 6 ን የሚጥስ ከህግ ውጭ የተከናወነ ተግባር ነው” ሲል የአፍሪካ
የሰዎች እና የህዝቦች መብቶች ኮሚሽን ትርጉም ሰጥቶበታል፡፡
ከላይ የጠቀስኳቸው ችግሮች አጠቃላይ የአንድ ሀገር ደካማ ስርአት እና ተቋማዊ አወቃቀር
የፈጠሩት ችግር ሊሆን ይችላል፤ወይም ደግሞ ለሙያው ታማኝ የሆነ፣ነጻ እና ገለልተኛ
ፖሊስ ፣አቃቤ ህግ፣ዳኛ ወይም ጠበቃ ያለመኖር ችግር የፈጠራቸው ሊሆንም ይችላል፡፡
ቁርጠኛ የፖለቲካ አመራር ያለመኖር ወይም የአንድ መንግስት አምባገነናዊ ባህሪ
የወለዳቸው ችግሮችም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ስለሆነም በአለምአቀፍ ህጎች ሆነ በሀገራት ብሄራዊ ህጎች የሰዎች መሰረታዊ መብቶች
እና ነፃነቶችን የሚያከብር እና የሚያስከብር የሰለጠነ የህግ ባለሙያ መገንባት ፤የሰብአዊ
መብቶች ጥሰት ሲያጋጥምም የህግ ተጠያቂነትን የሚዘረጉ የህግ ማእቀፎችና ጠንካራ
ተቋማት እንዲኖሩ ማድረግ፤የመብቶቹ አከባበር እና አፈፃጸም የሚከታተል ወይም የሰብኣዊ
መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላትም የሚጠየቁበት ሁኔታ በህግ መሰረት በአግባቡ
የሚከታተል ፣የሚያስፈጽም ፣የሚተረጉም እና ተገቢውን ቅጣት እና የእርምት እርምጃ
የሚወስድ ተቋማዊ እና ግለሰባዊ ነጻነቱን የጠበቀ የፍትህ አካል መኖር የግድ ይላል፡፡
በዚሁ መሰረት ሁሉም የአለም ሀገራት የሁሉም ሰዎች የነጻነት እና የአካል ደህንነት መብት
በእኩል እንዲያከብሩ በአለም አቀፍ ህግ መሰረት ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡በአለም አቀፍ
ደረጃ እውቅና ያገኙ መብቶችን ጥሰው የተገኙ ሀገራት አለም አቀፍ ህጋዊ ሃላፊነት
(Universal Legal Responsibility) ያስከትልባቸዋል፡፡ የነጻነት መብት ማለት
ማንኛውም ሰው የእለት ተእለት የሂወት እንቅስቃሴው ውስጥ ካለምንም መሸማቀቅ እና
ጣልቃ ገብነት ሙሉ የመንቀሳቀስ እና የመኖር መብት የሚጎናፀፍበት የተፈጥሮ መብት
ሲሆን የደህንነት መብት ማለት ደግሞ ማንኛውም ሰው በሂወቱ ላይ ሊደርስበት የሚችል
አደጋ ወይም ስጋት/ፍርሀትን መከላከል እና በነጻነት እንዲንቀሳቀስ መንግስታዊ ጥበቃ
ወይም ዋስትና የሚያገኝበት ሆኖ የተያዘ ሰውም ቢሆን የአካል ደህንነቱን እንዲጠበቅ
መንግስት እና የመንግስት አካላትን ግዴታ ውስጥ ማስገባትን የሚጨምር ተፈጥሮኣዊ
መብት ነው፡፡በዚሁ መሰረት ሀገራት የማንኛውም ሰው የነፃነት እና የደህንነት መብት
ለማክበር እና ለማስከበር ምክንያታዊ እና ተገቢ እርምጃ እንዲወስዱ አለም አቀፍ ግዴታ
ተጥሎባቸዋል፡፡የነፃነት እና የደህንነት መብቶች በአጠቃላይ እንዲሁም እነዚህ መብቶችን
የሚገደብባቸው ህጋዊ ምክንያቶችንና ልዩ ሁኔታዎችን ከአለም አቀፍ ህጎች፣ ከኢፌድሪ ህገ
መንግስት እና ከወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአት ህግ አንፃር እንደሚከተለው ይቃኛሉ፡፡
2) አለም አቀፍ እና ብሄራዊ የህግ ማእቀፎች
ሀ) የሰብአዊ መብቶች ሁሉ-አቀፍ መግለጫ
ይህ ሁሉ አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ በአንቀጽ 3 ላይ እያንዳንዱ ሰው የሕይወት
፣የነጻነት እና የተሟላ የድህንነት መብት እንዳለው ያሰፈረ ሲሆን በአንቀፅ 9 ደግሞ ማንም
ሰው በዘፈቀደ ሊያዝ ፣ሊታሰር ወይም ሊያዝ አይችልም በማለት በግልፅ ደንግጎ
እናገኘዋለን፡፡ይህ ድንጋጌ በሌላ መልኩ ስናነበው-- ማንኛውም ሰው በዘፈቀደ ነፃነቱን
ማጣት አይችልም የሚል አጠቃላይ መርህ ደነገገ እንጂ ሀገራት በህጎቻቸው ላይ በግልጽ
ተለይተው በተቀመጡ ምክንያቶች እና በተዘረጉ የአያያዝ ስርአቶች መሰረት መያዝ ወይም
ማሰር ክልክል ነው ማለት ግን አይደለም፡፡
ለ) የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች አለምአቀፍ ቃልኪዳን ፡-
በዚህ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ቃልኪዳን አንቀጽ 9(1) ላይ በግልፅ
እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው የግል ነጻነቱ እና ደህንነቱ እንዲረጋገጥለት መብት
አለው፡፡ማንኛውም ሰው ከህግ ውጭ አይያዝም ፣አይታሰርም ፡፡ማንኛውም ሰው በህግ
ከተደነገገው ምክንያት እና ስርአት ውጭ የግል ነፃነቱ አይገፈፍም፡፡ የተባበሩት የአለም
ሃገራት ደርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚቴ ይህን አንቀጽ መሰረት በማድረግ የሰጣቸውን
ትርጉሞችና አስተያየቶችን በጥቂቱ እንደሚከተለው ለማየት እንሞክራለን፡፡
ምሳሌ አንድ፡-አንድ ግለሰብ በከባድ የወንጀል ተግባር ተጠርጥሮ የተሰወረ ወንድሙን
ፈልጎና መርቶ እንዲያስዝ ቢገደድም መፈጸም ባለመቻሉ ምክንያት ብቻ ለአንድ ወር ቢታሰር
ከህግ ውጭ መያዝና ማሰር በመሆኑ አግባብነት የሌለው ተግባርና የህጋዊነት መርህን
የሚጥስ ነው ብሏል፡፡
ምሳሌ ሁለት፡-አንድ ግለሰብ የመያዣ ትእዛዝ ሳይቆረጥበት ወይም መጥርያ ሳይደርሰው
ከተያዘ በኃላ ወደ ፍርድቤት ሳይቀርብ ለረዥም ጊዜ ማሰር የግለሰቡን የነፃነት መብትን
ሙሉ በሙሉ የሚቃረን ህገ-ወጥ የመያዝና የማሰር ተግባር ነው ብሏል፡፡ በተመሳሳይ
መልኩ አንድ ግለሰብ በህጋዊ መልኩ ከተያዘ ወይም ከታሰረ በኃላም ቢሆን ፍርድቤቱ
መለቀቅ አለበት ብሎ ካዘዘ በኃላ በፖለቲካ ባለስልጣናት ወይም በሌላ አካላት ትእዛዝ
ምክንያት በእስር ላይ እንዲቆይ ማድረግ ኢ-ህጋዊ ተግባር ነው ብሏል፡፡
ሐ) የአፍሪካ የሰዎች እና የህዝቦች መብቶች ቻርተር (አንቀጽ 6)
ማንኛውም ሰው ነፃነቱ እና አካላዊ ደህንነቱ ተጠብቆለት የመኖር መብት አለው፡፡ቀድሞ
በህግ በተደነገጉት ሁኔታዎች እና ምክንያቶች ካልሆነ በስተቀር ማንም ሰው ነፃነቱን
እንዲያጣ ሊደረግ አይችልም፡፡ በተለይም ማንም ሰው በዘፈቀደ ሊታሰር ወይም ሊያዝ
አይችልም፡፡
• የአውሮፓ ሰብአዊ መብቶች መግለጫ እና የአሜሪካ ሃገራት ሰብኣዊ መብቶች
መግለጫም ከላይ ከተጠቀሱት የህግ ማእቀፎች ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ማንኛውም ሰው
በዘፈቀደ ሊያዝ ሆነ ሊታሰር እንደማይችል ደንግገዋል፡፡
መ) የኢፌድሪ ህገ መንግስት
የኢፌድሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 17(1) ስር እንደተመለከተው በህግ ከተደነገገው ስርአት
ውጭ ማንኛውም ሰው ወንድም ሆነ ሴት ነፃነቱን /ቷን አያጣም /አታጣም በማለት
ደንግጓል ፤በተጠቃሹ አንቀጽ ንኡስ ቁጥር ሁለት ላይም ማንኛውም ሰው በህግ
ከተደነገገው ስርአት ውጭ ሊያዝ ፣ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሣይፈረድበት ሊታሰር
አይችልም በማለት ደንግጓል፡፡
ሠ)የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነ ስርአት
ማንኛውም ሰው በህግ መሰረት ሊያዝ ወይም ሊታሰር የሚችለው አንደኛ ሊያስይዘው
ወይም ሊያስጠይቀው የሚችል የወንጀል ተግባር መፈጸሙ ሲረጋገጥ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ
ደግሞ የተጠረጠረበትን/የተከሰሰበትን የወንጀል ተግባር በህግ መሰረት የሚያስይዘው/
የሚያሳስረው መሆኑን ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ የወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ አንቀጽ
25፣ 26 እንዲሁም ሌሎች አግባብነት ያላቸው የስነስርአት ህጉ ድንጋጌዎች ይዘት እና
መንፈስ ያስረዳሉ፡፡
በረቂቅ ደረጃ ያለው የወንጀል ስነስርአት እና የማስረጃ ህግ በአንቀጽ 8 ላይ ስለመያዝና
ማሰር በሚል ርእስ ስር እንደተመለከተውም “ማንኛውም ሰው ወንጀል ስለመፈፀሙ በቂ
ጥርጣሬ ሳይኖር ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረደበት ሊታሰር አይችልም” በማለት
ደንግጓል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት አጠቃላይ መንግስታዊ ግዴታዎች የሚያስገነዝቡን፤ በመርህ ደረጃ
ማንኛውም ሰው ካለ ምንም ህጋዊ ምክንያት ሊያዝ ወይም ሊታሰር እንደማይችል
የሚያስረዱና የተፈጥሮ ችሮታ የሆኑ የሰው ልጆች መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች
እንዲከበሩ እውቅና የሚሰጡ አለም አቀፍ ግዴታዎችና ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ህገ-
መንግስቱን ጨምሮ የኢትዮጵያ ህጎችም ከአለም አቀፍ ህጎችጋር ተመሳሳይ አላማ በመያዝ
የተቀረፁ ናቸው፡፡
በዚሁ መሰረት የነጻነት መብት ህገ መንግስታዊ መብት ከመሆኑ በተጨማሪ ኢትዮጵያ
በፈረመቻቸው አለም አቀፍ ህጎች እና በሌሎች ዝርዝር የስነ ስርአት ህጎቿ ላይ በግልጽ
ሰፍረው ይገኛሉ፡፡ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ይህ መርህ በኢፌድሪ ህገ መንግስት
አንቀፅ 17፣ በአለም አቀፍ ፖሊቲካ እና ሲቪል ስምምነት ሰነድ አንቀጽ 9፤በሰብአዊ
መብቶች ሁሉ አቀፍ መግለጫ አንቀጽ 3 እና 9፣በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ አንቀጽ
25 እና 26 እንዲሁም በረቂቁ የወንጀል ስነ ስርአት እና የማስረጃ ህግ አንቀጽ 8 ላይ እና
ሌሎች ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ህጎች ላይ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ሆኖም ግን አንድ ግለሰብ
በወንጀል ድርጊት ተጠርጥሮ የሚፈለግ ከሆነ አጠቃላይ የህብረተሰቡ ሰላም እና ደህንነት
ለመጠበቅ ሲባል በህግ ተለይተው በተቀመጡ ስነስርአታዊ አካሄዶች መሰረት መያዝ
ወይም ማሰር ይቻላል፡፡
ይህ ማለት አንድ ግለሰብ ሊያዝ ወይም ሊታሰር የሚችለው በአንድ ፖሊስ የግል ፍላጎት
ወይም በባለስልጣን ፈላጭ ቆራጭነት ወይም በማንኛውም ግለሰብ ጥላቻዊ ጥቆማ
ወይም ቂም በቀልነት ሳይሆን ጉዳዩ በአንድ ምክንያታዊ ታዛቢ ሰው ሲለካ እንዲሁም
በግልጽ እና በሚያሳምን ሁኔታ እውነታዎቹ ሲታዩ እና ማስረጃዎቹ ሲመዘኑ ወይም
ሲመረመሩ ለማስያዝ እና ለማሳሰር በቂ ሆኖው ሲገኙ ብቻ ነው፡፡ዝቅተኛ የህግ ግንዛቤ እና
እውቀት ባለበት እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ ሃገራት ማሰር እና መያዝ ካለምንም ገደብ እና
ቅድመ ሁኔታ በዘፈቀደ ለፖሊስ የተሰጠ ስድ እና ያልተገራ ስልጣን የሚመስለው
የህብረተሰብ ክፍል ስፍር ቁጥር የለውም፡፡ ብዙዎቻችን ደንብ ልብስ ለብሶ ካቴና ይዞ
የመጣ ፖሊስ ሁሉ ህግን እያስከበረ ነው የሚል የተሳሳተ ህብረተሰባዊ እምነት እና
ልማዳዊ አሰራር ስለምናራምድ እና ለዚሁ ጸረ-ነጻነት የሆነውን አሰራር ተገዢ ስለምንሆን
ለመብታችን ስንታግል አይታይም፡፡ ይህ ስል ግን ራሳችንን ከህግ ውጭ በማድረግ
ለሚደርስብን ኢ-ፍትሀዊ ተግባር ኢ-ፍትሀዊ ግብረመልስ እየሰጠን ወደአላስፈላጊ እሰጣ
እገባ እና ንትርክ ውስጥ በመግባት በህግ አስከባሪ አካላት ላይ ችግር የመፍጠር መብት
አለን ለማለት ሳይሆን ብያንስ ግን በህግ እና በመብታችን ላይ የተሟላ እውቀትና ግንዛቤ
ኖሮን ህግን መሰረት በማድረግ መጓች እና ንቁ ዜጋን በመፍጠር አምባገነን መንግስትን እና
ፈላጭ ቆራጭ ባለስልጣንን የምንከላከልበት ሁኔታ ሊኖር ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ መንግስት
ጠንካራ ስርአት እና ተቋም እንዲመሰርት፤ተጠያቂነት እና ሃላፊነት መሰረት በማድረግ
ስራውን የሚያከናውን ባለሙያ(ባለስልጣን) እንዲኖር መንግስት በአንክሮና በቁርጠኝነት
እንዲሰራ በር ለመክፈት ያስችላል፡፡
ስለሆነም አንድ ግለሰብ ሊታሰር የሚችለው በልዩ ሁኔታ በህግ መሰረት በግልጽ ተለይተው
በተቀመጡ ዝርዝር ምክንያቶችና አካሄዶችን በጥብቅ በመከተል ብቻ ሲሆን ኢትዮጵያም
ከአለም አቀፍ ህጎች ጋር ተመሳሳይ አቋም እና ይዘት ያላቸው ድንጋጌዎች በብሄራዊ ህጎቿ
ላይ አስፍራለች፡፡ በዚሁ መሰረት አንድ ግለሰብ ሊያዝ ወይም ሊታሰር የሚችለው
በሚከተሉት ምክንያቶች ብቻ ነው፡፡
ሀ) በወንጀል ተግባር ሲጠረጠር፡-
ማንኛውም ሰው ወንጀል ሊመፈጸም በሙከራ ላይ እያለ ፣ወንጀል ስለመፈፀሙ በቂ
ጥርጣሬ መኖሩ ወይም የወንጀል ተግባርን ሲፈፅም እጅ ተፍንጅ ከተያዘ፣ወይም በህግ
መሰረት ወንጀልን ለመፈጸም የመሰናዳት ተግባራት ያስቀጣሉ ተብለው በተደነገጉ ጉዳዮችን
እንዳይፈጸሙ ለማስቆም/ለመከላከል በማሰብ እና ለዚሁም በቂ በሚባል ሁኔታ
ምክንያታዊ ጥርጣሬ ሲኖር በህግ ተለይተው በተቀመጡ ስነስርአታዊ አካሄዶችን በጥብቅ
በመከተል መያዝ ወይም ማሰር ይቻላል፡፡በኢፌድሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 17 ላይ በግልጽ
እንደተቀመጠው ማንኛውም ሰው ካለ ፍርድቤት የመያዣ ትእዛዝ ሊታሰር ወይም ሊያዝ
አይችልም ፡፡ሆኖም በህጉ መሰረት ተለይተው በተቀመጡ መስፈርቶች መሰረት አንድ
በወንጀል የሚፈለግ ሰው ካለ፤ በፍርድቤት የመያዣ ትእዛዝ በቁጥጥር ስር ሊውል
እንደሚችል፡ በዚሁ የህገ-መንግስት ድንጋጌ ንኡስ አንቀጽ 2 ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ አንድ
በወንጀል ድርጊት የተጠረጠረ ሰው የሚያዝበት ስርአትስ እንዴት ነው የሚል ጥያቄ
መመለሱ የሚያስፈልግበት ዋና ምክንያት በአንድ በኩል የተገራ የፖሊስ ተግባር እንዲኖር
እና ህግን የማስከበር ሃላፊነት በአግባቡ እንዲሰፍን የሚያደርግ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ
የልተገራና እና ልቅ የሆነ ነፃነትን ከመገደብ አንጻር የሚፈጥረው ሚዛናዊ አካሄድ የራሱ
የሆነ አስተዋጽኦ ስለሚኖሮው በህግ የሚፈለግ ሰው የሚያዝበት አግባብ አጠር አጠር ባለ
መልኩ እንደሚከተለው ማየቱ ይጠቅማል፡፡
1. መጥርያ
በየትኛውም የወንጀል ተግባር የተጠረጠረ ግለሰብን በመጀመርያ ደረጃ ፖሊስ በመጥርያ
እንዲያቀርብ ማድረግ ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞች ይኖሩታል፡፡ለምሳሌ ፖሊስ ፍርድቤት ድረስ
በመሄድ ፍቃድ ለማግኘት የሚያባክነው ጊዜ እና ጉልበት ይቀንስለታል፤ተጠርጣሪው
በመጥርያ የሚቀርብ ከሆነ በፖሊስ ላይ ሊያደርሰው የሚችል ተቃውሞ ሆነ ለህግ
አልታዘዝም ባይነት አይኖርም፤በሌላ አገላለጽ ተጠርጣሪው በፍላጎቱ እስከ ቀረበ ድረስ
በህግ አስፈጻሚ አካላት ላይ ሊያደርሰው የሚችል ጥቃት ወይም ተቋውሞ አይኖርም….
ወዘተ፡፡ እንደ እነ እንግሊዝ የመሳሰሉ የኮመን ሎው የህግ ስርአት የሚከተሉ ሃገራት
በየትኛውም የወንጀል ተግባር የተጠረጠረ ግለሰብ በፖሊስ መጥርያ ከቀረበ ፍርድቤቱ
የጥፋተኝነት ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ አይታሰርም፡በሙሉ ነፃነት እና ካለምንም ገደብ
በውጭ ሁኖ ወደ ፍርድቤት እየተመላለስ ጉዳዩን እንዲከታተል ፍርድቤቱ ይፈቅድለታል፡፡
በኢትዮጵያ የህግ ስርአት ግን ለቀላል ወንጀሎች ካልሆነ በስተቀር በሌሎች ወንጀሎች
ተጠርጥሮ በፖሊስ መጥርያ መሰረት ቢቀርብም ሊታሰር ወይም በገደብ-ለምሳሌ
በዋስትና -ሊለቀቅ ይችላል እንጂ በፖሊስ መጥርያ በመቅረቡ ብቻ ላለመታሰሩ ዋስትና
ሊሆነው አይችልም ፡፡መርማሪ ፖሊስ በየትኛውም የወንጀል ተግባር የተጠረጠረን ግለሰብ
በመጥርያ ይቀርባል ብሎ ግምት ከወሰደ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነ ስርአት አንቀጽ 25
መሰረት መጥርያ ማድረስ ይችላል፡፡በዚሁ መሰረት የቀረበ ተጠርጣሪ የተጠረጠረበትን
የወንጀል ተግባር ክብደቱ እና ቅለቱ ታሳቢ በማድረግ ፖሊስ በራሱ ህጋዊ ስልጣን
ተጠርጣሪውን በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነ ስርአት አንቀጽ 28 መሰረት በዋስትና መልቀቅ
ወይም ተጠርጣሪውን ከተያዘበት ሰአት ጀምሮ በሚቆጠር በ 48 ስአታት ውስጥ ወደ
ፍርድቤት በማቅረብ በዋስትና ላይ እልባት እንዲያገኝ ከልብ የመነጨ እርምጃ መውሰድ
ይኖርበታል፡፡
2. የመያዣ ትእዛዝ
ፖሊስ የመያዣ ትእዛዝ በማውጣት ተጠርጣሪን መያዝ የሚችለው ተጠርጣሪው በመጥርያ
ለመቅረብ ፍቃደኛ ሣይሆን ሲቀር ወይም እንደማይቀርብ እርግጠኛ ሲሆን ብቻ መሆን
አለበት፡፡የመያዣ ትእዛዝ የሚፈቀድበት መደበኛ ስነ ስርአት በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአት
ህግ ቁጥር 53 እና 54 ላይ በግልጽ የተደነገገ ሲሆን በዚሁ መሰረትም ማንኛውም
ፍርድቤት ትእዛዙን የመስጠት ስልጣን ቢኖሮውም በመርማሪ ፖሊስ የቀረበ ጥያቄ ሳይኖር
ግን መስጠት አይችልም፡፡መርማሪ ፖሊስ የመያዣ ትእዛዝ መጠየቅ የሚችለውም አንደኛ
ተጠርጣሪው በፍርድቤት መቅረቡ ፍጹም አስፈላጊ ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ተጠርጣሪው ወደ
ፍርድቤት የሚቀርብበት ሌላ አማራጭ አለመኖሩን መረጋገጥ ሲቻል ብቻ ነው፡፡
የተጠርጣሪው መቅረብ ፍጹም አስፈላጊነት(The criterion of Absolute Necessity)
እንደ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠበት ዋና ምክንያት ተጠርጣሪው የወንጀል ድርጊቱን
ስለመፈጸሙ የሚያሳዩ መነሻ ማስረጃዎች (Minimum standards of evidences)
ስለመኖራቸው በገለልተኛ ፍርድቤት እንዲረጋገጥ በማሰብ ነው፡፡በሌላ አነጋገር ማንኛውም
ሰው በስስ ማስረጃ ወይም ካለምንም ማስረጃ እንዳይያዝ /እንዳይታሰር ለመከላከል
ፍርድቤቱ በመርማሪ ፖሊስ በኩል የሚቀርብ የእስር መያዣ ማመልከቻን በአግባቡ
እንዲመረምር ስለሚፈለግ ነው፡፡ሌላ አማራጭ አለመኖሩን ማረጋገጡ ያስፈለገበት ዋና
አላማ ደግሞ ተጠርጣሪው መርማሪ ፖሊስ የሚያደርስለትን መጥርያ ሣይቋወም ህግን
አክብሮ የሚቀርብበት ሁኔታ ካለ እድሉን ለመጠቀም ሲሆን ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት
የመጥርያ ጠቀሜታ ከአዘገጃጀቱ፣ አደራረሱና ውጤቱ አንፃር ሲለካ በፍትህ ዘርፉ ላይ የላቀ
አስተዋፅኦ ስላለው የፍርድቤት የመያዣ ትእዛዝ ከመውጣቱ በፊት መጥርያ የመጀመርያ
አማራጭ እንዲሆን ስለተፈለገ ነው፡፡
3. ያለመያዣ ትእዛዝ
ማንኛውም በወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ ካለ ፍርድቤት ትእዛዝ ሊያዝ እንደሚችል በህገ
መንግስቱ አንቀፅ 17 እና በተለያዩ የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአት ህግ ድንጋገጌዎች ላይ
በግልፅ ሰፍረው እናገኛቸዋለን፡፡ከእነዚህ መካከል ሊጠቀሱ የሚችሉት የእጅ ከፍንጅ
ወንጀሎች (Flagrant Offences) ናቸው፡፡የእጅ ከፍንጅ ወንጀሎች በትርጉም ደረጃ
በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርአት ህግ ቁጥር 19 እና 20 ላይ የተቀመጡ ሲሆን ስነስርአታዊ
ውጤታቸው ደግሞ በአንቀጽ 20 እና 50 ላይ በግልጽ ሰፍረው ይገኛሉ፡፡በተጨማሪም
ተጠርጣሪው ወንጀሉን ሲፈጽም እጅ ተፍንጅ ባይያዝም እንኳ የፍርድቤት የመያዣ ትእዛዝ
እስከሚወጣበት ድረስ ሊሰወር ወይም ሊያመልጥ ይችላል ተብሎ ለመገመት የሚያስችሉ
አመላካች(ጠቋሚ) መረጃዎች ካሉ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ባገኘበት ቦታ መያዝ ይችላል፡፡
ለምሳሌ ከሃገር ለመሸሽ ሙከራ ሲያደርግ ከተያዘ ፖሊስ ለጊዜው የፍርድቤት የመያዣ
ትእዛዝ ማውጣት ሳይጠበቅበት ሌሎች በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ ላይ
የተቀመጡትን ህጋዊ ጥንቃቄዎችና እርምጃዎችን በመከተል ከፍትህና ህግ ለማምለጥ
የሚሞክር ማንኛውም ተጠርጣሪን መያዝ ይችላል፡፡
ለ) ስልጣን ባለው ፣ ነጻ እና ገለልተኛ በሆነ ፍርድቤት ሲፈረድበት ወይም ሲወሰንበት
አንድ ተጠርጣሪ በአንድ የወንጀል ተግባር ተጠርጥሮ ህጉና ስነ ስርአቱ በሚፈቅደው
መሰረት በቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉ በፍርድቤት የመጨረሻ ውሳኔ ተወስኖበታል
ማለት አይደለም፡፡ ማንኛውም ሰው በከባድ የወንጀል ድርጊት እንኳ ቢጠረጠር ከተያዘበት
ጊዜ ጀምሮ በሚቆጠርና ወደ ፍርድቤት ለማድረስ የሚፈጀው ጊዜ ሣይታሰብ በ48 ስአታት
ውስጥ ፖሊሰ ተጠርጣሪን ወደ ፍርድቤት የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡አንድን ተጠርጣሪ ወደ
ማረሚያቤት እንዲላክ ፣በነፃ እንዲለቀቅ፣ በገደብ እንዲፈታ ወይም በዋስትና እንዲወጣ
ማዘዝ የሚችለው ስልጣን ያለው፣ነፃና ገለልተኛ የሆነ ፍርድቤት ሲወስን ብቻ ነው፡፡በሌላ
አነጋገር የፖሊስ መጥርያ ደርሶት በፍላጎቱ የቀረበ ተጠርጣሪ ይሁን በፍርድቤት የመያዣ
ትእዛዝ ወይም ካለምንም የፍርድቤት የመያዣ ትእዛዝ ለፖሊስ እጁን የሰጠ ተጠርጣሪ
ነፃነቱን ተገፎ ወደ ማረሚያ ቤት የሚላከው ፍርድቤቱ እንዲታሰር ሲወስንበት ብቻ ነው፡፡
ከዚህ ውጭ የሚከናወን የእስር ተግባር ህጋዊ አይደለም፡፡
መደምደሚያ
ማንኛውም ሰው በመንግስት አካላት ሆነ በሌላ ማንኛውም ሰው ሊታፈን፣ሊጣስ ፣ሊገፈፍ
ወይም ሊገሰስ የማይችል በተፈጥሮ የታደለው የነጻነት እና የደህንነት መብት ቢኖሮውም
ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው አለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ህግጋት እንዲሁም
በኢፌድሪ ህገ መንግሰት በተደነገገው አጠቃላይ መርህ እና ይህን የበላይ ህግ መሰረት
በማድረግ በወጡ ግልጽ ህጎች እና ስነስርኣታዊ ሂደቶች የነፃነት መብት ሊገደብ
የሚችልባቸው ምክንያቶች በግልፅ ተደንግገዋል፡፡
ሀገራት ነፃነትን በመገደብ ሰውን መያዝ እና ማሰር የሚችሉ በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት
ካገኙ የሰብኣዊ መብቶች ህግጋት እና እነዚህ መሰረታዊ እና ስነስርአታዊ ህግጋትን ጋር
በሚጣጣም መልኩ በብሄራዊ ህጎቻቸው ላይ በተደነገጉት ግልጽ ህጎች እና ስነስርአታዊ
አካሄዶች መሰረት በማድረግ መሆን ስላለበት ህግን በማክበር እና ስርአትን በጥብቅ
በመከተል ብቻ መሆን ይኖርበታል፡፡ከዚህ ውጭ የሚከናወን የመያዝ እና የማሰር ሂደት
ብሄራዊ እና አለም አቀፋዊ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡ ምክንያቱም ሰዎችን የመያዝ እና
የማሰር ስልጣን ምንም አይነት ምክንያት ሳይኖር በዘፈቀደ የሚከናወን ገደብ አልባ ተግባር
አይደለም፡፡ በመጀመርያ ደረጃ በግልጽ የተጣሰ የህግ ድንጋጌ እና የተፈጸመ የወንጀል
ተግባር መኖር አለበት፡፡ በመቀጠል ከፖለቲካዊ ሴራ እና ጥቃት የፀዳ፣ምንም አይነት
አድልዎ የሌለበት፣ ምክንያታዊነቱ እና አስፈላጊነቱ ከአጠቃላይ የህዝብ ጥቅም አንጻር
ተለክቶ ህግ እና ህግን ብቻ የተከተለ መሆን አለበት ፡፡ በሌላ አገላለጽ አንድን ግለሰብ
ለመያዝ ወይም ለማሰር የህጋዊነት መርህን መከተል እንደተጠበቀ ሁኖ ህጎች እና የህጎች
ተፈጻሚነትም ፍትሃዊ እና ከምንም አይነት አድልዋዊ አሰራር ነጻ ለማድረግ ተገቢነት
ያላቸው እና ከኢ-ምክንያታዊት የፀዱ (Appropriate and Reasonable)
፣ተገማችነት እና ተመጣጣኝነትን (Foreseeable and Proportionality) እንዲሁም
ህግን የተከተለ አሰራር (Due Process of Law) መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ማረጋገጥ
አስፈላጊ ነው፡፡

Address

Wolkite

Opening Hours

Monday 09:00 - 17:00
Tuesday 09:00 - 17:00
Wednesday 09:00 - 17:00
Thursday 09:00 - 17:00
Friday 09:00 - 17:00

Telephone

+251 11 365 9884

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when የጉራጌ ዞን ፍትህ መምሪያ posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share

Category