![ትንሽ ስለ ሰሙነ ሕማማትእሮብ፣ አርብ እና እሁድበሕማማት ሳምንት ሰባቱም ቀን የየራሳቸው ታሪክ ቢኖራቸውም እንዚህ ሶስት ቀኖች ግን በክርስቶስ ሞት ላይ ቀጥተኛ አስተዋጽዎ በማድረግ ከሳምንቱ...](https://img5.medioq.com/035/405/817968820354057.jpg)
05/02/2024
ትንሽ ስለ ሰሙነ ሕማማት
እሮብ፣ አርብ እና እሁድ
በሕማማት ሳምንት ሰባቱም ቀን የየራሳቸው ታሪክ ቢኖራቸውም እንዚህ ሶስት ቀኖች ግን በክርስቶስ ሞት ላይ ቀጥተኛ አስተዋጽዎ በማድረግ ከሳምንቱ ቀደምት ናቸው።
በሐዋ ማቴዎስ እና ማርቆስ የታሪክ አመዘጋገብ መሠረት በዕለተ እሮብ ሦስት ነገሮች ተፈጽመዋል።
1. የካህናት አለቆች፣ የሕዝብ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ፈሪሳውያን በጌታችን ላይ ተማክረዋል።
2. ጌታችን በስምኦን ቤት ሳለ አንዲት የተጸጸተች ሴት ሽቱ ቀብተዋለች።
3. ከዳተኛው ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ለመስጠት ከጸሐፍት ፈሪሳውያን እና አለቆች ዘንድ ሠላሳ ብር ለመቀበል ተስማምቷል።
እሮብ እና ይሁዳ (ምህረት የጀመረበት ቀን)
ስለ አስቅሮቱ ይሁዳ መጻፍ የሚማርክ ነገር እንዳልሆነ የምናውቀው አራቱ ወንጌላት አስገዳጅ ካልሆነባቸው በስተቀር ስለ ይሁዳ ብዙ ነገር ባለመጻፋቸው ነው። ክህደት እና አስመሳይነት ምን ደስ ይልና።
ክህደቱ ከጌታው ጋር እየተመላለሰ በውጪ ሊሸጠው ማሰቡ አስመሳይነቱ ደግሞ ‹አሳልፌ የምሰጥህ እኔ እሆንን? ብሎ በድፍረት አይን አይኑን እያየ መጠየቁ ነው። ማቴ 26፤25 . . .
መቼም ጌታ በዕለተ አርብ በጠላቶቹ እጅ ከተሠቃየው ሥቃይ ይልቅ በወዳጁ ይሁዳ ምክንያት በዕለተ እሮብ የተሠቃየው የኅሊና ሥቃይ ይከፋል ብዬ አስባለሁ። ሳምንቱ የመስቀሉን ሞት የታገሰበት ብቻ ሳይሆን የሽንገላ መሳምን ያሳለፈበት ሳምንት ነበር።እንደ ዳታን እና አቤሮን መሬት ተሰንጥቃ ስላልዋጠችው፣ ምላሱ ከጉሮሮው ጋር ስላልተጣበቀ፣ ሽንገላ ያወሩት እንደበቱ ዲዳ ባለመሆናቸው የምህረት ጥጉን ከጲላጦስ በፊት በዚህ ሰው አየንበት።
እለተ እሮብ ታላቁ የአይሁድ ሸንጎ(the great sehedrin) ሰባ ሁለት አባላቱን ይዞ በሊቀ ካህኑ ቀያፋ አስተናባሪነት ተሰይሟል። ይህ መሰየም እርስ በእርሳቸው በነገረ ሃይምኖትም ሆነ በሃገራዊ ሁኔታ ብዙውን ተስማምተው የማያቁትን የአይሁድ ገዢዎች በጌታ መገደል ላይ ሊያስማማ ነው። ዳዊት ‹አለቆችም በእግዚአብሔርና በመሲሁ ላይ በአንድነት ተሰባሰቡ› መዝ 2:2 እንዳለ።
ይሁዳም የተሰበሰቡበትን አላማ ሊያስፈፅም ዳር ቆሟል: ለድርድር እንኳን ሳይግደረደር ‹ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ› ብሎ ተመኑን ለእነርሱ አሳልፎ ሰጣቸው። ይህም የገንዘብ ጥልቅ ፍቅሩን ያሳየናል።
ምናልባትም በውጪ ባሉት በጥፊ ከመመታት ይልቅ ያለተመን መሸጥ ምን ያህል ልብ እንደሚሰብር ማሰብ ቀላል ነው። መቼም የተሰበሰቡት አይሁድ እንደመሆናቸው ህግ ስለሚያውቁ ቢያንስ «በሬው ወንድ ባሪያ ወይም ሴት ባሪያ ቢወጋ፡ የበሬው ባለቤት ሠላሳ ስቅል ለጌታቸው ይስጥ» ዘጸ 21:32 የሚለውን ህግ ስለሚያውቁ ቢያንስ ከአንድ ባሪያ ዋጋ አላሳነሱትም እንጂ ሻጩማ በፈለጋችሁት ውሰዱት ብሎ ነበር።
ዳሩ ግን በዛው በእለተ እሮብ ጠዋት ከማትታወቅ እርቃ ከነበረች ሴት የሦስት መቶ ስቅል(ዲናር) ሽቶ በስምኦን ቤት እግሩ ስር ፈሶለት ነበር። እርሱ አይደለም በዛው ቀን የፈሰሰለት ሽቱ ከተሸጠበት አስር እጅ ይልቅ ነበር።
እዚጋ የተካደው ኢየሱስ በመሆኑ እንጂ ነቢዩ ኤልሳዕ ሎሌው ግያዝ የማይገባውን ገንዘብ ከሶሪያዊው ንዕማን ተቀብሎ ከሸሸገ በኋላ የንዕማን ለምጽ በአንተ ላይ ይጣበቃል ብሎ ለምጻም እንደሆነ (2ኛ ነገ 5:20-27) ወይም ሐዋሪያው ጴጥሮስ ሐናንያ እና ሰጲራ የተባሉ ባልና ሚስት ከቤታቸው ሸሽገው መንፈስ ቅዱስን ሊያታልሉና በማስመሰል በፊቱ ሊቆሙ ሲሞክሩ እንደሚቀሰፉ ሲነግራቸው (ሐዋ 5፡ 1-10) ይሁዳ ግን እስከማስመሰሉ ከነቢያትም ከሐዋሪያትም በላይ የምህረት ጥግ ኢየሱስ ላይ ስለጣለው በነገው ሐሙስ አብሮት ሊበላ፣ እግሩንም ሊያጥበው አዘጋጅቶት ነበር።
መነሻ ሃሳብ ሕማማት መጽሐፍ
በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
In Christ
Henok