01/06/2023
ከአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የተላለፈ መልእክት
ግንቦት 24, 2015
የከተማችን ህዝበ ሙስሊም የነገን ጁመዐ በሰላም እንዲያሳልፍ የተላለፈ ጥሪ
ህዝበ ሙስሊሙ ከዚህ ቀደም ሀይማኖታዊ መብቱን ለማስከበር ብሎም በሀገር ደረጃ ለተደረገው የስርአት ለውጥ ፈር ቀዳጅ በመሆን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ቀድሞ የነበረውን አምባገነን ስርአት ለመለወጥ ፊት-አውራሪ በመሆን ታግሏል።
የስረአት ለውጥ ከተስተዋለ ወዲህ በተለይ በጠቅላይ ሚነስትራችን በክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ አሊ የሚመራው የሀገራችን መንግስት ለህዝበ ሙስሊሙ ቀድሞ የነበሩ የሀይማኖት መብት ረገጣዎች እንዲቀንሱ ፣ ህዝባችን ከመንግስት ጋር የነበረው ግንኙነት እንዲሻሻል ፣ ማህበረሰባችን ለሌሎች መጠቀሚያ እንዳይሆን በማድረግ መንግስታዊ ሀላፊነቱን በመወጣት በመሪ ድርጅቱ ስር እንዲጠለል አስተዋፆ አበርክቷል።
መንግስትም ህዝበ ሙስሊሙ ሲጠይቃቸው ከነበሩ ጥያቄዎች መካከል ተቋሙን በአዋጅ የማቋቋም መብት፣ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ፣የእምነት ተቋማት ቦታዎችን በህጋዊ መልኩ የማግኘት መብት በማመቻቸት ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎችን አበርክቷል።
ከላይ በጥቂቱ የተጠቀሱ ፋይዳዎች ለምን ለሙስሊሙ ማህበረሰብ እንደ ዜጋ ተከበረለት ፣ ለምን ተጠቃሚ ሆነ የሚሉ በእምነቱ ላይ የውስጥ ጥላቻ ያነገቡ፣የግል ፍላጎት ያላቸው፣ድብቅ የፖለቲካ አስተሳሰባቸውን ለማሳካት እንዲሁም ሙስሊሙ ማህበረሰብ ተጠቃሚነቱ ከጎላ ፣ሰላሙን ከተጎናፀፈ ማየትን የማይችሉ መስማትን የማይወድ ፣አካላት ሌት ተቀን በመስራት ማህበረሰባችንን ከመንግስት ለመነጠል እየሰሩ ይገኛሉ ።
በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሸገር ከተማ (ሲቲ) የመስጅድ ፈረሳ ጋር በተያያዘ ማህበረሰባችን ያቀረበውን ህገ መንግስታዊ የመብት ጥያቄዎች ማለትም የመስጅድ ፈረሳው ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ፣የፈረሱትም መስጅዶች ወደ ቀድሞው ቦታቸው እንዲመለስ መሪ ድርጅታችን መጅሊስ ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሚቴ በማቋቋም በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት በተለያዩ ደረጃዎች ከሚገኙ የመንግስት አካላት ጋር እያደረገ ይገኛል።
በመሆኑም መንግስትም የፍትህን መጓደል የጥያቄውን አሳሳቢነት፣በሸገር ሲቲ አስተዳደር በውይይት ላይ ያልተመሰረተን አካሄድን ከግንዛቤ በማስገባት ለተከሰተው የመብት ጥሰት ፍትህ የማስፈን ሚናውን በአፋጣኝ እንደሚወጣ ተስፋ እናደርጋለን።
በመጨረሻም ህዝባችን ኮሚቴው የደረሰበትን እስኪያሳውቀን ድረስ ውጤቱን በትእግስትና በዱአ እንዲጠባበቅ ጥሪያችንን እያቀረብን
የነገ የጁመአ ሰላት የከተማችን ሙስሊሞች በሁሉም መስጅዶች በሰላም ሰግዶ ወደ ቤቱ በሰላም እንዲመለስ መልእክታችንን እያስተላለፍን ፣
በከተማችን የሚገኙ ኢማሞች በሰላምና በትእግስት ዙሪያ የጁመአ ኹጥባ እንዲያደርጉ እናሳስባለን።
መንግስትም ጉዳዩን በፍጥነት እልባት እንዲሰጥ እና ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ከእስር እንዲለቅ አጥብቀን እንጠይቃለን።