01/10/2025
በሰሜን ሸዋ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አረርቲ ማርያም ርብራብ እንጨት ተደርምሶ ከ20 በላይ ሰዎች ሞቱ!
በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አረርቲ ማርያም ለግንባታ የተረበረበ እንጨት ተደርምሶ ከ20 በላይ ሰዎች ሕይወት አለፈ።
ዛሬ መስከረም 21 2018 ዓ.ም. የማሪያምን ዓመታዊ ክብረ በዓል ለማክበር በስፍራው የተገኘው ምዕመን እየተሰራ ያለውን ቤተክርስትያን እየጎበኘ ባለበት ሰዓት የተረበረበው እንጨት በመደርመሱ በሰው ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት ደርሷል።
አደጋው የደረሰው ማለዳ ከጠዋቱ 1:45 ላይ መሆኑን የአረርቲ ከተማ ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አጥናፉ አባተ ለብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣብያ ተናግረዋል።
በአደጋው 22 ሰዎች እስካሁን ድረስ ሕይወታቸው ማለፉ ሲረጋገጥ ከ200 ሰዎች በላይ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አህመድ ገበየሁ ለፋና ብሮድካስቲንግ ተናግረዋል።
በመደርመስ አደጋው የተጎዱ ሰዎችን የአካባቢው ኃላፊዎች በወረዳው ወደሚገኙ የተለያዩ የሕክምና ተቋማት መወሰዳቸውን ይናገራሉ።
የአረርቲ ከተማ ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አጥናፉ አባተ ለብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣብያ አሁንም ከርብራቡ ሥር ያልወጡ ዜጎች እንደሚገኙ እና እነርሱን የማውጣት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የአረርቲ ሆስፒታል ኃላፊ ተወካይ አቶ ስዩም አልታዬ በበኩላቸው ከጠዋቱ 2:30 ጀምሮ ወደ አረርቲ ሆስፒታል የመጡ ተጎጂዎችን ሕክምና እየሠጡ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል አምስቱ ወደ አዲስ አበባ መላካቸውን ጨምረው ተናግረዋል።
ዘገባው የቢቢሲ ነው!