08/05/2021
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ መታሰቢያ ታደሰ ታስረው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የሰጠውን ትዕዛዝ አነሳ። ፍርድ ቤቱ በአቶ ኃይለማርያም ላይ ምንም የሰጠው አስገዳጅ ትዕዛዝ የለም።
ፍርድ ቤቱ ሀምሌ 12 ቀን በተከሳሽ እነ ሜጄር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው መዝገብ በተከሳሽ የመከላከያ ምስክርነት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ የወጣውን መጥሪያ ጽ/ቤቱ የማያገባው በመሆኑ መቀበል የማይኖርበት ቢሆንም የፋውንዴሽኑ ጽህፈት ኃላፊ ፈርመው ተቀብለው ነበር።
ይሁንና የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በውጭ ሃገር በሌላ ስራ ላይ የሚገኙ በመሆኑና ለረጅም ጊዜ ሊያገኟቸው ባለመቻላቸው መጥሪያውን ሳያደርሱ ቀርተዋል።
ይሄንኑም ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ሀምሌ 22 ቀን 2013 ዓ/ም በዋለው ችሎት መጥሪያውን ፈርመው የተቀበሉት ወ/ሮ መታሰቢያ ታደሰ ለምን ለአቶ ኃይለማርያም ሳያደርሱ እንደቀሩ በችሎት ታስረው ቀርበው እንዲያስረዱ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል።
ሃላፊዋ መጥሪያውን ለአቶ ኃይለማርያም ያላደረሱበትን ምክንያት በጽሑፍ ለፍርድ ቤት በወቅቱ ያላሳወቁት በህመም ምክንያት በቢሮ ስራ ላይ ስላልነበርኩ ነው በሚል በአካል ቀርበው ለችሎቱ አስረድተዋል።
በዚህም ምክንያት ወ/ሮ መታሰቢያ ታደሰ ታስረው ይቅረቡና ያስረዱ በሚል ፍርድ ቤቱ የሰጠውን የእስር ትዕዛዝ ማንሳቱን አስታውቋል።
በግል ስራ ምክንያት ለረጅም ወራት በሃገር ውስጥ የሉም የተባሉት አቶ ኃይለማርያም ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱበት ሁኔታ ከተፈጠረ እና ለመመስከር ፈቃደኛ ከሆኑ በምስክርነት የሚቀርቡ ከመሆን ውጭ ለግለሰብ ተከሳሾች የመከላከያ ምስክርነት ለመስጠት ግዴታ እንደሌለባቸው የህግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የሃይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ኃይለማርያም ከአፍሪካ ህብረትና አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የአረንጓዴ ልማትንና የአፍሪካ ኢኮኖሚ ሪፎርም በማዘጋጀት በጎ ተግባራት ላይ ተሰማርተው በውጭ ሀገራት እየሰሩ ይገኛሉ።
በዚህም ምክንያት ፍርድ ቤቱ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ተገደው ለምስክርነት እንዲቀርቡ በሚል የሰጠው ምንም አይነት ትዕዛዝ አለመኖሩን መረዳት ተችሏል።
የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ሀገር የመምራት ስልጣንን በሰላም በመልቀቅ ለሀገርና ህዝብ የላቀ ጥቅም ላበረከቱት አስተዋጽኦ በአፍሪካ በምሳሌነት ስማቸው ከሚነሱ ጥቂት የሀገር መሪዎች አንዱ ናቸው።