
04/03/2025
ከሀምሌ ወር አንስቶ ለሙዚቀኞች የሮያሊቲ ክፍያ ሊጀመር ነው
አዲስ በወጣው መመሪያ መሰረት ማናቸውም ሚዲያ ለሚያስተላልፈው ሙዚቃ ለሙዚቃው ባለቤቶች ክፍያ መፈፀም ይኖርበታል፡፡
መመሪያው የተዘጋጀው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ይህንን ጉዳይ የአእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን እንደሚከታተለውና እንደሚያስፈፅመው ተነግሯል፡፡ የሮያሊቲ ክፍያው ስርአት በቴክኖሎጂ ታግዞ በሶፍትዌር የሚመራ ሲሆን ሚዲያዎች የሚያሰራጩትን ሙዚቃ ወደሶፍትዌሩ የመላክ ግዴታ ይጣልባቸዋል፡፡
በመሆኑም በተሰራጨው ሙዚቃ ልክ ተሰልቶ ለሙዚቀኞቹ የሮያሊቲ ክፍያቸው እንደሚፈፀም ተሰምቷል፡፡ በአዲሱና ከሀምሌ ወር አንስቶ ተግባራዊ በሚሆነው መመሪያ መሰረት አንድ ሙዚቃ በሬዲዮ ወይንም በሌላ ሚዲያ ሲሰራጭ ለሙዚቀኞቹ ሀያ ሳንቲም የሚከፈል ይሆናል፡፡
ከዚህ በላይ ሙዚቀኞቹ ደግሞ ከጠቅላላ ገቢያቸው ላይ ሁለት ፐርሰንት ለመንግስት በግብር መልክ እንደሚከፍሉ መመሪያው አስረድቷል፡፡ ዲጄዎችና ሌሎች መዝናኛ ቦታዎች ለሚያጫውቱት ሙዚቃ ደግሞ በግምትና በድርድር ክፍያ እንዲፈፅሙ የሚገደዱ መሆኑን መመሪያው አስታውቋል፡፡