02/10/2025
* ፆመ ነነዌ*
“ምንተ እንከ ንረሲከ ወየኃድገነ ባሕር ይትሃወክ ባሕር ወይትነሣእ ማዕበል ዓቢይ”
"ባሕሩ ከእኛ ፀጥ እንዲል ምን እናድርግብህ" ትን/ ዮናስ ምዕ 1 ቁ 11
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከምትፈፅማቸው ከ ፯ቱ አፅዋማት አንዱ የሆነው ፆመ ነነዌ ይባላል::
ፆመ ነነዌ :- የተባለው የነነዌ ሰዎች በኃጢአት ምክንያት የመጣባቸውን የእግዚአብሔር ቁጣ ፣ ከጳጳስ እስከ ንጉሥ ፤ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ እንስሳትም ጭምር እንዲፆሙ በአዋጅ ታዞ የተፆመ ፆም ስለሆነ ነው::
ነነዌ :- ጥንታዊ ከተማ ስትሆን ምድር ካሏት ከዓራቱ አፍላጋት/ወንዞች/ መካከል አንዱ ጤግሮስ ወንዝ ዳር የምትገኝ በናምሩድ የተመሠረተች /ዘፍ 10: 11-12/ ለአሦር መናገሻ የነበረች እና ሰናክሬም ብዙ ሕንፃዎች የሰራባት በእንግሊዘኛው /Nineveh/ በአሁኑ Modern day city of Mosul in North Iraq/ ሞሱል የምትባል ከተማ ነበረች:: ነች::
የነነዌ ሰዎች ግፍ እና ክፋት ቅድመ እግዚአብሔር በመድረሱ ምክንያት አምላካችን ሳይመክር የማይገስፅ ፣ ሳይናግር የማያደርግ ፣ ትዕግሥቱ ብዙ ፣ ቸርነቱ ለዘለዓለም ነውና የነነዌ ሰዎች ከጥፋታቸው ተመልሰው ንሥሐ ይገቡ ዘንድ የአማቴ ልጅ ወደሆነው የስሙ ትርጉም ርግብ ከመ የዋህ ወደ ተባለው ወደ ነቢዩ ዮናስ ቃል መጣ::
ትንቢተ ዮናስ 1 ቁ 2
“ተነስተህ ወደዚያች ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሂድ::ክፋታቸውም ወደ ፊቴ መጥቷልና በእርሷዋ ላይ ስበክ::”
ነቢዩም ከአምላኩ የተሰጠውን ትዕዛዝ በማስተሀቀር ከእግዚአብሔር ሀሳብ ይልቅ የራሱን ሀሳብ አስቀድሞ ፣ ሀሰተኛ ነቢይ ላለመባል ፣ ካምላኩ ትዕዛዝ ይልቅ የራሱን ክብር አስበልጦ፣ ያስከበረውን፣ ነቢይ ያስባለውን፣ የሚወደውን፣ አምላኩን ትቶ፣ የነገረውን ላለመናገር፣ ያዘዘውን ላለመፈፀም፣ ኢዯጴ ወርዶ ገንዘብ ከፍሎ ወደ ተርሴስ በመርከብ ተሳፈረ::
ነቢዩ ሲሳፈር ኃይሉ ደክሞ፣ ተሰላችቶ፣ ጸሎቱን ትቶ፣ ካምላኩ ጠፍቶ፣ ራሱን ደብቆ፣ እውነትን አንቆ ነውና መርከቧ ውስጥ ሲገባ ዝሎ ነበር : : እንደ ገባም ከባድ እንቅልፍ ወሰደው::
ብዙም ሳይቆይ ከእንቅልፉም ሳይነቃ መርከቧ ማዕበል ተነሳባት:: አውሎ ነፋስም ነፈሰባት:: የእግዚአብሔር ቁጣ አናወፃት:: በውስጧ የተሳፈሩት ተጨነቁባት::ኡኡታ በዛባት::ዋይታ እና እሪታ ቀለጡባት:: ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚል ትንባሌ ተሰማባት ::
ይገርማል! አንድ ሰው ግን አይሰማም አይለማም፣ አያለቅስምም፣ አይጮህም፣ አይለምንም :: ሰው እያለቀሰ ብዙዎች በጭንቀት ተውጠው ብቻውን የተኛ ብቸኛ ሰው :: ዓቢይ ንዋም ላይ ያለ :: በከባድ እንቅልፍ የተወሰደ።
ተኝተው ዋይታ ጩኸት የማይሰማቸው፣
የሕዝብ ለቅሶ የማይጨንቃቸው፣
እውነትን የሚሸሹ፣
ሀቅን የሚንገሸገሹ፣
እግዚአብሔርን የሚዋሹ ዛሬም ከባድ እንቅልፍ ላይ ያሉትን ቤት ይቁጠራቸው:: እውነትን በሀሰት ቅድስናን በርኩሰት ሃይማኖትን በፍቅረ ንዋይ የለወጡትን ነቢያተ ሃሰትንማ እዚህ ታሪክ ውስጥ አንጨምራቸውም :: እነሱ ከዲያብሎስ ናቸው::
ነቢዩ ዮናስ ግን፣ የዋሁ ዮናስ ግን፣ ሁሉን አውቆ አንድ ነገር የተዘነጋው የእግዚአብሔር ነቢይ "እግዚአብሔር ሁሉም ሥፍራ መገኘቱ " የተሸፈነበት ሰው:: መፅሀፍ “ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ
ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ” እንዳለ (መዝ: ዳዊ 139 ፥ 7)። ከአምላኩ ሸሽቶ ተኝቶ ነበር:: ብዙም ሳይቆይ ግን ከእግዚአብሔር የሸሸው ዮናስ ከከባድ እንቅልፉ በተጨነቁት የመርከቧ ተሳፋሪዎች ቅስቀሳ እንዲነሳ ሲደረግ፤ ደነገጠ፣ ነገር ተለውጧል :: ሁሉም ነገር ከሰዎች ዓቅም ብላይ ሆኗል:: የሚደብቅበት ጥግ የሚሸሽበት ጫካ የሚሄድበት ሀገር የለውም :: በውቅያኖስ ተከቦ ነፍስ ውጪ ንፍስ ግቢ ጭንቀት :: ከሞት ጋር ግብ ግብ:: ከመልዓከ ሞት ጋር ትንቅንቅ:: ያስፈራል። በሚያየው ነገር ሁሉ ይሄ ነገር የመጣው በኔ ምክንያት ነው የሚል ውሳኔ ወዲያው ወደ አዕምሮው ገባ:: ጥፋቱ ገባው:: ዳዊት :- "ለስሒት መኑ ይሌብዋ " እንዲል ስሕተቱን ያላስተዋለው ዮናስ ጥፋቱን በማዕበል ውስጥ አያት:: በእግዚአብሔር ቁጣ ውስጥ አስተዋላት:: የሸሸው ቦታ ድረስ የተከተለውን አምላኩን ሥራ አየና ባሕሩ ጸጥ እንዲል ጥፋቱ እንዲቆም ምን እናድርግ ባሉት የሰዎቹ ጥያቄ ውስጥ : “እኔ ጣሉኝ!” ይሚል ድምፅ ለራሱ ተሰማው:: ራሱ በራሱ ላይ ወስኖ " የወደደከውን አድርገሀልና እናመሰግንሃለን" እስኪሉ ድረስ በሚያስገርም ሁኔታ ከጥልቁ እንዲወድቅ ሆነ::
ነገር ግን በሥህተቱ ሊያስተምረው፣ በነፍሱ ላያጠፋው፣ ትዕዛዙን እዲያደርስ አስቀድሞ ነቢዩን የዋሁን የወደደው የመረጠው አምላክ ሳይተወው በጥልቁ ውስጥ እንዲያመሰግን አፉን ለምስጋና ሳይዘጋ፣ አንደበቱን ሳይከለክል፣ በከርሰ አንበሪ ሆድ ውስጥ ሳያሟሟው፣ ነፍሱን ከሥጋው ሳይለየው፣ እስትንፋስ ሰጥቶ በዓሳ አሳፍሮ ነነዌ ጠረፍ ላይ ወርውሮ የአንድ ቀን መንገድ በእግሩ አስጉዞ "ነነዌ ትገለበጣለች" ብሎ እንዲሰብክ አደረገው::
"በልዎ ለእግዚአብሔር ግሩም ግብርከ"
"እግዚአብሔር ሥራህ ድንቅ ነው በሉ"
የነነዌ ሰዎችም የነቢዩን ቃል ሰምተው ከገቢረ ኃጥዕ ወደ ገቢረ ፅድቅ፤ ከርኩሰት ወደቅድስና ተመልሰው መዓቱ በምህረት ቁጣው በትዕግስት ተመልሶላቸው ንስሐ ገብተው ከቁጣው ዳኑ:: የእሳት ምልክት አይተው የምህረቱ ደጅ ተከፈተላቸው:: የነደደው እሳት የዛፍ ቅጠል በልቶ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ተመለሰ:: ምክንያቱም “አንኳኩ ይከፈትላችሁአል፤ እሹ ታገኛላችሁ፤ ለምኑ ይሰጣችሁአል” የማቴዎስ ወንጌል ምዕ 7፥ 7 (ቀሪውን ትን/ ዮናስ ከምዕ 4 እስመ ፍፃሜ ምዕራፍ ያንብቡ)።
የትምህርቱ ምስጢር:-
ዮናስ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሰ አንበሪ ማደሩ:-
ጌታችን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር የማደሩ ምሳሌ፤
ነቢዩ በሦስተኛው ቀን ከዓሳው ሆድ ውስጥ መውጣቱ:-
ጌታም በሶስተኛው ከሙታን የመነሳቱ ምሳሌ፤
የነነዌ ሰዎች ንስሐ መግባታቸው እና መመለሳቸው:-
በንስሐ የማይመለስ ኃጢአት አለመኖሩ፤
ነቢዩ እንደ ስሙ የዋህ ርግብ እንደሆነ ሁሉ:-
እናንተም እንደ ዮናስ ቅኖች የዋሆች ሲል፤
በአንደኛው ጥሪ እና ትዕዛዝ እንቢ ብሎ ቢሸሽም በሁለተኛው ግን ከስህተቱ ተምሮ ከአምላኩ እንዳልተለያየ ክብሩም እንዳልጎደለ :-
እናንተም ብትሳሳቱ የዋህ ከሆናችሁ፣ እውቀት ከጎደላችሁ፣ ከስህተታችሁ ከተመለሳችሁ ሁለተኛ እድል እንደሚሰጥ ለማስተማር ነው፤
"ወኩሉ ዘተፅህፈ ለተግሳፀ ዚአነ ተፅህፈ እንዲል መፅሀፍ ""መፃህፍት ለኛ በህይወተ ሥጋ በቁመተ ሥጋ ላለነው ለምክር እና ለተግሣፅ ይሆኑን ዘንድ ተፅፈዋልና ነው። ይቆየን
የቅድስት ሥላሴ በረከት በሁላችን ላይ ይደርብን!!!
የበረከት ፆም ያድርግልን!
ቨርጅንያ ቅድስት ሥላሴ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን
የካቲት 01 ቀን 2017 ዓ/ም