20/09/2023
የሁምቦ ወረዳ አስተዳደር ለ50 አቅም ደካሞችና 480 በላይ ወላጅ አጥ ተማሪዎች የመማርያ ቁሳቁስ፣ አልባሳትና የተለያዩ ድጋፍ አድርጓል
ወላይታ ሶዶ፣ መስከረም 09/2016 ዓ.ም በወላይታ ዞን ሁምቦ ወረዳ ከሁሉም ቀበሊያትና ታዳጊ ማዘጋጃዎች ለተወጣጡ ለ50 አቅም ደካሞችና ወላጅ አጥ 480 በላይ ተማሪዎች የመማርያ ቁሳቁስ፣ አልባሳትና የተለያዩ ድጋፍ ተደርጓል።
የሁምቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፀጋዬ ቀልታ በዛሬው ዕለት የሚደረገው ድጋፍ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት አካል መሆኑን ገልጸው፣ በወረዳው በክረምት ወራት በረካታ ማህበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ ያደረገ ሥራ በሁሉም ትኩረት መስኮች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በጎ ሥራ ከፍተኛ የአእምሮ እርካታ የሚሰጥ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በዛሬው ዕለትም አንድም ተማሪ በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ከትምህርት ገበታ እንዳይቀሩ ያለመ ተግባር ተከናውኗል ብለዋል።
በጎ ፍቃድ አገልግሎት በክረምት ወራት ብቻ ሳይሆን በበጋም እንዲሁም ባህል ሆኖ እንዲቀጥል እየተሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
የወላይታ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ም/ኃላፊና ወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ደረጀ በወረዳው በጎ ፍቃድ አገልግሎት የተሰሩ ሥራዎች በጣም ተስፋ ሰጪና ለሌሎች አካባቢዎች ተሞክሮ የሚሆን ነው ብለዋል።
ወላጅ አጥና የአቅም ደካማ ቤተሰብ ልጆች በትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ከትምህርት ገበታ እንዳይቀሩ ለማድረግ የተሰራው ሥራ እጅግ በጣም ጥሩ በመሆኑ ወረዳውን አመስግነው፣ ይህ ተግባር የአእምሮ እርካታ የሚሰጥና ከፈጣር ዘንድም ዋጋ ያለው ተግባር ነው ብለዋል።
የሁምቦ ወረዳ ዋና የመንግሥት ተጠሪና የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አመኑ ጎአ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚመራ ዐቢይና ቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ ተግባሩን መምራቱን ገልጸዋል።
አቶ አመኑ አክለውም በሁሉም ቀበሊያት በጎ ፍቃድ አገልግሎት በትኩረት መሰራቱን ጠቁመው፣ በዝህም በረካታ ወጣቶች መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።
በዛሬው ዕለትም የመማርያ ቁሳቁስ እጥረት ላለባቸው ተማሪዎች የተለያዩ የመማርያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ጠቁመው በቀጣይም በጎ ፍቃድ አገልግልት ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።