27/08/2024
ቻግኒ
#ከተሞቻችን
ቻግኒ ከተማ በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ ዞን ውስጥ ትገኛለች፡፡ ከተማዋ በ1842 ዓ.ም እንደተቆረቆረች ይነገራል፡፡ ቻግኒ የሚለው የከተማዋ ስያሜ የአገውኛ ቋንቋ ሲሆን "ቻ" ማለት ነገ የሚል ትርጉም ሲኖረው፣ "ኒ" ማለት ደግሞ ቤት ማለት ነው፡፡ በዚህም "የነገ ቤት" የሚል የአማርኛ ፍቺ አለው።
ከባህር ጠለል በላይ 1 ሺሕ 538 ሜትር ከፍታ ላይ የከተመችው ቻግኒ ከተማ ቆላማ የአየር ንብረት አላት፡፡ ከመዲናችን አዲስ አበባ 495 ኪ.ሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ቻግኒ ለኑሮ የምትመች ከተማ ናት፡፡
ከተማዋ በአምስት የከተማ እና የገጠር ቀበሌዎች የተዋቀረች ስትሆን ልዩ ልዩ የሰፈር ስያሜዎች አሏት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ቴክኒክ፣ ጂጂ፣ መድሀኒያለም፣ ቦሌ፣ አባሙሳ፣ ሽሮ ሜዳ የሚባሉ የሰፈር ስሞች ይጠቀሳሉ።
በቻግኒ ሕዳሴ ቻግኒ 2ኛ ደረጃ፣ መሰረት 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ፣ ቻግኒ 2ኛ ደረጃ፣ ሂባ አካዳሚ፣ ቻግኒ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ እና ሌሎች የትምህርት ተቋማት ይገኛሉ፡፡
ከቻግኒ ከተማ በደቡብ አቅጣጫ 1 ኪ.ሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው "ዶንዶር ፏፏቴ" ልዩ የከተማዋ ተፈጥሯዊ መስህብ ሥፍራ ነው።
ከ35 ሜትር ከፍታ ላይ ቁልቁል እየተወነጨፈ ከሚወርደው ፏፏቴ የሚወጣው የውሃው ጭስ ለቻግኒና ለአካባቢዋ ድንቅ የተፈጥሮ ውበትን አላብሶታል፡፡ በፏፏቴው ዙሪያም እዕዋፋትን ጨምሮ የተለያዩ የዱር እንስሳት ይገኛሉ፡፡
ቻግኒ የሀገር ባለውለታ የሆኑ ታላላቅ ሰዎችን፣ ሙዚቀኞችንና ጋዜጠኞችን ያፈራች ከተማ ነች።
በዚህች ውብ ከተማ ተወልዳችሁ ያደጋችሁ እንዲሁም በተለያየ አጋጣሚ አይታችኋት ልዩ ትዝታን ያተረፋችሁ ትዝታችሁን አጋሩን።
መልካም ሳምንት!
በአዲስዓለም ግደይ