05/12/2024
አቶ ታዬ ደንደዓ ዛሬ ህዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ከእስር ተለቀዉ ከቤተሰባቸዉ ተቀላቅለዋል
ትናንት አመሻሹን ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ተለቀው ቤተሰቦቻቸውን ሳያገኙ ከማረሚያ ቤቱ በራፍ በጸጥታ ኃይሎች የተወሰዱት የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደዓ፤ ዛሬ እኩለ ቀን ደግሞ ሜክሲኮ ከሚገኘው የወንጅል ምርመራ ማዕከል ተለቀው ቤታቸው መድረሳቸውን ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ ዓለማየሁ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ ወ/ሮ ስንታየሁ እንዳሉት ጠዋት ቤተሰብ ሜክሲኮ ምግብ አድርሰዉላቸው ከተመለሱ በኋላ ዛሬ እኩለ ቀን ምሳ ሰዓት ከማቆያው እንዲወጡ ተወስኖ ሰባት ሰዓት ግድም መኖርያ ቤታቸዉ መድረሳቸውን አክለው አብራርተዋል፡፡
ባለፈው ሰኞ ህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም. የዋስትና መብት ተጠብቆላቸው ከእስር እንዲለቀቁ በፌዴራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት ከተወሰነላቸው በኋላ የማስለቀቂያ ሂደቶች ተጠናቀው አቶ ታዬ ትናንት በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር አመሻሹን 11 ሰዓት ላይ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቢለቀቁም የፀጥታ ኃይሎች የማረሚያ ቤቱ በራፍ ላይ ጠብቀው ወደ አልታወቀ ስፍራ እንደወሰዱዋቸው ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ ዓለማየሁ ለዶይቼ ቬለ ተናግረው ነበር፡፡
ባለፈው ሰኞ በፍርድ ቤት በ20 ሺህ ብር ዋስትና ክሳቸውን ከውጪ መከታተል እንዲችሉ በታዘዘው መሰረት ትናንት ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቢለቀቁም ለምን ወደ ሜክሲኮ የወንጀል ምርመራ ማዕከል እንደተወሰዱ ግን ቤተሰብ እንዳልተረዳ ነው የተነገረው፡፡
ትናንት አመሻሹን በዶይቼ ስለጉዳዩ የተጠየቁት የፌዴራል ፖሊስ ቃል አቀባይ አቶ ጀኢላን አብዲ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸውልናል፡፡
የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታና የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩት አቶ ታዬ ደንደዓ ከተከሰሱባቸው ሦስት ክሶች ሁለቱ ውድቅ ተደርጎላቸው “ከህግ አግባብ ውጪ የጦር መሳሪያ ይዘው ተገኝተዋል” በሚል የተመሰረተባቸውን አንዱን ክስ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በመከላከል ሂደት ላይ እንደሆነ ዶቼ ቬለ ዘግቧል።