27/01/2024
አትርፎ ደብረ-ወርቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድሪያል
" የደቡብ ቁልቢ "
የአትርፎ ደብረ-ወርቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ገደብ ቀበሌ የገረሙጀ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ከዞናችን ዋና ከተማ ወልቂጤ በ52 ኪ.ሜ እና የእዣ ወረዳ ዋና ከተማ ከሆነችው አገና በ10 ኪ.ሜ ርቀት በስተ-ምስራቅ አቅጣጫ የሚገኝ ነው።
ካቴድሪያሉ በ12ኛው መቶ ክፈለ-ዘመን በስደት ከአክሱም ፂዮን "ወሰናይ " ተብለው ይጠሩ በነበሩት አባት ከብዙ በጉዞአቸው ላይ ከነበረው ብዙ ተዓምር በኋላ ይዘው በማምጣት እንደሰየሙት በጉራጌ ሀገረ-ስብከት የእዣ ወረዳ ቤተ-ክህነት ስራአስኪያጅ እና የአትርፎ ደብረ-ወርቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል አስተዳዳሪ የሆኑት መላከ ብርሃን ብስራት አካለ ወልድ ይናገራሉ ።
በየዓመቱ ጥር 18 በርካታ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች በመሳተፍ በድምቀት የሚከበረው ካቴድሪያሉ በአባታችን በአቡነ መልከ-ፄዲቅ ከተለያየ ቦታ በመምጣት እጅግ ቁጥር ያላቸው እንግዶች በክብረ -በዓሉ መገኘትና የተሳሉትን ስለት ቶሎ የሚሰማ መሆኑን ብዙዎቹ በመመስከራቸው ምክንያት " የደቡብ ቁልቢ " የሚል ስያሜ እንደሰጡትም የደብሩ አስተዳዳሪ መላከ ብርሀን ብስራት አካለወልድ ያስረዳሉ ።
በካቴድሪያሉ ከነሀስና ብር የተሰሩ ጥንታዊ መስቀሎች ፡ ፅዋዎች ፡ የተለያዩና እድሜ ጠገብ የብራና መፅሀፎች ፡ የጥበቃ መሳሪያዎችና በርካታ ቅርሶች የሚገኙ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ በቀድሞ ሀገርመሪ በነበሩ እንደ አፄ ሚኒሊክ ፡ ደጅ አዝማቾች ፡ ደጅ አዝማች ባልቻ ፡ ደጅ አዝማች ሀብተ -ጊዮርጊስ የተበረከቱ ቅርሶች በካቴድሪያሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ በተሰራው ዘመናዊ ሙዚየም ውስጥ መመልከት ወይም መጎብኘት ይቻላል ።
ካቴድሪያሉ ከሀይማኖት ስርዓት በተጨማሪ ከእምነቱ ተከታዮች ውጪ ያሉትም ጨምሮ በተለያየ ማህበራዊ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ድጋፍ በማድረግ የሚታወቅ ሲሆን በደንና አካባቢ ጥበቃ ስራ አሻራ እያኖረ ያለና ከቫይረሱ ጋር ለሚኖሩ ወገኖች በቋሚነትም ይረዳል ።
ይህን ታሪካዊ ፡ ተፈጥሮዓዊ እና የበርካታ ቅርስ ባለቤት የሆነውን ካቴድሪያል እንድትጎበኙ እንጋብዛለን ።