29/11/2025
ኢሕአፓ ለህዳር 27 ለጠራው “ ታላቅ ሕዝባዊ ” ስብሰባ መንግስት አዳራሽ እንደከለከለው ለአዲስ ማለዳ ገለጸ
ቅዳሜ፣ ህዳር 20 ቀን 2018 ዓ.ም ( )
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ለህዳር 27 ቀን 2018 ዓ.ም “ ታላቅ ” ህዝባዊ ስብሰባ የጠራው ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ ነበር።
ፓርቲው ይህንን ታላቅ ሲል የጠራው ስብሰባም “ በብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ ” እንደሚያካሂድ ከሰኞ በኋላ ባሉት ቀናት ሲያስተዋውቅ ሰንብቷል።
ስብሰባውን ለማድረግም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድጋፍ ደብዳቤ እንዲጽፍለት ጠይቋል። አዲስ ማለዳ በተመለከተችውና ቦርዱ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት በጻፈው ደብዳቤ “ ፓርቲው ከቦርዱ ህጋዊ ዕውቅና አግኝቶ የሚንቀሳቀስ መሆኑ ታውቆ በህጉና ሥርዓቱ መሠረት ተገቢው ትብብር እንዲደረግለት ” ጠይቋል።
ይሁንና የከተማው አስተዳደር፣ ፓርቲው ለሚያደርገው “ ታላቅ ሕዝባዊ ስብሰባ ” አዳራሽ እንደከለከለ ኢሕአፓ ለአዲስ ማለዳ ነግሯታል።
ይህ ክልከላ ግን የተነገረው በቃል ደረጃ ብቻ መሆኑን አስታውቋል።
አዲስ ማለዳ ፓርቲው አዳራሹን እንደተከለከለ በገለልተኝነት ለማጣራት ያደረገችው ጥረት ለጊዜው አልተሳካላትም።
ክልከላውን አስመልክቶ ለአዲስ ማለዳ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን የሰጡት የኢሕአፓ ፕሬዝደንት አብርሃም ኃይማኖት “ ስብሰባውን ለማካሄድ አስተዳደሩ እንቅፋት እየፈጠረ ቢሆንም አዳራሹን ለማግኘት ከፌደራሉ መንግስት ተቋማት ጋር እየተነጋገሩ ” መሆኑን አመልክተዋል።
ፕሬዝደንቱ “ ሕዝብ የሚጠቀምበትን አዳራሽ አለመስጠት፣ የፖለቲካ ምህዳሩን መዝጋት ነው “ ሲሉም በይነውታል።
በተያዘው ዓመት ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ያስታወሱት አብርሃም “ ‛መንግስት ነጻ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እናደርጋለን’ ሲል ቃል ቢገባም፣ ለሂደቱ ወሳኝ የሆኑትን ጉዳዮች ከወዲሁ መከልከሉ ህገ ወጥነት ነው “ ሲሉም ገልጸውታል።
የአዳራሽ ክልከላው ተገቢም፣ ጠቃሚም አለመሆኑን የጠቀሱት የኢሕአፓው ፕሬዝደንት ድርጊቱ “ የፖለቲካ ምህዳሩን አደጋ ውስጥ መክተት ነው” ብለዋል።
የፌደራሉ መንግስትም ግዴታውን እንዲወጣ አጥብቀው ያሳሰቡት ፕሬዝደንቱ ይህንን ክልከላ የሚያደርጉት የታችኛው የመንግስት መዋቅር አካላትንም ከደርጊታቸው እንዲታቀቡ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ “ ታላቅ ሕዝባዊ ስብሰባ ” ሰላማዊ፣ ዋነኛ ዓላማውም ከህብረተሰቡ ጋር መወያየት ብቻ መሆኑን አጽዕኖት የሰጡት አብርሃም ታላቅ ያሉትን ስብሰባ መከልከል “ ምርጫ አታድርጉ እንደማለት ነው ” ሲሉ አስገንዝበዋል።
ኢሕአፓ ሰኞ ባወጣው መግለጫ “ በዚህ ታላቅ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ የንጹሃን እልቂት፣ የግፍ እስር፣ ጦርነት፣ ድህነት፣ ረሃብ፣ የሰላም እጦት፣ ስደት፣ መፈናቀል እና ሕዝባችንን ያጎሳቆሉት መከራዎችን ማብቂያ ዙሪያ እንደሚመከርም ” አስታውቆ ነበር።
ልክ የዛሬ ሁለት ዓመት፣ በተመሳሳይ ህዳር ወር፣ ጦርነት ይቁም፤ ተፈናቃዮች ወደቀዬያቸው ይመለሱ፣ መከላከያ ወደ ካምፑ ይግባ! የሚሉ መሪ ሃሳቦችን የያዘ ሰላማዊ ሰልፍ ህዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም ለማካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ህዝባዊ ትዕይንቱ ሳይካሄድ፣ የኢሕአፓ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የሰልፉ አስተባባሪዎች ለአራት ወራት ገደማ በአዋሽ አርባ በእስር አሳልፈው፣ መለቀቃቸው አይዘነጋም፡፡
ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA