29/04/2024
ሙሐመድ ዘይን ቢን ሐጅ ሲራጅ ቀኜ ይባላል። አላህ መልካም ስራውን ይወደድለት እና።
አባቱ "አባ ሐጅ ሲራጅ ቀኜ" (እነ-ሸኽ ቆላድባ) በርካታ የመንዙማ ኪታቦችን የከተቡ ሲሆን.... በወቅቱ እንዲህ እንደዛሬው ወረቀት አይገኝም ነበር እና የወረቀት እጥረት በመኖሩ... ከዘጋጇቸው በርካታ መድሆች በተጨማሪ እንዳይከትቡ አግዷቸዋል። በኪታብ ተከትበው ያሉትም ቢሆን... ወረቀት እንዲበቃ በማሰብ በእጅጉ ተጠጋግተው እና ተጣበው የተከተቡ ነበሩ። ሆኖም ግን በስነፅሁፍ እና በጋዜጠኝነት ዘርፍ መስራት ይፈልግ የነበረው ልጃቸው "ሙሐመድ ዘይን ቢን ሀጅሲራጅ ቀኜ" ከፍተኛ የሆነ የአረበኛ ኸጥ (ክትብ) ችሉታ ነበረው እና... ከረዥም አመታት የሱዳን ኑሮው ቡኃላ...ወደ ሐበሻ ሲመለስ፤ እነዛን ተጣበው እና ተጠጋግተው የተከተቡ፤ የመንዙማ ስንኞችን በህመም አልጋ ላይ ሆኖ፤ መድ ከወረቃት ማቆራኘት ችሏል። "ሙሐመድ ዘይን ቢን ሀጅ ሲራጅ ቀኜ" በቀላሉ በሚነበብ ባማረ የክትብ ዘዬ መንዙማዎቹን፤ በወረቀት ከትቦ ከጠረዘ ቡኃላ.... ይህን ኪታብ ያያችሁ፣ የቀራችሁ "አላህ ሙሐመድ ዘይንን እንዲምረው ዱአ አድርጉልኝ" በማለት የነሸኽን ተዕሊፋቶች ሙሉ በሙሉ ከትቦ አጠናቋል።
"ሙሐመድ ዘይን" ከተባውን "በነሸኽ ቆላድባ" ኪታቦች ሳያባራ በመቀጠል የ"ነሸኽ ምስላይ "ሐብለና" የተሰኘውን የተውሂድ ኪታባቸውን መክተብ እንደጀመረ፤ ህመሙ መጫጫን በረታ። "ሙሐመድ ዘይን" ኻቲማው ሊቃረብ ሶስት ቀን ያህል ሲቀረው፤ በጥልቅ የሐዘን ስሜት ውስጥ ሆኖ ለወንድሙ "ሙሐመድ ጀማል ቢን ሐጅ ሲራጅ ቀኜ"።እንዲህ አለው።
"አይ የኔ ነገር... ከሁሉ ሁሉ የሚቆጨኝ እንደ ሰዉ ቤት ኖሮኝ! ወንድሞቼን ጠርቼ፤ ዱአ ሳላስደርግ፤ ወንድሞቼን ሳላስተናግድ ሐያቴ በዚሁ ማለቁ ነው። አባቴም... አብሽር እንጂ አላህ ያሽርሀል እኮ አብሽር ይለዋል። ሆኖም ግን...አላህ የሻው በለጠ። መዱን ለቀቀ። ላይመለስ አሸለበ። በወረሀ የካቲት በ1995 ዓ.ኢ አረፈ።መካነ መቃብሩም በአ/አ እንቁላል ፋብሪካ ጉለሌ እስላም መቃብር ተፈፀመ።
ሙሐመድ ዘይን በቁመቱ ሎጋ ነበር። አንገተ መለሎ።
ሱዳን ሐገር አግብቶ የነበረ ቢሆንም... ልጅ ግን.. ከሚነላህ አልተቸረም። የልጅ ያህል መታወሻ የሆኑት ግን.... የአባቱን ኪታቦች አሳምሮ፣ አስውቦ መክተቡ ነበር።
አሁን ላይ የነሸኽ ቆላድባ ኪታብ፤ በሙሐመድ ዘይን ክትብ፤ በኮፒ ተባዝቶ፤ በጎንደር፣ በጎጃም፣ በሰሜን ወሎ በስፋት ተዳርሷል። ዛሬም፣ ነገም፣ ወደፊትም የነሸኽ ቆላድባ ኪታብ የተመለከተ ሙሐመድ ዘይንን ያስታውሳል። ፋቲሀ ይቀራል። ታሪክም በጥሩ ይሰንዳል። አላህ መልካም ስራውን ይውደድለት እና።
አባ ሀጅ ሲራጅ ቀኜንም ልጃቸው ሙሐመድ ዘይንንም አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸው። ረህመተሏሂ አለይሂ ራህመተን ዋሲዓ።
ምንጭ:- "ሙሐመድ ጀማል ቢን ሐጅ ሲራጅ ቀኜ"
"ከቀይ አራጣ እስከ ቆላድባ"
"ሰፊውን ታሪክ በሰፊው ይሰነዳል"
ኢንሻአላህ....
"ቆላድቦች መጀን"
✍ አብዱረቢ ሙሐመድ ጀማል