15/12/2024
ዳለቲ በሚገኘው ኑር መስጅድ ግቢ ውስጥ 1 ሺህ ለሚጠጉ አቅም ለሌላቸው አረጋውያን እና ህፃናት የነፃ የህክምና አገልግሎት ተሰጠ!
- ሀሩን ሚድያ፣ ታህሳስ 6/2017፣ ዳለቲ
የኢትዮጵያ ሙስሊም ጤና ባለሙያዎች ማህበር WPV 2050 እና ከዳለቲ ሽማግሌዎች ምክር ቤት ጋር በመተባበር በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ በሚገኘው በዳለቲ ኑር መስጅድ ጊቢ ውስጥ 1ሺህ ለሚጠጉ የአካባቢው ነዋሪ ለሆኑ አቅመ ለሌላቸው ወጣቶች፣ እናቶች፣ አባቶች እና ህፃናት የነፃ የህክምና አገልግሎት መሰጠቱ ተገልጿል።
የሙስሊም ጤና ባለሙያዎች ማህበር በየ15 ቀኑ የነፃ ህክምና አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን በዛሬው ዕለት በዳለቲ ኑር መስጂድ የተሰጠውም የነፃ ህክምና ለስምንተኛ ዙር መሆኑን የማህበሩ አመራሮች ለሀሩን ሚድያ ተናግረዋል።
ዛሬ በተከናወነው የነፃ ህክምና አገልግሎት ላይ ከ1,000 በላይ የሚሆኑ የዳለቲ አካባቢ ነዋሪዎች ተገኝተዋል። ከሀሩን ሚድያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የነፃ ህክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎች እንደገለፁት ይህ ተግባር መስጂድ ውስጥ በመደረጉ መደሰታቸውን አንስተው በበጎ ፍቃድ ለተሳተፉ ጤና ባለሙያዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በዛሬው በነፃ ህክምና መርሀግብር ላይ ለአካባቢው ነዋሪዎች የአይን ህክምና፣ የጥርስ ህክምናን ጨምሮ የአጠቃላይ ምርመራ አገልግሎት ተሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ሙስሊም ጤና ባለሙያዎች ማህበር በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተመዝግቦ የሚገኝና ሙስሊም ጤና ባለሙያዎችን በማስተባበር ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።
በተለያየ ቦታ ህብረተሰቡን በማገልገል የምትገኙ የሙስሊም የጤና ባለሙያዎችም ማህበሩን በመቀላቀል በሚሰሩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ እንድታሳተፉ የሙስሊም ጤና ባለሙያዎች ማህበር የበላይ አመራሮች ጥሪ አቅርበዋል።
- ሀሩን ሚድያ በዝግጅቱ ላይ በመገኘት ያጠናቀረውን የቪድዮ ዝግጅት በአላህ ፍቃድ ወደ እናንተ የሚያደርስ ይሆናል።
© ሀሩን ሚድያ