13/09/2024
ዝም ብለህ ሥራ!
ያስነሣህ ያውቅሃል፣
ውድህ ያልቅሃል፣
ሥራህ ይገልጥሃል፣
ያደለው ያይሃል፤
ዝም ብለህ ሥራ
ይች ሀገር መች አጣች ሺ ተሥፋዎች አውሪ፣
ይች ሀገር መች አጣች አቃቂር ነጋሪ፣
ይች ሀገር መች አጣች ቱማታ ቀማሪ፣
ይች ሀገር መች አጣች ተችና አነዋሪ፣
ዝም ብለህ ሥራ!
ለሞተው ሕዳሴ ካሳየህ ትንሣኤ፣
ግንባሩ ተንዶ ከሆነ ጉባኤ፣
ከተማው ከሞቀ በሦስት ወር ሱባኤ፣
ሥራ አይቶ ከጮኸ የሠናይ ጸላዔ፣
ዝም ብለህ ሥራ!
ወንጪና ሐላላ፣ እንጦጦ ጎርጎራ፣
ባያገኝም ሰሚ ሲናገር ሲጣራ፣
ዓባይ ስሙኝ ቢልም አሻቅቦ እያየ ድልድይ እንደ ጣራ፣
ዓለም ዝም ቢልም ለአረንጓዴ ዐሻራ፣
ዝም ብለህ ሥራ!
ሕዝብ እንደሁ ገብቶታል ዕሴት በቁዔቱ፣
ቢያደነቁረውም ልሂቅ በየዓይነቱ፣
ያየውን ጭላንጭል ይሻዋል በብርቱ፣
አይቷልና ፍሬ በዓይኑ በብረቱ፣
ዝም ብለህ ሥራ!
በዘመንህ ካየህ ኃያላን ሲወድቁ፣
ብርቱዎች ነን ያሉት ሲፈጩ ሲደቁ፣
ለክፉ ያበሩት ሲሰነጣጠቁ፣
ሩቆቹ ቀርበው ቅርቦቹ ሲርቁ፣
ዝም ብለህ ሥራ!
ያሳይሃል ገና
ሲናድ ያ ተራራ፣
ሲሞላ ጎተራ፣
ችግኙ ሲያፈራ፣
ኢትዮጵያ ስትመራ፣
ዝም ብለህ ሥራ!
አትስማ ፈጽሞ
አንበሳው ቢያጓራ፣
ቀበሮው ቢያቁራራ፣
ጭልፊቱ ቢያጭራራ፣
ዘንዶው ቢያስፈራራ፣
ሁሌም ስለሚበልጥ ያለው ካንተ ጋራ፤
ዝም ብለህ ሥራ!
Via Daniel kibret