29/03/2023
ተሽከርካሪዎች በመንገድ ላይ ችግር ሲገጥማቸው በፍጥነት እገዛ ለማግኘት የሚያስችላቸው አዲስ የሞባይል መተግበሪያ (Mobile Application) ይፋ ተደረገ፡፡
ረብዑ መጋቢት 20 ቀን 2015 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል ይፋ የተደረገው ይህ መፍትሔ ሰጪ መተግበሪያ ‹‹ኑሀ የመንገድ ዳር እርዳታ ሰጪ /Nuha Roadside Assistant/›› የተሰኘ መተግበሪያ ነው፡፡
‹‹የሰው ልጅ የጤና ችግር ሲገጥመው የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና እርዳታ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ተሸከርካሪዎችም በመንገድ ላይ እክል ሲገጥማቸው የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል›› ያሉት የአዲስ አበባ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና የትራፊክ ደህንነት የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ የሆኑት ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ‹‹ኑሀ መተግበሪያ ለተሸከርካሪ የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ የሚሰጥ መፍትሔ ነው›› ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ የትራፊክ ሕግ አንድ ተሸከርካሪ በብልሽት ምክንያት በከተማ ውስጥ ከሁለት ሠዓታት በላይ ከከተማ ውጪ ደግሞ እንደመንገዱ ሁኔታ ከስምንት ሠዓታት በላይ መቆም እንደማይፈቀድለት ያወሱት ኢንስፔክተር አሰፋ ይሁንና አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ መኪኖች በብልሽት ምክንያት ከህግ ውጪ ለቀናት ቆመው ይታያሉ ብለዋል፡፡ ‹‹በእዚህ ሳቢያ በከተማዋ ስለሚደርሰው የትራፊክ አደጋ እና መጨናነቅ ከእኔ በላይ አስረጂ ሊኖር አይችልም›› ያሉት ኢንስፔክተር አሰፋ ‹‹ኑሀ መተግበሪያ ለእዚህ ችግር ፍቱን መፍትሔ ነው›› ብለዋል፡፡
ኑሃ መተግበሪያ አሽከርካሪዎች በቀላሉ ከጉግል ፕሌይ ስቶር አውረደው በስልካቸው ላይ ሊጭኑት የሚችሉት መተግበሪያ ነው፡፡ ይህንን መተግበሪያ ጭነው የተመዘገቡ አሽከርካሪዎች በጉዞ ላይ የተሽከርካሪ ችግር በሚገጥማቸው ጊዜ ቢበዛ ከግማሽ ሠዓት ባልበለጠ ጊዜ ሙያተኛ ያሉበት ድረስ መጥቶ እገዛ እንዲያገኙ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡ የተሽከርካሪው እክል በስፍራው በተገኘው የቴክኒክ ሙያተኛ ወዲያው የሚፈታ ካልሆነ ደግሞ መኪናውን አስጭኖ ጥገና የሚያገኝበት ቦታ ድረስ በነፃ የማድረስ አገልግሎት ይሰጣል፡፡
በእዚህ መተግበሪያ ወይም በአጭር የስልክ ቁጥር 6516 ላይ ተመዝግበው የኑሀን አገልግሎት ለሶስት ወራት ለማግኘት 825 ብር የሚከፈል ሲሆን ለስድስት ወራት አገልግሎት 1,500 ብር ለአንድ ዓመት አገልግሎት ደግሞ 3,000 ብር ይከፈላል፡፡
የደንበኝነት ክፍያን በቴሌ ብር ለመክፈል እንዲቻል በኑሀ የመኪና ብልሽት እርዳታ ሰጪ ድርጅትና በቴሌ ብር እልፍ ጉዳይ መተግበሪያ መካከል ስምምነት ተደርጓል፡፡
በኑሀ መተግበሪያው ይፋ ማድረጊያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የኢትዮ ቴሌኮም የቴሌ ብር ዳይሬክተር አቶ ሞሃመድ አብዱልሠመድ በኢትዮ ቴሌኮም ብቻ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ እንደማይቻል አስታውሰው ‹‹ዛሬ በተለይ በትራንስፖርቱ ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃት አለ፡፡ ይህ የኑሀ ተግባር ያንን መነቃቃት የበለጠ የሚያጠናክር እመርታ ነው›› ብለዋል፡፡
በኑሀ መተግበሪያ ለመገልገል የተመዘገበ አሽከርካሪ በጉዞ ላይ የጎማ ብልሸት፣ የነዳጅ ማለቅ፣ የመኪና በጭቃ ወይም በጉድጓድ መያዝ ቢያጋጥመው እንዲሁም ባትሪ ቢደክምበት እና የመኪናውን ቁልፍ ከውስጥ ሳያወጣ በሩ ቢቆለፍበት በፍጥትነት የእገዛ አገልግሎት እንደሚያገኝ ታውቋል፡፡ ፊውዝ መቀየርን ጨምሮ በአጠቃላይ ለሚያጋጥሙ ቀላል ብልሽቶች በሁሉም ክፍለ ከተሞች ለእዚሁ ተግባር በተመደቡና በተጠነቀቅ በሚጠባበቁ የድርጅቱ ሙያተኞች እገዛ የሚሰጥ መሆኑንም የድርጅቱ መሥራች የሆኑት ወንድማማቾቹ ፍፁም እና ነቢዩ ዘካሪያስ ገለፀዋል፡፡