Asash Media

Asash Media Contact information, map and directions, contact form, opening hours, services, ratings, photos, videos and announcements from Asash Media, Media/News Company, Adama Express Way, Addis Ababa.

12/11/2022
06/07/2022

የቤት ኪራይ ዋጋ መጨመር አይቻልም!

| ለቤት ኪራይ የወጣው ደንብ እስኪሻሻል ድረስ የኪራይ ዋጋ መጨመር የማይቻል መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

ከንቲባዋ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ ለቤት ኪራይ የወጣው ደንብ እስኪሻሻል የቤት ኪራይ መጨመር አይቻልም ብለዋል።

ከንቲባዋ በመግለጫቸው የከተማ አስተዳደሩ በየ3 ወሩ የሚታደስ መመሪያ እንደነበረው አስታውሰዋል።

ለቤት ኪራይ የወጣው ደንብ እስኪሻሻል ድረስ የቤት ኪራይ ዋጋ መጨመር የማይቻል መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማዋ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት በመኖሩ በዜጎች ላይ ጫና እያስከተለ በመሆኑ የቤት ኪራይ መጨመር መከልከሉን አስረድተዋል።

በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ በልዩ ሁኔታ አይቶ ደንቡ እስካልተሻሻለ ድረስ ምንም አይነተ የቤት ኪራይ ጭማሪ ማድረግ አይቻልም ብለዋል።

አከራዮችም ሆኑ ተከራዮች ይህንኑ ማወቅ እንዳለባቸው ጠቁመው ክልከላውን ተላልፈው በሚገኙ ላይ ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ዙሪያ ዜጎች መብትና ግዴታቸውን በቅጡ ተገንዝበው እንዲሰሩም አስገንዝበዋል።
Temesgen

29/06/2022

100.05 ቢሊዮን ብር!!!

የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ ለ2015 ዓ.ም 100.05 ቢሊዮን ብር በጀት እንዲፀድቅ ለከተማው ምክር ቤት አቅርቧል።

ረቂቅ በጀቱ ከ2014 በጀት ዓመት በ41.6 በመቶ አጠቃላይ እድገት አሳይቷል።
Office

09/06/2022

ዛሬ ምሽት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የግብፅ አቻውን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

12/05/2022

#መልካምዜና ጉግል የትርጉም መስጫ አገልግሎቱ (Google Translate) 24 አዳዲስ ቋንቋዎችን ማስጀመሩን ያስታወቀ ሲሆን በዚህ ውስጥ አፋን ኦሮሞ እና ትግርኛ ተካተዋል!

ከኢትዮጵያ ከአማርኛ በተጨማሪ ሌሎች ሁለት ቋንቋዎችን በ Google Translate አማካኝነት መተርጎም ይቻላል ማለት ነው። ከዚህ በኋላ "የተፃፈው ምን ይሆን?" ከማለት በቀጥታ ኮፒ አርጎ በማስገባት ትርጉሙን ማየት ይቻላል። አንዳንድ ግዜ የጉግል ትርጉሞች ችግር ያለባቸው ቢሆንም ብዙ ግዜ ግን እጅግ ጠቃሚ ናቸው።
Mesret

ጋዜጠኛዉ ተመልሷል!!ከኢድ አልፈጥር አንድ ቀን ቀደም ብሎ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት በአጥር ዘለው አፍነው ከወሰዱኝ በኋላ አሁን ከምሽቱ 3:00...
09/05/2022

ጋዜጠኛዉ ተመልሷል!!

ከኢድ አልፈጥር አንድ ቀን ቀደም ብሎ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት በአጥር ዘለው አፍነው ከወሰዱኝ በኋላ አሁን ከምሽቱ 3:00 አይኔን በጨርቅ አስረው ቤቴ በር ላይ ጥለውኝ ሄደዋል።
እስከ ዛሬ የት እንዳቆዩኝ ግን አላውቅም። በጤናዬ ላይ የደረሰ ነገር የለም።

07/05/2022

ዜናነህ መኮንን -ZENANEH MEKONEN

ተወዳጅ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን የሚዲያ ሰዎች ታሪክ ከአንጋፋ እስከ ወጣት በሚል ሀሳብ ከ130 በላይ የሚዲያ ሰዎችን ታሪክ ደረጃውን በጠበቀና ጠንካራ ሽፋን/hard cover/ ኢንሳይክሎፒዲያ ሊያሳትም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከዚያ ድረስ ታሪካቸው በዚህ ዊኪፒዲያ እና በተወዳጅ ሚዲያ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ከሚነገርላቸው መካከል ጋዜጠኛ እና ዜናነህ መኮንን ይነሳል፡፡

አሁን ታሪኩን የምናቀርብላችሁ ሰው ጋዜጠኛ ፤ ደራሲ ፤ ገጣሚ ሀያሲና የዜና አንከር ወይም ስመጥሩ የዜና አቅራቢ ነበር፡፡ ዜናነህ መኮንን፡፡ ተወዳጅ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን የሚዲያ ሰዎችን ታሪክ አሳብስቦ በኢንሳይክሎፒዲያ ቅርጽ ለማሳተም ጉዞ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ እስከ ህትመቱ በዚህ ገጽ ስለ ዜናነህ መኮንን አጭር ግለ-ታሪክ ታውቁ ዘንድ
ይህን ጽፈናል፡፡ የዚህ ግለ-ታሪክ አዘጋጅ የተወዳጅ ሚድያ ከፍተኛ የዊኪፒዲያ ኤክስፐርት የሆነችው ዘቢባ ሁሴን አሊ ናት፡፡ ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ በአርትኦት እና መረጃዎችን በማቅረብ እገዛ አቅርቧል፡፡ ታሪኩን በጥሞና ታነቡ ዘንድ እነሆ ብለናል፡፡

አንጋፋዎቹ መገናኛ ብዙሀን የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በ1970ዎቹና 80ዎቹ ሲታወሱ ዛሬም ድረስ ስሙ በጉልህ ይነሳል። የታሪክ ተመራማሪ፣ የመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ተንታኝ የጀርመን ድምፅ ሬዲዮ ልዩና ተወዳጅ ዘጋቢ ነዉ፡፡ ዜናነህ መኮንን፡፡ ከጋዜጠኛነቱ በተጨማሪ ደራሲ ፣ገጣሚና ሃያሲም ነው። ከግርማ ሞገሱ ጋር ግርማ ሞገስን የሚያላብስ ልብስ ለብሶ በኢትዮጲያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሸቱ ሁለት ላይ “ጤና ይስጥልኝ እንደምን አመሻችሁ ከሰዓቱ ዜና ጋር ዜናነህ መኮንን ነኝ” በማለት እጅ ሲነሳ የብዙዎች ትዝታ ሆኖ አልፏል። በበርካታ የቲቪና የሬድዮ ተከታታዮች ዘንድም የሚወደድ ነው፡፡ የጀርመን ድምጽ (ዶቼ ዌሌ ሬዲዮ) የጣቢያው መክፈቻና መዝጊያ ድምፅ የዚሁ አንጋፋ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ይህ ሰዉ ኑሮውን በእየሩሳሌም ካደረገ ዘመናት ተቆጥረዋል።
ውልደትና እድገት
ዜናነህ በ1945 ዓ.ም ጎንደር አዘዞ በምትባል ከተማ ውስጥ መስከረም ወር ላይ አደይ አበባና አዲስ ዓመቱን ተከትሎ ነበር ወደዚህች ምድር የመጣው። ውልደቱ አዘዞ ይሁን እንጂ በቤተሰቦቹ የስራ ጸባይ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ የመጣው በልጅነቱ ነበር፡፡ በመቀጠልም ወደ ጂማ ሄዶ “ቆጪ” ሰፊር ይኖሩና ፃዲቁ ዮሀንስ (አሁን የመምህራን ማሠልጠኛ ተቋም ሆኗል)ይማር ነበር፡፡ ጂማ እስከ ሶስተኛ ክፍል ድረስ ከተማረ በኋላ ወደ ጎንደር በመሄድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ጨርሶ የሁለተኛውንም አጋምሷል። ከዚያም ወደ ድሬዳዋ በመጨረሻም ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ የሙዚቃ ፍቅር ስለነበረው በ60ዎቹ ገደማ ያሬድ ትምህርት ቤት ሙዚቃን ለመማር ገብቶም ነበር። የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱንም የጨረሰው እየሠራ በመማር ነበር።
የጋዜጠኝነት ሕይወት
ዜናነህ፣ በጄኔራል ዊንጌት የሁለተኛው ዙር የፖለቲካ ተማሪ ሳለ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ፓለቲካን የተለማመደው። በዚሁ አጋጣሚ በጣም ተከራካሪና ላመነበት ሟች መሆኑን ያዩ ወዳጆቹ ማስታወቂያ ሚኒስቴር እንዲቀጠር ይገፋፉት ነበር። ከዚያ 1968 ገደማ በሬዲዮ ሪፓርተርነት ተቀጠረ። የመጀመሪያው ንባቡ ‹‹የአብዮት መድረክ›› የሚባል የኢህአፓና የሜኤሶን የግጭት ሁኔታ የሚገልፅ በርካታ አድማጮች የነበሩት መሰናዶ ነበር።
እነ አሳምነው ገብረ ወልድ፣ እነ ዘውዱ ታደሠ፣ እነ መሀመድ እንድሪስ፣ እነ ንጉሴ ተፈራና እነ አብዱ ሙዘይን በኢትዮጲያ ሚዲያ ላይ ትልቅ አበርክቶ ያደረጉና የእኔም ሞዴል የምላቸው ናቸው ሲል በተለያዩ ሚዲያዎች ቃለ- መጠይቅ ሲያደርግ ይደመጣል።
በዋነኛነት ግን ወደ ጋዜጠኝነት ሞያ እንዲገባ አርአያ የሆነው አሳምነው ገብረወልድ እንደሆነ ይናገራል። ሌላዉ ደግሞ ጎንደር ትምህርት ላይ እያለ ሰኞ ሰኞ የጀርመን ራዲዮ ድምፅን አዘውትሮ ያደምጥ ስለነበር ያን ይዞ ሰልፍ ላይ ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀል ለመላ ተማሪዎቹ ያነብ ነበር። ይህም በኋላ ለነገሰበት የጋዜጠኝነት ሞያ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደነበረው ይናገራል።
ለመጀመሪያ ግዜ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ አዘጋጅ የነበሩት አቶ ማዕረጉ በዛብህ ግጥሞቹን በጋዜጣ ላይ ያወጡለት አጋጣሚ ጥሩ መነቃቃትና የእችላለሁ መንፈስ እንዲያድርበትም ያደረገው እንደነበር ይናገራል፡፡
አንዳንዴም ስምን መልዐክ ያወጣዋል እንዲሉ ዜናነህ ዜናን ሲያነብ አድማጮቹን የሚያከብር ፤ለማህበረሰቡ ቅርብ የሆኑ ጉዳዮችን አድኖ የሚዘግብ ጎበዝ ጋዜጠኛ ነበር። መንግስትን የሚቃወሙና በመንግስት ያኮረፉ ሰዎች የዜናነህን ዜና አድማጮች ነበሩ፡፡ የዜና አቀራረቡ፣ አከፋፈትና አዘጋጉ ላይ የሚያሳየው ትህትና ዜናነህን አይረሴ አድርገውታል።
የማስታወቂያ ሚኒስተር ዉስጥ ሲቀጠር ዘመኑ ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር ይካሄድ የነበረበት ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ከራዲዮ ወደ ቴሌቪዥን ገብቶ ዜናንና ከየአቅጣጫው የሚባል ፕሮግራም ተሰጠው፡፡ ይህ ወቅት ጥሩ መለማመጃ ሆኖለትም አለፈ። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ታሪክ ለ7 ዓመታት ያህል እንቁጣጣሽን አንባቢ የነበረውም ይሄው ዜናነህ ነበር። በጊዜው በነበረው ትእዛዝ መሰረት የቲቪ ወይም የሬድዮ አንከሮች እንኳን አደረሳችሁ ማለት አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡ ይልቁንም እንኳን ደረሳችሁ ብቻ እንዲሉ ይገደዱ ስለነበር ነው፡፡ ምክንያቱም ያኔ የነበረው የሶሻሊዝም አስተሳሰብ በእግዚአብሄር መኖር ወይም ሀይማኖት ላይ ጥብቅ ተቃውሞ ስለነበረው ነው፡፡ ዜናነህ ግን አልፎ አልፎ አውቆ እንኳን አደረሳችሁ በማለት ተመልካችን ሰላም የሚልበት ጊዜ ነበር፡፡
አንድ ወቅት ጄኔራልን ኮሎኔል ብሎ ዘግቦ በመሪዎች ዘንድ በእኩይ አይን ታይቶ እንደነበር ያታወሳል፡፡ ዜናነህ ዜና ማንበብ ሲጀምር "ይህ የኢትዮጵያ ድምፅ ነው" ብሎ መጀመሩን ሳይቀር እንዲያቆም የተከለከለበት አጋጣሚም ነበር። ዜናነህ በሃላፊው ተፈርሞ ያልተሰጠውንና እርሱ ያላመነበትን ጉዳይ የማይዘግብ፤ የራሱን ስሜት፣ አመለካከትና አተያይ በፍፁም በሚያነበው ዜና ውስጥ ጨምሮ አድማጭን የማያደናግር ሰዉ ነበር፡፡
በ1967 ዓ.ም በማስታወቂያ መምሪያ ጋዜጠኝነትን “ሀ” ብሎ የጀመረው ባለ ነጎድጓዳማው ድምፁ አንጋፋው ጋዜጠኛ ዜናነህ ሃሳቡን ያለ ይሉኝታና ፍርሃት በነፃነት መግለፅ መቻል ባህሪው ነው። ይህንንም የማይወዱለት ታዲያ ብዙ ዋጋን አስከፍለውታል። በደርግ ግዜ ከ1969-1971 ለ2 አመት በሙያው ብቻ የታሰረ ጋዜጠኛ ጥቀሱ ቢባል ዜናነህ ነበር። የኢህአፓ አባል ነህ በሚል የክስ ጭብጥ አስረውት ይህ አላስኬድ ሲላቸው ደግሞ የልዑል መኮንን ልጅ ነው በሚሉ አሉባልታዎች ከከፍተኛ አንድ ማዕከላዊ እስከ ዓለም በቃኝ ድረስ እሥር ቤቶቹን አፈራርቋል፡፡ ከእስሩ ሲፈታ ለሶስት ዓመት ያህል ያለ ኪራይ ከመምሪያው ሀላፊ ጎን ብስራተ ወንጌል ውስጥ ቤት ተሰጥቶት በነፃ እንዲኖር በማድረግ የሞራል ካሳም ተከፍሎት ነበር፡፡
ሁሌም ሽክ እና በሱፍ ግርማ ሞገስን ተላብሶ የሚታየው ዜናነህ ቡና የሚጠጣው እንኳን ቦታዎችን መርጦ ነበር። በተለይ የኢትዮጵያ ሆቴል ቡና ነፍሱ ነች፡፡ ይህ የሚያስቀናቸው ሰዎች ደግሞ ጠላቶቹ ሆኑ፡፡ “ቅናት የሚባለው ነገር የእውነት ደምና አጥንት እንዳለው የተረዳሁት ያኔ ነበር” የሚለው ዜናነህ ከዚህም ተነስቶ ነበር ‹‹ነፃነት›› የሚለውን የመጀመሪያ መጽሀፉን የፃፈው። “ትምህርት ከድል በኋላ” የሚለውን አባባል እና አመለካከት አጥብቆም ይቃወም ነበር፡፡ ይህ ልዩነት አሁንም ድረስ አብሮት ዘልቋል።

አበርክቶ
ዜናነህ፣ በሙያው በትላልቆቹ ዘንድ ትልቅ ከበሬታ ያገኘ ሰው ነው፡፡ አብዬ መንግሥቱ ለማ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ሲያስተምሩ “ዜና ዜናነህ አነበበ ሲባል ዘመዳዊ ተሳቢ ነው” እያሉ ስሙን ይጠሩትና ያደንቁትም ነበር፡፡
ዜናነህ “ነፃነት” የተሰኘ በአምስት ዓመቱ የጣሊያን ጦርነት የኢትዮጵያ ጀግኖች የከፈሉትን መስዋዕትነት የሚዘክር ታሪካዊ ልቦለድና በአዲስ አበባ ህይወት ላይ የሚያጠነጥን የመሀበረሰቡን አኗኗር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተጻፈ “ከጣሪያው ስር” የተሰኘ ልቦለድን ለአንባቢያን እንካችሁ ብሏል። በ1999ዎቹ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ማለት ነው አሜሪካን ሀገር ያሳተመውና ወደ 30 የግጥም ስብስብን የያዘ “በረከተ መርገም”ን የሚሞግት “በረከተ ራዕይ” በሚል ርዕስ የግጥም ሲዲ አውጥቷል፡፡ "የመንገድ ላይ ወግ" ኢትዮጲያን ወደ ኋላ ከሚጎትቷት ባሀርያት መካከል ቅናት ላይ የተሰራ ትያትርም ፅፏል። ዜናነህ በድርሰቶቹ ሀይማኖታዊ ፖለቲካዊና የፍትህ ጥያቄዎችን ይጠይቃል፡፡ ብዙዎቹ ስራዎችህ እንጉርጉሮ ይበዛባቸዋል ብለው ሲጠይቁት የኔ ስራዎች የማህበረሰቡ ቅጂዎች ናቸው "ኑሮ ካሉት መቃብርም ይሞቃል" ከሚል ማህበረሰብ ወጥቼ ከዚህ የተለየ ልፅፍ አልችልም ሲልም ይደመጣል።
በ1975 ላይ ቤተሰብ ለመጠየቅ ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር ተጉዞ ነበርና የተወለደባት አዘዞ መብራት ስላልነበራት በወቅቱ ከነበሩ ሺህ አለቃ መላኩ ተፈራ ጋር ተነጋግሮ መብራትም አስበርቶ ዜናነህ መብራት አስበራልንም ተብሎ ይነገር ነበር። ዓለም በቃኝ በእስር ላይ እያለም ስፖርቱ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴዎች ያደርግ ነበር።

የትዳር ህይወት
ዜናነህ ትዳር የመሠረተው ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ ነው። ከወይዘሮ አልማዝ ጥላሁን ጋር ትዳር መሰረተ፡፡ ገና ሚስት ሳያገባ ልጆች ብወልድ ስማቸውንም “ቢታንያ (ከሞት መዳን) እና ነፃነት (የመፀሀፌን ስያሜ) ለልጆቼ እሰጣቸዋለሁ ብሎ ያልም የነበረውን ለልጆቹ ስያሜ አድርጓል፡፡ አሁን ላይ የሦስት ሴት ልጆች አባት ሲሆን የመጀመሪያ ልጁ ቢታንያ 37 አመቷ የታሪክ ምሩቅ ነች፡፡ የ30 ዓመቷ ነጻነት ደግሞ ጎበዝ ተዋናይት ነች። ሶስተኛዋ ከፈረንጅ ሴት የተወለደችው የሩሲያ ዜግነት ያላት “ሩኒያ” ትባላለች፡፡
ከትዳር አጋሩ ጋር ለ5 ዓመት ያህል አብረው ከቆዩ በኋላ በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ትኩሳት ወደ አሜሪካ ሄዳ እንድትኖር አደረገ። ከባለቤቱ ጋርም ርቀት ለያያቸው። በአንድ ሰው ደመወዝ የልጆችን ፍላጎት አሟልቶ ማስተማሩ እየከበደው ሲመጣ ከሀገር መውጣት ግዴታ ሆነበት፡፡ ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ ቦታውን ሲቆጣጠረው ወደ እስራኤል ሀገር ሄደ። ልጆቹ ገና የ2 እና የ3 ዓመት ህፃን ሳሉ ነበር እናታቸው ጥላቸው የሄደችው። እነርሱ ዛሬ የደረሱበት እንዲደርሱ ትልቅ ስራ ነበረበት፡፡
ዜናነህ አሜሪካን ሀገር ፣ጀርመን ከዚያም ወደ ስዊድን፣ ኖርዌይ ተዘዋውሯል፡፡ ኖርዌይ በነበረበት ጊዜም ሊደርሺፕን ተምሯል፡፡ ልጆቹንም በእነዚህ ሀገራት ልኮ ማስተማር ይችል ነበር፡፡ ስብእናቸው ላይ መስራትና በእንክብካቤው ስር እንዲያድጉ በመፈለጉ ነበር በእስራኤል እንዲያድጉ የወደደው።
ዜናነህ፤ ትምህርት ቤቱን ብቻ አምኖ የሚተው አባት ሳይሆን የልጆቹን የቀን ተቀን ህይወት የሚከታተልና ስለ ልጆቹም አብዝቶ የሚጨነቅ አባት ነበር። በጣም አስቸጋሪ የፈተና ግዜንም አሳልፏል። ልጆችን ያለ እናት ብቻውን የማሳደጉ ሀላፊነትም በጫንቃው ላይ አርፏል። ሌላ ማግባት ሳያምረው ልጆቹን በኢትዮጵያዊ ስነ ምግባር አንፆ ያሳደገ እና የልጅ ልጅ ለማየትም የበቃ ጠንካራ ኢትዮጲያዊ አባትም ነው።
ህይወት ከሃገር ዉጭ
“አንተ ከአገርህ ልትወጣ ትችላለህ። አገር ግን ካንተ ውስጥ አትወጣም! ... እናም ኢትዮጵያ፤ አገሬ ሳልገባ አምላክ አይግደለኝ! “ሲል ይደመጣል፡፡ ዜናነህ መኮንን ከሀገሩ ወጥቶ ወደ እስራኤል ሃገር የተጓዘው በ1984 ዓ.ም አጋማሽ ነበር፡፡
ወደ እስራኤል ሀገር ከሄደ በኋላ ትምህርታዊ የሆኑ ፊልሞችን ዳይሬክት በማድረግ ሰርቷል። ለመጀመሪያ ጊዜ የ24 ሰዓት የግል ሬዲዮ ጣቢያ መስርቶ ይሰራ ነበር። በርካታ ሬዲዮ ጣቢያዎችን በማቋቋምና ወጣቶችን በማሰልጠን ዛሬ ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ ወጣቶችንም ማፍራት ችሏል።
በኋላም በ1991 አካባቢ ወደ አሜሪካም አቅንቶ ነበር። አሜሪካንም እንዳሰበውና እንደጠበቀው ስላላገኘው 9ወር አካባቢ እንደተቀመጠ ወደ ኖርዌይ ሄዶ በሊደር ሺፕ ተምሮ ተመርቋል። ከዚያ ወደ ልጆቹ ወደ እስራኤል ሀገር ተመልሷል። እስራኤል ሀገርም በርካታ ኮርሶችን ወስዷል።
እስራኤል ሀገር መኖሬ ምርጫ ሳይሆን የፈጣሪ ፍቃድ ነው ብሎ ያምናል። እስራኤል የአለም ማእከል ነችና በየግዜው ህይወት አለ ፤ዜና አለ ፤የፈጣሪን መኖር እንዳረጋግጥ አድርጎኛልና እስራኤል ለእኔ መማሪያ ትምህርት ቤቴ ነች ይላል።
እስራኤል ሀገር ከገባ በኋላ ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑ አካዳሚክ የሆኑና የፍልስፍና መፀሃፍትን ማንበቡን የሚያስታውሰው ዜናነህ በሳምንት አንድ ቀን ቅዳሜን ጠብቆ ከልጆቹ ጋር የሚወያይበትና መፀሀፍ ቅዱስን የሚያነብላቸው ቀን እንዳለው ይናገራል፡፡
ዜናነህ በዚህ በ30 ዓመት ጉዞ ውስጥ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ በርካታ የራዲዮና የቴሌቪዥን አስተማሪ ፕሮግራሞችን መስራት የቻለ ጠንካራና ተወዳጅ ጋዜጠኛ ነው።
“ጋዜጠኛ ጡረታ አይወጣም” በሚል ንግግሩ የሚታወቀው ዜናነህ አሁንም የጀርመን ራዲዮ ጣቢያ (ዶቼዌሌ) የመካከለኛው ምስራቅ ዘጋቢ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡
ሶስት መንግስታትን በጋዜጠኝነት ህይወት የኖረዉ ዜናነህ አሁን ሀገራችን ያለችበትን ለውጥ ይደግፋል፡፡ ነገር ግን ሀገራችን ኢትዮጵያ እንድታድግ ማህበረሰቡ እንደገና መወለድ አለበት የሚል እምነትም አለው። ወደ ፊት ሀገሩ ትልቅ ተስፋ እንዳላት አድርጎ ያስባል፡፡ በተለያዩ ዘርፎች ትክክለኛነትን የሚያሳዩ ሞዴል የሚሆኑ ባለሙያዎችም እንደሚያስፈልጓት ይናገራል፡፡አሁንም ኑሮውን በእስራኤል አድርጎ በሶሻል ሚዲያ ላይ ድምፅ ላነሳቸው ድምፅ እየሆነም ይገኛል።
የዜናነህ አንዳንድ ትዝታዎች
ዜና ነህ መኮንን እንደሚያስታውሰው ማእከላዊ እስር ቤት ሳለ ደርግ እነ ሃይሌፊዳ ዶ/ር ንግስት አዳነን በህይወት እንደሌሉ እየታወቀ ለምርመራ ስማቸውን ሲጠራ ይገርመው ነበር፡፡ እነ ሀይሌ እና ንግስት ተገድለው ሳለ ነገር ግን ይህ በደርጎች ሳይታወቅ ስማቸው ይጠራ ነበር፡፡
ታዲያ በዚያን ጊዜ ዜናነህ ደርጎች ያሰሩትን አያውቁም እንዴ ?ያለ በት ጊዜ ነበር፡፡
የኢህአፓው ብርሃነ መስቀልም እዛው ማእከላዊ ታስሮ ነበር ትዝ ይለዋል፡፡

ዜናነህ ኩላሊት ባይኖረኝም ለሃገሬ የምሰጣት ልብ አለኝ ይላል፡፡ ይህን ከአንድ ጣቢያ ጋር ባደረገው ቃለመጠየቅ የተናገረው ነው፡፡

አንድ ወቅት ዜናነህ ኖርዌይ ሳለ መፅሀፍ መሸጫ ገብቶ አንዳንድ ኖት ይወስዳል፡፡ ታድያ ኦስሎ መፅሃፍት መሸጫ ገብቶ እያነበበ ማስታወሻ ሲፅፍ ወደ 7 ፖሊሶች ከበቡት፡፡ ምን ወንጀል ሰራሁ ሲል መፅሃፍ እያነበብክ ማስታወሻ መያዝህ ነው አሉት፡፡ እሺ ብሎ ይቅርታ ያደርጉልኛል ሲል አላደረጉለትም፡፡ ዜናነህ ስለዚህ ጉዳይ ሲያስታውስ ‹‹ ከዚህ በፊት የነበረ ማስታወሻ የያዝኩትን ሁሉ ከዚህ መፅሃፍት መደብር አለመሆኑን እየነገርኳቸው ማስታወሻዬን ወረሱት፡፡ ስፍራው የሰላም የኖቤል ሽልማት ከሚሰጥበት ኦስሎ ከተማ ህንፃ ፊት ለፊት ከፓርላማው አጠገብ ነው›› ብሎ ትዝታውን አውግቶናል፡፡
መዝጊያ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ የዊኪፒዲያ ቦርድ አባላትን አቋም የሚያንጸባርቅ ነው፡፡
ዜናነህ መኮንን በዚያ ሞገስ ባለው ድምጹ መረጃ ሲያቀብል ከብዙዎች ከበሬታን ማትረፍ ችሏል፡፡ ዜናነህ ዜና አንባቢ ብቻ ሳይሆን በበርካታ ጉዳዮች ላይ መጽሀፍትን የሚያነብ በሳል ነው፡፡ ዜናነህ ከማንበቡ በፊት ጉዳዩ ላይ ቀድሞ ጥልቅ ግንዛቤ ይይዛል፡፡ ከዚያም በሚነበበው ጉዳይ ላይ ነፍስ ይዘራበታል፡፡ በ1970ዎቹና በ1980ዎቹ የነበርን የቲቪ እና የሬድዮ ዜና አድማጭ ተመልካቾች ዜናነህ ልንረሳው አንችልም፡፡ ዘመኑን ሊከስትልን በሚችል መልኩ አንድ ትዝታ አእምሯን ላይ ጥሎ ነበር፡፡ ዜናነህ እንዲሁ አንብብ የተባለውን ዜና የሚያነብ ሳይሆን ይልቁንም ካላመነበት እንዲህ ተብሎ መነበብ የለበትም ብሎ ክርክር የሚገጥም በሳል አንባቢ መሆኑ በብዙዎች ይመሰከርለታል፡፡ይህ ጠያቂነቱና በምክንያት ማመኑ ገና በወጣትነቱ የጀመረ ነበር፡፡ ላመነበት ነገር ፊት ለፊት ይገጥማል፡፡ ያላመነበት ነገርን ደግሞ እንደዋዛ የሚቀበል ሰው አልነበረም፡፡ ዜና ነህ በኢትዮጵያ የዜና አንከሮች ታሪክ ውስጥ ጉልህ አሻራ ያስቀመጠ መሆኑ ይመሰከርለታል፡፡ እርሱ በእውቀት ላይ ተመስርቶ ስለሚሰራ የሚያነባቸው ዜናዎች ወደ እውነት የተቃረቡ ነበሩ፡፡ ዜናነህ ጎበዝ አንባቢ ስለነበር፤ ያነበበውን ደግሞ ስለሚያካፍል ይህም ትልቅ ርካታ ይሰጠዋል፡፡ ለህትመት ያበቃቸው መጽሀፎቹ ጥልቅ አንባቢነቱን የሚነግሩን ናቸው፡፡ ዜናነህ ለሀገሩ ያለውም ፍቅር ጥልቅ ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ አይተን ይህ ጠንካራ ሰው ለትውልዱ ታሪኩ ያስተምራል ብለን ስላመንን እነሆ ዜናነህን እናውቀው ዘንድ ሰንደነዋል፡፡ ዜናነህ ዛሬም ከሚኖርበት እስራኤል ሆኖ ብዙ ሀሳቦችን ያካፍላል፡፡ በሀገሩ ጉዳይ ላይ መደረግ አለበት ብሎ በሚያምነው ነጥብ ላይ ቃለ-ምልልሶችን ይሰጣል፡፡ በዚህም ለሀገሩ ያለውን ተቆርቋሪነት በአቅሙ ያሳያል፡፡ ዜናነህ መኮንን ለኢትዮጵያ ሚድያ ለዋልከው ውለታ እናመሰግናለን፡፡ መልካም የስራ ዘመን ብለን አክብሮታችንን መግለጽ እንወዳለን፡፡/ ይህ የዊኪፒዲያ ግለ-ታሪክ በዘቢባ ሁሴን እና በእዝራ እጅጉ የተጠናከረ ሲሆን ዛሬ ህዳር 28 2014 በተወዳጅ ሚዲያ የፌስ ቡክ ገጽ እና በዊኪፒዲያ ላይ ወጣ፡፡ አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገበትም በየጊዜው ይወጣል፡፡
Media

02/05/2022

“በሁከት እና ብጥብጥ የተሳተፉ 76 ግለሰቦችን በቁጥጥር ዋሉ” - የጋራ ግብረ ኃይሉ

በ1443ኛ የኢድ አልፈጥር በዓል ላይ በሁከት እና ብጥብጥ በግንባር ቀደምትነት የተሳተፉ 76 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።

1443ኛ የኢድ አልፈጥር በዓል በአዲስ አበባ በሰፊ ፕሮግራም ታጅቦ በሰላማዊ ሁኔታ የተከናወነ ሲሆን ነገር ግን ጥቂት ከሀይማኖታዊ ሥርዓቱ ውጭ ሌላ የሁከትና ብጥብጥ ዓላማ ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ለብጥብጥ መነሻ በማይሆን ምክንያት ከስታዲዮም ውጭ በተለምዶ የቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየም አጠገብ ሆነው ባስነሱት ረብሻና ብጥብጥ በጸጥታ ኃይሎችና በንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን 76 ግንባር ቀደም ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል።

የጋራ ግብረ ኃይሉ የኢድ አልፈጥርን በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ስምሪት መግባቱ ይታወቃል።

በዓሉን ለማክበር ከወትሮው በተለየ መልኩ ህዝበ ሙስሊሙ በነቂስ ወደ በዓሉ ስፍራ በመሄድ የስግደት ስነ ስርዓቱ እንደ ተጀመረ ሁከትና ግርግር የተፈጠረ ሲሆን የፀጥታና ደህንነት ግብረ ኃይሉ መንስኤውን እየጣራ እንደሚገኝና ውጤቱንም ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡

የጋራ ግብረ ኃይሉ ባደረገው ክትትል አብዛኛው የበዓሉ ታዳሚ ስግደቱን ፈፅሞ የበዓሉን በረከት በመቋደስ ወደ ቤቱ ለመመለስ አስቦ የመጣ ቢሆንም አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች በቀልና ጥላቻን ቋጥረው እንዲሁም ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቻችን ስውር ተልዕኮ ወስደው ሀገራችን የምትታወቅበትን የሀይማኖት መቻቻል በመናድ ህዝቡን በሀይማኖት በመከፋፈልና በመለያየት ሀገራችንን ለማፍረስ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ግጭት በማባባስ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

እነዚህ ፀረ-ሰላም ግለሰቦችና ቡድኖች ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ ተደራጅተው በአንዳንድ አካባቢዎች ስለታማ ነገሮችን፣ የውጭ ሀገር አክራሪዎችን አርማና የተለያዩ ግጭት ቀስቃሽ ጽሁፎችን በመያዝ ጥቃትና በቀል ለመፈፀም ወደ በዓሉ ስፍራ መምጣታቸውን ግብረ ኃይሉ በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ፀረ-ሰላም ኃይሎች እጅ መያዙን ገልጿል። የፈጠሩትን ሁከትና ግርግር ተጠቅመው ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቻችን የተቀበሉትን ስውር ተልዕኮ ለመፈፀም ጥረት አድርገዋልም ሲል ገልጿል፡፡

በዚህም የተነሳ የጸጥታ አካላት ላይ የአካል ጉዳት የደረሰ ሲሆን በህዝብና በመንግስት ተቋማት ላይም ጉዳት መድረሱ ታውቋል።

ይህንን እኩይ ተግባር ሲፈዕሙ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ሁከቱን በትዕግስት በመከታተልና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በህዝበ ሙስሊሙ በተለይም በሴቶች፣ ህፃናትና በሰላማዊ የሀይማኖቱ ተከታዮች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ብርቱ ጥረትና ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጓል።

ከዚህ ሁከትና ብጥብጥ ጋር በተያያዘ በግንባር ቀደምትነት የተሳተፉ 76 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን በቀጣይም ጉዳዩን በማጣራት ሌሎች የድርጊቱ ተሳታፊዎችን አድኖ በመያዝ ለህግ እንደሚያቀርብ ግብረ ኃይሉ አስታውቋል።

ግብረ ኃይሉ ክቡር የሰው ልጅ ህይወት እንዳይጠፋና የአካል ጉዳት እንዳይደርስ ከሰላም ወዳዱ የሙስሊም ህብረተሰብ ጋር በመሆን ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍሎ መቆጣጠር የቻለ ሲሆን በበዓሉ ታዳሚዎች ላይ የሞትም ሆነ የአካል ጉዳት እንዳልደረሰ አረጋግጧል። ይህ ደግሞ የሀገራችን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ጥንካሬና ብቃት እንዲሁም ለህዝቡ ያለውን ወገንተኝነት ያረጋገጠ ነው ሲል ግብረ ኃይሉ ገልጿል።

02/05/2022

በዛሬው ዕለት በኢድ ሶላት ላይ ጥቂት ግለሰቦች ባስነሱት ረብሻ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የታሪክ ሰናጁ ሰው ታሪክ- እዝራ እጅጉ በሀገራችን የመገናኛ ብዙኃን ታሪክ የህትመት ሚዲያው ፈርጣማ ክንዱን ባሳየበት 1980ዎቹ መጨረሻ፣ ትታተም በነበረች “ኩኩሉ” የልጆች መጽሔት ላይ አንድ...
01/05/2022

የታሪክ ሰናጁ ሰው ታሪክ- እዝራ እጅጉ

በሀገራችን የመገናኛ ብዙኃን ታሪክ የህትመት ሚዲያው ፈርጣማ ክንዱን ባሳየበት 1980ዎቹ መጨረሻ፣ ትታተም በነበረች “ኩኩሉ” የልጆች መጽሔት ላይ አንድ የ15 ዓመት ብላቴና የወደፊት ምኞቱን አሰፈረ። በየትኛው የትምህርት ተቋም ምን መማር እንደሚፈልግ፣ ምን ዓይነት መጽሐፍ ማሳተም እንደሚሻ፣ “እግዚአብሔር ብሎለት” ሃብታም ቢሆን መክፈት ስለሚፈልገው ድርጅት... የመሻቱን ሁሉ መጽሔቷ ላይ በዝርዝር አሰፈረ። ምንም እንኳ የዚህ ጽሁፍ አቅራ ቢበዘመኑ ለአቅመ ንባብ ባልደርስም ምኞቱን ያነበቡ አዋቂዎች ግን “ያሳድግህ” ከማለት አልፈው “የምኞቱን ቢያሳካስ” ብለው ያሰቡ አይመስለኝም።
ይህ ከሆነ ከሶስት አስርታት በኋላ፣ የያኔው ብላቴና አሁን ባለው ዘመኑ የሆነውንና በለጋ እጁ ከትቦ የልጆች መጽሔት ላይ ያኖረ የልጅነት ምኞቱን ብናስተያይ መስመር በመስመር ይገጥማሉ። የፈለገውን ተምሮ፣ ያሻውን ጽፎ፣ ያሰበውን ድርጅት ከፍቷል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ተመርቆ፣ የተፈጥሮ ውበት ስለሆነው የሰው ልጅ መጽሐፍትን ጽፎ፣ የሥነ ጽሑፍ ፍቅርና ችሎታ ላላቸው ልጆች የስራ እድልን የፈጠረ “ተወዳጅ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን”ን አቁሟል፦ እዝራ እጅጉ። የስራ እድሉ በረከት ከደረሳቸው አንዱ ነኝ እኔ አማረ ደገፋው፤ ዛሬ ሌላ እድል ደርሶኛል፦ የታሪክ ሰናጁን ሰው ታሪክ መሰነድ።

የተወዳጅ መነሻ 1996 ዓ.ም የካቲት ወር ቢሆንም ለታሪካዊ ስራዎች ትኩረት መስጠት የጀመረው ከ2008 ዓ.ም ወዲህ ነው። ያለፈውን አንድ አመት ደግሞ “ዘመነኞቹን በዊኪፒዲያ” በሚል ፕሮጀክት በሀገራችን ባልተለመደ መልኩ ሰዎች በህይወት እያሉ ታሪካቸውን በወጉ ሰድሮ ስላበረከቱት በጎ ተፅዕኖ ማመስገን ጀመረ። 170 የሚደርሱ የሚዲያ ሰዎችን ታሪክ ሰንዶ ጠንካራ ሽፋን ባለው መዝገበ አዕምሮ(ኢንሳይክሎፒዲያ) ለማሳተም ሲሯሯጥ ከግማሽ በኋላ ያለውን መንገድ አብሬው ስለሮጥኩ ‘የዚህን ሁሉ ሰው ታሪክ እየሰራ እንዴት የራሱን አይጽፍም...? ለራሱ እንዴት ሰነፈ?’ የምትል የጎን ሃሜት ነበረችኝ። መዝገበ አዕምሮ ወደ ማተሚያ ቤት ለመግባት ሳምንት ሲቀረው የእርሱም ታሪክ መሰነድ እንዳለበት ተማምነን ለቃለመጠይቅ ተቃጠርን። ወደ ቤቱ ሄድኩ፤ ላፕቶፑ ላይ ሆኖ ከጽሁፉ ጋር ግብ ግብ ይገጥማል፡፡
ከልጅነቱ ጀምሮ ይይዛቸው የነበሩ ዲያሪዎች ልቅም ባለ የኮምፒውተር ጽሑፍ ተተይበው በዘመን ቅደም ተከተላቸው የሰፈሩበት ዳጎስ ያለ ጥራዝን ሳይ፣ ከአመታት በፊት ለህትመት የበቁ ስራዎቹን የያዙ ባለጠንካራ ሽፋን መዝገቦችን ሳገላብጥ፣ በቃለመጠይቁ ወቅት ከሃያና ሰላሳ አመት በፊት የነበሩ ክስተቶችን ትላንት የሆኑ ያህል ሲያስታውስና ልክ ቅድም ያገኛቸው ይመስል የሰዎችን ስም ድንቅፍ ሳይል መጥራቱን ስታዘብ፤ ‘ለራሱ እንዴት ሰነፈ’ የሚል ትዝብቴን ሽሬ ለረዥም አመታት በትጋት ከተሰነደ ሰፊ ታሪኩ ለአንባቢ እንዲሆን መቀንጨቡን ማሰብ ጀመርኩ። እነሆ የታሪክ ወዳዱ እዝራ እጅጉ ቅንጭብ ታሪክ፦

የታሪክ መውደዱ ማሳያ መቼ እንደተወለደ ሲጠየቅ “የደርግ መንግስት የድል በዓልን ባከበረ በሁለተኛው ቀን እሁድ መጋቢት 30፣ 1971 ዓ.ም ተወለድኩ” ነው መልሱ። በዚያው በ1971 አመት ግንቦት ወር የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ይሰሩ የነበሩት አባቱ አቶ እጅጉ ሙላት ወደ ጅቡቲ በመዛወራቸው እትብቱ የተቀበረባትን መሬት ሳይድህባት በእናቱ ወይዘሮ በለጥሻቸው ስዩም እቅፍ ሁኖ አባቱን ተከትሎ ጅቡቲ ገባ። የ4ኛ እመት ልደቱን እስኪያከብር በቆየባት የጎረቤት ሀገር ትዝታዎች መካከል አንዱ እሳት ነው። በልጅነት የመመራመር መንፈስ ሁኖ ‘እሳት ያቃጥላል አያቃጥልም?’ የሚለውን ለማረጋገጥ ያደረገው ሙከራ ሙሉ ቤቱን በልቶ አሳይቶታል።

ከጅቡቲ መልስ በ1976 ዓ.ም ‘ማርች ኤይት’ ትምህርት ቤት ገብቶ ለሁለት አመታት የመዋእለ ህጻናት ትምህርቱን ተከታትሏል። ቀጥሎ ወደ ‘ቦሌ ህብረተሰብ’ አቅንቶ በ1978 ዓ.ም 1ኛ ክፍል ገባ፤ እስከ 4ኛ ክፍል በዘለቀ ቆይታው ዝምተኛና ፈሪ እንደነበር ያኔ አብረውት የተማሩ ጓደኞቹ ያስታውሳሉ፤ እርሱም የያኔ ጭምትነቱን ያምናል።

በ1981 ዓ.ም ክረምት አባቱን ድጋሜ የምስራቁ ማግኔት ስቧቸው ወደ ድሬደዋ ሲያቀኑ እርሱም ከታናሽ እህቱ ጋር ሁኖ ተከተላቸው። እርሱም እህቱም ዛሬም ድረስ ‘ልዩ’ ብለው የሚገልጿቸውን ሁለት አመታት በድሬደዋ አሳለፉ። ቦሌ ህብረተሰብ እያለ የተረት መጽሐፍትን ማንበብ ድረስ ብቻ የነበረ የሥነ ጽሑፍ ቅርበቱ፤ በድሬዳዋ ቆይታው በብዙ እጥፍ አድጎ ልቦለዶችን እስከመጻፍ ደረሰ። ጥበብ ትጣራ ከሆነ በሥነ ጽሑፍ በኩል የጠራችው በዚህ ዘመን እንደነበር ራሱም ያምናል። ዛሬም ድረስ በቃሉ የሚወጣቸውን ግጥሞች የያዘችው የክፍሌ አቦቸር “የኔ ጋሻ” መድብልን ደጋግሞ ማንበቡን ያስታውሳል። አባቱ ቢሮ ይመጡ የነበሩ አዲስ ዘመንና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦችንና የካቲት መጽሔትን የማንበብ እድሉም ነበረው።

ልዑል መኮንን የተማሩትና በጅቡቲ አመታትን የሰነበቱት አባቱ ለፈረንሳይኛ ቅርብ ስለነበሩ የፈረንሳይኛ ኢንሳይክሎፒዲያ ነበራቸው። ብላቴናው እዝራ ገና ያኔ ይህን መጽሐፍ ሲያገላብጥ ነበር አሁን እያሰናዳ ያለውን መዝገበ አዕምሮ(ኢንሳይክሎፒዲያ) የማዘጋጀት ሃሳብ የመጣለት። እንዲህ ባለ የመነቃቃት መንፈስ ውስጥ ሁኖ 5ኛ እና 6ኛ ክፍልን በድሬደዋ ከተማረ በኋላ ወደ አዲስ ተመልሶ ለ7ኛ ክፍል ትምህርቱ በድጋሜ ወደ ቦሌ ህብረተሰብ አቀና። የቀድሞ ወዳጆቹ የቀደመ ጭምትነቱን ሲያጡበት ‘እዝራ ፈነዳ’ አሉ። አብሮ አደጉ ናይእግዚ ህሩይ ይህን ጊዜ ሲያስታውስ “ድሬደዋ ምን አግኝቶ እንደመጣ ገርሞናል” ይላል።
“ከመፈንዳቱ” እኩል ንባቡን አበረታ፤ ግቢያቸው ተከራይ ከነበሩ ሰዎች እየተዋሰ፣ የቅባት ጠርሙሶችን ለቆራሊዮ ሽጦ መጽሔት እየገዛ፣ ናይእግዚና ፍቃዱ ሞላ የተባሉ ጓደኞቹ የሚያመጡለትን መጽሐፍት እየተቀበለ ለንባብ አቀረቀረ፤ እናቱ ወይዘሮ በለጥሻቸው “እስኪ እንደልጆቹ ወጣ ብለህ ተጫወት” እስኪሉት ድረስ ከወረቀት ጋር ተዋደደ። 8ኛ ክፍል ሲደርስ ለተለያዩ መጽሔቶች አስተያየትና ስራዎቹን ‘እዝራ እጅጉ ከቦሌ’ በሚል አድራሻ መላክ ጀመረ። 42ቱ የዩኒቨርስቲ መምህራን ሲባረሩ ስሜቱን ጽፏል፤ በቃሉ ከያዘው የክፍሌ አቦቸር ግጥም አንዱን “አፍሪካ ቀንድ” ለተባለ መጽሔት ምንጭ ሳይጠቅስ ልኮ በመታተሙ እንደተከሰሰም ያስታውሳል። በንባቡና በተሳትፎው ከእኩዮቹ ተለየ፤
9ነኛ ክፍል ሲሻገር ቦሌ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ገባ። በ1986፡፡ ንባብና ተሰጥዖውን ለማሳደግ ሚኒ ሚዲያ ለመግባት ቢያመለክትም ሳይጠራ ይቀራል። በዚህ ተናዶ የሚኒ ሚዲያው በር ላይ ያገኘው አንተነህ ዓለሙን እንዴት በጉልበት ገፍቶት እንደገባ ሲያስታውስ “ምን አለ ካሜራ ኑሮ ሁኔታውን ይዞት በነበር” ይላል፤ ሳያልፍ በጉልበት በገባበት ቤት ችሎታውን በሚገባ አሳይቶ በ4ኛ ወሩ የሚኒ ሚዲያው ምክትል ሊቀ መንበር ለመሆን በቃ።
በዚያው አመት ወደ ለገዳዲ ሬዲዮ ጣቢያ አቅንቶ መሳተፍ ጀመረ። ለመጀመሪያ ጊዜ ለገዳዲ ሲደርስ ተቀብለው፤ ሻይ ጋብዘው፤ ቤተ መጽሐፍቱን አስጎብኝተው ያበረታቱት መምህራንን ዛሬም ድረስ ከነስማቸው ያስታውሳል። “ጣሰው ተፈራ፣ ሃይሉ ማሞ፣ ኤርሚያስ ተገኝ፣ ህሊና ማሞ፣ ከድጃ ሰይድ” እያለ ሲዘረዝራቸው ትላንት ያገኛቸው እንጂ ከ30 አመት በፊት ያዋራቸው አይመስሉም። ቤተ መጽሐፍቱን በአግባቡ ተጠቅሞበታል፤ ‘ዘ ወርልድ ቡክ ኦፍ ኢንሳይክሎፒዲያ... ብሪታኒካ’ ጋር ተዋውቆበታል፣ ለገዳዲ ሬዲዮ የጥያቄና መልስ ዝግጅት ከ300 ያላነሱ ጥያቄዎችን አዘጋጅቶበታል።

በ1989 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ይተላለፍ የነበረ “አካፑልኮ ቤይ” የተሰኘ ፊልምን ወደ አማርኛ መልሶ ከያኔ የትምህርት ቤት ተጋሪው አርቲስት ስናፍቅሽ ተስፋዬ ጋር በመሆን በቦሌ ሚኒ ሚዲያ ተረከ። በወቅቱ ብቼኛ የመዝናኛ አማራጭ በነበረው ኢቲቪ የሚተለለፈው ይህ ፊልም የብዙዎች መነጋገሪያ እንደነበር ያስታውሳል፤ እግር በእግር እየተከታተለ ተርጉሞ ሲተርክ ተማሪዎች በተለየ ጉጉት ነበር የሚከታተሉት። የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ‘ተማሪ እንዳይፎርፍ ስላደረክ’ ብሎ አመስግኖታል።
ከፊልሙ ትረካ መጠናቀቅ በኋላ የሚዲያዎችን ትኩረት ሳበ። ፋንታሁን ኃይለማርያም ከኢቲቪ፣ መስፍን አሸብር ከሬዲዮ ፋና፣ ሰለሞን ጥዑመልሳን ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ስለሰራው የትርጉም ስራ በየተራ አነጋገሩት። መስፍን አሸብር የፋና ስቱዲዮ ድረስ ወስዶ ቃለመጠይቅ እንዳረገውና ከብዙ ጋዜጠኞች ጋር እንዳስተዋወቀው ያስታውሳል። ከቴሌቭዝን ከሬዲዮና ከጋዜጣ በመጡ ጋዜጠኞች ቃለመጠይቅ ተደርጎ ከትምህርት ቤት ውስጥ ዝናው ከፍ አለ። እንዲህ ያለ አድናቆትና መወደድ ያተረፈለትን የትርጉም ስራ በመጽሐፍ መልክ ቢያሳትመው ምን ያህል ገዥ ሊኖረው እንደሚችል ጥናት አደጎ አጥጋቢ ውጤት በማግኜቱ ለማሳተም ቢጥርም አሳታሚ በማጣቱ ደብተሩን ቅርጫት ውስጥ ወረወረው።

በ1990 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍን ለመማር በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማታው መርሃ ግብር ተመዘገበ። ከአብሮ አደጉ ናይእግዚ ጋር በመሆን የሚዲያ ፈቃድ አውጥተው “ልጅነት” የምትል የልጆች መጽሔት ለማሳተም ቢሞክሩም በስፖንሰር ማጣት ምክንያት ሀሳባቸውን ሳያሳኩ ቀሩ። በተመሳሳይ አመት ወደ ሪፖርተር ጋዜጣ አምርቶ ቅጥር ጠይቆ ስላልተሳካ በነፃ ማገልገል ጀመረ። ለወራት በዘለቀ የነፃ ግልጋሎቱ ደረጀ ደስታ፣ ከበደ ደበሌ ሮቢ፣ ሰለሞን አባተ፣ እሸቴ አሰፋና አብዱ አሊ ሂጅራን ጨምሮ ከሌሎች አንጋፋዎች ጋር ቢሮ ተጋርቶ ጽሑፎቻቸውን አርሟል፣ ዝንቅና ሌሎች አምዶችን አዘጋጅቷል፣ ደሞ በልጅ እግሩም ለአንጋፋዎቹ ተላልኳል። ከሪፖርተር ጋዜጣ በኋላ በተመሳሳይ ግልጋሎት እፎይታ መጽሔትንም ለጥቂት ወራት አገልግሎ፣ “እፍታ” የተሰኘች የወጎች መድብል ላይ ስራው ወጣለት።
ቀጥሎ አዲስ ልሳን ጋዜጣ ላይ አመለከተ፤፤ ከብዙ መቶዎች ተወዳድሮ ሃይለ ገብርኤል ይመርን ተከትሎ፣ ታገል ሰይፉን አስከትሎ፣ በሁለተኝነት አለፈና ጋዜጠኛ ሆነ። 1992 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ በ21 አመቱ፣ ገና የ3ኛ አመት የዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለ፣ በ347 ብር የሙሉ ጊዜ ጋዜጠኛ ሲሆን የተሰማውን ደስታ ሲገልጽ “አሁን ላይ ማርስ ብሄድ የሚሰማኝ ስሜት ነበር ያኔ የተሰማኝ” ይላል።
መዝናኛ ክፍልን እየፈለገ ዜና ክፍል ሲመድቡት መጀመሪያ ላይ አልከፋውም ነበር፤ እንዲያውም ‘በሳምንት 4 ዜና ማምጣት አለብህ’ ያለ አለቃውን በተለየ ጉጉት ሁኖ “7 አይቻልም?” ብሎ ጠይቆት ነበር። የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታትን ሰባትም ስድስትም ዜናዎችን መስራት ቢችልም እየቆየ ሲሄድ ግን እንዳሰበው ቀላል ሊሆንለት አልቻለም። በዜና እጦት ራሱን እያመመው ሻሽ አስሮ ቢሮው ይገባ እንደነበር ያስታውሳል። ከስድስት ወራት ቆይታ በኋላ የአዲስ ልሳን ጋዜጠኝነቱን ተወ።
አዲስ ልሳኖች የጻፉበትን ደብዳቤ ይዞ ከአዲስ አድማሶች ደጅ ደረሰ። “ለኔ የሚሆን ትክክለኛ ሰው” በማለት የሚገልፀው አሰፋ ጎሳዬ በጥሩ ፊት ተቀብሎ በ400 ብር ቀጠረው። ከነብይ መኮንን፣ ኤፍሬም እንዳለ፣ ሰለሞን ገ/እግዚአብሔር እና ሌሎችም ጋር ባልደረባ ሁኖ ሲሰራ ዜናንም መዝናኛንም አቀላጥፎ ሰርቷል። አዲስ አድማስ ለአንድ አመት ከሰራ በኋላ ወደ ሩህ ጋዜጣና መጽሄት አቀና፡፡

በ1994 ዓ.ም ከተመረቀ በኋላ በ500 ብር ደመወዝ ‘ዘ ፕሬስ’ ገባ። በዚያ ጋዜጠኝነትን ብቻ ሳይሆን ማስታወቂያ የማፈላለግ ስራንም ሰርቶ ዳጎስ ያለ ኮሚሽን እንደተቀበለ ያስታውሳል። ምን አልባት ይህቺኛዋ ኮሚሽን ሳትሆን አትቀርም ወደ ቢዝነሱ ዓለም ቀልቡ እንዲሳብ ያደረገችው። በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ማርኬቲንግን መማር ጀምሮ ነበር። ዮቴክ ኮንስትራክሽን ውስጥ በፐርሶኔልነት ለ11 ወራት እንዳገለገለም ይናገራል። የቁምነገር መጽሔት ምክትልዋና አዘጋጅና ሴልስ ሁኖም ሰርቷል።

በዚህ ሁሉ የስራ ዙረት ውስጥ ልምዶችን ሲቃርም የሰነበተው እዝራ በየካቲት 2፣ 1996 ዓ.ም “ተወዳጅ” ብሎ የሰየማትን ጋዜጣውን ማሳተም ቻለ። ማስታወቂያዎችን ብቻ ይዛ የምትወጣው ይህች ጋዜጣ በነፃ ነበር የምትታደለው። ማስታወቂያ መፈለጉ አያስቸግርም ወይ ተብሎ ሲጠየቅ “ለጥረት ነው የተፈጠርኩት” ነው ምላሹ። ገቢዋ ከሽያጭ ሳይሆን ከማስታወቂያ አስነጋሪዎች ቢሆንም ከመጀመሪያ እትሟ ብቻ 10ሺ 100 በብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ያስታውሳል። በዚያው ሰሞን “አካፑልኮ ቤይ” የትርጉም መጽሐፉ ታትሞ ከ36ሺ ብር አጠቃላይ ትርፍ 30 በመቶውን እንደወሰደ አይዘነጋም።
1997 ዓ.ም ሲገባ አየሩን ሁሉ ፖለቲካ ሲሞላው የተወዳጅ ገበያም እየቀነሰ መጣ። “ጋዜጠኛ ፖለቲከኛ መሆን የለበትም” ብሎ ስለሚያምን ነው እንጂ ተወዳጅን የፖለቲካ ጋዜጣ ማድረግ ይችል እንደነበር ያስረዳል። ቀጥሎ ለቢዝነስ እየሸፈተ ያለ ልቡን ጠቅልሎ የወሰደ ድርጅትን በሞክሼ ጓደኛው እዝራ ገ/ሥላሴ አማካኝነት ተቀላቀለ። “ጎልድ ኩዌስት” የተባለው ይህ የሆንግ ኮንግ ድርጅት በኔትወርክ ማርኬቲንግ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራ ሲሆን መንግስት እስኪያግደው ድረስ በሀገራችን ተንቀሳቅሷል። እዚሁ ድርጅት ውስጥ እያለ በእንግሊዝኛ ብቻ የነበሩ የኔትወርክ ማርኬቲንግ ማንዋሎችን ወደ አማርኛ ሲመልስ ከቆየ በኋላ በመጽሐፍ መልክ አሳተመው። ከመጽሐፉ ህትመት ማግስት “ኢትዮ ቪዥን የችሎታ ማግኛ” የሚል የስልጠና ማዕከል ከፍቶ በርካቶችን ከችሎታቸው ጋር ማገናኘት ቻለ።
የጥረት ሰው ስለሆነ አደርገዋለሁ ያለውን ሁሉ አድርጓል። ይህች ዓረፍተ ነገር የወዳጅ የተጋነነ አድናቆት እንዳልሆነች መግቢያዬ ላይ ያሰፈርኩት የኩኩሉ መጽሔት እትም በቂ ማሳያ ቢሆንም ሌላ ምሳሌ እጠቅሳለሁ። መስከረም 22፣ 2000 ዓ.ም ከ22 ወደ ፒያሳ ይጓዝ በነበረ ታክሲ ውስጥ ያገኛትን ወጣት ጥቂት ካዋራት በኋላ ሰባ ደረጃ ላይ ከመድረሱ ቀድሞ “ኔትወርክ ማርኬቲንግ” የሚል መጽሐፉን እየሳጣት “አንቺን ነው የማገባው” ብሏት ወረደ። ከሁለት አመታት በኋላ የሰርጉ ቀን ከጎኑ የቆመችው ሙሽራ የያኔ ታክሲ ተጋሪው የዛሬ ባለቤቱ አመለወርቅ ወልደኪዳን ነበረች።
2000 ዓ.ም ጥር ወር ላይ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የቅጥር ማስታወቂያ አውጥቶ ቢወዳደርም ተጠባባቂ ነበር መሆን የቻለው። ከወራቶች ቆይታ በኋላ ከፋና ተደውሎለት ከፍተኛ ሪፖርተር ሁኖ በ1415 ብር ተቀጠረ። የራሱ ትርፋማ ተቋም እንደነበረውና ማሰልጠኛ ከፍቶ ሰዎችን ከተቀጣሪነት ውጡ እያለ ሲመክር መክረሙን የሚያውቅ ግማሽ ልቡ ‘ለምን ትቀጠራለህ?’ ቢለውም ሌላኛው የልቡ ክፍል ደግሞ ‘ዓላማህን ይዘህ ተቀጥረህ ሞክረው’ ይለዋል፤ ሁለተኛውን ሰማና ተቀጠረ። ተቀጠረና 13 ከዓመታት ከ 5ወር ፋና ቤት መቆየት ቻለ።ከጥር 19 2019 በኋላ ግን ፋና እና እዝራ ተለያዩ፡፡
በእነዚህ 13 ዓመታት ብዙ ከፍና ዝቅታዎችን አሳልፏል። 2001 ዓ.ም የአባቱን ማለፍ ተከትሎ ከሃዘኑ በኋላ ወደ ቤተክርስቲያን ተጠጋ። የትኛውም እምነት ውስጥ ቢሆን የሰው ልጅ መንፈሳዊ መሆን አለበት ብሎ ያምናል። እስከ 2006 ዓ.ም ያሉትንና ‘የዝምታ ጊዜ’ ብሎ በሚገልጻቸው ዓመታት መንፈሳዊነቱ ላይ አብዝቶ ሰራ፤ ብዙ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችንም ተማረ። ፋና ውስጥ ቀድመው ያልነበሩ ፎርማቶችን ጀምሯል፣ የሀገር ውስጥ ታሪኮች እንዲለመዱ አድርጓል፣ ቴሌቭዥኑ ሲጀመር ደግሞ በርከት ያሉ አጫጭር ታሪካዊ ተንቀሳቃሽ ምስሎችንና ዶክመንተሪዎችን ሰርቷል።ለብዙዎች የሬድዮ ኤዲቲንግ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
ለታሪክ ያለው ፍቅር የተለዬ ነው፤ ይህ ፍቅሩ ለሀገር መልካም የሆነ አበርክቶን እንዲያኖር ረድቶታል። ራሱም ሲናገር “አንዳንዴ ያንተ ፓሽን የሀገሪቱ ክፍተት ይሆንና መሻትህን በመኖር እግረ መንገድ ሀገርህን ትጠቅማለህ” ይላል። እዛው ፋና ቤት እያለ የጀመረው የታሪክ ፍቅሩን መወጣት ቢያስቀጣውም ቢያስነቅፈውም በረታበት እንጂ አልቆመም። ጎን ለጎን በአንጻራዊነት የተሻለ ነጻነት ላለው ድሬ ቲዩብ ታሪካዊ ጽሑፎችን ማድረስ በመጀመሩ ብዙ ትውውቆችን ፈጠረለት።

በ2008 ዓ.ም የግለሰቦችን ታሪክ በሲዲ የመሰነድ ሀሳቡን ሲያነሳ ብዙዎች እንደ እብደት ቢቆጥሩበትም፤ ያለውን ከማድረግ ሰንፎ አያውቅምና የተሾመ ገ/ማርያም ታሪክን በሲዲ በማውጣት ትርፋማ መሆን ቻለ። የጸሃፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተወልድ፣ የአርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ፣ የአማረ አረጋዊን ጨምሮ 44 ሲዲዎችን ለማውጣት በቃ። ማማ በሰማይ፣ የኤርትራ ጉዳይ፣ ማህሌት፣ ምንትዋብና ሌሎች 10 የሚደርሱ መጽሐፍትን በኦዲዮ አሳተመ። ከአካፑልኮ ቤይና ኔትወርክ ማርኬቲንግን በተጨማሪ ‘10 ነገሮች አለኦቲዝም’ እና ‘የአንኮበሩ ሰው በጄኔቭ’ የሚሉ ሌሎች መጽሐፍትን ለንባብ አብቅቷል።
ፋና በቆየባቸው ጊዜያት 1476 ፕሮግራሞችን አየር ላይ ሲያውል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 67 ያህሉ ለቲቪ የተሰሩ ናቸው፡፡ ስራዎቹን ሰንዶ የማስቀመጥ ባህል ያለው እዝራ በየጊዜው ያለፉ ስራዎቹን የማየት ልምድ አለው፡፡
ያለፈውን አንድ አመት 170 የሚደርሱ የሚዲያ ሰዎችን ታሪክ በመዝገበ አዕምሮ ለማስፈር ደፋ ቀና ሲል ከርሞ አሁን ለማሳተም ችሏል። ‘ለሚዲያ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ሙያ መዝገበ አዕምሮ እንዲኖር እፈልጋለሁ’ ይላል፤ ካለ ደግሞ ያደርገዋል። ገንዘብ አያስገኝም በሚባልለት የሀገር ውስጥ ታሪክ ስነዳ በትጋት 5 አመታትን ብቻ ተመላልሶ ትርፍ ማግኘቱን በኩራት ይናገራል። ይህ ሁሉ እንዲሆን ከፈጣሪ ቀጥሎ ዋጋ የምትከፍለው ባለቤቱ ድርሻዋ የጎላ መሆኑን ያወሳል። በመጀመሪያ ትውውቃቸው “አንቺን ነው የማገባው” ያለው ሰምሮለት በጥቅምት 7፣ 2002 ዓ.ም በመሰረተው ትዳር ክርስቲያን እዝራ እና ካሌብ እዝራ የተባሉ ሁለት ልጆችን አፍርቷል።
ወደ ሰላሳ ለሚደርሱ ጸሐፍትና ሌሎች ባለሙያዎች የስራ እድል ፈጥሮ ትርፉን እያጋራ ይገኛል፤ አብረውት የሰሩት ሁሉ ስለእዝራ ሲናገሩ ባንድ ድምጽ ስለትጋቱና አንድ ነገር ከጀመረ ሳያሳካ አለመልቀቁን ያወራሉ። ታሪካቸውን ከሰነደላቸው ሰዎች አንዷ ዝናሽ ማሞ ስለእዝራ ስትናገር “ሀሳቡን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያሳየውን ትጋትና ጥረትን አስተውያለሁ። እዝራ ከጀመረ አይለቅም ደጋግሞ ለመደወል አይታክትም፤ ለማሳመን አይደክምም፤ ተከታትሎ ታሪኩን በእጁ ለማስገባት አይሰለችም፤ ምንም የሚፃፍ ታሪክ የለኝም፣ ስራ ይበዛብኛል፣ ጊዜ የለኝም የመሳሰሉት መልሶች ተስፋ አያስቆርጡትም። በጥበብ አስተናግዶ የማሳመን ተሰጥኦ አለው።” ትላለች።
ቅድስት ወልዴ የተባለች ባልደረባውም ትናገራለች “የእዝራ ትልቁ ጥንካሬው ራዕዩ ነው፤ እውቀትም ሆነ ገንዘብ ያለውን የሚያካፍል ነው፤ ሌላው እና ትልቁ ነገር በእግዚአብሔር ማመኑ ነው። ራዕዩን ለማሳካት እንቅፋቱን አልፎ የትም መድረስ የሚችል እና እሱን እያሳየ ያለ መሆኑ ነው። በታሪክ ስራዎቹ ብዙ ያልተነገረላቸውን የሀገር ባለውለታዎችን ከተረሱበት ታሪካቸውን በመፈልፈል በኦዲዮ ሲዲ እና በዶክመንተሪ ያለመታከት በመስራት በሀገራችን ቀዳሚው ባለሙያ ይመስለኛል።’
“38 ዓመታት በትምህርት አብረን ነበርን” የሚለው አብሮ አደጉ ናይእግዚ ህሩይ፤ የእዝራ ንባቡ ላይ የሙጥኝ ማለት እንደእናቱ ሁሉ ይገርመው ነበር “እንደልጅም እንደጎረምሳም ሳይሆን ማሳለፉ ይገርመኛል” ይላል። የራሱን ስራዎች፣ ታሪካዊ ብሎ የሚያምንባቸውን ነገሮች እና በቴሌቭዥን ይተላለፉ የነበሩ ዜናዎች በካሴት ቀርጾ ማስቀመጡን እያስታወሰ “በወቅቱ የግሉ ዩቲዩብ ነበረው ማለት እንችላለን” ይላል።
በርካታ ወዳጆች በተለይ አብረውት የሚሰሩ ከእዝራ ባህሪ የሚገርማቸውን ሲጠየቁ ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ የሚጠቅሱት የጀመረው ስራ እስኪያልቅለት እረፍት ማሳጣቱና “ችክ” ማለቱን ነው፤ እኔ ግን ይህን ችክታ ትጋት ነው የምለው። ትጋቱ ደግሞ አሁን ላለበት የስኬት ደረጃ ሊያቃርበው ችሏል፡፡

መዝጊያ፦
ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን የመዝገበ አዕምሮ(ኢንሳይክሎፒዲያ) ቦርድ አባላት አቋም የሚንጸባረቅበት ነው። እዝራ እጅጉ በጋዜጠኝነት ሙያ በተለያዩ ሚዲያዎች ሀገሩን በርከት ላሉ ዓመታት ሲያገለግል ከቆየ በኋላ በተወዳጅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን በኩል የተዘነጉ የሀገር ባለውለታዎችን ታሪክ በመሰነድ ለሀገር ከፍ ያለ ውለታን አኑሯል። በዚህ ሳይቆም በህይወት ያሉ የዚህ ዘመን የሀገር ወለታ ዋይ የሚዲያ ሰዎችን ታሪክ ሲሰንድ የደጋሽ ነገር ሁኖበት የራሱን ታሪክ ሳይሰንድ ቢቆይም በመጨረሻ በአማረ ደገፋው እንዲህ ባለ መልኩ ተሰንዶለታል። በህይወት ያሉ ሰዎች ሳያመልጡን ስላበረከቱት መልካም ስራ በቁማቸው ማመስገንን እንድንለምድ የእዝራ ስራ በትልቁ ያስተምረናል። ቀደም ባሉት ዓመታት የሰዎችን ታሪክ በሚዲያዎቻችን ስንሰማ ቀድመን “ሞተ እንዴ?” እያልን ሙት አመስጋኝ ለነበርነው ሁሉ አይን ገላጭ ስራን እየሰራ ስላለ በመንግስትም በግለሰብም ደረጃ መመስገንና መበረታታት አለበት ብለን እናምናለን።
ም ን ጭ :-Tewdaje Media

28/04/2022

በ 9192 ይጠቁሙ

ማንኛውም ሰው የጥላቻና ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ፣ ሃሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ በተለይም የሚዲያ ተቋማት የዩቲዩብ ቻናሎች እና ሌሎችንም ሲመለከት በ91 92 የስልክ ቁጥር ለመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ጥቆማ መስጠት ይችላል።
ምንጭ:-Fbc

አርቲስት ዘነቡ ገሠሠ  ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች::
24/04/2022

አርቲስት ዘነቡ ገሠሠ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች::

22/04/2022

በወቅታዊ ሀገራዊ የደህንነትና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር፣ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ የሰጠው መግለጫ
የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች፣
ሀገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የደረሰችው በየዘመናቱ የገጠሟትን ፈተናዎች በድል እየተሻገረች ነው። እንድትጠፋ የሚፈልጉ ኃይሎች ሊያጠፏት ሲነሡ ምንጊዜም ሦስት ኃይሎችን እንደሚጠቀሙ እሙን ነው።
የመጀመሪያዎቹ ምንጊዜም የማይተኙት ታሪካዊ ጠላቶቻችን ናቸው። እነዚህ ጠላቶቻችን ጠላትነታቸውን የሚያቆሙት ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር ከምድር ገጽ ስትጠፋ ብቻ ነው። ይኼ ምኞታቸው እንዲሳካ ብቻቸውን አይሠሩም። ተላላኪ አላቸው። እነዚህም ሁለተኛዎቹ ናቸው። ለገንዘብና ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ወገናቸውን እንደ ይሁዳ የሚሸጡ፣ ሀገር የጣለባቸውን እምነት በሽርፍራፊ ሳንቲም የሚለውጡ ሀገር አልባ ባይተዋሮች ሞልተዋል። የተናገሩትን ሆነው የማይገኙ፣ ቀን ቀን በአደባባይ ስለ ሕዝብ ፍቅር እና ስለ ሀገር አንድነት የሚደሰኩሩ፤ ማታ ማታ ከጠላት ጋር እያሴሩ ወገንን የሚክዱና ሀገር ለማፍረስ ጉድጓድ የሚቆፍሩ ናቸው።
ሦስተኛዎቹ የኢትዮጰያ ጠላቶች ደግሞ ባለማወቅ የእነዚህ የሁለቱ አካላት ተባባሪ የሚሆኑት ናቸው። ግዴለሽ ስለሆኑ፣ የሚያደርጉት ነገር የሚያስከትለውን ውጤት ሳይገምቱ እንዲሁ በነሲብ የጠላትን ተልዕኮ የሚፈጽሙ ውል አልባ ኢትዮጵያውያን ናቸው። እነዚህ ኢትዮጵያውያን አንድን ነገር ተቀብለው ማውራታቸውን፤ ወይም አድርጉ የተባሉትን ነገር ማድረጋቸውን፤ ወይም ሳይመረምሩ የሰጧቸውን መረጃ ሁሉ ማስተላለፋቸውን እንጂ በሀገራቸውና በሕዝባቸው ላይ የሚያስከትለውን ጣጣ አይመረምሩትም። ከመረመሩም ጉዳቱ ከደረሰ በኋላ ብቻ የሚፀፀቱ ናቸው።
ኢትዮጵያ ይበልጥ እየተፈተነች ያለችው በእነዚህ በሁለቱ ነው። ታሪካዊ ጠላቶቻችን በአንድ ስሙ ቁርጣቸው የታወቀ ጠላቶቻችን ናቸው። ባይተዋሮችና ውል አልባ ኢትዮጵያውያን ግን በወቅቱ ልብ ሳንላቸው ደጋግመው ዋጋ ያስከፍሉናል። በዚህ መልኩ እስከመቼ? ለዚህ ጥያቄ ሁላችንም ቆም ብለን ምላሽ ልንሰጥ ይገባል።
ለውጡ ከመጣ ጀምሮ እንኳን እንደ ሀገር በብዙ ተፈትነናል፤ የሰነቅነውን ተስፋ እንዳናይ የሚከልሉ ስንት ጋሬጣዎች ገጠሙን? ስንቱን ተሻገርን? በስንቱ ወደቅን? አንድ በአንድ ብንዘረዝረው ቁጥሩ ቀላል አይደለም። እነዚህ ፈተናዎች የመጡት ከላይ ከተጠቀሱት የኢትዮጵያ ጠላቶች ነው። ለውጡ እንዳይሳካና ኢትዮጵያ ጠንካራ የአፍሪካ ኃይል ሆና እንዳትወጣ ለማድረግ ዐቅማቸው የፈቀደውን አድርገዋል። ኢትዮጵያውያን በዘር ተከፋፍለው እርስ በርስ እንዲጋጩ፣ ሀገር በኢኮኖሚ እንድትዳከም፣ ሀገር ተሸክመው የኖሩ ተቋሞቻችን እንዲፈራርሱ በብርቱ ሲሠሩ ነበር። ሚዲያና የጦር መሳሪያ የታጠቁ ሰዎችን በመጠቀም ማህበራዊ እሴቶቻችንን ለመበጣጠስ፣ የእምነትና ማኅበራዊ ተቋማትን ለማቃጠል፣ በሕዝብ መካከል ሽብር ለመንዛትና ዜጎቻችንን ዕረፍት ለመንሣት ክፋት የተባሉትን ተግባራት ሁሉ ፈጽመዋል። የፈጸሙት እኩይ ሥራ እጅግ አሰቃቂና ዜጎቻችንን የጎዳ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያውያን ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ለሀገራቸው ባላቸው የጸና ፍቅር ምክንያት ጠላቶቻችን የሚፈልጉትን ግብ ሊያሳኩ አልቻሉም።
ውድ ኢትዮጵያውያን፣
ከለውጡ በፊት ተቋማዊ ስብራት ከገጠማቸው መካከል የሕግና ጸጥታ ተቋማት ይገኙበታል። እነዚህ ተቋማት እንዲሰበሩ የተደረጉት ሆን ተብሎ የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ዓላማ ለማሳካት አንዲቻል ነው። በሀገር ውስጥ ሥልጣንና ሀብት ይዘው የነበሩት የታሪካዊ ጠላቶቻችን ተላላኪዎች፣ የሕግና የጸጥታ ተቋማትን በሞትና በሕይወት መካከል እንዲኖሩ አድርገዋቸው ነበር። ከለውጡ በኋላ በእነዚህ ተቋማት ላይ በተሠራው ሥራ የኢትዮጵያን ህልውና ለመታደግ ወደሚችሉበት ደረጃ ለማድረስ ተችሏል። እስከዛሬ ድረስ እነዚህን ተቋማት ለማጠናከርና ለዛሬ ችግሮች ምላሽ፣ ለነገ ፈተናዎች ዝግጁ እንዲሆኑ ለማድረግ ሲባል፣ እያመመንም ቢሆን አያሌ ችግሮችን ተሸክመን ለማለፍ ተገደናል።
ዳሩ ግን ትዕግሥትም ልክና መጠን አለው። አሁን የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት በተሻለ ቁመና ላይ ስለሚገኙ አስፈላጊ በሆነ ሰዓት ሁሉ ተመጣጣኝ ምላሽ ከመስጠት ወደኋላ አንልም። ከደህንነትና ከጸጥታ ጋር የተያያዙ ችግሮቻችን በዘላቂነት እንዲቀረፉ የብዙ አካላት ርብርብና ተናብቦ መሥራትን እንደሚጠይቅ ምንም ጥርጥር የለውም። እኛኑ ለሚያሸብሩና እኛኑ ለሚያሰቃዩ ጠላቶች ሕዝብ ምሽግ ከሆነ የጸጥታ አካላት ጥረት ብቻውን መፍትሔ አያመጣም። ስለዚህ እያንዳንዱ ዜጋ፣ የሐይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሚዲያና ሌሎች የሕዝብ ዐይን፣ ጆሮና ክንድ ሆናችሁ የምትሰሩ አካላት ከጸጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅትና በመግባባት ለመሥራት በሙሉ ልብ ቁርጠኞች መሆን አለባችሁ።
በለውጥ ጎዳና ላይ በመጓዝ ዴሞክራሲን የሚገነቡ ሀገራት በሁለት ጫፍ መካከል የሚቆም ፈተና ይገጥማቸዋል። በአንድ በኩል ዴሞክራሲያዊ ባህልን መገንባት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የሀገርንና የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት በጥብቅ ርምጃዎች ማስከበር ነው። ዴሞክራሲያዊ ባህልን ለመገንባት ስንነሣ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የሚያስከብሩ ጥብቅ ርምጃዎችቻን በነጻነትና መብት ስም እንዳይላሉ፤ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ለማስከበር የምንወስዳቸው ጥብቅ ርምጃዎችም ዴሞክራሲያዊ ባህልን እንዳያቀጭጩ በሚዛን መንቀሳቀስ ይገባናል። ሁለቱን በሚዛን ለማከናወን ደግሞ የእያንዳንዱ ዜጋ፣ ተቋም፣ ፓርቲ፣ ቡድን፣ ወገን፣ የሚጠበቅበትን ማድረግ አለበት። የሕግና የጸጥታ ተቋማትም ሕገ መንግሥታዊና ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው።
በመሆኑም ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ ቡድኖችንና ግለሰቦችን፣ ሐሰተኛ መረጃዎችን በማሠራጨት ሕዝብና ሀገርን ሰላም የሚነሡ አካላትን፣ በሕገ ወጥ መንገድ ታጥቀው የሕዝብን ሰላም የሚነሡና ለታሪካዊ ጠላቶቻችን በተላላኪነት የሚያገለግሉ ቡድኖችን፣ በመሬት ወረራና በተለያዩ የሥርቆትና የማታለል ተግባራት የተሠማሩትን፣ የትራንስፖርትና ሕዝብ እንቅስቃሴዎችን የሚያውኩትን፣ የልማትና የኢንቨስትመንት ተግባራትን የሚያደናቅፉትን፣ በጥናትና በመረጃ በመለየት አስፈላጊው ሁሉ ሕግ የማስከበር ርምጃ እንዲወሰድ የደኅንነት ምክር ቤቱ ወስኗል። በተመሳሳይ የምግብና ልዩ ልዩ ሸቀጦች ዋጋ እንዲንር በሕገ ወጥ መንገድ ምርት የሚያከማቹ፣ በኮንትሮባንድ መልክ ነዳጅና ሌሎች ምርቶችን ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚያሾልኩ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ተገቢው እርምጃ ይወሰዳል።
ወላጆች ልጆቻችሁን፣ ሽማግሌዎች ወጣቶቻችሁን፣ የሃይማኖት አባቶች ምእመኖቻችሁን፣ የፓርቲ መሪዎች አባሎቻችሁን፣ የጎሳ መሪዎች ወገኖቻችሁን፣ በመምከር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከግጭትና ከሽብር ራሱን አርቆ፣ ለሰላምና ለሀገር ደኅንነት የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ እንድታደርጉ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪያችንን እያቀረብን፣ ከዚህ በተቃራኒው ተሰልፎ የሚገኝ ማንኛውም ሰው፣ አካልና ቡድን ላይ ሕጉ የሚፈቅደውን ተገቢውን ሕግና ጸጥታ የማስከበር ሥራ የምንሠራ መሆኑን እናሳውቃለን።
መጭው ቀናት ለሕዝበ ክርስቲያኑም ሆነ ለሕዝበ ሙስሊሙ የበዓላት ሰሞን እንደመሆኑ መጠን አማኞች በትብብርና በመግባባት የጠላቶቻችንን ፍላጎት በማክሸፍና የጋራ ደህንነታችንን በማረጋገጥ እንደ ሀገር የተሳካ ጊዜያት እድንናሳልፍ የደህንነት ምክር ቤቱ አበክሮ ይጠይቃል።
የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት
ሚያዚያ 14፣ 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ

22/04/2022

የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኪባኪ ማረፋቸው ተነገረ ::

Source:-NTV kenya

18/03/2022

ጋዜጠኛው በከባድ ሙስና ወንጀል ተከሰሰ

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ከርፖሬሽን (EBC) የኦሮምኛ ክፍል ሀላፊ በላቸው ጃቤሳ ከሸገር ውሀ አምራች ድርጅት ሀላፊ ግማሽ ሚሊዮን ብር ጉቦ በመቀበል ከባድ ሙስና ወንጀል ተከሰሰ።

ከበላቸው ጀቤሳ ጋር በተጨማሪ የሰበታ ከተማ ወረዳ 08 ኗሪ የሆነው አለማየው ቂጢባ የተባለ ግለሰብም ከባድ ሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።

1ኛ ተከሳሽ በላቸው ጀቤሳ የEBC ኦሮምኛ ክፍል ሀላፊ ሆኖ ሲሰራ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር የሸገር ውሀ አምራች ኩኒስ ጠቅላላ ንግድ ስራ/ሀ/የተወሰነ ማህበር ድርጅት የሚያመርተውን የውሀ ምርት ባዓድ ነገር እንዳለው በሚዲያ እንደሚቀርብ ማስፈራራታቸው በክሱ ተመላክቷል።

በዚህም 2ኛ ተከሳሽ በጥር ወር 2014 ዓ.ም የድርጅቱ ባለሀብት ወደሆነው ዶ/ር ሀሰን መሀመድ ሩር ስልክ በመደወል አዳማ ከተማ አንድ ሱቅ ውስጥ ውሀ ለመጠቀም ገዝቼ ሶፍት መሳይ ቆሻሻ ስላገኘሁበት በጥር 26 እና 27 ቀን ለኢትዮጵያ ብርድካስት ኮርፖሬሽን ጥቆማ ያቀረብኩ በመሆኑ
በላቸው ጃቤሳ የተባለ የEBC ሰራተኛ አናግሩ በማለት የ1ኛ ተከሳሽን ስልክ ለውሀ አምራች ድርጅት ባለቤት ለዶ/ር ሀሰን መሀመድ መስጠቱ በክሱ ተገልጿል።

ባለሀብቱም በተሰጣቸው ስልክ ለ1ኛ ተከሳሽ ለEBC ኦሮምኛ ክፍል ሀላፊ ለበላቸው ጀቤሳ ስልክ በመደወል በአ/አ ብሔራዊ አካባቢ በሚገኝ ራስ ሆቴል በመገናኘት ይኺው 1 ተከሳሽ የውሀው ጥቆማ ለተቋሙ የደረሰ መሆኑን ገልጾ ነገር ግን በሚዲያው እንዳይተላለፍ ከፈለጉ ገንዘብ እንዲከፍሉ መጠየቁ ተመላክቷል በክሱ።

በጥር 28 ቀን በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ለቡ ጋርመንት አካባቢ በሚገኝ አንድ ካፍቴሪያ ከባለሀብቱ ጋር በመገናኘት ወደ ለተቋሙ የደረሰው በምስል የተደገፈ ጥቆማ እንዲመለስ ከፈለጋችሁ ግማሽ ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ ከጠየቁ በኋላ ባለሀብቱ በገንዘቡ መጠን ሳይስማሙ ከተለያዩ በኋላ በድጋሚ በየካቲት 2 ቀን 2014ዓ/ም ደግሞ በዛው ቦታ ተገናኝተው ባለሀብቱ ዶ/ር ሀሰን መሀመድ 100 ሺህ ብር በጥሬው ለ1ኛ ተከሳሽ ሰጥተውት ተከሳሹም ብሩን መኪና ውስጥ ካስገባ በኋላ ቀሪውን የ400 ሺህ ብር ሶስት ቼክ ደግሞ መኪና ውስጥ ሲቀበሉ በፌደራል ፖሊስ አባላት እጅ ከፍንጅ መያዛቸው በክሱ ተዘርዝሮ ጉቦ በመቀበል ከባድ ሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል ።

ተከሳሾቹ ዛሬ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በጽ/ቤት ቀርበው የክስ ቻርጅ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

ፍርድ ቤቱ ክሱን በችሎት በንባብ ለማሰማት ለመጋቢት 12 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰቷል።

9/7/2014
ዘገባው የታሪክ አዱኛ ነው::

07/02/2022

ሶስቱ ሳታስቡት የተቆጣጠሯችሁ ሰዎች
በሕይወታችሁ በሰዎች አጉል ቁጥጥር ስር ሆናችሁ እንድትኖሩና ነጻነታችሁን እንድትቀሙ ከሚደርጓችሁ አጉል ልምምዶች መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
1. ለመቆጣጠር የምትሞከሯቸው ሰዎች
የት እንደገቡ፣ ምን እንዳደረጉ፣ ከማን ጋር ወዳጅነት እንደጀመሩ፣ ምርጫቸው ምን እንደሆነና የመሳሰሉትን ነገር ካላወቃችሁና በጉዳዩ ላይ እናንተ ከሌላችሁበት ቅር የሚላች ሰዎች እናንተ የተቆጣጠራችኋቸው ይመስላችኋል እንጂ የተቆጣጠሯችሁ እነሱ ናቸው፡፡ እነሱን መከታተል፣ ሳታስቡት ጊዜያችሁን፣ ስሜታችሁንና ጉልበታችሁን ስሚወስደው ቀስ በቀስ በእነሱ ቁጥጥር ስር እንዳላችሁ አትርሱ፡፡
2. ቂም የያዛችሁባቸው ሰዎች
በቂምና በጥላቻ የምታስቧቸውን ሰዎች እነሱ በሚሄዱበት መንገድ ላይ ማለፍ፣ እነሱ በሚውሉበት አካባቢ መገኘትና እነሱ በሚሳተፉበት ነገር ላይ መሳተፍ ስለማትፈልጉ ብትወዱም ባትወዱም በእነሱ ቁጥጥር ስር ናችሁ፡፡ በተጨማሪም እነሱን ባሰባችሁ ቁጥር በስሜት ስለምትንተከተኩ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ከዋናው ዓላማችሁ ስምትገቱ በእነሱ ቁጥጥር ስር ናችሁ፡
3. የምትቀኑባቸው ሰዎች
በፍቅር ጓደኝነት ሆነ በሌሎች ዘርፎች በጣም የምትቀኑባቸውን ሰዎች ካሉ የእነሱን ውሎ፣ ስኬትና የመሳሰሉትን ነገር ከመከታተል ማረፍ ስለማትችሉ እነዚህ ሰዎች በተዘዋዋሪ መንገድ ሕይወታችሁን ተቆጣጥረው እንደያዙት አትዘንጉ፡፡ ትኩረታቸውን ከእናንተ ይልቅ ለሌላ ሰው እንደሰጡ፣ ስኬትና ዝናቸው ከእናንተ የበለጠ እንደሆነና የመሳሰሉት ስሜቶች ካልተገቱ እጅጉን የወረደና በቁጥጥር ስር የዋለ ሕይወት እንዳላችሁ ላስታውሳችሁ፡፡
የምትቆጣሯውን ሰዎችን ትንሽ ለቀቅ አድርጉ፣ በሰዎች ላይ ያላችሁን ቂምና ጥላቻ ተወት አድርጉ፣ በሰዎች የመቅናታችሁን ጉዳይ ጣል አድርጉትና ራሳችሁን ከቁጥጥር ነጻ አድርጉ!
ምንጭ፡-Dreyob

Address

Adama Express Way
Addis Ababa

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Asash Media posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Business

Send a message to Asash Media:

Videos

Share