03/11/2022
ገና የ22 ዓመት ኮረዳ ናት ሳዑዲ ዓረቢያዊቷ ሁዳ አል፡፡ የመናዊው አራፋት መሐመድ ጣሂር ደግሞ የ25 ዓመት ጉብል፡፡ እሱ በሳዑዲ ዓረቢያ ስደተኛ ሆኖ በአንድ የሞባይል ስልክ መሸጫ ተቀጥሮ ይሠራ ነበር፡፡ ፍቅር የተባለው ረቂቅ ነገርም ሁለቱን ወጣቶች አቀራረባቸው፣ አስተሳሰባቸው፣ አፋቀራቸው፡፡ ውሎ ሲያድርም ከአንድ ጣራ ሥር ለመኖር አስወሰናቸው፡፡
ይሁንና የሁዳ ወላጆች ጋብቻቸውን አልፈቀዱም ነበር፡፡ ‹‹በቡሃ ላይ ቆርቆር›› እንዲሉም የሁለቱን ፍቅር አደጋ ላይ የጣለ አንድ ማዕበል ተከሠተ፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ የሌላቸውንና ‹‹ሕገ ወጥ ስደተኞች›› ብላ የፈረጀቻቸውን የተለያዩ አገር ዜጎች ስታባርር፣ የመናዊው አራፋት መሐመድም ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ምድሪቷን ለቀው ወደ አገራቸው ከሚመለሱት ሰዎች አንዱ ሆነ፡፡
‹‹ሕጋዊና ሕገወጥ››፣‹‹አባራሪና ተባራሪ››፣‹‹ባላገርና ስደተኛ›› ነገር ግን ልቦቻቸው በፍቅር ሠንሠለት የተሠናሠሉት ሁዳ እና አራፋት ፍቅራቸው ዱብ ዕዳ ገጠመው፡፡ በፍቅራቸው ላይ የመጣውን መዓት ሊያስቀሩም ተመካከሩ፡፡ መላ መቱ፡፡ መፍትሔ ግን አልተገኘም፡፡ የመናዊው አራፋት ‹‹ሕገ ወጥ›› ስደተኛ ነውና የግድ ወደ አገሩ መመለስ አለበት፡፡ ካልተመለሰ ያ…. የሳዑዲ ፖሊሶች በትርና ቀሪ ዘመንን በዘብጥያ ማሳለፍ እጣ ፈንታው ይሆናል፡፡ ግና ፍቅረኛውስ? . . . አራፋት እንደ ሞት የበረታውን የመለየቱን አባዜ ሲያስበው መፈጠሩን ጠላ፡፡
በሳዑዲ ዓረቢያ በፍቅር ሰበብ ወንድ ተከትሎ መኮብለል በቤተሰብ ዘንድ ያስነውራል፡፡ ይባስ ብሎ ድንበር ጥሶ ወደ ሌላ አገር መጓዝ ደግሞ እንደ አገር ከሀዲ ያስቆጥራል፡፡ ታዲያ ምንድነው የሚሻለው?….
ሁዳ ፍቅረኛዋን ተከትላ ለመኮብለል ብትፈልግም ከቤተሰቦቿ የሚጠብቃትን ድብደባ ስታስበው አንገፈገፋት፡፡ ይሁንና የመጣው ይምጣ ብላ ‹‹አብሬህ እሄዳለሁ፡፡ አገርህ አገሬ፣ ሕዝብህም ሕዝቤ ነው›› በማለት ቁርጥ ውሳኔ አደረገች፡፡ አራፋት አብራው የመኮብለሏን ውሳኔ ሲሰማ አላመነም፡፡ ቃሏን ደገመችለት፡፡ ተቃቅፈው በደስታና ሐዘን የተቀየጠ እንባ አነቡ፡፡ በመጨረሻም የሳዑዲ ትዝታቸውን አራግፈው ፍቅራቸውን ብቻ ሰንቀው፣ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ በረሃ አቋርጠው፣ ድንበር ተሻግረው የመን ገቡ፡፡
ዳሩ ምን ያደርጋል የመን ለሁዳ እንደጠበቀቻት አልሆነችላትም፡፡ እንዳለመችው እጆቿን ዘርግታ አልተቀበለቻትም፡፡ ድንበሬን ያለፈቃድ አቋርጠሻል ስትል የክስ ዶሴ ከፈተችባት እንጂ፡፡
ወሬውም ቢቢሲን ጨምሮ ታላላቅ ሚዲያዎችን እና የማኅበረሰብ ድረ ገጾችን አጨናነቀ፡፡ ‹‹የዘመናችን ሮሚዎና ዡሊየት›› ሲሉም ከእንግሊዛዊው ጸሐፌ ተውኔት ዊሊያም ሼክስፒር ዝነኛ ድርሰት ከሆነው ‹‹ሮሚዎና ዡልየት›› ቴአትር አውራ ገጸ ባሕርያትን በመጥቀስ ወሬውን አራገቡት፡፡
በፍቅረኛዋ አገር የመን ያልጠበቀችው ዱብ ዕዳ የገጠማት ሁዳ፣ ‹‹እባካችሁ እጅግ የምወደውን ጓደኛዬን አግብቼ በአገራችሁ እንድኖር ብቻ ፍቀዱልኝ ሌላ ምንም ነገር አልፈልግም›› ስትል ተማጽኖዋን በሕገወጥ ስደተኝነት ለከሰሳት የየመን ፍርድ ቤት አቤት አለች፡፡ አብሯት እስር ቤት የገባው ፍቅረኛዋ አራፋት ነፃ ነህ ቢባልም፣ የለም ሞቴን ከሁዳ ጋ ያርገው በማለት አብሯት መታሰርን መረጠ፡፡
ጉዳዩን የሰሙ በመቶ የሚቆጠሩ የመናውያን፣‹‹ፍቅር ከድንበር እና ዜግነት ይቀድማል››፣ ‹‹ለሁዳ ዘብ ቆመናል›› እና መሰል መፈክሮችን በመያዝ ፍርድ ቤቱ አካባቢ የሚገኘውን ጎዳና አጥለቀለቁት፡፡
በየመን የሚገኘው የሳዑዲ ዓረቢያ ኤምባሲ፣ ምንም እንኳ ለሁዳ ጠበቃ ቢያቆምላትም፣ ጠበቃው ወደ አገሬ እንድመለስ ጫና ሊያደርግብኝ ይችላል በሚል ሥጋት ኤምባሲው ያቆመላትን ጠበቃ አልፈልግም አለች፡፡ ሁድ የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ያቆመላትን ጠበቃ ግን እሰየው ብላ ተቀብላለች፡፡ ጠበቃዋ አብዱል ራብ አልቃዲም፣ ‹‹ይህ የሰብአዊነት ጉዳይ በመሆኑ ሁለቱን አገሮች የሚያሳስብ ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡›› ሲሉ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የወሬ ወኪል ተናግረዋል፡፡
የሁዳ ጉዳይ ውሎ አድሮ መቀመጫውን በአሜሪካ፣ ኒውዮርክ ያደረገውን የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ቀልብ ስቧል፡፡ ተሟጋቹ ለየመን ባለሥልጣናት በላከው መልዕክትም፣ ልጅቱን ወደ አገሯ ፈፅሞ እንዳይመልሷት አሊያ ግን ሕይወቷ በተደጋጋሚ ይደበድቧት በነበሩት ቤተሰቦቿ እጅ ላይ መውደቅ ይሆናል ሲል አስጠንቅቋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ተወካይም፣ ለሁዳ የፖለቲካ ጥገኝነት ይሰጣት ዘንድ የየመንን መንግሥት አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን፣ ሁዳ በየመን የስደተኞች ማዕከል እንድትገባ ፈቅዶላታል፡፡ እንደ ተወካዩ ገለጻም በቀጣዮቹ ቀናት ሁዳ ሙሉ መብት የሚያጎናጽፋትን የስደተኛ ፈቃድ አግኝታ ሁለቱ ፍቅረኞች ነፃ ሆነው በጋብቻ አንድ ጣራ ሥር መኖር ይጀምራሉ ብለዋል፡፡ ይሁንና ባለጠጋዋ ሳዑዲ ዓረቢያ ደሃ ጎረቤቷ የመንን ሁዳን ጠርዛ እንድትልክላት ልታስገድዳት ትችል ይሆናል ሲሉ ፍርሃታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ያም ሆኖ የመን ለሳዑዲ ማስገደድ አዎንታዊ ምላሽ የምትሰጥ ከሆነ ሁለቱን ፍቅረኞች ወደ ሌላ ሀገር ለመውሰድ እንደታቀደ ተስፋ መስጠታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል