18/12/2023
የ2016 ዓ.ም የሀላባ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ የሴራ በዓል ለማክበር በየደረጃው የሚደረገው ዝግጅት ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ!
*******
ሀላባ ቲቪ ታህሳስ 7/2016 ዓ.ም
የ2016 ዓ.ም "ሴራችን የአንድነታችን ማሳያ ድንቅ ምልክታችን በሚል መር ቃል የሚከበረው የሀላባ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ (መንገሳ) በዓል አከባበር አስመልክቶ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በዛሬው ዕለት ውይይት የተደረገ ሲሆን በውይይቱ ወቅትም ከ11 ሚሊዬን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የሀላባ ዞን ዋና አስተዳደር አቶ ሙሂዲን ሁሴን ፣የሀላባ ዞን አስተዳደር አማካሪ አቶ ከድር ቆርቾ፣የሀላባ ቁሊቶ ከተማ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ታገል ጌታቸው በጋራ በመሆን መርተዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳደር አቶ ሙሂዲን ሁሴን በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት የሀላባ ሴራ በዓል በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ጥናታዊ ስራ እየተሰራ መሆኑን በመግለፅ ለሚከበረው በዓል የባለሀብቱ ሚና የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
የዘንድሮው ሴራ በዓል ልዩ የሚያደረገው በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በተለያዩ ሀገራት ደረጃ በድምቀት ለማከበር የተለያየ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ከወትሮ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
ዋና አስተዳዳሪው አክለውም ለሴራ በዓል አከባበሩ የሚደረገው የሀብት አሰባሰብ ስራ በየደረጃው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፀው ባለሀብቱ ብሎም የንግዱ ማህበረሰብ ባህላችንን በማስተዋወቅ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
የዞኑ አስተዳደር አማካሪ አቶ ከድር ቆርቾ እንደተናገሩት የሀላባ ሴራ (መንገሳ ) በብሔረሰቡ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን በመግለፅ አርሶ አደሮች አዝመራቸውን በመሰብሰብ እፎይታ የሚያገኙበት፣ ግርዛኞች ወደ ወጣትነት (ወደ ሃላፊነት) የሚሸጋገሩበት ፣እናቶች በቃላ ጀግኖችን የሚያወድሱበት ወር መሆኑን ገልፀዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስታየት እንደገለጹት የሀላባ ሴራ በዓል ለማክበርና በዩኔስኮ እንዲመዘገበ በሚደረገው እንቅስቃሴ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ ለመውጣት ዝግጁ መሆነቸውን ገልጸዋል።
በዛሬው ውይይትም ከውስን ባለሀብቶች ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን የሀብት አሰባሰብ ስራው በየደረጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
በያድሳ ሃጂ ታማም