11/04/2023
በወቅታዊ ጉዳይ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ!
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የገዥው ብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ አደረጃጀት ላይ ለውጥ ለማድረግ ውሳኔ ማሳለፉን ከገለጸበት ካለፉት ሶስት ሳምንታት ወዲህ ተከታታይ መግለጫ ሲያወጣ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ድርጅታችን አብን ባወጣቸው ተከታታይ መግለጫዎች የገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ በሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች ላይ በእኩል ደረጃ ተፈጻሚ የማይሆን እና የውሳኔው ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ የአማራ ልዩ ኃይልን ትጥቅ ማስፈታት መሆኑን ፤ የገዥው ፓርቲ ውሳኔ ከሕጋዊነት ፣ ከወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች አንጻር ወቅቱን ያልጠበቀ ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያላስገባ እና ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የአማራ አካባቢዎችን እና የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተገማች እና ቀጥተኛ ለሆነ ጥቃት እና አደጋ የሚዳርግ ውሳኔ መሆኑን እና ክልሉን ለከፍተኛ አለመረጋጋት እና የጸጥታ መደፍረስ የሚዳርግ ጊዜውን ያልጠበቀ እና ኃላፊነት የጎደለው አደገኛ ውሳኔ መሆኑን በመግለጽ መንግስት ውሳኔውን እንዲያጥፍ ድርጅታችን ጥሪ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
የገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔው እና ውሳኔውን ለማስፈጸም የወሰዳቸው እርምጃዎች በአማራ ክልል ላስከተሉት ከፍተኛ አለመረጋጋት ፣ የመደበኛ እንቅስቃሴዎች መስተጓጓል እና ለጸጥታ መደፍረስ ኃላፊነት ከመውሰድ እና መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሕግ አግባብ ውጭ እና በሌለው ሥልጣን ያሳለፈው ውሳኔ ላስከተለው ከፍተኛ ቀውስ የጦስ ደሮ ማፈላለግ ላይ ተሰማርቷል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ትናንት ሚያዚያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የክልል ልዩ ኃይል ፖሊሶችን “መልሶ የማደራጀት” ውሳኔ በብዙ ጥናት፣ በጥልቅ ውይይት፣ በሰከነ ንግግር እና በጋራ መግባባት የተደረሰበት ውሳኔ መሆኑን ፣ ልዩ ኃይልን ትጥቅ የማስፈታት ሳይሆን የተሻለ የማስታጠቅ ፤ የመበተን ሳይሆን በጠንካራ መሰረት ላይ የማደራጀት ሥራ ላይ መሆኑን ፤ የልዩ ኃይል አባላት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የተለየ አክብሮት እና ፍቅር እንዳለው፤ ውሳኔው በአማራ ክልል ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በተመሳሳይ የጊዜ መስመር የሚተገበር መሆኑን በመግለጽ መግለጫ አውጥቷል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ያወጣው መግለጫ እውነታን የካደ እና አሁንም ገዥው ፓርቲ ለመፍትሄው ዝግጁ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ውሳኔው በአማራ ክልል ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በተመሳሳይ የጊዜ መስመር የሚተገበር ነው ቢልም ከአማራ ክልል በቀር በየትኛውም ክልል የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላትን ትጥቅ የማስፈታት ወይም በገዥው ፓርቲ አነጋገር “መልሶ የማደራጀት” እንቅስቃሴ አልተደረገም፡፡ ገዥው ፓርቲ ሁሉም ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች የተስማሙበት ውሳኔ ነው እያለ ቢሰነብትም ፣ የአማራ ክልልን ጨምሮ የየትኛውም ክልል ካቢኔ ወይም ምክር ቤት ጉዳዩን አስመክቶ ያደረገው ውይይትም ሆነ ያሳለፈው ሕጋዊ ውሳኔ የሌለ ሲሆን፤ ለዚህ ድርጅታዊ ቅጥፈት ቀላል ማስረጃዎች የሚሆኑን አብነቶች፦
1:- የማስፈጸሚያ እቅድ ነው የተባለው ሰነድ በፌዴራል መንግስት ባለስልጣናት ደረጃ ውይይት የተደረገበት በቀን 30/07/2015 ዓ.ም መሆኑ፣
2:- የሱማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ካቢኔ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳለፈው በቀን 02/08/2015 ዓ.ም መሆኑ መገለጹ፣ ገዥው ፓርቲ ያወጣው መግለጫ እውነትነት የራቀው መሆኑን የሚያጸና ነው፡፡
ገዥው ፓርቲ የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የተለየ አክብሮት እና ፍቅር እንዳለው ቢገልጽም በአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ላይ የተደረገው እና የሆነው ግን የመግለጫውን ቃል ከምጸት የሚያስቆጥረው ነው፡፡ በተጨባጭ የሆነው እና እየሆነ ያለው የአማራ ክልል የልዩ ኃይል አባላት ከፍተኛ አመራሮች ፣ የብርጌድ እና የክፍለጦር አዛዦች በድንገት ከሥራ ውጭ ተደርገው የልዩ ኃይሉ የእዝ ሰንሰለት እንዲፈርስ መደረጉ፤ የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት ስንቅ ፣ ሎጂስቲክ እና ደሞዝ ተነፍገው ለርሃብ እና ለከፍተኛ እንግልት መዳረጋቸው እና ከካምፕና ከግዳጅ ምድብ ቦታቸው እህል ውሃ ወደሚያገኙበት ቦታ ለመድረስ በርካታ መቶ ኪሎሜትሮችን በእግራቸው ለመጓዝ የተገደዱበት ልብ የሚሰብር እና ክብረ-ነክ ክስተት የተስተዋለበት ሲሆን፣ ለሀገር አንድነት እና ኅልውና በከፍተኛ መስዋዕትነት ጀብድ ለፈጸሙ የዘመናችን ጥቁር አንበሶች የማይመጥን፣ ገዥውን ፓርቲ እና የውሳኔው አካል የሆኑ ወገኖችን በሙሉ ዝንተ-ዓለም አንገታቸውን የሚደፉበት ታሪክ ሁኖ ተመዝግቧል፡፡
ገዥው ፓርቲ ያወጣው መግለጫ እውነታን የካደ ብቻ ሳይሆን የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሌለው ሥልጣን በወሰነው ውሳኔ እና ውሳኔውን ለማስፈጸም በወሰደው ኃላፊነት የጎደው እርምጃ አንጻራዊ ሰላም በነበረው አማራ ክልል ላይ ለፈጠረው ከፍተኛ አለመረጋጋት እና የጸጥታ መደፍረስ ኃላፊነት ያልወሰደበት እና በአስር ሽህዎች የሚቆጠሩ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ላይ ላስከተለው እንግልት እና መጎሳቆል እውቅና የነፈገበት ይልቁንም የተሳለቀበት በመሆኑ ፓርቲያችንን ፣ የአማራን ሕዝብ እና መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን አሳዝኗል፡፡ የገዥውን ፓርቲ ውሳኔ በመቃወም የክልሉ ሕዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተቃዉሞ እያሰማ ሲሆን ፣ በገዥው ፓርቲ የተሳሳተ ውሳኔ ምክንያት ላለፉት በርካታ ቀናት በአማራ ክልል መደበኛ እንቅስቃሴዎች ተስተጓጉለዋል ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረ የጸጥታ መደፍረስ የሰው ህይወት አልፏል ፣ የክልሉ ዋና ዋና ከተሞች የቀውስ አስተዳደር ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ተገደዋል፡፡
ድርጅታችን አብን ሁልጊዜም እንደሚለው የሀገራችን ሕዝብ መልከ ብዙ ብዝሃነቶችን እውቅና የሚሰጥ እና የሚያከብር ፣ ለግለሰቦች መሰረታዊ መብቶች መከበር እና መጠበቅ ዋስትና የሚሰጥ ፣ የሀገር ሉዓላዊነትን ፣ ሀገራዊ አንድነትን እና የግዛት አንድነትን የሚያረጋግጥ እውነተኛ ፌዴራላዊ ሥርአት እንዲዋቀር እና በሥራ ላይ ያለው ሃሳዊ “ፌዴራሊዝም” በሃቀኛ ፌዴራላዊ ሥርአት እንዲተካ ትግል የሚያደርግ ድርጅት ነው፡፡ አብን ለበርካታ አስርት ዓመታት ሲዳከም የቆየው የማዕከላዊ መንግስት ስልጣን በእውነተኛ ፌዴራላዊ የመንግስት ሥርአት አወቃቅር አግባብ እንዲጠናከር እና መንግስት የመላ ኢትዮጵያውያን መብት እና ደኅንነት የማክበር ፣ የማስከበር እና የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የራሱን ሚና ለመወጣት ቁርጠኛ አቋም ያለው ድርጅት ነው፡፡ አሁን በሥራ ላይ ባለው የፌዴራል አወቃቀር ፣ ሕገ-መንግስት እና አስተዳደራዊ መዋቅር በርካታ ሕጎች እና ተቋማት መሰረታዊ ችግር እንዳለባቸው ድርጅታችን አብን ያምናል ፣ ይህንን ሁኔታ ለመቀየርም ይታገላል፡፡
ድርጅታችን አብን ከዚህ ቀደም አቋሙን ግልጽ እንዳደረገው በየክልሉ የተደራጁ ልዩ ኃይሎች አፈጣጠር እና አደረጃጀት የራሱ የሆነ ችግር የነበረበት ቢሆንም አሁን ባለው ተጨባጭ እና ነባራዊ ሁኔታ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን በድንገት እና ያለበቂ የጸጥታ ዋስትና ማፍረስ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የአማራ ክልል አካባቢዎችን ተገማች እና ቀጥተኛ ለሆነ ጥቃት ተጋላጭ የሚያደርግ በመሆኑ ውሳኔውን አብን አጥብቆ የሚቃወመው ነው፡፡ የጸጥታ ስጋት ካለባቸው የክልሉ አካባቢዎች አንዱ በሆነው አጣየ ከወዲሁ ጥቃት የተከፈተ ሲሆን ፣ ትሕነግ በወልቃይት እና ራያ ሕዝብ ላይ ጥቃት እንደሚከፍት እየዛተ ይገኛል፡፡
ስለሆነም ገዥው ፓርቲ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን ለማፍረስ ያሳለፈውን ውሳኔ እና ውሳኔውን ለማስፈጸም እየሄደበት ያለው መንገድ በአሁኑ ሰዓት በአማራ ክልል የተከሰተውን አለመረጋጋት እና የጸጥታ መደፍረስ ያስከተለ እና ሕዝባችንን ለጥቃት ፣ ክልሉን ለከፍተኛ አለመረጋጋት እና የሰላም እጦት የዳረገ መሆኑን እያሳሳብን ፣ የፌደራል መንግስት እና የአማራ ክልል መንግስት የክልሉ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ያቀረበውን ጥያቄ እንዲያከብሩ እና ድርጅታችን አብን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ያቀረባቸውን ጥሪዎች እና የውሳኔ ሃሳቦች ተቀብለው ሥራ ላይ እንዲያውሉ በድጋሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
አዲስ አበባ ፣ ሸዋ ፣ ኢትዮጵያ
ሚያዚያ 3 ቀን 2015 ዓ.ም