
25/03/2025
በለውጡ ዓመታት የሐረርን የታሪክ ልክ እና የመስህብ ሃብቶች የገለጡ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል
ሐረር፤መጋቢት 16/2017(ሐክመኮ)፡- በለውጡ ዓመታት የሐረርን የታሪክ ልክ እና የመስህብ ሃብቶች የገለጡ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ ገለጹ።
በክልሉ ባለፉት ሰባት ዓመታት በከተማ ልማት ዘርፍ የተከናወኑ የልማት ስራዎችንና የተመዘገቡ ስኬቶቸን እንዲሁም ቀጣይ እቅዶችን በማስመልከት አቶ ሙክታር ሳሊህ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ከለውጡ በፊት የከተማ ፕላንን መሰረት ያደረጉ የልማት ስራዎችን ለማከናወን የነበሩ ችግሮችን በማስታወስ በተለይም ህገ-ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ በስፋት ይስተዋሉ ነበር ብለዋል።
በመሆኑም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ሀረር ከተማ በፕላን እንድትመራ ማድረግን ጨምሮ የከተማዋን የታሪክ ልክ የሚመጥኑ የልማት ስራዎችን በማከናወን የተሳካ ውጤት ተመዝግቧል ነው ያሉት።
በለውጡ ሰባት ዓመታት የሐረርን የታሪክ ልክ እና የመስህብ ሃብቶች የገለጡ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች ስለመከናወናቸውም ጠቅሰዋል።
የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበት የነበረውን የጀጎል የአለም አቀፍ ቅርስ በማደስ ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችል ትልቅ አሻራ ያረፈበት ስራ መከናወኑንም ለአብነት አንስተዋል።
በከተማው በኮሪደር ልማት የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎችንና መናፈሻዎችን በመገንባት የከተማዋ የውበት መገለጫና ተጨማሪ የቱሪስት መስህብ ማድረግ መቻሉንም እንዲሁ።
እንደ አጠቃላይ በለውጡ ሰባት ዓመታት የነበሩ ቅርሶችን በማደስና በመጠበቅ የሀገር ሃብት ሆነው እንዲቀጥሉ በማድረግ በኩል የሚታይ ውጤት ተመዝግቧል ነው ያሉት።
በክልሉ ለተመዘገበው ተጨባጭ ውጤት የአመራር ቁርጠኝነት የህዝቡ እገዛና ትብብር ታክሎበት የተገኘ ስኬት መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይም ሐረርን የማስዋብ፣ ልማቷን የማስቀጠልና የህዝቡን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ አረጋግጠዋል።