17/04/2024
ስለ ሰላም እንዘምራለን፤ ደግሞም እንሰራለን!
የዴሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋት ሲንከባለሉ የመጡ እና በየጊዜው ቅርፃቸውን የሚቀያይሩ ሳንግባባ ያደርንባቸውን አገራዊ ጉዳዮች ጭምር ህዝባችንን በማሳተፍ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት በመስጠት አገራዊ አንደነታችንን በማይናወጥ መሰረት ላይ ለመገንባት ከለውጡ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ።
በእሳት ተፈትኖ ነጥሮ እየወጣ ያለው የለውጡ መሪ መንግስታችን እና ፓርቲያችን "ኢትዮጵያ አበቃላት" ያስባለውን ከውጭም ከውስጥም የተደቀነባትን ምናልባትም በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ውስብስብ ፈተና ህዝቡን ከጎኑ አሰልፎ እንደ ጉም ከመግፈፉ በተጨማሪ የቆመለትን ኢትዮጵያን የማበልፀግ ዓላማ ለአፍታም ሳይገታ አጠናክሮ አስቀጥሏል።
በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያን መለወጥ የማይመኙ፣ በልፅጋ ማየት የማይፈልጉ የውስጥና የውጭ ፀረ-ሰላም ሀይሎች ፍላጎታቸው የሚሳካው እርስ በእርስ ስንጣላ እንጅ ስንፋቀር ባለመሆኑ 24 ሰዓት በታዛቢነት ከዳር ሆነው የሚመለከቱትን የጦርነት ፊሽካ መንፋታቸውንና ከእሳት ላይ ቤንዚን ማርከፍከፋቸውን አላቆሙም።
ኢትዮጵያዊያን የጦርነትን እና የግጭትን አስከፊነት በየጊዜው የህይወት መስዋዕትነት እና የንብረት ውድመት ውድ ዋጋ እያስከፈለን እያለፍንበት ያለ የአስከፊ ታሪካችን ገፅታ ጭምር እንጂ ከርቀት የምንሰማው ጉዳይ አይደለም።
የግጭት አትራፊዎች ያልተቋረጠ የገቢ ምንጭ በሬ ወለደ የሚሉ የሀሰት ወሬዎች በመሆናቸው ሳያረጋግጡና ሳያመዛዝኑ የሚያዳምጡ ግለሰቦችን ወደ እኩይ መረባቸው ለማስገባት ጠዋት ማታ ያሰራጫሉ።
ከሀሰተኛ መረጃዎች ራስን መጠበቅ እንዲሁም በዘመኑ የሚዲያ አማራጮች ውሸታቸውን ማጋለጥም ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል።
የአገር ዋልታ የሆነው መከላከያ ሰራዊታችን እና ሌላውም የፀጥታ ሀይላችን አስተማማኝ ሰላማችንን ለማረጋገጥ ለሚወስዳቸው አጥፊዎችን ወደ ህግ የማቅረብና ህግን የማስከበር እርምጃዎች እንደተለመደው ደጀንነታችንና ድጋፋችንን ማጠናከርም ይገባል።
የግጭት አትራፊዎች ስለሰላም ማውራትን፣ ስለሰላም ነገሮችን በትዕግስት ማለፍን እንዲሁም የሀይማኖት አባቶችን የሰላም ምክር እንደ ሞኝነት ቢቆጥሩትም የኢትዮጵያን አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ እንዲሁም ሁለንተናዊ ብልፅግናዋን እውን ለማድረግ ቆርጠን በመነሳታችን ዛሬም ሆነ ነገ ስለ ሰላም እንዘምራለን፤ ደግሞም እንሰራለን!