13/05/2024
የሴቶችን የልማት ህብረት አደረጃጀት ማጠናከር ልማት፣ መልካም አስተዳደርና ሰላም ለማስፈን የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተገለፀ።
የኮንታ ዞን ሴ/ህ/ወ/ማ/ጉዳይ መምሪያና የኮንታ ዞን ጤና መምሪያ በጋራ በመሆን በሴቶች ልማት ህብረት አደረጃጀት እና አሠራር መመሪያ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂደዋል።
የኮንታ ዞን ሴ/ህ/ወ/ማ/ጉ/መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ድንቅነሽ በፍቃዱ ሴቶች በተፈጠረላቸው ምቹ የፖሊሲና የህግ አሰራር፣ አደረጃጀትና ስትራቴጂ ማዕቀፍ በመጠቀም በመረጡት ዓላማ ላይ ተደራጅተው ለላቀ ተሳትፎና ተጠቃሚነት መብቃት እንዲችሉ ከምንም ጊዜ በላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የሴቶችን የልማት ህብረት አደረጃጀት ማጠናከር ልማት፣ መልካም አስተዳደርና ሰላም ለማስፈን የጎላ ፋይዳ እንዳለው የገለፁት ኃላፊዋ ሴቶች በህብረተሰቡ ውስጥ በማንኛውም መስክ እኩልነታቸው ተረጋግጦ በኢኮኖሚ በማህበራዊና በፖለቲካው ዘርፍ እኩል ተሳታፊ፣ ተጠቃሚና ውሳኔ ሰጪ የሚሆኑበትን ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዓለሙ ኮቾ በበኩላቸው የሴቶች ልማት ህብረት የሴቶችና ህፃናት ጤና ተጠብቆ አምራች ዜጋ እንዲፈጠር ጉልህ ሚና የሚጫወት በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በመድረኩ የተገኙት የዞኑ ረዳት የመንግስት ተጠሪና በብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ባሻ በላቸው የሴቶች የልማት ህብረት በጋራ ዓላማና ግብ ሴቶች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት ታስቦ ለረጅም ጊዜ ተግባራዊ ሆኖ ውጤት የተመዘገበበት ጠንካራ አደረጃጀት መሆኑን አስረድተዋል።
አደረጃጀቱ መነሻው ከዚህ በፊት የነበረው ኢ-ፍትሃዊ የሴቶች ተጠቃሚነትና ከመብት ጋር ተያይዞ የነበሩ ችግሮችን እየፈታ እንደሚገኝ አንስተው ሴቶችን በልማት ህብረት ማደራጀትና ማብቃት የሁሉም ኃላፊነት እንደሆነ አስገንዝበዋል።
የሴቶች የልማት ህብረቶች ተቋማዊ አቅም በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አቅም በመገንባት በየአከባቢው ሁሉም እንዲሳተፍና እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን የማድረግ ሥራ ትኩረት ልሰጥ ይገባል ተብሏል።
የሴቶች የልማት ህብረት ማለት የጋራ ዓላማና ግብ ያላቸውና በአንድ ቀበሌ ውስጥ በተቀራረበ አካባቢ ከ25-30 ሆነው ዕድሜአቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸው የተደራጁ ሴቶች የሚመሰርቱት ንዑስ አደረጃጀት መሆኑ ተገልጿል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች የሴቶች አደረጃጀት ትልቅ ትርጉም የሚሰጥ ከመሆኑ አንፃር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ ብሎም የሴቶችን አቅም ማጎልበት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
የሴቶች የልማት ህብረት የቁጠባ ባህል ማሳደግ፣ የልማት ሥራዎችን ማሳለጥና የሴቶች አደረጃጀት በቀበሌዎች ደረጃ የማጠናከር ሥራ ሊተኮር ይገባል ብለዋል።