12/10/2023
ከእብደት ውጣ!!
፨፨፨////////፨፨፨
እብደት አስተሳሰብ ውሱንነት ጋር ብቻ የሚገናኝ ጉዳይ አይደለም። አብዛኛው የዓለማችን ሰው እብደቱን ባለማወቁ ሙሉ በሙለ የሚያስብና እንዳላበደ ያምናል። እውነታው ግን እያንዳንዱ ሰው ይብዛም ይነስም በየጊዜው በእብደት ውስጥ ያልፋል፤ ምንነቱ በማይታወቅ የአስተሳሰብ ውልብታ ይመታል፤ በቅጡ እንኳን ሊረዳውና ሊገልፀው የማይችለው ሁኔታ ውስጥ እራሱን ያገኛል። ማድረግ ያለበትን ነገር ሳያደርግ መጠበቅ የሌለበትን ውጤት በጉጉት ይጠብቃል። አንድ ከአንድ ደረጃ ወደሌላኛው ደረጃ የማለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ የሆነ ተማሪ ስሙን ከሰቃዮቹ ተርታ ሲፈልግ ብንመለከት ከእርሱ የባሰ እብድና ግራ የተጋባ ሳው እንደሌለ እናስባለን። ነገር ግን የብዙዎቻችን ህይወት ከእርሱ የተለየ አይደለም። የማይመጥነንን ውጤት በመጠበቅ እድሜ ዘመናችንን የምንፈጅ ሰዎች ጥቂቶች አይደለንም።
አዎ! ጀግናዬ..! ከእብደት ውጣ! እራስህን እያወክ እራስህን አታስጨንቅ፤ በገዛ ፍቃድህ እራስህን ጫና ውስጥ አትክተት፤ ያልዘራሀውን ለማጨድ፣ ያልተከልከውን ለመቁረጥና ያንተ ያልሆነውን ለመብላት አትሯሯጥ። ሰጥቶ የመቀበልን ምድራዊ ህግ አክብር፣ ታግሎ የማሸነፍን መርህ ተከተል፣ ዋጋ ከፍሎ ለውጤት የመብቃትን ህግ ፈፅም። ላንተ ሲሆን የሚቀየር ምድራዊ አሰራር የለም። የምርም ጥበብ እንደታደለው፣ ማስተዋል እንደተሰጠው፣ ልቡም በብረሃን እንደተሞላ ሰው የምታስብ ከሆነ በምንም መንገድ ቁጭ ብለህ በሰዎች ላብ ማትረፍን የምታስብ፣ ያለስራህ ሙገሳን የምትጠብቅ፣ በጥፋትህ አድናቆትን የምትመኝ ሰው አትሆንም። ዛሬ ያለስራህ ብትደነቅ ነገ በስራህ እንደምትዋረድ አስታውስ።
አዎ! ዘወትር ተመሳሳይ ተግባር እየፈፀምክ የተለየ ውጤት መጠበቅ አቁም፤ ሁሌም አንድ ቦታ እየተገኘህ የህልምህን መሳካት አትመኝ፤ እራስህን አሳንሰህ እየተመለከትክ ሰዎች ከፍ እንዲያደርጉህ አትጠብቅ። ዓለም በልብህ የያዝከውን፣ በአዕምርህ የሚመላለሰውን፣ በእምነትህ የሚታየውንና በልማድህ የሚገለጠውን ያንኑ እንደምትሰጥህ እወቅ። የቤቱ ዋንኛ ችግር እራሱ ሆኖ፣ ለውድቀቱና ስህተቱ ተጠያቂው እራሱ ሆኖ፣ ደስታ ለማጣቱ ምክንያት እራሱ ሆኖ ሳለ ለእራሱ ቤት መፍትሔ ፍለጋ ሃገሩን እንደሚያስስ፣ ለውድቀቱ፣ ለስህተቱና ለወረደ ህይወቱ ውጫዊውን አካል እንደሚወቅስና ለደስታው ብሎ እራሱን አደጋ ላይ እንደሚጥል ሰው በእብደት ጎዳና ላይ እየተመላለሰ ያለ ሰው አለን? በፍፁም። እብደትህን አቁምና እራስህን ተረዳ፣ የዓለምን አሰራር ተገንዘብ፣ የምድርን ህግ እወቅ፣ ሃላፊነትህን በአግባቡ ስትወጣ የሚገባህ ነገር በእጅህ እንደሚገባ እመን።
ሰናይ ቀንይሁንልን! 🌘🌒💫✨
አብርሃም 🤜🤜🫷🫷