09/06/2024
ከተረጂነት ተላቀን የተሟላ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የጋራና የተቀናጀ ጥረት ማድረግ አለብን~ አቶ አወሉ አብዲ
ከተረጂነት ተላቀን የተሟላ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የጋራና የተቀናጀ ጥረት ማድረግ አለብን ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ ገለጹ።
"ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነት እና ክብር" በሚል መሪ ሀሳብ ህዝባዊ የውይይት መድረክ በዲላ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ በዚሁ በወቅት ባደረጉት ንግግር ፤ ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙንን የተለያዩ ፈተናዎች ተቋቁመን በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ መገንባት ችለናል ብለዋል።
በተለይ በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል በተደረገ ጥረት አበረታች ውጤት መገኝቱን ጠቅሰው ለዚህም በጌዴኦ ዞን በግብርና ልማትና በኢንዲስትሪ ምርት የተገኘው ለውጥ ተጨባጭ ማሳያ ነው ሲሉ አመልክተዋል።
ከተረጅነት ተላቀን የተሟላ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የጋራና የተቀናጀ ጥረት ማድረግ አለብን፤ መድረኩም ይህንኑ ለማምጣት ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።
በተለይ ከተሞችን ከድህነት በማላቀቅ የኢንዱስትሪና የስራ ፈጠራ ማዕከል ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ህብረተሰቡ በሙሉ አቅሙ ሊያግዝ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፤በዞኑ ከተረጅነት የወጣ በምግብ ሰብል እራሱን የቻለ ህብረተሰብ ለመፍጠር ዘርፈ ብዙ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ የበጋ መስኖ፣ የሌማት ቱርፋትና መሰል ሀገራዊ ፕሮግራሞችን ወደ መሬት በማውረድ የአርሶ አደሩንና የከተማውን ነዋሪ ሕይወት የቀየሩ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
እነዚህን አጠናክሮ ለማስቀጠል የህብረተሰብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አመልክተው፤ በተለይ በከተሞች የምግብ ዋስትናና የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለማቃለል የተቀናጀ ጥረት መደረግ እንዳለበት ገልጸዋል።
በዞኑ ከተረጂነትና ከድህነት በአጭር ጊዜ ለመውጣት እየሰራ ባለው ሥራ 32 ሚሊዮን የእንሰት ችግኝ መተከሉ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ገልፀዋል።
ዘንድሮ ክረምት ለአቅመ ደካሞች ጨምሮ 4 ሺህ 500 ቤቶች ግንባታ ለማከናወን መታቀዱን ጠቅሰው በዚህም ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደግ ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይቱ ላይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ውሃና ማዕድን ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝን ጨምሮ ሌሎች የክልል፣ የጌዴኦ ዞን የወረዳና ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል ።