28/10/2023
የአራትኛ አመቷን ልደት ለማክበር ለልደቷ በተጠመቀ ጠላ በርሜል ዉስጥ የገባችው ታዳጊ ህይወቷ አለፈ!
በካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ ጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ.ም ጎጀብ ቀበሌ ልዩ ስሙ ቁጥር ሁለት ተብሎ በሚጠራበት ከጠዋቱ 4:00 ሰዓት የአራት አመቷ ህፃን ለልደቷ በተጠመቀ በጠላ በርሜል ዉስጥ ገብታ ህይወቷ ማለፋን ተገልፇል።
ም/ኢ/ር መሠረት ገለፃ ወላጆቿ የህፃኗን የአራተኛ አመት ልደት ለማክበር ጠላ መጠመቁን ለልደቷ የሚያስፈልጉ ዝግጆቶች መሠናዳቱን እና እናት ማልዳ ጠላዉን እያጣራች ሳለ ህፃኗ ከመኝታ ተነስታ እናቷ ወደምትሰራበት ቦታ እንደመጣች እና ወንበር ላይ ቆማ ወደ በርሜሉ ዝቅ ብላ እያየች እናት ወጣ ብላ እስክትመለስ ጠላ ዉስጥ ገብታ ህይወቷ እንዳለፈ አስረድተዋል።
አክለዉም በድንጋጤ እናት ብትጣራ ምላሽ በማጣቷ ወደስፍራዉ መጥታ ህፃኗን ከበርሜል ውስጥ ብታወጣትም ህይወቷ እንዳለፈ ፖሊስ ከስፍራዉ የነበሩ እማኞች አረጋግጫለሁ ብሏል።
የልደት ደስታዉ ወደለቅሶና ሀዘን መቀየሩን የጠቀሰዉ ፖሊስ የአራት አመቷ ህፃን ለአራተኛ አመቷን ልደት የተገዛላትን ልብስ ለብሳ፣ ጫማ፣ ሻማ ለኩሳ ከመንደሩ እኩዮቿ ጋር መልካም ልደት ሳትባል፣ ለወዳጅ ዘመድ ጥሪ የተጠመቀዉ ጠላ፣ ዳቦ፣ እንጀራ እና ወጥ ለሀዘንተኛ ማስተዛዘኛ መዋሉን ታዉቋል።
በመጨረሻም ፖሊስ ወላጆች የህፃናትን እንቅስቃሴ መከታተል እንዳለባቸዉ መልዕክቱን አስተላልፏል ሲል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነትና ኮሚንኬሽን ዘገቧል።