19/08/2024
የአማራ ክልል ፖሊስ በህፃን ሄቨን ጉዳይ ያወጣው መግለጫ
| ህፃን ሄቨንን በተመለከተ ፖሊስ የሚጠበቅበትን ተወጥቷል፤ የአማራ ክልል ፖሊስ ቀዳሚ ተልዕኮው ወንጀል መከላከል ነው። በተለይም ልዩ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸውን ህፃናትና አረጋዊያን ከመጠበቅ አልፎ ወንጀል ሲፈፀም መርምሮ ለፍርድ ማቅረብ ቀዳሚ ተግባሩ ነው። ለዚህም የሴቶችን ጉዳይ ብቻ የሚከታተል የስራ ክፍል አቋቁሞ ፍትህ ለተነፈጋቸው በሚችለው ደርሷል።
ከሰሞኑ በልዩ ልዩ ማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች አዲስ ሆኖ ብዙዎቹን ያሳዘነው የህፃን ሄቨን ጉዳይ ለክልሉ ፖሊስ በተለይም ለባህርዳር ከተማ 8ኛ ፖሊስ ጣቢያ ከአመት በፊት ሐምሌ 25/ 2015 ዓ.ም ከረፋዱ 4:00 ሪፖርት ከደረሰን ጀምሮ እስከ ፍርድ ቀን አብሮን የዘለቀ ጉዳይ ነው።
በባሕር ዳር ከተማ ዳግማዊ ሚኒሊክ ክፍለ ከተማ ቆጠጢና አካባቢ የ7 አመት ከ 8 ወር ታዳጊዋ ህጻን ሄቨን ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ድርጊትና ህልፈተ ህይወት መርምሮ ለፍርድ ለማቅረብ ከፍትህ ነጣቂዎች ጋር ታግለን መረጃና መስረጃ አሟልተን ለፍርድ አቅርበናል።
በዚህ ሂደት ለሙያቸው ታምነው ለፍትህ መረጋገጥ የሚችሉትን ለፈፀሙ ፖሊሶቻችን ምስጋና እናቀርባለን።ጉዳዩ ብዙ ሂደቶችን አልፎ ውሳኔ ከተሰጠ በኅላም ልዩ ትኩረት በመስጠት ለህዝብ ተደራሽ እንዲሆን በአማራ ፖሊስ ቴልቨዥን ፕሮግራም በተደጋጋሚ እንዲተላለፍ ተደርጓል።
ከሰሞኑ የህፃኗን ጉዳይ ህብረተሰቡ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መከታተሉ የሚደነቅ ሆኖ አንዳዶች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ተቋማችን ኀላፊነቱን እንዳልተወጣ ይልቁንም የችግሩ አካል አድርገው ለማቅረብ ሲሞክሩ ታዝበናል።
ትችት ለጋራ መሻሻል ጠቃሚ ቢሆንም መርህ አልባ ሲሆን የተግባር እንቅፋት ይሆናል። እንደተቋም ለፍርድ የማቅረብ ተልኳችንን ተወጥተናል ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ከህፃን ሄቨን በተጨማሪ በክልሉ በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ከ92 በላይ አስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ተፈፅመዋል።
የቤት ውስጥ ጥቃቶች በቅርብ ሰውና ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ አዳጋች በሆነበት አግባብ የሚፈፀም በመሆኑ ለፖሊስ የምርመራ አስቸጋሪ ነው።
ስለሆነም ማህበረሰቡ የህፃን ሄቨን ጉዳይ በማህበራዊ ሚዲያ ትኩረት እንደሰጠው ሁሉ ነገ ለሌሎችም የወንጀል ድርጊቶች መረጃና ማስረጃ በመሆን ፍትህን በጋራ እንድናረጋግጥ እንጠይቃለን ።
አማራ ክልል ፖሊስ
ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም
ባህርዳር