14/09/2022
ያለፈው ጉዳት ጉዳይ!
አዲስ ጅማሬ በአዲስ ዓመት!
ባለፈው ዓመት ደጋግሞ የጎዳችሁና ደጋግማችሁ በይቅርታ አልፋችሁት አሁንም እየተጎችሁበት ያለ ሰው ካለ፣ የይቅርታው ልምምድ እንደተጠበቀ ሆኖ በያዝነው ዓመት ምናልባት መማሰተካከል ያለባችሁ አካሄድ ሊኖር እንደሚችል ላስታውሳችሁ፡፡
ከሰዎች ጋር ያለንን አስቸጋሪ ግንኙነት የመያዣው መንገድ ሁለት ነው፡- 1) ሰዎቹን ለመለወጥ መሞከር፤ ወይም 2) ራሳችንንና አደራረጋችን መቀየር፡፡
በዚህች አለም ላይ የሰዎችን አስቸጋሪ ባህሪይ እንደመሸከምም ሆነ ለመለወጥ እንደመሞከር አስቸጋሪ ነገር የለም፡፡ ከዚያ የተሻለው መንገድ ራሳችንንና አያያዛችንን መለወጥ ነው፡፡
ራሳችንንና አደራረጋችንን ለመለወጥ፡-
1. የሰዎቹ ሁኔታ ስሜታችንን እንዳይጎዳው መጠንከርና መታገስ፡- ይህ ሂደት እጅግ አድጋሚና ታላቅ ጥንካሬን የሚጠይቅ ነው፡፡ ሆኖም፣ ከሰዎቹ ጋር ያለን ግንኙነት የጠለቀና በቀላሉ የማንፋታው አይነት ከሆነ የሚመረጥ መንገድ ነው፡፡
2. ከሰዎቹ ጋር ያለንን ግንኙነት ሚዛናዊና በልኩ ማድረግ፡- አንዳንድ ሰዎች ራሳችንን በነጻነት ስናቀርብላቸውና ጠጋ ስንላቸው አያያዙን አይችሉበትም፡፡ ከእንደዚህ አይነት ሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት መጠነኛ፣ እንዲሁም በአስፈላጊው ሁኔታና ጊዜ ላይ ብቻ የተወሰነ እንዲሆን ማድረግ የግድ ነው፡፡
3. ከሰዎቹ መለየት፡- ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት እንደ ትዳር ያለ በቃል-ኪዳን የተሳሰረ ካልሆነና ከእነሱ መለየት የሚያስከትለው ሁኔታ በሚገባ ከታሰበበት (ይቅር የማለትና ልብን ከቂመኝነት የመጠበቁ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ) ከአንዳንድ ሰዎች የመላቀቂያው ቀላሉ መንገድ የሚከፈለው ዋጋ ተከፍሎ ከእነሱ መለየት ነው ።