05/02/2024
የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር የፌዴራል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ጥር 23 /2016 ዓ.ም የሰጠውን መግለጫ አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ አውጥቷል።
በዚህ መግለጫው ፤ ከፕሪቶርያ ስምምነት አፈፃፅም ጋር በተያያዙ በኮሚኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ ላይ የተጠቀሰውና ከትግራይ ሉአላዊ ግዛት መረጋገጥ ጋር በተያያዘ " ጉዳዩን በሪፈረንደም ለመፍታት መረዳዳት ተደርሶ ነበር " በሚል የቀረበው መግለጫ ፍፁም የተሳሳተ ነው ብሏል።
" ጊዚያዊ አሰተዳደሩም ሆነ ፌደራል መንግስቱ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ሕገ መንግስቱን መሰረት በማድረግ ጉዳዩን ለመፍታት ከደረሱበት ስምምነትም ሆነ ካላቸው ስልጣን ውጪ የሆነ ተግባር መሆኑን በተደጋጋሚ ያነሳነው ስለሆነ ተቀባይነት የሌለዉ መሆኑን መግለፅ እንወዳለን። " ሲል አክሏል።
ሌላው ፤ ከተፈናቃዮች መመለስ ጋር ተያይዞ " ትክክለኛ ተፈናቃዮች ተመልሰዋል " በሚል የቀረበው የመግለጫው ክፍል እጅግ አደገኛና በጉልበት የሃገሪቱ ካርታ ለመቀየር የፌዴራል መከላከያ ሆነ የጎረቤት ሃገራትን አቅም ተጠቅሞ የተደረገን አውዳሚ እንቅስቃሴ ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት የሚያግዝ ነው ብሏል።
ከምንም ነገር በላይ ግን " ትክክለኛ ተፈናቃይ " ፤ " ትክክለኛ ያልሆነ ተፈናቃይ " በሚል መፈታት የነበረበትን ችግር የበለጠ የሚያባብስ አደገኛ ትንታኔ ስለሆነ አንቀበለዉም ሲል አሳውቋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው ፤ " አሁንም ከሚልዮን በላይ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃዮች በአስከፊ ሁኔታ የሚኖሩበት፤ ያፈናቀላቸዉ ፀረ ህዝብ እና ሕገ ወጥ አስተዳደሪዎች ፌደራል መንግስቱ ከመንበራቸው ሊያስወግዳቸው ሲገባ አሁንም ሕግ አስከባሪዎች ነን ብለው በሚመፃደቁበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንደዚህ ዓይነት መግለጫ መውጣቱ የፌደራል መንግስቱ የመፍትሄው አካል መሆን ሲገባው የችግሩ አካል ለመሆን የወሰነ የሚያስመሰለው ስለሆነ በፍፁም ተቀባይነት የለውም " ብሏል።
" የፌደራል መንግስቱ ከፕሪቶርያ ስምምነት ወዲህ የወሰናቸው በተለይም ከበጀትና መሰል ጉዳዮች ጋር የተያያዙ አበረታችም ሆኑ መታረም ያለባቸው ጉዳዮች በሚመለከት ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፓርት የሚቀርብ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ የምንለው ነገር አይኖርም " ሲል አሳውቋል።
የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ ፤ ሰላም በሁሉም የትግራይ እና የኢትዮጵያ አከባቢዎች በተሟላ መልኩ የሚረጋገጥበት ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ ከፌደራል መንግስት በመቀራረብ እንደሚሰራ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል።
(ሙሉ መግለጫው ከላይ ተያይዟል)