Ahun Times - አሁን ታይምስ

  • Home
  • Ahun Times - አሁን ታይምስ

Ahun Times - አሁን ታይምስ ታማኝ ፣ ወቅታዊ እና አዝናኝ መረጃዎችን ለማግኘት ወዳጃችን ?
(2)

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣ...
10/12/2023

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሲሆን፣ ኅዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በፍሬንድሺፕ ሆቴል ውይይት በተካሄደበት ወቅት ‹‹ኢትዮጵያዊ ባህልና እሴት እየተሸረሸረ በመሆኑ›› ደንቡ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡

በቢሮው የቱሪዝም አገልግሎት ደረጃ ምደባና አቅም ግንባታ ቡድን መሪ አቶ ዓምደማርያም ማሞ፣ ‹‹ቢሮው በአዋጅ ቁጥር 74/2014 አንቀፅ 22 ቁጥር 6-13 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዙሪያ ኢትዮጵያዊ ባህልና ዕሴት እየተሸረሸረ በመሆኑ የደንብ ረቂቅ አውጥቷል፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ደንብ በካቢኔው ሲፀድቅ በተለያዩ ሆቴሎች፣ ባሮች፣ ሥጋ ቤቶች እንዲሁም መሰል አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ላይ የሚታየው ከኢትዮጵያ ባህልና እሴት ያፈነገጠ የአለባበስ እንዲሁም ጌጣጌጥ አጠቃቀም እንዲስተካከል እንደሚረዳ ጠቁመዋል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) በበኩላቸው ቱሪዝም ዓለም አቀፋዊ ውድድር መሆኑን ገልጸው፣ ሆቴሎች በተቀመጠላቸው ስታንዳርድ መሠረት መሥራት ስለሚገባቸው፣ እንዲሁም በአገሪቱ ወግ፣ ባህልና እሴት መሠረት ማገልገል ስለሚጠበቅባቸው ይህ ደንብና መመሪያ እንዲወጣ ግድ ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል።

‹‹ከዚህ አንፃር በአገራችን የሚገኙ ሆቴሎችና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የግንዛቤ ችግር አለባቸው›› ያሉት ዶ/ር ሒሩት፣ ‹‹እነዚህ ተቋማት ዓለም አቀፍ መደበኛ አሠራር፣ ፕሮቶኮል (ድሬሲንግ ኮድ) ባለመረዳታቸው ልቅ የሆነ ዘመናዊነትን አልፎ ተርፎም የፋሽን ማሳያ እስኪመስሉ ድረስ ተቀይረዋል፤›› ያሉ ሲሆን ይህ ደንብ ፀድቆ ተግባራዊ ሲሆን እነዚህንና የመሳሰሉ ችግሮችን እንደሚቀርፍ እምነታቸውን መሆኑን አመልክተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ‹‹ይህንን ደንብ በማውጣት ሒደት ውስጥ ብዙ ተዋናዮች ተሳትፈውበታል›› ያሉት ኃላፊዋ፣ ከሆቴልና ቱሪዝም ማሠልጠኛ ተቋም አስተማሪዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲሁም የሕግ አካላት እንደተሳተፉበት ጠቅሰዋል።

የቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ሃፍታይ ገብረ እግዚአብሔር ስለ ደንቡ አስፈላጊነት ሲያስረዱ፣ ‹‹በአዲስ አበባ ያሉ ሆቴልና መሰል ተቋማት ወጥ የሆነ ሥርዓት እንዲሰፍን ከማገዙም በላይ፣ ባህልና ወጉን ያልጠበቀ የአለባበስ ሥነ ሥርዓትን በመቆጣጠር ኢትዮጵያዊ አለባበስና መስተንግዶ ሥርዓትን ለማስከበር እንዲሁም ባለሙያዎች የሚደርስባቸው አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጫናን ለማስቀረት ይረዳል›› ሲሉ ተደምጠዋል።

ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎች የተካተቱበት ረቂቅ ደንቡ በቢሮው ቀደም ተብሎ ሊሠራ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ ቶሎ እንዳይወጣና ወደ ሥራ እንዳይገባ ግን የተለያዩ ምክንያቶች ማነቆ እንደነበሩ አቶ ሃፍታይ ጠቅሰው፣ ከእነዚህም ውስጥ በዋነኝነት የአመራሮች መለዋወጥ፣ የግብዓት ማነስና በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች አንድ ላይ ሆነው ትኩረት ሰጥተው አለመሥራታቸው ጉዳዩ እንዲንከባለል አድርጎታል ብለዋል፡፡

‹‹ይህ ደንብ በሚፀድቅ ጊዜ ተቋማት አይተገብሩትም ብዬ አላስብም›› ያሉት አቶ ሃፍታይ፣ ተቋማቱ የዚህ ሕገ ደንብ ደጋፊ እንደሚሆኑ እምነታቸውን ገልጸዋል።

‹‹በወጣው ረቂቅ መሠረት በተዋረድ ከማዕከል እስከ ክፍለ ከተማና ወረዳ ድረስ በባለሙያዎች ክትትልና ቁጥጥር መመሪያው የሚፈጸም ይሆናል፤›› ያሉት ደግሞ አቶ ዓምደማርያም ማሞ፣ የቁጥጥርና ክትትል ሥራ ባለሙያዎች የመንግሥት የሥራ ሰዓትን መሠረት በማድረግ በክትትል የሚያረጋግጡ ሲሆን፣ የተለየ ጥቆማ ከደረሰ ግን ቢሮው ባልተጠበቀ ሰዓት በመፈተሽ እርምጃ መውሰድ እንደሚችል ጠቅሰዋል።

አክለውም በክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት መሠረት ደንቡን ጥሶ የተገኘ አካል በደንቡ መሠረት የሚጠየቅ ሲሆን፣ የቃልና የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ከተሰጠው በኋላ ከሌሎች የፍትሕ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ቅጣቱ እስከመታሸግ ሊደርስ እንደሚችል ገልጸው፣ በዚህ አካሄድ አቤቱታ ያለው ተቋም ወይም ወገን በፍትሐብሔር ሕግ መሠረት አቤቱታውን የማቅረብ መብት እንዳለውም ጠቁመዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቢሮው በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ያወጣውን ደንብ ከፍትሕ ተቋማት ጋር ሙሉ በሙሉ የማስፈጸም መብት እንዳለው አስገንዝበዋል።

በደንቡ ከተጠቃለሉት ውስጥ አንዱ ክፍል የሆነው የቅጣት አሰጣጥ ሁኔታን የሚደነግግ ሲሆን ይህም ደረጃ ሀ፣ለ፣ሐ በመባል ተከፍሏል።

ደረጃ ‹ሀ› አሥር ለቅጣት የሚዳርጉ ድርጊቶችን የሚገልፅ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ የደረት ክፍልን ያልሸፈነ/ች፣ ከአንገት በታች የሚሸፍን ሸሚዝ ያለበሰ/ች፣ ሴቶች ጉርድ ቀሚስ ከለበሱ ቁመትና ቅዱ ከጉልበት በታች ካልሆነ፣ ወንድ ጆሮ ጌጥ ካደረገና የመሳሰሉት ድርጊቶች በዚህ ቅጣት ደረጃ ተጠቃለዋል።

ደረጃ ‹ለ› አራ ስድስት ለቅጣት የሚዳርጉ ድርጊቶችን የሚገልፅ ሲሆን፣ ከነሱም መሀል የወንድ ባለሙያ ፀጉሩን በአጭሩ ያልተቆረጠና ያላበጠረ፣ ፂሙን ያልተቆረጠ፣ የአንገት ሀብል ያልሸፈነ/ች፣ ከጋብቻ ቀለበት ውጪሌላ ቀለበት ያደረገ/ች እና የመሳሰሉት በዚህ ቅጣት ደረጃ ተጠቃለዋል።

ደረጃ ‘ሐ’ ሁለት ለቅጣት የሚዳርጉ ድርጊቶች የተቀመጡበት ሲሆን፣ እነዚህም ወንድ በጆሮው ፊት ለፊት ያለው ፂም ከጆሮው እኩሌታ ካለፈና የገነነ ሽታ ያለው ሽቶ፣ ሎሽን፣ ዶድራንት የተጠቀመ በዚህ ቅጣት ደረጃ ተጠቃለዋል።

ደንቡ ከፀደቀ በኋላ የተጠቀሱትን ክልክል ድርጊቶች ሲያደርግ ተገኝቶ እነዚህን ነገሮች በቁጥጥር ባለሙያዎች እንዲያስተካክል ታዞ፣ በአሥራ አምስት ቀን ሳያስተካክል የተገኘ ተቋም፣ ሃምሳ ሺሕ ብር ቅጣት ያለው ሲሆን፣ ያጠፋው ግለሰብም አንድ ሺ ብር ያስቀጣዋል።

ይህንንም ክፍያ እንዲከፍሉ ከታዘዙበት ቀን ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ካልከፈሉ ድርጀቱ እንደሚታሸግ ደንቡ ይደነግጋል፡፡

በውይይቱ ላይ የቢሮው የቱሪዝም ባለሙያዎች፣ የኢትዮጵያ መስተንግዶ ማኅበር፣ የአዲስ አበባ ሆቴሎችና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማኅበር፣ የቱሪዝም ማሠልጠኛ ተቋምና የአዲስ አበባ ሆቴሎች ሥራ አስኪያጅ ማኅበር አባላት ተገኝተዋል፡፡ ተሳታፊዎቹም ‹‹በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዙሪያ ከከተማችን ማኅበረሰብ የተለያዩ ጥያቄዎች ሲነሱ ስለነበር ደንብና መመሪያው አስፈላጊ ነው፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን ገልጸዋል።
ሪፖርተር ጋዜጣ

በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለው የኮንትሮባንድ ተሳትፎ ጥብቅ መፍትሔ ይፈልጋል ተባለበሶማሌ ክልል በሁሉም ደረጃ በሶማሌ ክልል በሁሉም ደረጃ ያሉ የመንግሥት መዋቅሮች በኮንትሮባንድ የሚያደርጉት...
10/12/2023

በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለው የኮንትሮባንድ ተሳትፎ ጥብቅ መፍትሔ ይፈልጋል ተባለ

በሶማሌ ክልል በሁሉም ደረጃ በሶማሌ ክልል በሁሉም ደረጃ ያሉ የመንግሥት መዋቅሮች በኮንትሮባንድ የሚያደርጉት ተሳትፎ፣ ጥብቅ የሆነ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በተጠቀሰው አራት ወራት ጊዜ ውስጥ የተሰጠው የቀረጥ ነፃ ተጠቃሚነት ዕድል 30 ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የአንድ ቢሊዮን ብር ቅናሽ ታይቶበታል ብለዋል፡፡

በተጠቀሰው ጊዜ 321 የቀረጥ ነፃ አገልግሎት ተጠቃሚ ከነበሩ አካላት መካከል 278 ብቻ ሲጠቀሙ፣ ከቀሪዎች መካከል ደግሞ 42 ከታለመላቸው ዓላማ ውጪ መጠቀማቸው መረጃ በመገኘቱ ተጣርቶ ዕርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡ ወደ አገር ውስጥ ከገቡ 1231 የቱሪስት ተሽከርካሪዎች ውስጥ አገልግሎታቸውን ያጠናቀቁ ለታለመላቸው ዓላማ መዋላቸው ተረጋግጦ 250ዎች ወደ መጡበት አገር መመለሳቸው ተገልጿል፡፡

ሚኒስትሯ ባለፉት አራት ወራት ብቻ የነበረው የሠራተኛ ፍልሰት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ 57 ሠራተኞች መልቀቃቸውን አስረድተዋል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው የፋይናንስ ተቋማት እየበዙ መሆናቸውና የግሉ ዘርፈ የመቅጠር አቅም እያደገ መሄድ ሠራተኞችን እያስኮበለለ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በጹሑፍ ባቀረበው ጥያቄ በወጪ ንግድ አፈጻጸም በተለይ በሕጋዊ መንገድ የሚለካው መጠን እየቀነሰ በሕገወጥ መንገድ ለመላክ የሚደረገው ጥረት እየጨመረ ስለመሆኑ አንስቶ፣ ይህንን ሕገወጥ ንግድ መቆጣጠርና ከመሠረቱ ለምን መፍታት አልተቻለም ሲል ጠይቋል፡፡ የጉምሩክ ኮሚሽኑ በአራት ወራት ውስጥ ከመደበኛ ገቢ ዕቃዎች ፍተሻ ብቻ 29 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉን የጉምሩከ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

የሰማዕቱ ሊቀ ጳጳስ የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ፊልም ጽሑፍ በሊቃውንት ጉባኤ እንዲመረመር ታዘዘ👉 በሲነርጂ ሀበሻ ፊልምና ኮሚኒኬሽን ሃላፊ ይቅርታ ጠይቀዋልየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስ...
09/12/2023

የሰማዕቱ ሊቀ ጳጳስ የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ፊልም ጽሑፍ በሊቃውንት ጉባኤ እንዲመረመር ታዘዘ

👉 በሲነርጂ ሀበሻ ፊልምና ኮሚኒኬሽን ሃላፊ ይቅርታ ጠይቀዋል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ሲነርጂ ፊልምና ኮሚኒኬሽን በኢትዮጵያዊው ሰማዕት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳስ የስማዕትነት ተጋድሎ ዙሪያ የሚያጠነጥን ፊልም ለመስራት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ታሪክን የሚያጎድፍ ሆኖ ስለተገኘ ሊቆም እንደሚገባ በመግለጽ ኅዳር 25 ቀን 2016ዓ.ም በቁጥር 1673/2789/2016 በተጻፈ ደብዳቤ መግለጹ ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎ የፊልሙ ጸሐፊ እና ዳይሬክተር ሞገስ ታፈሰ ዶ/ር 'እየተዘጋጀ የሚገኘውን ፊልም ቤተክርስቲያናችን በሊቃውንቶቿ አማካኝነት መርምራ፣ የሚታረም ካለ አርማና የሚቃናውን አቅንታ በምትሰጠን አስተያየትና ማስተካከያ መሠረት ፊልሙን የምንሠራ መሆኑ ታውቆ አስፈላጊው ትብብር ሁሉ ይደረግልን' በማለት በጽሑፍና በአካል ጠቅላይ ቤተ ክህነት በመገኘት በፊልሙ ዝግጅት ዙሪያ ማብራሪያ በመስጠት ለተፈጠረው የመረጃ ክፍተት ይቅርታ ጠይቀዋል።

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስም ዶ/ርሞገስ ታፈሰ ያቀረቡትን ይቅርታ በመቀበል በአካልና በጽሑፍ በፊልሙ ጽሑፍ ዝግጅት ዙሪያ መረጃ ከመስጠት ባለፈ በቤተ ክርስቲያናችን በኩል የፊልሙ ጽሑፍ እንዲመረመርላቸውና እርማት በሚያስፈልገው ጉዳይ ዙሪያ እርማት እንዲደረግበት መጠየቃቸው የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ማህበረ ቅዱሳን ቴቪ

የአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል  ታካሚዎች ቁጥር ጨምሯል!የስነ ልቦና ታካሚዎች ቁጥር መጨመሩን  የአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስታውቋል።የሆስፒታሉ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬ...
08/12/2023

የአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ታካሚዎች ቁጥር ጨምሯል!

የስነ ልቦና ታካሚዎች ቁጥር መጨመሩን የአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስታውቋል።
የሆስፒታሉ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አብዩ የኔአለም ለትርታ እንደገለጹት፡ ባለፉት ሶስት ወራት የተመዘገበው የስነ ልቦና ታካሚዎች ቁጥር ሆስፒታሉ ከያዘው እቅድ በላይ ነው።

ሆስፒታሉ ባለፉት በሶስት ወራት 400 ታካሚዎችን ለማስተናገድ አቅዶ፣ 833 ታካሚዎች አገልግሎቱን ማግኘታቸውን ነው ያስታወቁት። በኢትዮጲያ ባለው ነባራዊ የፖለቲካ ውጥረት፣ የኑሮ ውድነት፣ የሰላም እጦት እና በሌሎችም ገፊ ምክንያቶች ሳቢያ ታካሚዎች የስነ ልቦና ህክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ተቋሙ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

የዘንድሮው የህክምና አፈጸጸም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም ከፍተኛ የአሀዝ ልዩነት እንዳለው ነው ያስታወሱት። በ2015 በጀት ዓመት በሩብ ዓመቱ ለ875 ታካሚዎች ህክምና ለመስጠት ታቅዶ አገልግሎት ለማግኘት የመጡ ታካሚዎች ብዛት 726 እንደሆነና ይህም 83% በመቶ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሰላማዊ የዕለት ተለት ህይወትን መምራት የሚችሉበት ሁኔታ ካልተፈጠረ፣ የስነ ልቦና ጉዳት የሚገጥማቸው ዜጎች ቁጥር መጨመሩ የማይቀር እንደሆነ ነው የአማኑኤል ሆስፒታል የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አብዩ የኔአለም ለትርታ የተናገሩት።

ትርታ 97.6 FM

“የዳሬሰላሙ ድርድር እንዳይሳካ ያደረገው መንግሥት ነው ብዬ አምናለሁ” - አቶ ታዬ ደንደአየኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት አቶ ታዬ ደንደአ በኦሮሞ ፖለቲካ እና በኢትዮጵያ...
07/12/2023

“የዳሬሰላሙ ድርድር እንዳይሳካ ያደረገው መንግሥት ነው ብዬ አምናለሁ” - አቶ ታዬ ደንደአ

የኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት አቶ ታዬ ደንደአ በኦሮሞ ፖለቲካ እና በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሃሳባቸውን እና አቋማቸውን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በማጋራት ይታወቃሉ።

የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ) አባል የሆኑት አቶ ታዬ፣ አገሪቷን በሚያስተዳድረው የብልጽግና ፓርቲ ውስጥ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው ያገለግላሉ።

በአጠቃላዩ በኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እየተከሰቱ እና አሁንም ባሉ ችግሮች ዙሪያ እራሳቸው አባል የሆኑበትን መንግሥት ይወቅሳሉ።

ከአምስት ዓመት በፊት የተገባውን ቃል፣ ኦሮሚያ ውስጥ ባለው ጉዳይ፣ በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል በነበረው ድርድር እና ቤተሰባቸው ላይ በደረሰው ጉዳት እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በኦሮሚያ ስላለው ሁኔታ

በ2010 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ውስጥ በመጣው የፖለቲካ ለውጥ ኦሮሞ ወደ ከፍተኛው የፖለቲካ ሥልጣን መጣ። ያኔ ብልጽግና እና ዲሞክራሲ ይመጣል ተብሎ ተስፋ ተደርጎ ነበር ይላሉ አቶ ታዬ ደንደአ።
“ትልቅ ደስታ ነበር የተፈጠረው። ሰው ተስፋ ያደረገው ለ150 ዓመታት የነበረው ችግር ተዘግቶ ዲሞክራሲ ይመጣል፣ የሚል ነበር። የሕዝብ ጥያቄ የሆኑት የቋንቋ፣ የምጣኔ ሃብት እና ሌሎች ትልልቅ ጉዳዮች ተቆጥረው ይመለሳሉ ተብሎ ተስፋ ተደርጎ ነበር” ይላሉ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ታዬ ደንደአ።

ሕዝብ ሰላም እንደሚያገኝ፣ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ፣ ሰው በጋራ ሠርቶ እድገት ይመጣል ተብሎ እንዲሁም ፖለቲካችን ይሰለጥናል የሚል የብዙ ሰዎች ተስፋ ነበር ይላሉ።

“ኦሮሞ እርስ በእርሱ ተነጋግሮ ችግሩን ይፈታል፣ ከብሔር ብሔረሰቦች ጋርም በሰላም ይኖራል የሚል ትልቅ ተስፋ ነበር። የፖለቲካ ምኅዳሩም መጀመሪያ አካባቢ ክፍት ነበር። የሰው ተስፋም ትልቅ ነበር። የሕዝብ ተነሳሽነትም ትልቅ ነበር” በማለት በለውጡ ወቅት የነበረውን ያስታውሳሉ።

ይህ ለውጥ እንዲመጣ፣ ሌሎች የሕዝብ ክፍሎች የሕይወት መስዋዕትነት ሲከፍሉ ሌሎች ደግሞ በሚችሉት ሁሉ አስተዋጽኦ ያደርጉ ነበር የሚሉት አቶ ታዬ፣ ከዚያ በኋላ እንዴት ወደፊት እንሄዳለን የሚል ዕቅድ ባለመኖሩ፣ አሁን ያለው ችግር መፈጠሩን ያነሳሉ።

“ለውጡ ከመጣ በኋላ ሰው ወደ ጥቅም እና ሥልጣን ማጋደል ጀመረ። እርስ በእርስ መጠላለፍ መጣ። ወደ ቀኝ እና ወደ ግራ መሳሳብ መጣ። ሌላው ቀርቶ በኦዲፒ ውስጥ ተመካክሮ በአንድ አጀንዳ ላይ አብሮ መሥራት ራሱ አልተቻለም ነበር” ይላሉ።

በፓርቲያቸው ውስጥ መመካከር ከቀረ በኋላ የኦሮሞ ፖለቲካ አንድ ከመሆን ወደ መበታተን አመራ። በኦሮሞ ፖለቲካ ሜዳ ውስጥ በተፈጠረው ግራ መጋባት፣ ሌሎች ወደ ጫካ እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ የሕዝቡ ሰቆቃ በማምታታት ሥልጣናቸውን ማራዘም ለሚፈልጉት ትልቅ ዕድል ፈጠረላቸው ሲሉ ይከሳሉ።

ማዕከሉን ተቆጣጥሮ በሕዝብ ሰቆቃ ይነግዳል የሚሉትን አካል አቶ ታዬ በስም አልጠቀሱም።
ከለውጥ በኋላ የኦሮሞን ትግል በትክክል እና መጀመሪያ ቃል በተገባው መንገድ ሥራ ላይ አለመዋሉ ኦሮሞ በ150 ዓመት ውስጥ አይቶ በማያውቀው መከራ ውስጥ አድርጎታል የሚሉት አቶ ታዬ “በ150 ዓመት ውስጥ በትግል ከተሰዉት ይልቅ፣ ከአሸነፈ በኋላ መልሶ በኪሳራ ሰቆቃ ውስጥ ገባ።”

ላጋጠመው ችግር ተጠያቂ ማን ነው?

ለተፈጠረው ችግር ከዚህ ቀደም በተለያየ መንገድ በኦሮሞ ትግል ውስጥ የተሳተፉት ተጠያቂ እንደሚሆኑ የሚጠቅሱት አቶ ታዬ ራሳቸውም ቢሆን ዝግጁ መሆናቸውን ይናገራሉ።

“መንግሥት ትልቅ ተጠያቂነት አለበት። የፖለቲካ ሜዳው ምቹ እንዲሆን፣ ሕዝብ ወደ ዲሞክራሲ እንዲሻገር ማድረግ የመንግሥት ግዴታ ነበር። መንግሥት ውስጥ የነበሩ ደግሞ ውይይትን አልመረጡም” ይላሉ።

አቶ ታዬ እንደሚሉት አሁን በኦሮሚያ እና በአገሪቷ የተከሰቱ ችግሮች ከዚህ በፊት በ2011 ዓ.ም. በድርጅት ጉባዔ ላይ እንደሚከሰቱ ተናግረው ሰሚ ማጣታቸውን ያስታውሳሉ።

“በ2011 ምሁራን ጋር ባደረግነው ውይይት አራት ትልልቅ ችግሮች እንደሚከሰቱ ተናግሬ ነበር። የመጀመሪያው የሰላም እና የደኅንነት እጦት ሊከሰት እንደሚችል፣ የምጣኔ ሃብት መናጋት፣ የአስተዳደር እና ዲፕሎማሲ ውድቀት እንደሚከሰቱ ተናግሬ ነበር” በማለት መንግሥት ቀድሞ መዘጋጀት እንዳለበት ተናግረው እንደነበር ያስታውሳሉ።

አሁን ላይ ሆነው ወደ ኋላ ሲመለከቱ እርሳቸው ከጠቀሱት ችግሮች ውስጥ ሦስቱ በተጨባጭ ተከስተው ችግር እየተፈጠረ መሆኑን ያነሳሉ።
እነዚህ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት አስቀድሞ መሥራት ባለመቻሉ፣ አገሪቷን የሰብዓዊ እና የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲሁም ድቀት ማስከተሉን በማስታወስ፣ በትግራይ ጦርነት ብቻ የ28 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ መድረሱን ይናገራሉ።

የመረብ ቀይ አፈር(በእውቀቱ ስዩም)ተስፋየ ገብረአብ ገና በጉብዝና ዘመኑ ለደራሲ ብርሀኑ ዘሪሁን አራት ገጽ ያለው ደብዳቤ ልኮ ነበር፤ ከደብዳቤው ቀንጭቤ ማብራሪያ ብጤ አስከትላለሁ፤“ ለክቡር...
06/12/2023

የመረብ ቀይ አፈር
(በእውቀቱ ስዩም)

ተስፋየ ገብረአብ ገና በጉብዝና ዘመኑ ለደራሲ ብርሀኑ ዘሪሁን አራት ገጽ ያለው ደብዳቤ ልኮ ነበር፤ ከደብዳቤው ቀንጭቤ ማብራሪያ ብጤ አስከትላለሁ፤

“ ለክቡር አቶ ብርሀኑ ዘሪሁን
መጀመርያ ሰላምታየን አቀርባለሁ፤ ይህንን ደብዳቤ የምጽፍልዎት ማንም ሰው የማያውቀኝ፥ ስሆን፥ እርስዎም ስለ አኔ ምንም ነገር ሰምተው አያውቁም፤ ፥ እኔ ግን የእርስዎንና የአቶ በአሉ ግርማን ፥ የአቶ ሀዲስ አለማየሁን እንዲሁም የሌሎችን ደራስያን የስነጽሁፍ ስመለከት አውቅዎታለሁ፤በጋዜጣም ስለ እርስዎ አንብቢያለሁ፤ …በአሁኑ ሰአት የምኖረው ደብረዘይት ውስጥ ነው፤ በኤርትራ ክፍለሀገር አረዛ በምትባል ፥መረብ ወንዝ ዳርቻ ከተቆረቆረች መንደር መወለዴን እናቴ ከመሞቷ በፊት ትነግረኝ ነበር፤ በሕጻንነቴም ብዙ ታሪክ ማንበብ እና መስማት እወድ ነበር፤ በ1974 አጋማሽ ላይ ፥ እናቴ ከሞተች በሁዋላም ፥ አባቴ ሌላ ሚስት አግብቶ ሁለተኛ ትዳሩን ተያያዘው፤ የአንድ ድርጅት ዘበኛ ነበር፤ የነበርነውን ልጆችም በታተነን ፤ እኔም እዛው ደብረዘይት ውስጥ ካንድ ዘመድ ተጠጋሁ፤ ነገሩን ልቁረጠውና ለወሬ የማይመች በደል ደረሰብኝ፤ በደል ስል በልብስ ወይም በምግብ እጦት አልነበረም፤ የሞራል ውድቀት ነበር፤ ይኸውም ከምኖርባቸው ሰዎች ጋራ ትምህርት እስክጨርስ ለመኖር ስል አይኮኑ አኩዋሁን እሆን ነበር፤ የሱ ልጆች አሽከር መሆኔን ማመን ነበረብኝ፤ባስለፈለጋቸው ጊዜና ሰአትም ከህጻን እሰከ ትልቅ ይልኩኛል፤ ለመኖር ስል የግድ ያሉኝን መፈጸም ነበረብኝ፤”
በደብዳቤው እንደተገለጸው ተስፋየ “ ኤርትራ ውስጥ አረዛ በምትባል መንደር እንደተወለደ ይናገራል፤ በገዜው ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል( ክፍለሀገር) ነበረች፤ ተስፋየ በጊዜው ደራሲ የመሆን ፍላጎቱን ለማሳካት እንዲያግዙት ሀዲስ አለማየሁንና ብርሁኑ ዘሪሁንን ደጅ ጠንቶ ነበር፤ ሁለቱም ልዩ መብት( ፕሪቪለሌጅ) ሰጥተው ቢያግዙትም ሁኔታዎች ፈቅደው ስራዎቹ አልታተሙለትም፤ የማትሪክ ውጤት ገገመበት፤ የመጨረሻው አማራጭ ወታደር መሆን ነበር፤ ግን ተስፋየ የመዋጋት ፍላጎት አልነበረውም፤ ሲጀመር ደመወዝ እና የጽሁፍ ሀሳብ ለማግኘት እንጂ ለመስዋእትነት አልዘመተም፤ እንደ አዲስ አድማስ ዘገባ፥ በተሳተፈበት የመጀመርያ ጦርነት በበረደ ጥይት እጁ ላይ ቆስሎ ተማረከ፤

እነ መለስ ዜናዊ ምርኮኛቸውን ተንከባከቡት’ ተሰጥአውን አይተው የፕሮፖጋንዳ ስልጠና ሰጡት፤ የመንግስቱ ሀይለማርያምን መንግስት ከገረሰሱ በሁዋላ ለተስፋየ ትከሻውን የማይመጥን ትልቅ ሹመት አሸከሙት፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ መምርያ ሀላፊ ሆነ፤ በሰማንያዎቹ አጋማሽ፥ ኢህአዴግ እና ሻእቢያ ኢትዮጵያን እንደ ሽልጦ ተካፍለው፤ አልፎ አልፎ በትብብር አልፎ አልፎም በፉክክር እያስተዳደሩ ነበር፤ ኤርትራ ከክፍለሀገርነት ወደ ጎረቤት አገርነት ተሸጋግራለች፤ በጊዜው አንድ የኤርትራ ተወላጅ የሆነ ታጋይ የኢትዮጵያ ልሳን በሆነው መስርያ ቤት ላይ አዛዥ ሆነ ቢባል ምላሹ ቀላል አይሆንም፤ ተስፋየ በተለይ ከኢትዮጵያ ብሄርተኞች ሊሰነዘር የሚችለውን ትችት ለመሸወድ ይመስላል መነሻውን ፥ ከመረብ ወንዝ ዳርቻ አራቀ፤ ጽሁፎቹ ላይ እና ቃለመጠይቆቹ ላይ እትብቱ ቢሾፉቱ ላይ እንደተቀበረ አድርጎ ማስተዋወቅ ጀመረ፤ ታዋቂ ከሆነ በሁዋላ፥ በማስታወሻዎቹ ላይ ስለ ልጅነቱ የብሾፍቱ የሚተርከው ያሸበረቀ ትዝታ ለብርሀኑ ዘሪሁን ከተናዘዘው “ የሞራል ውድቀት “ እጅግ የተለየ ነበር፤

ተስፋየ የጽሁፍ ተሰጥኦ የታደለ ሰው ነበር፤ የሚጥሙ አጫጭር ልቦለዶቹን ጽፉዋል፤ ለወጣት ደራሲያን ቸርና አበረታች እንደነበር አውቃለሁ፤ በዋናናት የፕሮፖጋንዳ ሰው ነበር ፤ ታሪክ ላይ ከፍተኛ ዝንባሌ ነበረው፤ ይሁን እንጂ የታሪክ አጠናን አተራክ ሀ ሁ የሚያውቅ አይመስልም፤ ስለ ተነባቢነት የሚጨነቀውን ያክል ስለ እውነት ደንታ የነበረው አይመስለኝም፤ ማጋነን ሁለተኛ ባህሪው ነበር፤ የሚወደውን በጣም ያደንቃል የሚደብረውን እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ አድርጎ ያዋርዳል፤

የፖለቲካ ዝንባሌው ሰርነቀል የኤርትራ ብሄርተኛ ነበር፤ በተለይ በመጨረሻዎቹ አራት መጽሀፍቶቹ ውስጥ ያቀረባቸው ወጎች በኢትዮጵያና በኤርትራ ግኑኘትን ታሪክ የሚከልሱና የሚበርዙ ናቸው፤ (ጥቂት ምሳሌዎችን ይዤ እመለሳለሁ)

የኢትዮጵያ አጼ- ግዛት መስራቾች አያሌ ድክመቶች እንደበሩባቸው አያጠራጥርም፤ ይሁን ተስፋየና መሰሎቹ ሊረዱት የማይፈልጉት ወይም ሊረዱት የማይችሉት ብዙ አስደናቂ ሰበአዊ እሴቶች ገንብተዋል፤ ሌላው ቢቀር የሱን ቤተሰብ ጨምሮ ማንም ኢትዮጵያዊ በመረጠው ስፍራ ተዘዋውሮ፥ ሰርቶ ፥ ቤትና ንብረት አፍርቶ እንዲኖር የሚያደርግ አስተማማኝ ስርአት መዘርጋት ችለዋል፤ በቢሾፍቱና በመረብ መካከል ገደል እንዳይኖር ታግለዋል፤

(ይቀጥላል)

ለሲነርጂ ሀበሻ ፊልምና ኮሚኒኬሽን በመዘጋጀት ላይ የሚገኘው የሰማዕቱን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ አኩሪ ታሪክ የሚያጎድፍ ፊልም ቀረጻ እንዲቆም ተጠየቀ ሲነርጂ ፊልምና ኮሚኒኬሽን በኢትዮ...
06/12/2023

ለሲነርጂ ሀበሻ ፊልምና ኮሚኒኬሽን በመዘጋጀት ላይ የሚገኘው የሰማዕቱን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ አኩሪ ታሪክ የሚያጎድፍ ፊልም ቀረጻ እንዲቆም ተጠየቀ

ሲነርጂ ፊልምና ኮሚኒኬሽን በኢትዮጵያዊው ሰማዕት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳስ የስማዕትነት ተጋድሎ ላይ የሚያጠነጥን ፊልም ለመሥራት ቀረጻ ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች በተገኘው መረጃ እና ከፊልሙ እስክሪፕት ቅጅ ለመረዳት የቻለው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ለተቋሙ በጻፈው ደብዳቤ ስክሪፕቱን "እንኳን እኛ የታሪክ ባለቤቶች ይቅርና ሰማዕቱን በግፍ ረሽኖ የገደላቸው የጠላት የኢጣሊያን ወራሪ ኃይል ሊናገረው ቀርቶ ሊሰማው የማይችልን የሐሰት ታሪክ በመፍጠር የሰማዕቱን ሊቀ ጳጳስ አባት አኩሪ ታሪክ የሚያጎድፍ ብሎም የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር የሚነካ ጽሑፍ ሆኖ አግኝተነዋል" ብሏል።

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እንዲህ አይነቱ ታሪክን የሚያጎድፍ እና ከቤተ ክርስቲያናችንም አልፎ የመላ ኢትዮጵያውያንን ሥነ ልቦና የሚጎዳ የፊልም ቀረጻ ሥራችሁን እንድታቆሙ እና በቀጣይም በቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶችና ታሪክ ዙሪያ ማንኛውንም አይነት ፈልምና ቀረጻ ከማከናወናችሁ በፊት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ ፈቃድ የመጠየቅ ግዴታ ያለባችሁ መሆኑን እየገለጽን ከዚህ ውጭ በራሳችሁ የሐስት ትርክት ፍላጎት ብቻ በመነሳሳት የቤተ ክርስቲያናችንን ታሪክ እናበላሻለን የምትሉ ከሆነ ግን በምትፈጽሙት ሕገ-ወጥ አድራጎት በሕግ ለመጠየቅ የምንገደድ መሆኑን እናሳውቃለን ሲል ተቋሙን አስጠንቅቋል።

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በዚሁ ደብዳቤው መንግስታዊ የፀጥታ አካላትም ደርጅቱ እያከናወነ ያለውን የቤተ ክርስቲያኒቱን አባቶች ታሪክ የማዛባት ሕገ-ውጥ እንቅስቃሴ ተከታትለው በማስቆም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስቧል።

(ተዋህዶ ሚዲያ ማዕከል)

የፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት የፖለቲካ ውይይት ለማድረግ መስማማታቸው ተገለጸየፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የፖለ...
06/12/2023

የፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት የፖለቲካ ውይይት ለማድረግ መስማማታቸው ተገለጸ

የፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ውይይት ከሁለት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ለማድረግ መስማማታቸውን፣ የአፍረካ ኅብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት አስታወቀ።

ሁለቱ ወገኖች ይህንን ስምምነት ያደረጉት በአፍሪካ ኅብረት የተቋቋመው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የአፈጻጸም ክትትል፣ ማረጋገጥና ተገዢነት ሥርዓት (MVCM) የጋራ ኮሚቴ ስብሰባ በተካሄደበት ወቅት መሆኑን መገልጫው አመልክቷል።

የጋራ ኮሚቴው ውይይት ባለፈው ዓርብ ኅዳር 21 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን፣ በወቅቱም ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት፣ የፖለቲካ ውይይት መጀመር አስፈላጊ መሆኑን ሁለቱ ወገኖች እንዳረጋገጡና ለዚህም ቁርጠኝነታቸውን እንደገለጹ መግለጫው ጠቁሟል። ከዚህ በተጨማሪም፣ ስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ ሐሳባቸውን የሚገልጹበት የውይይት መድረክ የአፍሪካ ኅብረትን የከፍተኛ ደረጃ ፓነል ባሳተፈ መልኩ ለመጥራት መስማማታቸውን አስታውቋል። ይህንን ውይይትም በተቻለ ፍጥነት ቢበዛ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ለማካሄድ ተግባብተው መወሰናቸውን መግለጫው አስታውቋል።

የጋራ ኮሚቴው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የአፈጻጸም ሒደት፣ ተግዳሮቶችና ዕድሎች ላይ መወያየቱን የጠቆመው መግለጫው፣ ሁለቱም ወገኖች የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን፣ ትጥቅ የማስፈታትና የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራን እንዲሁም በነበረው ጦርነት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉትን የመመለስና መልሶ የማቋቋም ተግባርን ማፋጠን እንደሚያስፈልግ መግባባታቸውንና ለዚህም ቁርጠኝነታቸውን እንዳረጋገጡ መግለጫው አመልክቷል።

በአፍሪካ ኅብረት የተቋቋመው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የአፈጻጸም ክትትል፣ ማረጋገጥና ተገዢነት ሥርዓት Monitoring Verification and compliance Mechanion (MVCM) የሥራ ዘመንም ለተጨማሪ አንድ ዓመት እስከ ዲሴምበር 2024 እንዲራዘም መወሰኑን የኅብረቱ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት በመግለጫው አስታውቋል።

ከሕወሓትና ከፌዴራል መንግሥት ተወካዮች በተጨማሪ፣ የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ደረጃ ፓነል ተወካዮች ማለትም ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ፣ ኡሁሩ ኬንያታ የቀድሞ የኬንያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ደረጃ ፓነል አባል እንዲሁም ፑምዚሌ ንጉካ (ዶ/ር)፣ የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ደረጃ ፓነልና አምባሳደር ባንኮሌ አዴዮሌ፣ የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ፀጥታ ኮሚሽነር ውይይቱን መታደማቸው ታውቋል።

ለተራዘመው ስምምነቱ አፈጻጸም ክትትል፣ ማረጋገጥና ተገዢነት ሥርዓት የሥራ ዘመን ከአፍሪካ ኅብረት የሰላም ፈንድ አንድ ሚሊዮን ዶላር እንዲለቀቅ ተፈቅዷል፡፡

በምሥራቅ አርሲ ሮቤ የኅዳር ጽዮንን በዓል አክብረው በተመለሱ ሦስት ኦርቶዶክስ ምዕመናን ተገደሉበምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት በሮቤ ወረዳ ቤተ ክህነት  ወልተኢ  ቀበሌ ገበሬ ማኅበር በደብረ ...
02/12/2023

በምሥራቅ አርሲ ሮቤ የኅዳር ጽዮንን በዓል አክብረው በተመለሱ ሦስት ኦርቶዶክስ ምዕመናን ተገደሉ

በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት በሮቤ ወረዳ ቤተ ክህነት ወልተኢ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር በደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም የኅዳር ጽዮንን በዓል አክብረው በሚመለሱ ሦስት ምዕመናን ላይ ግድያ መፈጸሙን ሀገረ ስብከቱ ለጣቢያችን መረጃውን አድርሶናል።

ግድያው የተፈጸመው ትናንት ኅዳር 21/2016 ዓ/ም ከክብረ በዓሉ ፍጻሜ በኋላ ምሽት 12:00 ሰዓት አካባቢ መሆኑም ተገልጿል።

በግፍ ከተገደሉት ኦርቶዶክሳውያን መካከል አባትና ልጅ የሚገኙበት ሲሆን ስማቸውም
1.አቶ ቃኛው ይልማ
2.አቶ ሙላቱ ቱሉ
3.አቶ ጌቲ ሙላት (የአቶ ሙላቱ ልጅ) የሚባሉ ሲሆኑ በምሥራቅ አርሲ ዞን በሮቤ ወረዳ ወልተኢ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነዋሪዎች የነበሩ ናቸውም ተብሏል።

ሀገረ ስብከቱ የመከራውን ግፍና ኦርቶዶክሳውያን ላይ ያነጣጠሩ ግድያዎች እንዲቆሙ በተደጋጋሚ ለመንግሥት የጸጥታ አካላት እያሳወቀ ቢሆንም እስካሁን ግን ምንም ሊሻሻል አለመቻሉንም ለጣቢያችን ጨምሮ ገልጿል።

በቅርብ ወራት ወስጥ በምሥርቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ሥር በዴራ አማኑኤል የካህናት ግድያ ፣ ባሳለፍነው ሳምንት ከ ኅዳር 14_17/2016 ዓ/ም በሦስት ቀናት ውስጥ በተለያዩ ቀበሌዎች 36 ኦርቶዶክሳውያን የተገደሉ ሲሆን ከነዚህም ከአንድ ቤተሰብ ብቻ 8 ኦርቶዶክሳውያን በጅምላ መገደላቸውን የሚታወስ ነው።

መረጃውን ያደረሰን የምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ድርጅት በግፍ በተገደሉ ምዕመናን ኅልፈት እጅግ ማዘኑን እየገለጸ ነፍሳቸውን በአብርሃም በይስሐቅና ያዕቆብ ዕቅፍ እንዲያኖራቸውና ለቤተሰቦቻቸው ለኦርቶዶክሳውያንም መጽናናቱን ይመኛል፡፡

ኢኦተቤ ቴቪ

01/12/2023

ከአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሐሙስ ኅዳር 20/2016 ዓ.ም. አገሪቱ ከኢትዮጵያ አንጻር የምትከተለውን ፖሊሲ በተመለከተ ምስክርነት የመስማት እና ማብራሪያ የተጠየቀበት ስብሰባ ተካሂዷል።

በዚህ ስብሰባ ላይ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር እንዲሁም የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጀት ዩኤስኤአይዲ የአፍሪካ ቢሮ ምክትል ረዳት አስተዳዳሪ ታይለር ቤክልማን ቀርበው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለምክር ቤቱ አባላት ምስክርነት ሰጥተዋል።

ሐመር በዋናነት በኢትዮጵያ እና በአካባቢው ስላሉ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ከአገራቸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አንጻር እንዲሁም ቤክልማን አሜሪካ በኢትዮጵያ ስለምታካሂደው የሰብዓዊ እርዳታ ምስክርነት እና ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም ማይክ ሐማር በትግራይ ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት ጨምሮ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ስላጋጠሙ ግጭቶች አንስተው የአሜሪካ መንግሥት ያደረገውን ጥረት እና እያከናወነ ያለውን ተግባር አብራርተዋል።

ልዩ መልዕክተኛው በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ሲያደራድሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ በአማራ ክልልም ዕድሉ ከተሰጠ ሰላማዊ ንግግር እንዲደረግ ድጋፍ ለማድረግ አሜሪካ ዝግጁ መሆኗን አመልክተዋል።

ማይክ ሐመር በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች እየተካሄደ ያለውን ግጭት ለማስቆም ወታደራዊ እርምጃ መፍትሄ እንደማይሆን እና መንግሥት ልዩነቶቹን በንግግር እንዲፈታ አሜሪካ ግልጽ አቋሟን ለኢትዮጵያ መንግሥት ማስታወቋን ጨምረው ተናግረዋል።

ማይክ ሐመረ በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች በምክር ቤቱ ከታደሙ አባላት ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ

የአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ጉዳዮች የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ጆን ጄምስ በመክፈቻ ንግግራቸው የኢትዮጵያን መንግሥት አስተዳደር ተችተዋል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ለመፈተሽ በተጠራው ስብሰባ ላይ የኮሚቴው ሰብሳቢ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ የተከሰቱ እና አሁን እየሆኑ ያሉ ጉዳዮችን በማንሳት ምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱን አውስተዋል።
ጆን ጄምስ “[ስለ ኢትዮጵያ] ብዙ ባወቅኩ መጠን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም ፍላጎት እንደሌለው እየተረዳሁ ነው። ብቸኛው [የኢትዮጵያ መንግሥት] ፍላጎት በተለይ ደግሞ ከአሜሪካ የሚፈልገው እየተባባሰ ለመጣውን የምጣኔ ሃብት ችግር መፍሄ ማግኘት ነው” ብለዋል።
ከሚሺጋን ግዛት የተወከሉት የሪፐብሊካን ፓርቲ አባሉ ጆን ጄምስ፤ የትግራዩ ጦርነት ያስከተለውን ጥፋት፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ግጭት መቀጠሉን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎትን በተመለከተ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው አስተያየት ተጨማሪ የጦርነት ስጋት ይፈጥራል ወይ ሲሉ ለማይክ ሐመር ጥያቄ አቅርበዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት

ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ከኮሚቴ አባላት ንግግር እና ጥያቄ በኋላ የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊስ እንዲሁም አሜሪካ በኢትዮጵያ ያላትን ፍላጎት አብራርተዋል።

የባይደን እና የሐሪስ አስተዳደር ለመላ ኢትዮጵያውያን ጥቅም ሲባል በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን እና ልማት እንዲኖር ፍላጎት አለው ያሉት ማይክ ሐመር፤ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ከተሾሙ በኋላ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ማስቆም እንዲሁም ከሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር የተያያዙ ውጥረቶችን ማርገብን ትኩረት አድርገው ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት አብቅቶ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ ካደረጉ በኋላ፣ በጦርነቱ ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነት ማስፈን አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላት የውጭ ጉዳይ ፖሊስ ቁልፍ አጀንዳ እንደሚሆን ይፋ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

በትግራዩ ጦርነት በሰብዓዊነት ላይ ወንጀሎችን የፈጸሙት ላይ ክስ እንዲመሠረት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መንግሥት ላይ ጫና እያሳደርን ነው ብለዋል።
ማይክ ሐመር በትግራይ በከፍተኛ ደረጃ ይፈጸሙ የነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መቀነሳቸውን የሚያመለክት ሪፖርት እንደደራሳቸውም ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የኤርትራ ኃይሎች ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ድንበር ለቅቀው አለመውጣታቸው፣ የህወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት እና የማሰናበቱ ሂደት እንደተጓተተ የጠቀሱት ሐመር ቀርተዋል ያሏቸውን ሂደቶችን አንስተዋል።

ጨምረውም በትግራይ እና በአማራ ክልሎች መካከል የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ጉዳይ መፍትሄ አለማግኘቱን በማስታወስ፣ ህወሓት እና የፌደራሉ መንግሥቱ የተፈራረሙት ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ አለመሆኑን ተናግረዋል።

ማይክ ሐመር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ሥራ በመጀሩበት ወቀት ወደ ቱርክ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች አቅንተው የቱርክ መንግሥት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ለኢትዮጵያ ጦር መስጠቱ አሜሪካን እንዳሳሰባት እና ድሮኖቹ በአገሪቱ ያለውን ሁኔታ የበለጠ እያወሳሰበ መሆኑን ስጋታቸውን መግለጻቸውን አመልክተዋል።

ኦሮሚያ እና አማራ

የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ያስቆመው የሰላም ስምምነት መፈረሙ ትልቅ ስኬት ነው ያሉት ሐመር፤ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያለውን ግጭት ለማስቆም ንግግር እና ድርድር እንዲደረግ ጫና እያሳደሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ልዩ መልዕክተኛው አሜሪካ በአሁኑ ወቅት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶች በእጅጉ እንደሚያሳስባት ለኮሚቴ አባላቱ ተናግረዋል።
በሁለቱ ክልሎች የሕይወት መጥፋት፣ የመብት ጥሰት እና የምጣኔ ሃብት ውድመት አለ ያሉት ማይክ ሐመር፤ ሁሉም አካላት ከግጭት እንዲቆጠቡ አሜሪካ ስታሳስብ ቆይታለች ብለዋል።

በዚህም “ተዋጊዎች ልዩነቶቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ለማደራደር ጥያቄ አቅርበናል” በማለት ከሳምንት በፊት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና የኢትዮጵያ መንግሥት በታንዛኒያ ከሳምንት በላይ ሲያደርጉት በነበረው ድርድር መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

በታንዛኒያው ድርድር ለግጭቱ ወታደራዊ አማራጭ መፍትሄ እንደማይሆን በመጥቀስ የአሜሪካ መንግሥት ለወራት ውትወታ ካደረገ በኋላ ሁለቱ ወገኖቸ ለንግግር እንደተቀመጡ እንዲሁም የሚፈለገው ውጤት እስኪመጣ ጊዜ ሊወስድ ይችላል ብለዋል።

“የምንፈልገውን አይነት ውጤት በአጭር ጊዜ ማምጣት ከባድ ነው። ንግግሩ ከባድ ነበር። በዳሬሰላም ለሁለት ሳምንት ተኩል ቆይቻለሁ። አዎንታዊ ለውጦች ግን አሉ። ሰላማዊ መፍትሄ እስኪመጣ ድረስ ቁርጠኞች ነን።”
ለዚህም ድርድሩ ውጤታማ እንዲሆን በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና በመንግሥት በኩል ቁርጠኝነት እና ሰጥቶ የመቀበል ውሳኔ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከተባባሰ ወራት ያሰቆጠረውን በአማራ ክልል እየተካሄደ የለውን ግጭትም ለማስቆም “ዕድሉ ካለ ለማደራደር እና ሰላማዊ ንግግር እንዲደረግ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን” ያሉት ማይክ ሐመር ግጭቶቹ በወታደራዊ እርምጃ እልባት ሊያገኙ እንደማይችሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
አክለውም ከወራት በፊት በፌደራሉ መንግሥት በአማራ ክልል ላይ ተጥሎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ እና መገናኛ ብዙኃን ወደ ክልሉ እንዲደርሱ እንዲሁም ተቋርጦ የሚገኘው የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲጀመር የኢትዮጵያ መንግሥትን መጠየቃቸውን ተናግረዋል።
“በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የሚፈጸሙት ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች፣ ስቃዮች እና እስሮች በእጅጉ አሳስበውናል” ያሉት ሐመር፤ “ይህን ለመንግሥት ግልጽ አድርገናል።...በእያንዳንዱ ንግግራችን የሰብዓዊ መብት መከበር የባይደን አስተዳደር የውጭ ጉዳይ ፖሊስ ዋና አካል መሆኑን ግልጽ አድርገናል።”
በአገሪቱ ባለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ደስተኛ አይደለንም ያሉት ማይክ ሐመር ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሚደረገው ንግግር ይቀጥላል ብለዋል።
ምጣኔ ሃብት
ልዩ መልዕክተኛው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሚባል የምጣኔ ሃብት ቀውስ ውስጥ መግባቷን ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ማብራሪያ ወቅት አንስተዋል።
“የውጭ ምንዛሬ ክምችት በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባለፉት ሁለት ዓመታት የዋጋ ግሽበቱ በአማካይ 30 በመቶ ነው” ያሉ ሲሆን፣ የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት በተመለከተ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ንግግር እያደረገ ነው ብለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ሆና ከቆየችበት የአፍሪካ የእድገት እና ዕድል ድንጋጌ (አጎዋ) መታገዷ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ጦርነቱን ለማቆም የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ኢትዮጵያ ዳግም ከአጎዋ ተጠቃሚ የምትሆንበት ዕድል እየተጠና መሆኑን ሐመር ተናግረዋል።
“ኢትዮጵያ ለአጎዋ ብቁ ስለመሆኗ ዳግም እየተጠና ነው። በሳምንታት ውስጥ ውሳኔ ያገኛል።...ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የቀጠለው ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሳሳቢ ነው። በተለይ ደግሞ በአማራ እና በኦሮሚያ። ...በአጎዋ መስፍርቶች መሠረት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ቀድመው መሻሻል አለባቸው” ብለዋል።
የሕዳሴ ግድብ እና የባሕር በር ጉዳይ
የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተም ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እንዲሁም የተቀሩት የታችኛው የተፋሰስ አገራትን በሙሉ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ስምምነት እንዲደረስ አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቷን ትቀጥላለች ብለዋል ሐመር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “የወደብ ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው” ብለው መናገራቸው በቀጠናው ካሉ አገራት አልፎ ለአሜሪካ የስጋት ምንጭ እንደሆነ ማይክ ሐመር ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባሕር በር ፍላጎቱ በኃይል ተፈጻሚ እንደማይሆን በይፋ እንዲሁም በግል ማረጋገጫ እንደሰጧቸው አመልክተዋል።
“ይህ ቀጠና በፍጹም የማይፈልገው ነገር ሌላ ጦርነት ነው።...በቀጠናውም ሆነ በኢትዮጵያ ግጭት እና አለመግባባት በሰላማዊ ንግግር ነው መፈታት ያለበት” ብለዋል።
በምክር ቤቱ ውስጥ በተሰጠው ምስክርነት እና ለቀረቡ ጥያቄዎች ሰፊውን ቦታ ይዘው የነበሩት አምባሳደር ሐመር ቢሆኑም፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጀት ዩኤስኤአይዲ የአፍሪካ ቢሮ ምክትል ረዳት አስተዳዳሪ ታይለር ቤክልማንም በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ተናግረዋል።

ቤክልማን በኢትዮጵያ ውስጥ ለእርዳታ ተብሎ የቀረቡ የምግብ ድጋፎች ላይ ስርቆት መፈጸሙ ከተገለጸ በኋላ ለወራት ተቋርጦ ስለቆየው የእርዳታ አቅርቦት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከአምስት ወራት በላይ ተቋርጦ የነበረው አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው የምግብ እርዳታ አቅርቦትን መልሳ መጀመሯን ከጥቂት ሳምንታት በፊት ማስታወቋ ይታወሳል።

በምሥራቅ አርሲ ሁለት አብያተ ክርስቲያናት ላይ 35 ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸወረ ተነገረበወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫበምሥራቅ አርሲ  ሽርካ ወረዳ  በሶሌ መድኃኔ ...
01/12/2023

በምሥራቅ አርሲ ሁለት አብያተ ክርስቲያናት ላይ 35 ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸወረ ተነገረ

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ

በምሥራቅ አርሲ ሽርካ ወረዳ በሶሌ መድኃኔ ዓለም እና ሴሮ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ኅዳር ፲፫ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም በተፈጸመ ጅምላ ጭፍጨፋ ፳፯ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ንጹሐን ዜጎች በአስቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ከአካባቢው ነዋሪዎች ለመረዳት ችለናል። ይኸው ጥቃት ቀጥሎ ኅዳር ፲፯ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም ደግሞ ፰ ሰዎች በተመሳሳይ መልኩ ሲገደሉ በድምሩ ፴፭ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ንጹሐን ዜጎች መገደላቸውን አረጋግጠናል፡፡ በርካቶችም ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውም ታውቋል፡፡ በዚህ ጥቃት ነፍሰጡር ሴትን ጨምሮ ጨቅላ ሕጻናት የተገደሉ ሲሆን ፲፩ ሟቾች የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው።

በአካባቢው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ንጹሐን ዜጎች ላይ መሰል ጥቃት ሲፈጸም በ፳፻፲፮ ዓ.ም ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደሚገኙ ለማረጋገጥ ችለናል።

በተለይ የአካባቢው ነዋሪ እራሱን ይከላከልበት የነበረውን ትጥቅ በመንግሥት አመራሮች እንዲፈታ ከተደረገ በኃላ የተፈጸመ ጥቃት መሆኑ መላው ኢትዮጵያውያንን አሳዝኗል። የአካባቢው የመንግሥት አመራሮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የዚህ የተቀናጀ የጅምላ ጭፍጨፋ ተባባሪ ስለመሆናቸው ከዚህ በላይ ማሳያ ሊኖር አይችልም።
ባለፉት አምስት አመታት በሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎች የደረሱት የጅምላ ጭፍጨፋዎች አልበቃ ብለው ዛሬም ይህንኑ እኩይ ተግባር በመዋቅራዊ አሰራር ማስፈጸም ያለንበትን አሳፋሪ ሥርዓት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ስር በሰደደ ጥላቻ ተጠምዶ ጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸም በፈጣሪም ሆነ በሕግ ፊት ፈጽሞ ምህረት እንደሌለው ሊታወቅ ይገባል።

ይሁን እንጂ ሥርዓቱ ራሱ የጅምላ ግድያው አቀናባሪ በመሆኑ ለፈሰሰው ደም ፍትህ ይሰጣል ብለን አናምንም፤ ከዚህ ቀደምም ሲያደርግ አልታየም። ዛሬ በአርያም የሚጮኸው የጅምላ ግድያ ሰለባ የሆኑ ንጹሐን ዜጎቻችን ደም የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ፍትህ እንደሚያገኝ አንዳች ጥርጥር የለንም። በአማራ ክልል ዛሬ ከዳር እስከ ዳር የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመጽ አንደኛው መንስኤ ለተከታታይ ሦስት አስርት ዓመታት በላይ ይህን ዓይነቱን ጨምሮ በአጠቃላይ የዜጎች በማንነታቸው በጅምላ መጨፍጨፍ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

የድርጊቱ አቀናባሪዎችና ፈጻሚዎች ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ እየገለጽን፤ ግጭት ጠማቂ አካላት ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ በደም የተለወሰ እጃችሁን እንድታነሱ አጥብቀን እናሳስባለን።

ስለ ሃይማኖታቸው ሕይወታቸው ያለፈውን ዜጎቻችንን ነፍስ እግዚአብሔር በገነት እንዲያሳርፍና በሕይወት ለተረፉ ቤተሰቦቻቸው መጽናናትን እንዲሰጥ እንመኛለን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ይጠብቅ!
እናት ፓርቲ
ህዳር ፳ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

ጉመሮ ሻይ ቅጠል ምርቱን ለሃገር ውስጥ ገበያ ማቅረብን አቋረጠ። ጥንታዊ እንደሆነ የሚነገርለት ጉመሮ ሻይቅጠል ምርቱን ለአውሮፓ ገበያ ብቻ እንደሚያቀርብ አስታውቋል። በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ...
01/12/2023

ጉመሮ ሻይ ቅጠል ምርቱን ለሃገር ውስጥ ገበያ ማቅረብን አቋረጠ።

ጥንታዊ እንደሆነ የሚነገርለት ጉመሮ ሻይቅጠል ምርቱን ለአውሮፓ ገበያ ብቻ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።

በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ስር የሚገኝው ጉመሮ ሻይ ቅጠል ካምፓኒው ባስቀመጠው አዲስ አሰራር መሰረት ለሀገር ውስጥ ያቀርበው የነበረው ምርት አቋርጦ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን ገልጿል።

የጉመሮ ሻይቅጠል የምርት ዘርፍ ሃላፊ የሆኑት አቶ ሶሎሞን ምትኩ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት ድርጅቱ ባሁኑ ሰአት ምርቱን ለውጭ ገበያ ብቻ ነው እያቀረበ ያለው ብለዋል።

በኢሉ አባቦራ ዞን ጎሬ ከተማ በ1ሺህ ካሬ መሬት ላይ ያረፈው የሻይ ቅጠል ምርቱ በቀን 88ሺህ ኪሎ ግራም ምርት እንደሚያመርት አቶ ሶሎሞን የተገለጹት።

በድርጅቱ በቋሚነት 534 ሰራተኞች ተቀጥረው የሚሰሩ ሲሆን በኮንትራት 3ሺህ 500 ሰራተኞች እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

ጉመሮ ሻይቅጠል ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ለሃገር ውስጥ ገበያ ምርቱን ሲያቀብ የቆየ ቢሆንም አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ትኩረቱን የውጭ ገበያ ላይ አድርጓል ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም

ወርቅ እንዲያመርቱ ፈቃድ ከተሰጣቸው 13 ኩባንያዎች ሁለቱ ብቻ ሥራ መጀመራቸው ተነገረበፌዴራል ደረጃ ፈቃድ ከተሰጣቸው 13 የማዕድን ኩባንያዎች ውስጥ በ2016 ዓ.ም. ሩብ ዓመት ሁለቱ ብቻ ...
29/11/2023

ወርቅ እንዲያመርቱ ፈቃድ ከተሰጣቸው 13 ኩባንያዎች ሁለቱ ብቻ ሥራ መጀመራቸው ተነገረ

በፌዴራል ደረጃ ፈቃድ ከተሰጣቸው 13 የማዕድን ኩባንያዎች ውስጥ በ2016 ዓ.ም. ሩብ ዓመት ሁለቱ ብቻ እያመረቱ መሆናቸውን፣ ቀሪዎቹ 11 ኩባንያዎች በስድስት ወራት ውስጥ ወደ ሥራ ካልገቡ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ይህንን ያስታወቀው ኅዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የ2016 በጀት ዓመት የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርብ ነው፡፡

የ2016 በጀት ዓመት ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት የማዕድን ሚኒስትሩ ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር)፣ ወርቅ እንዲያመርቱ ፈቃድ የተሰጣቸው 13 ኩባንያዎች ቢሆኑም፣ ያመረቱት ሚድሮክ ጎልድና ስቴላ የማዕድን አውጪ ኩባንያዎች ብቻ ናቸው ብለዋል፡፡

ከሁለቱ የወርቅ አምራች ኩባንያዎች የተሻለ አፈጻጸም ያለው ሚድሮክ ጎልድ መሆኑንና በመቀጠል ስቴላ የተሰኘው ማዕድን ኩባንያ እንደሆነ ገልጸው፣ የተቀሩት ግን በሩብ ዓመቱ ለማዕከላዊ ገበያ ምንም ወርቅ እንዳላቀረቡ አስረድተዋል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር በ2016 በጀት ዓመት ከከፍተኛ ወርቅ አምራች ኩባንያዎች 996.1 ኪሎ ግራም ወርቅ ለማግኘት ዕቅድ ቢኖውም፣ 719.6 ኪሎ ግራም ወይም 72.2 በመቶ ብቻ እንደተገኘና ለዚህም ትልቁን ድርሻ የያዘው ሚድሮክ ጎልድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ሀብታሙ (ኢንጂነር) ገለጻ፣ የተቀሩት ማዕድን አውጪዎች በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ ወደ ምርት ካልገቡ ፈቃዳቸው ላይ ዕርምጃ ይወሰዳል፡፡

በኢትዮጵያ ፈቃድ አግኝተው ከሚንቀሳቀሱ 13 የማዕድን ኩባንያዎች በዓመት 17 ቶን ወርቅ ማምረት እንደሚቻል ሚኒስትሩ ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡

ፈቃድ ከተሰጣቸው 11 ኩባንያዎች አብዛኛዎቹ ዝግጅት ላይ እንደሆኑ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

ከሚድሮክ ጎልድና ከስቴላ ከፍተኛ የወርቅ አምራቾች ውጪ ያሉት ኩባንያዎች የፀጥታ ችግር ባሉባቸው አካባቢዎች መሰማራታቸውን ተናግረዋል፡፡

በሩብ ዓመቱ ክልሎች ከሚያስተዳድሯቸው አነስተኛና ባህላዊ ወርቅ አምራቾች የተገኘው 22 በመቶ ብቻ መሆኑን በሪፖርታቸው ያወሱት ሚኒስትሩ፣ ከፍተኛ የወርቅ ምርት ሲያስገኙ የነበሩ ባህላዊ አምራቾች ማሽቆልቆላቸውን አክለዋል፡፡ ይህም የሚያሳየው ፈቃድ ሰጪው አካል (ክልሎች) በሚያስተዳድሯቸው አምራቾች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባቸው የሚያመለክት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ወርቅ የሚገኝባቸው አካባቢዎች ተብለው መለየታቸውን፣ ይሁን እንጂ በቅርቡ በተደረገው ዳሰሳ በሌሎች ክልሎች ወርቅ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ሁኔታ ወርቅ ሲያመርት የነበረው የኦሮሚያ ክልል እንደነበር፣ ነገር ግን የ2016 በጀት ዓመት የሩብ ዓመት አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የተሻለ የወርቅ ምርት ያቀረበው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሆኑን፣ ከዚያ ቀጥሎም የተሻለ አፈጻጸም ያለው ጋምቤላ ክልል እንደሆነ ገልጸዋል፡

በትግራይ ክልል ኢዛና ወርቅ አምራች ኩባንያ አንዱ መሆኑን፣ በፌዴራል መንግሥት ዕገዛ ተደርጎለት እስከሚቀጥለው ታኅሳስ ወር ድረስ ወደ ምርት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሩብ ዓመቱ ከትግራይ ክልል የተገኘ ምንም ዓይነት ወርቅ የለም ብለዋል፡፡

በ2016 በጀት ዓመት በወርቅ፣ በታንታለም፣ በሊቲየምና በሌሎች ማዕድናት ለማግኘት የታቀደው የውጭ ምንዛሪ 512 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን፣ በሩብ ዓመቱ ደግሞ 112 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል ተብሏል፡፡ ይሁን እንጂ በሩበ ዓመቱ ከታቀደው አኳያ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፈቃድ ያገኙ የማዕድን አምራቾች በሙሉ አቅማቸው ካመረቱ በዓመት 1.1 ቢሊዮን ዶላርና በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት 11 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አማረች በካሎ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ከማዕድን ሀብት የተሻለ ገቢ ማግኘት እንድትችል በዘርፉ የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮች ሊቀረፉ ይገባል ብለዋል።

መንግሥት የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለማሳካት አምስት የስትራቴጂ ዕቅዶች ነድፎ እየሠራባቸው ከሚገኙ ዘርፎች አንዱ የማዕድን ዘርፉ በመሆኑ፣ የሚስተዋሉ ችግሮች ሊቀረፉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የማዕድን ዘርፍ ውስብስብ ፍላጎቶች ያሉበት በመሆኑ ኮንትሮባንድና ብልሹ አሠራሮችን ጨምሮ ሌሎች ችግሮች ላይ ተገቢው ቁጥጥርና ክትትል የማድረግ ተገቢነትን ሰብሳቢዋ አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል በማዕድናት መረጃ አያያዝ፣ በዘርፉ ስለተፈጠረው የሥራ ዕድል፣ በማዕድን ምርመራና ፈቃድ አሰጣጥ፣ እንዲሁም ማዕድናት ባሉባቸው አካባቢዎች የመሠረት ልማት ግንባታ ውስንነትና በመሳሰሉት ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሠራ እንደሚገባ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሀብሩ-መርሣ ወረዳ ቤተክህነት ጋቲራ ደብረ ፀሐይ  ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በከባድ መሣሪያ ተደብድቦ ዘጠኝ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።ትናንት ኅዳር 18 ቀን ...
29/11/2023

በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሀብሩ-መርሣ ወረዳ ቤተክህነት ጋቲራ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በከባድ መሣሪያ ተደብድቦ ዘጠኝ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።

ትናንት ኅዳር 18 ቀን 2016 ዓ.ም ምሽት 11:00 በሰሜን ወሎ ዞን ውርጌሳ ከተማ ጋቲራ ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የሠርክ ጉባኤ ትምህርት ላይ እያሉ ወደ ቤተክርስቲያኑ በተተኮሰ ከባድ መሣሪያ ዘጠኝ ካህናትና ፀበልተኞች መቁሰላቸውን ወረዳ ቤተክህነቱ ገልጧል።

በትምህርታዊ ጉባኤ ላይ እያሉ በቤተክርስቲያኑ ቅጽረ ግቢ፣ በቤተሌሔሙና በፀበልተኛ መጠለያ ቤቶች በርካታ ከባድ መሣሪያ ያረፈ ሲሆን በደብሩ አስተዳዳሪ፣ ሰባኬ ወንጌልና በፀበልተኛ ህሙማን ላይ ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ መድረሱን ከወረዳ ቤተ ክህነቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የሐብሩ-መርሣ ወረዳ ቤተክህነት ዋና ጸሐፊ ዲ/ን ታዴዎስ ይመር እንደገለፁት ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች በውርጌሣ ጤና ጣቢያ መታከማቸውንና 3 ሰዎች ለከፍተኛ ህክምና ወደ ደሴ እና ወልድያ ሪፈራል ሆስፒታሎች መላካቸውን ገልፀዋል።

የከባድ መሣሪያ ተኩሱ በአካባቢው ዛሬም መቀጠሉን የገለፁት ዋና ጸሐፊው የአብነት ተማሪዎችና ለፀበል የመጡ ህሙማን ከቤተክርስቲያን ወጥተው ተበትነዋል ብለዋል።
በተመሳሳይ በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ጋዞ ወረዳ ቤተክህነት ብርአፋፍ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ኅዳር 16 ቀን 2016 ዓ.ም በከባድ መሣሪያ ጥቃት ሦስት ካህናት ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

(ሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሚዲያ)

ተስፋዬ ገ/አብ በችሎታው የተመሠከረለት ነበረ።(ኦሃድ ቢናሚን እንደፃፈፉት)ከትልቅ ችሎታ ጋር ትልቅ ኃላፊነት መኖር አለበት። አቅምና ኃላፊነት ካልተመጣጠኑ አደጋው ከባድ ነው። የዘመናችን ሌጋ...
29/11/2023

ተስፋዬ ገ/አብ በችሎታው የተመሠከረለት ነበረ።

(ኦሃድ ቢናሚን እንደፃፈፉት)

ከትልቅ ችሎታ ጋር ትልቅ ኃላፊነት መኖር አለበት። አቅምና ኃላፊነት ካልተመጣጠኑ አደጋው ከባድ ነው። የዘመናችን ሌጋሲ ችግር።
ሙት ወቃሽነት ነውር ነው። ያልሞተ ክፉ ሥራ ግን ከውግዘት ያለፈ ተመጣጣኝ ምላሽ ያስፈልገዋል።

ተስፋዬ በጥላቻ ደም የተቀመሙት ብዕሮቹ የሚቀዱት ከብዙዎች እሱንም መጽሓፎቹንም ፈጽመው ከማያውቁ የዋህ ዜጎች የሚቀዱ የደም ጠብታ ጥርቅሞች ነበሩ።

ተስፋዬ ትሁትና ለስለስ ያለ ስብዕና ነበረው። ነገርግን ከዛ ስብዕና ውስጥ ያን ያክል የታመቀ ጽልዕና የብዕሮቹን ጫፎች አልፎ ሲመጣ እገረም ነበር።

በነበረችን ትንሽ ግንኙነት ከብዕሩ ውስጥ ቀዩን ቀለም እንዲያወጣው ሃሳብ ሰንዝሬለት ነበር። ያን ወስዋስ ግን ሳያሸንፈው ተስፋዬገ/አብ አሸልበ።

ራሱን ከጥላቻ ያላነጻ ሰው ጥላቻውን ይዞ ዝም ቢል ደግ ነው። አለበለዚያ የራሱን ጥላቻ ወደሌሎች እያዛመተ ይቀጥላል። ሰዎችን በጥላቻ ከመንደፍ ጋር የሚነጻጸሩ የፍላጸዎች አይነት ብዙ አይደሉም።

ተስፋዬ መቼ ላይ በጥላቻ እንደተነደፈ ባላውቀውም ከብዕሮቹ አቅም ተነስቼ መርዙን ማርከስ የሚችልባቸው ብዙ ዕድሎችና ምዕራፎች ነበሩት። አልተጠቀመባቸውም። እናም ጥላቻው የህይወቱ የቤት ሥራ ሆኖበት ቀጠለ። ጥሩ ዕድል አይደለም።

በተስፋዬ ብዕሮችና በወለጋ ንጹሃን ደም መካከል ያለው የቀለም መመሳል ያስደምመኛል።

በዛ ተሰጥዖውና ችሎታው ፍቅርን ሰላምንና ወንድማማችነትን ጽፎ ቢያልፍ ኖሮ የላቀ የታሪክ ቦታ ይኖረው ነበረ። ምኞት ነው።

ተስፋዬ ምን ያክል የቤት ሥራውን ጨርሶ መሄዱን አላውቅም። ለኛ ግን በፊክሽን ያሰከራቸውን ወገኖቻችንን ወደልባቸውና ወደቀልባቸው የመመለስ የቤት ሥራ ትቶልን አፈር ወደ አፈር (Ashes to ashes dust to dust) ሆኖ ተመልሷል።

Ashes to Ashes Dust To Dust.

"ቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍ 'የአንተ መኪና ቆንጆ ራቫ ፎር አዲስም በመሆኑ መንግስት ይፈልገዋል አሉኝ' "ማንን ምን እንጠይቅልዎ ሸገር ኤፍ ኤም 102. 1 ሬዲዮ
28/11/2023

"ቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍ 'የአንተ መኪና ቆንጆ ራቫ ፎር አዲስም በመሆኑ መንግስት ይፈልገዋል አሉኝ' "

ማንን ምን እንጠይቅልዎ

ሸገር ኤፍ ኤም 102. 1 ሬዲዮ

#ጉምሩክ "ቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍ 'የአንተ መኪና ቆንጆ ራቫ ፎር አዲስም በመሆኑ መንግስት ይፈልገዋል' አሉ! መኪናዬ ብሔራዊ ደንነት እየተጠቀመበት ነው"የሸ....

Pepsi bottler on verge of shutdown, thousands of jobs on the lineMoha Soft Drinks Industry S.C. has taken steps to shutt...
26/11/2023

Pepsi bottler on verge of shutdown, thousands of jobs on the line

Moha Soft Drinks Industry S.C. has taken steps to shutter operations at all of its production facilities, potentially putting close to 8,000 employees out of work.

Anonymous sources familiar with the matter told The Reporter that a severe shortage of foreign currency has crippled Moha’s operations. The bottler has been unable to import crucial inputs such as syrup, bottles, crates, and spare parts for its production machinery, according to the source.

Moha is the bottler for PepsiCo products in Ethiopia (including popular soft drink brands Pepsi, Mirinda, and 7UP) as well as Kool carbonated mineral water. The company, which is a member of MIDROC Ethiopia, was established in May 1996. It operates three plants in Addis Ababa, and five more in other parts of the country, including Hawassa and Mekele.

Production has been halted completely at all eight plants for the past year, according to the source. The company has been supplying the market with products from its stock, which has now run out, disclosed the source.

“Moha has been unable to meet consumer demand for the past four months,” the source told The Reporter.

The source alleges that any Moha products currently being sold in the market are either counterfeit or have outlived their expiration date, raising concerns about health and quality.

The bottler has also been forced to let its enormous workforce go, according to the source. More than 8,000 employees have lost or resigned from their jobs at Moha over the past year, according to the source.

Those in management positions are leaving either through voluntary resignations or being laid off, disclosed the source.

Moha employees, who allege they were not given adequate notice or paid severance packages, have turned to the Confederation of Ethiopian Trade Unions (CETU) for help.

Kassahun Follo, CETU president, was in discussions with Moha’s management over the past week. A source told The Reporter the talks yielded “positive signals”, hinting at a potential resolution for beleaguered employees.

Getachew Birbo, general manager of Moha Soft Drinks, did not respond to queries from The Reporter.

The CETU is reportedly drafting an appeal to Sheikh Mohammed Hussein Al-Amoudi, the major shareholder in Moha Soft Drinks, on behalf of the company’s employees.

It is not the only one looking to the tycoon for help, as Prime Minister Abiy Ahmed (PhD) reportedly discussed the country’s pressing foreign currency problems with the Sheikh during a recent trip to Saudi Arabia.

The billionaire reportedly told the PM he would not funnel any foreign currency investments into Ethiopia due to security concerns, according to a source in Moha’s senior management team.

Jemal Ahmed, CEO of MIDROC Investment Group, has also made the trip across the Red Sea to discuss the challenges facing Moha Soft Drinks with the Sheikh.

Ethiopian Reporter

Address


Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Ahun Times - አሁን ታይምስ posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Business

Send a message to Ahun Times - አሁን ታይምስ:

Videos

Shortcuts

  • Address
  • Alerts
  • Contact The Business
  • Videos
  • Claim ownership or report listing
  • Want your business to be the top-listed Media Company?

Share