08/03/2023
የሴቶች ሚና ለብልፅግናችን ጉዞ ወሳኝ ነው !!
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ112ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ47ኛ ጊዜ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡
ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን “ማርች 8” ሴቶች በማህበረሰቡ ውሰጥ ተገቢውን ስፍራ እንዲያገኙ መሰረት የጣለ ነው፡፡ የዓለማችን ሴቶች ባደረጉት ተጋድሎ በሴቶች ላይ ይደርሱ የነበሩ ጫናዎች ቀንሰው የእኩል ተጠቃሚነት አጀንዳ በመንግስታት ፖሊሲ ውስጥ እንዲካተት ሆኗል፡፡
በሀገራችን የፆታ እኩልነትን በማስፈን ሴቶች ከነበረባቸው ድርብርብ ተጽዕኖ ተላቀው በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲሆን ተጨባጭ እርምጃዎች ሲወሰዱ ቆይተዋል፡፡
በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ከራሳቸው አልፈው ለማህበረሰቡ እና ለሀገር የሚጠቅሙ አኩሪ ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከፍ በሚያደርጉ የስራ መስኮች ላይ በመሰማራት እና ሴቶችን በማሳተፍና ተጠቃሚ በማድረግ በስራቸው አንቱታን ያተረፉ የአገራችን ሴቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡
በፖለቲካ መስክም በውሳኔ ሰጭነት ቀሪ ስራዎች እንደተጠበቁ ሆኖ የአገራችን ሴቶች ከፊት እየመሩ ይገኛሉ፡፡ የአለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ስናከብርም ይሄንን የተገኘውን ድል ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ በመትጋት እና ሴቶች እርስ በእርስ ያላቸውን ትስስር እና ትብብር ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ቃል በመግባት ሊሆን ይገባል።