28/05/2020
የአማራን ህዝብ ካለበት ፈታኝ ሁኔታ አውጥቶ ለሁለተናዊ ስኬት ለማብቃት በአንድነት እንቁም!
ይድረስ ለአማራ ምሁራን
ይድረስ ለሲቪክ ማህበረሰብ አባላት
ይድረስ ለአማራ የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅቶች
ይድረስ ለአማራ የማህበራዊ ሚድያ አንቂዎች
ይድረስ ለአማራ ወጣቶች ማሕበራትና አባላት
ይድረስ ለአማራ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች
ይድረስ ለአማራ ክልል መንግስት የስራ ሃላፊዎች
ይድረስ ለአማራው ህዝብ ታሪካዊ አጋር እና ወንድም ህዝቦች
በመጀመሪያ የከበረ ሰላምታ እናቀርባለን።
እኛ ስማችን ከዚህ በታች የተዘረዘረው በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው መከራ ያሳሰበን በጎ አሳቢ ዜጎች የአማራ ህዝብ እያደረገ ካለው አጠቃላይ የህልውና ትግል አንጻር በማህበራዊ ሚዲያው እየተፈጠሩ ያሉ ውዥምብሮች አሳሳቢና አስጊ ሁነው ስላገኘናቸው ይህንን ደብዳቤ ለሚመለከታቸው ሁሉ ለማድረስ ተገደናል፡፡
በተለይ በዚህ ወቅት ምርጫ ለምን ተራዘመ በሚሉ ማደናገሪያ አጀንዳዎች ሸፋን አፓርታይዳዊ ለሆነው ለህዎኃት ህገ-መንግስት ጥብቅና በመቆም የአማራ ሕዝብ ዋነኛ ጠላቶችና የእነሱ የውስጥ ተልእኮ አስፈጻሚ ሀይሎች ግንባር በመፍጠር ሃገር የማፍረስ ደባ ላይ ተጠምደው ይገኛሉ፡፡
ይህን ውስብስብ የክፋት ሃይሎች ሴራ በመቀልበስ ህዝባችን ከተጋረጠበት አደጋ መታደግ የሚቻልው በአንድ ልብ መካሪ በአንድ አፍ ተናጋሪ መሆን ሲቻል ነው።
የአማራ ህዝብ ትግል ዋነኛ ዓላማ ከተለያዩ አካላት እየተፈፀመበት ያለውን ማንነት ተኮር ጥቃትና መገለል ራሱን መከላከል ሲሆን፤ ህዝባችን ከሚገኝበት እጅግ አሰቃቂ የድህነት ሁኔታ ማላቀቅና ፍትህን ማስፈን የዚህ ትግል አካል ነው።
ነገር ግን በማህበራዊ ሚድያው እየታዩ ያሉ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች፤ ከአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ባፈነገጠ መልኩ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የአማራን ህዝብ ትግል ውዥምብር ውስጥ በመክተት፤ የኋሊት በመጎተት ለኪሳራ እየዳረገው፣ የአማራ ህዝብ ጥያቄዎችም ትኩረት እንዳያገኙ እያደረገ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም በአማራ ሕዝብ ትግል ውስጥ ክፍፍልን በመፍጠር አላስፈላጊ ዋጋ እንዲከፈል እያደረገ ነው።
ከተከበረው የአማራ ህዝብ እሴት ያፈነገጡ የማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴዎች ህዝባችንን ወዳጅ አልባ በማድረግ ከሁሉም አቅጣጫ ለሚሰነዘሩ ጥቃቶች ተጋላጭ እንዲሆን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ከዚህም በላይ የአማራ ህዝብን ትግል ከውስጥ የሚከፋፍሉ መረን የለቀቁ መረጃዎች በማሰራጨት፤ የልዩነት ቀዳዳን በማስፋት ትግሉን በማዳከም ላይ ናቸው።
የዚህ ማህበራዊ ሚድያ ትልም አልባ ተግባራት፤ ከቻሉ አማራውን ለማጥፋት፤ ያም ካልተሳካ ዝንተዓለም አንገቱን ለማስደፋት ለሚመኙ የጥፋት ሀይሎች መሳሪያ በመሆን የከፋ የፖለቲካ ኪሳራ እያስከተለ ይገኛል።
ለአማራ ህዝብ በእውነትና በዓላማ የሚሰሩ ሁሉ በእነዚህ መርህና ግብ አልባዎች ምክንያት እየተገለሉ ሀሳባቸውም እንዳይደመጥ ተስፋ እንዲቆርጡ እየሆኑ ነው።
በመሆኑም ይህን አይነት ሃላፊነት የማይሰማው የማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ አሳሳቢነት በቸልታ የሚታለፍ ሆኖ ስላላገኘነው ይህን ግልጽ ደብዳቤ ለመጻፍ ተገደናል።
በሌላ በኩል ገዥው ፓርቲ በራሱ በኩል መውሰድ ስላለባቸው እርምጃዎችና ማሻሻያዎች ራሱን የቻለ ደብዳቤ በማዘጋጀት ላይ እንደምንገኝ ለመግለጽ እንወዳለን።
1. በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው መከራ የሚያሳስበው እና ለአማራ ህዝብ በጎ አሳቢው ዜጋ በብአዴን ውስጥ አማራ ያልሆኑ ጸረ አማራዎች ከአመራርነት ተወግደው፤ በሃገራችንም ሆነ በክልሉ ነጻነት እና እኩልነት ሰፍኖ ማየትን ተመኝተን ብዙ መስዋዕትነትን የከፈልንበት ትግል በከፊልም ውጤት አምጥቶ በቀድሞው ብአዴን ውስጥ በቂና የጠበቅነውን ያህል ባይሆንም መጠነኛ ለውጦች መደረጋቸውን አስተውለናል።
አዴፓም ከሎሌነት ተላቆ ከአሳዳሪው ከህወሃት ጋርም ኦፊሴላዊ ፍቺ ፈጽሞ ተመልክተናል።
2. ቁጥሩ ቀላል የማይባል ታጋይ የተፈጠረውን ለውጥ ተቋማዊ ለማድረግ መሰራት ባለባቸው ስራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ለውጡ ዘላቂ እንዲሆንና አገራችንን ወደ ሙሉ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት አሸጋጋሪ የሆኑ እንደ የምርጫ ቦርድ፤ ፍርድ ቤቶችና ዓቃቤ ሕግ፤ የፖሊስና ደህንነት፤ የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር፤ ወዘተ ተቋማት ገለልተኛና ሙያዊ ብቃት ባላቸው ስዎች መልሰው እንዲዋቀሩ፤ ለወጡን እየመራ ባለው አካል ላይ ግፊት በማድረግ ላይ ይገኛል።
3. ማህበራዊ ሚድያው ህዝባችን ድምጽ አልባ በነበረበት ውቅት የህዝብ ድምጽ በመሆን፤ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን በማሰባሰብ፤ የአምባገነኖችን እንቅስቃሴዎች ለህዝብ በማድረስ እና በማህበራዊ ሚድያው ዘመቻ በማካሄድ ታሪካዊ ሚና ተጫውቷል።
4. በሌላ በኩል ደግሞ ለእንቅስቃሴው አላማ ያላስቀመጠ እና በስሜት የሚገፋ የማህበራዊ ሚድያ ሃይል፣ እያካሄደ ያለው እንቅስቀሴ ከፍተኛ የሆነ መሰናክል እየፈጠረ ይገኛል።
ይህ የማህበራዊ ሚድያ ሃይል በተለያየ የማሳሳቻ ስሞች ማንነትን ደብቆ፤ አቋሙን በየቀኑ በመቀያየር፤ ትናንት የደገፈውን ዛሬ እየተቃወመ፤ ጠዋት የገነባውን ከሰዓት እየናደ በውዥንብር ጎዳና ላይ እየነጎደ ይገኛል።
5. ይሄ ስሜታዊ ሀይል የሚመራው ማህበራዊ ሚዲያ ከወዳጅም ከጠላትም የሚደርሰውን መረጃ ሳያጣራና ግራና ቀኙን ሳይመዝን በማህበራዊ ሚዲያ አጀንዳ አድርጎ እያጦዘ ይገኛል፡፡
በመጣው ለውጥ ጥቅማቸው የተነካባቸው ሃይሎች የማህበራዊ ሚዲያውን ድክመት እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅመው የተዛባ መረጃ በዚህ ልጓም አልባ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በመልቀቅም ላይ ይገኛሉ።
ይህም ድርጊት የክልሉ አመራርን ለሁለት በመክፈል ደም ባፋሰሰ እልቂት ተጠናቀቀ። በተፈጠረው ትርምስ ከሁለቱም ወገን ባጣናቸው አመራሮች የተፈጠረውን ክፍተት መድፈን አልተቻልም። ይባሱኑ ትቶት ያለፈው ጥርጣሬ እና አለመተማመን ክልሉንም እስከአሁን ሊወጣው ባልቻለው አዘቅት ውስጥ ከቶቷል።
6. ሌላው አስጊ አዝማሚያ፤ ቁጥራቸው ትንሽ የማይባል የማህበራዊ ሚድያ አንቂዎች፤ ከነሱ የተለየ ሃሳብ መስማት አለመፈለግ ብቻ ሳይሆን ሌላው ሰው ሃሳቡን እንዳይሰጥ በስድብ ዘመቻ የማሸማቀቅ ተግባር ነው።
እንደ አሸን በፈሉ የሃሰት ማህበራዊ ሚዲያ ገጾች እና ሃሰተኛ ስሞችን በመጠቀም የበይነ መረብ ማህበረሰቡን (Digital community) በማንጓጠጥ፣ ስም በማጥፋትና በመሳደብ የዳር ተመልካች እንዲሆን አድርገዋል።
በመሆኑም ለሃገራቸው እና ለማህበረሰባቸው ጥሩ ሃሳብ የመሰንዘር ብቃቱም ሆነ ችሎታው ያላቸው ወንድም እና እህቶች ሃሳብ እንዲታፈን ተደርጓል።
በዚህም የተለየ ሃሳብ እና የፖለቲካ አመለካከት እንዳይቀርብ እና ህዝቡ አማራጭ የማግኘት እና የመወሰን መብቱን የመገደብ ጸረ-ዴሞክራሲያዊ የሆነ ድባብ እየተፈጠረ ይገኛል።
7. ምንም እንኳን ለአማራ ህዝብ በሚታገሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በአማራ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎች ላይ መግባባት እንዲፈጥሩ በማድረግ የሚመካከሩበት እና የሚወቃቀሱበት የጋራ መድረክ እንዲፈጥሩ ማድረግ የተቻለ ቢሆንም በእነዚህ ግብ አልባ ስሜታዊ ሃይሎች አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ የተነሳ በፖለቲካ ፓርቲዎቹ መካከል እርስ በርስ መጠራጠር ከመፈጠሩ አልፎ አላስፈላጊ የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል።
8. ግብ አስቀምጦ፤ ደርጅት ፈጥሮ፣ በጽናት እና በዲሲፕሊን መታገል ያቃተው የማህበራዊ ሚድያ ሰራዊት፤ በሆነ ባልሆነው እርስበርስ እየተባላ ለሚፈጠረው ክፍፍል፤ ሌላ አካልን ተጠያቂ ለማድረግ እየሄደበት ያልው ርቅት ጉዳዩን በቅርብ ለምንከታተል ወገኖች አሰተዛዛቢ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪም ነው።
ድርጅት ፈጥረው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ ያሉ ወገኖችን በጸረ አማራነት ፍረጃ ለማሸማቀቅ ይሞከራል። እንደ ድርጅት በውስጥ ማለቅ ያለባቸውን ችግሮች ለአደባባይ ፍጆታ በማዋል የወዳጅም ሆነ የጠላት መሳለቂያ እያደረገን ይገኛል።
9. በሚከተሉት ጠላትን የማብዛት ስትራተጂ በሌሎች የሃገሪቱ ክፍሎች ተሰባጥሮ የሚኖረው የአማራ ማህበረሰብን ለጥቃት ተጋላጭነት እየጨመረ መሆኑ እየታየ ያለበት ወቅት ላይ እንገኛለን።
ይህ ወያኔ የጀመረውን የአማራ ሕዝብ በሽዎች ዘመናት የገነባዉን ከሁሉም ማህበረሰቦች ጋር ድርና ማግ ሁኖ የመኖር እሴቱን በመበጣጠስ አማራን ለብቻው የመነጠል እቅድ ዛሬ የአማራው ልጆች ነን የሚሉ ጥራዝ ነጠቆች ይህን ዓላማ ለማስፈጸም ደፋ ቀና በማለት ላይ ይገኛሉ።
10. በዚህም የተነሳ የአማራ ህዝብ መሰዋትነት የከፈለባችው እና የታገለላቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች ተዘንግተው ከፋፋይ እና አሉታዊ አጀንዳዎች ገነው የህወሀትን ማህበራዊ ሚዲያ ሰራዊት ተግባራት እየከወነ ይገኛል፡፡
እንደ ቅን አሳቢ ዜጋ እና የክልሉ ተወላጅ ሃገርና ህዝብ ወደ ቁልቁለት እየተምዘገዘጉ ዝም ብሎ ማየቱ ከሞራልም ሆነ የታሪክ ተጠያቂነት እንደማያድን በመረዳት ይህን ጥሪ ለማድረግ ተገደናል።
የተከበራቹህ የአማራ ተወላጆች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ድርጅቶች እና የአማራ ወዳጆች በሙሉ፦
ከላይ በዝርዝር ለማስረዳት እንደሞከርነው በአማራ ህዝብ ላይ ከተደቀኑት በርካታ አደጋዎች መካከል መፍትሄ ማግኘት ያለበት ማህበራዊ ሚድያው ሆን ተብሎ አንዳንዴም ባለማወቅ በህዝባችን ህልውና፣ አንድነት፣ አብሮነት እና እድገት ላይ የተከፈተው ዘመቻ ነው።
ስለሆነም ይህን ዘመቻና ሴራ ከስሩ ለማድረቅ የሚከተሉትን ምክረ ሃሳቦች ከአክብሮት ጋር እናቀርባለን፡፡
1. በማህበራዊ ሚድያው የሚለቀቁ መረጃዎችን ለሌሎች ከማጋራታችን (share) ከማድረጋችን በፊት ምንጫቸውን፣ እውነትነታቸውን፣ ለምን አላማ እንደተለቀቁ በሚገባ መመርመርና ማጣራት አለብን፡፡
2. በአማራ ህዝብ ላይ ጥላቻ የሚነዙ፣ ክፍለ አገርን፣ ጎጥን ወይም ሌላን ነገር ሰበብ አድርጎ የህዝባችንን አንድነት የሚቦረቡሩ፤ ከሌሎች ህዝቦች ጋር አብሮነቱን የሚያላሉ መረጃዎችን በምንም መንገድ ከማሰራጨት መቆጠብ አለብን፡፡
3. እኛ የአማራ ልጆች ታሪካዊው የአማራ ህዝብ ባላንጣ የሆነው ህወሃት ያሰማራው የማህበራዊ ሚዲያ ግሪሳ ቀን ከሌሊት በህዝባችን ላይ ጥላቻና ሽብር በመሸረብ ላይ እንደሆነ እና የእኛኑ ስሞች በመጠቀም፣ ለአማራ ሀዝብ ወይም ለአንድ አካባቢ የሚቆረቆሩ በመምስል ወይም የተወሰነ እውነት ላይ በውስጡ የጥላቻ መርዝ ጨምሮ በማሰራጨት አንድነታችንን በመከፋፈል ህልውናችንን እየተፈታተኑ መሆኑን ተገንዝበን በማነኛዉም ሁኔታ ተባባሪ ከመሆን በመቆጠብ ይህን ሴራ ልናከሽፈው ይገባል፡፡
4. በየትኛውም መንገድና መድረክ፣ በየትኛውም ሚዲያ፣ በማህበራዊ ሚድያውም ጭምር በሌሎች ስንጠላው የነበረውን የስድብ፤ የመወራረፍ፣ የጥላቻ ንግግር ባህል በፍጥነት ማቆም እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
ጠላቶቻችን የወረዱበት የሞራል ዝቅጥት ድረስ እኛም መውረድ በጣም አሳፋሪ ነው፤ አማራዊ ባህልና ትውፊትም አይደለም።
5. በተለይ ደግሞ በአንድ ወቅት ከፍታ ላይ የሰቀልናቸውን ጀግኖቻችንን፤ ምሁራኖቻችንን፣ ታዋቂ ሰዎቻችንን በማህበራዊ ሚድያው ማሳጣት፤ መሳደብ፣ ማዋረድ፣ሰድቦ ለሰዳቢ መስጠት፣ ክብራቸውንና ስብናችወን መስበር፤ አንገት ማስደፋት የመሳሰሉትን በአስቸኳይ ማቆም አለብን።
ጀግኖቻችንን አንኳስሰን መሪ እና አውራ አጣን፡፡ አንድነታችንን ተፈታተነው። ጀግና የሚበላ ህዝብ ጀግና ሊወልድ አይችልም።
6. የአማራ ህዝብ ጉዳይ ያገባናል፤ ይመለከተናል የሚሉ የፖለቲካ ድርጅቶችም (ክልላዊ ይሁኑ አገር አቀፋዊ) የቱንም ያህል የሃሳብ ልዩነት ይኑራቸው በማህበራዊ ሚዲያው መዘላለፉን ትትው የውስጥ ጉዳዮቻቸውን የአማራን ህዝብ በሚመጥን መንገድ ተግቢነት ባላችው መድረኮች መደራደር እና መነጋገር መጀመር ይኖርባቸዋል። በፍጹም ሊባክን የሚገባ አንድም አማራዊ አቅም መኖር የለበትም።
7. የፖለቲካ ቡድኖች፤ ማህበራት እና አባላቶቻችውም እንዲሁም መላው የአማራ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎቻቸውን የተመለከቱ ውይይቶችና ክርክሮችን በወሳኝ መልኩ ከማህበራዊ ሚዲያው አውጥቶ ውስጣዊ አንድነቱን ሊያጠናክሩ በሚችሉ እና በእውቀትና በስነ አመክንዮ ለመነጋገር በሚያስችሉ ሌሎች መድረኮች፣ ለምሳሌ በአዳራሽ ስብስባዎች፤ በውይይት ክበቦችና የጥናት ቡድኖች አማካኝነት ማከናወን ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ረገድ በክልሉ ያሉ ዩኒቨርሲቲወችም ደረጃቸውን የጠበቁ ውይይቶችን በማዘጋጀት ወሳኝ ማእከል መሆን ይገባችዋል።
የተከበራችሁ የአማራ ምሁራን የአማራ ህዝብ በዚህ ወቅት የሚገኝበት አስቸጋሪ ሁኔታ የእናንተን ዕውቀት፣ ልምድና ችሎታ በከፍተኛ ሁኔታ ይፈልጋል፡፡
በዚህ መሰረት ባላችሁ እውቀት እና ችሎታ ተጠቅማችሁ ህዝባችን ከተደቀነበት አደጋ ለመውጣት በሚደረገው ጥረት አቅጣጫ በማሳየት የበኩላችሁን ሚና እንድትጫወቱ ጥሪ እናስተላልፍላችኋለን፡፡
በተለይ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ እይታየ ያለውን አደገኛ አዝማሚያ በማስተካከል ረገድ የመሪነቱን ሚና ትወስዱ ዘንድ ወገናዊ ጥሪ እናቀርባለን።
ለተከበራችሁ የአማራ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመሃከላችሁ ካለው አነስተኛ የስልት ልዩነት ባሻገር የአማራን ህዝብ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም መኖሩን በውል እንገነዘባለን፡፡
ይሁን እና የጊዜው ሁኔታ የሚጠይቀው በጋራ በመቆም ይህ ህዝብ ከተደቀነበት አደጋ ለመታደግ በመተጋገዝ እና በመርህ ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ እንደሆነ ለማንም የተሰወረ አይደለም።
ይህን ታሳቢ በማድረግ በአማራ ህዝብ ስም የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በርስ ከመፈራረጅ በመውጣት፤ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ከሚታዩ አላስፈላጊ ቁርቋሶች በመራቅ የአማራውን ህዝብ ስነ ልቦና የሚመጥን አመራር እንዲሰጡ ጥሪ እናስተላለፋለን።
በተጨማሪም በአክቲቪስትነት እና የፓርቲ ፖለቲካ መሃከል ያለውን ልዩነት በቅጡ በመረዳት በመንጋ ከመነዳትና ካላስፈላጊ መፈራረጅ በመራቅ የበኩላችሁን ገንቢ ሚና እንድትጫወቱ ጥሪያችንን በአክብሮት እናቀርባለን።
ለተከበራችሁ የአማራ ወጣቶች ማህበራት እና አባላት፡-
እናንተ ወጣቶች የአማራ ህዝብ የገጠመውን የህልውና አደጋ ለመታደግ እየከፈላችሁት ያለው መስዋዕትነት ግልጽ በሆነ ግብ እና በጠንካራ አመራር ካልታገዘ ስኬታማ ትግል ሊሆን አይችልም።
ስለዚህ ይህን ለውጥ ለማምጣት ያደረጋችሁት ትግል እና የከፈላችሁት መስዋዕትነት ፍሬያማ እንዲሆን ነገሮችን በሰከነ መልኩ በመመልከት አስተዋይነትና ብልህነት በተላበሰ ሁኔታ እንደከዚህ ቀደሙ የትግሉ ሞተር ሆናችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪ እናስተላልፍላችኋለን፡፡
ለተከበራችሁ የማህበራዊ ሚድያ አንቂዎች:_
በአንዳንድ የማህበራዊ ሚድያ አንቂዎች እስከ አሁን ባለው ጊዜ በአላሰፈላጊ መነቃቀፍ እና የመወነጃጀል ፖለቲካ በመጠመዳቸው ብዙ ዕድሎች አምልጠውናል፡፡
ስለሆነም ወቅቱ የሚጠይቀውን የአንድነትና የአብሮነት መንፈስ በመተጋገዝ እና ሃላፊነት የሚሰማው ግቡን ያወቀ የማህበራዊ ሚድያ እንቅስቃሴ በማድረግ ህዝባችንን ከጥፋት ለመታደግ እየተደረገ ባለው ትግል ላይ ገንቢ ሚና በመጫወት ከታሪክ ተወቃሽነት እራሳችሁን ነጻ እንድታወጡ ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባልን።
ለተከበራችሁ የክልሉ መንግስት የስራ ሃላፊዎች:_
በክልሉ እና ከክልሉ ባሻገር የሚኖረው ህዝባችን በተገቢው ሁኔታ ደህንነቱ እንዲጠበቅ፤ ጥቅሙ እንዲከበር በሚደረገው እንቅስቃሴ የበኩላችሁን አስተዋጾ ልትወጡ የሚገባችሁ ሀይሎች ናችሁ ብለን እናምናለን፡፡
ይሁን እና በአመራሩ መካከል የስልጣን ሽኩቻ እና በሶሻል ሚዲያ አሉባልታ መነዳት እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለእናንተ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው።
በመሆኑም በክልሉ የሚኖረው ህዝብ ችግሮች እንዲፈቱ እና በሌሎች ክልሎች የሚኖረው የአማራ ማህበረሰብ መብት እንዲረጋገጥ በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል የበኩላችሁን ሚና እንድትወጡ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ እናስተላልፍላችኋለን፡፡
ከላይ ከጠቀስናቸው ወቅቱን የጥበቀና መርህን የተከተለ አመራር ከመስጠት በተጨማሪም የክልሉ መንግስት የህግ የበላይነትን በሚያስከብርበት ግዜ የዜጎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ትኩረት እንዲሰጠው፤ ሕዝቡን ከውዥንብር ለማዳንም ወቅታዊ መረጃዎችን በአግባቡ ለህዝቡ መስጠት በጣም አስፈላጊዎች ናቸው ብለን እናምናለን።
ለተከበራችሁ የአማራው ህዝብ ታሪካዊ አጋር እና ወንድም ህዝቦች:_
ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር ቆሞ ለበርካታ ሽህ ዘመናት ክፉውን እና ደጉን ሲካፈል የኖረውን የአማራ ህዝብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ሌሎችም ጥቅሞቹን የሚያሳጣ እና የሚያገል ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ የተጠመዱ ፀረ አማራ ሀይሎችን ከወንድማችሁ የአማራ ህዝብ ጎን በመቆም እንድትታገሏቸው ወንድማዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
ፍትህ፤ ዴሞክራሲ፤ እኩልነት፤ ወንድማማችነት!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
የስም ዝርዝር
1. አቶ ማሙሸት አማረ፡-
የቅንጅትና መኢአድ ከፍተኛ አመራር፣ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የህሊና እስረኛ፣ “የተጋረደው ጀግንነት” መጽሀፍ ጸሀፊ፣ የወቅቱ የመኢአድ ፕሬዚዳንት
2. አቶ አግባው ሰጠኝ
በቀድሞ ፓርላማ የቅንጅት ተወካይ የፓርላማ አባል፣የቅንጅትና የሰማያዊ ፓርቲ የሰሜን ጎንደር ተጠሪ፣የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የህሊና እስረኛና የሰብዓዊ መብት ታጋይ
3. ዶ/ር ንጉስ ደመላሽ
የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር፣ የሰብዓዊ መብት ታጋይና ማህበራዊ አንቂ
4. ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ አስራደ
በወያኔ ዘመን የፖለቲካ እስረኛ የነበረ፣ አሁን የትጉህ ማህበር ሊቀመንበር (በወያኔ ዘመን በዱር ገደሉ የነበሩ ታጋዮችና በወያኔ ስርዓት ከፍተኛ በደል የተፈፀመባቸው የግፍ ሰለባዎች ያቋቋሙት ማህበር)፣ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ
5. ረዳት ፕሮፌሰር ሞላ አባቡ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ማህበር ምክትል ሊቀመንበር የነበረ፣
6. ረዳት ፕሮፌሰር እውነቴ አማረ
የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝና ማህበራዊ አንቂ ፤ የከፍተኛ ትምህርት መምህር እና የሶስተኛ ዲግሪ ተመራማሪ
7. መምህር መኳንንት ወንዴ በወያኔ ዘመን የፖለቲካ እስረኛ የነበረ፣ የሰብዓዊ መብት ታጋይና ማህበራዊ አንቂ
8. አቶ አብርሀም ጌቱ
በወያኔ ዘመን የፖለቲካ እስረኛ የነበረ፣ አሁን የመኢአድ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትና የውጭ ጉዳይ ሀላፊ
9. አቶ ዘመነ ምህረት
በወያኔ ዘመን የፖለቲካ እስረኛ የነበረ፣ በወያኔ ዘመን በዱር በገደል ታጋይ የነበረ ፋኖና አስተባባሪ፣ በአሁኑ ሰዓት የመኢአድ የምክር ቤት አባልና የሰሜን ቀጠና ተጠሪ
10. አቶ አስከብር ገብሩ ፡-
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ንቅናቄ መሪ፣ በዩኒቨርስቲ የኢዴፓ አመራር፣ በወያኔ ዘመን የህሊና አስረኛ፣ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ
11. አቶ አንተነህ ሙሉጌታ፡-
በ97 ምርጫ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ተመራጭ ዋና ጸሀፊ፣ የቅንጅት ከፍተኛ አመራር፣ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የህሊና እስረኛ፣ “የተዋረደው ፍርድ ቤት” መጽሀፍ ጸሀፊ፣ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ
12. አቶ መስፍን አማን
የመኢአድና ቅንጅት አመራር፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ንቅናቄ መሪ፣ በወያኔ ዘመን የህሊና እስረኛ፣ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ
13. አቶ ይርጋለም ታደሰ
የሰብዓዊ መብት ታጋይና ማህበራዊ አንቂ
14. አቶ ያረጋል ይማም እምሩ፡-
በእነ ጀነራል ተፈራ ማሞ በተመራው መፈንቅለ መንግስት አስተባባሪ፣ የአማራ ብሄርተኝነት መሪ ፖለቲከኛ፣ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ
15. አቶ ኃይለመለኮት መኮነን
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ማህበር አመራር የነበረ፣ የሰብዓዊ መብት ታጋይና ማህበራዊ አንቂ
16. ወ/ት አምሳለ ማህቶት
የአለማያ ዩኒቨርስቲ የተማሪዎች ንቅናቄ መሪ የነበረች፣ የሰብዓዊ መብት ታጋይና ማህበራዊ አንቂ
17. አቶ ሞላ ሙሉጌታ
የአማራ ብሄርተኝነት መሪ ፖለቲከኛ፣ የሰብዓዊ መብት ታጋይና ማህበራዊ አንቂ
18. አቶ አዱኛው ዘላለም
በምርጫ 97 በአዲስ አበባ የቅንጅት የፓርላማ ተመራጭ፣ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝና ማህበራዊ አንቂ
19. አቶ ሄኖክ አበበ
የሕግና ፍትሕ ተመራማሪ፣ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ፣ ማህበራዊ አንቂ
20. ጋዜጠኛ ምናላቸው ስማቸው
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና ኢሳት ጋዜጠኛ የነበረ እና በአሁኑ ወቅት የኢትዮ 360 ቲቪ ዋና ስራ አስኪያጅ