09/01/2022
ከ473 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት በህገ-ወጥ መንገድ ያስተላለፉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ክስ ተመሰረተባቸው
አሶሳ፤ ጥር 1 ቀን 2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ 473 ሺህ 504 ካሬ ሜትር የኢንቨስትመንት ቦታ በህገ-ወጥ መንገድ በማስተላለፍ የተጠረጠሩ 10 ግለሰቦች በቁጥጥር ውለው ክስ እንደተመሰረተባቸው ተገለጸ።
ድርጊቱን የፈጸሙ የግልገል በለስ ከተማ ከንቲባ፣ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ሃላፊ፣ ሶስት መሃንዲች፣ ሁለት ደላሎች፣ አንድ የማተሚያ ቤት ድርጅት ባለቤት እና ሁለት የኮምፒዩተር ቤት ባለቤቶች የሆኑ 10 ግለሰቦች ሰሞኑን በቁጥጥር ስር ውለው ክስ እንደተመሰረተባቸውም ተገልጿል፡፡
ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው በተነገረው የመሬት ወረራ የግልገል በለስ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ በጉዳዩ የተጠረጠሩ 10 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ክስ እንደተመሰረተባቸው የክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ህግና ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቀዋል።
የክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ምክትል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አቶ ብርሃኑ አየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ ህገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለማስቆም ቡድን ተደራጅቶ ለሶስት ተከታታይ ወራት ጥናት አካሂዷል፡፡
በጥናቱ ላይ ከክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ህግ፣ ፖሊስ ኮሚሽንና ስራና ከተማ ልማት የተውጣጡ አካላት መሳተፋቸውን ጠቁመዋል፡፡
ቡድኑ ባደረገው ምርመራ በግልገልበለስ ከተማ 473 ሺህ 504 ካሬ ሜትር ቦታ የሊዝ አዋጅን በሚቃረን መንገድ ለግለሰቦች ተላልፎ መሰጠቱን ማረጋገጡን አስታውቀዋል።
ለግለሰቦች በህገ-ወጥ መንገድ ተላልፎ የተሰጠው መሬት የክልሉ መንግስት በስፍራው ለሚገኙ ግለሰቦች 17 ሚሊዮን ብር ካሳ ከፍሎ ለኢንቨስትመንት ያዘጋጀው መሬት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ግለሰቦቹ መሬቱን በህገ-ወጥ መንገድ ያስተላለፉት ለኢንቨስትመንት ምትክ ቦታ እና ሰነድ አልባ ይዞታ ማረጋጫ በሚል እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ብርሃኑ የቀበሌ መሬት አጣሪ ኮሚሽን በሚል ሃሰተኛ ኮሚቴ እና በተጭበረበረ ማሀተም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ድርጊቱን የፈጸሙ የግልገል በለስ ከተማ ከንቲባ፣ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ሃላፊ፣ ሶስት መሃንዲች፣ ሁለት ደላሎች፣ አንድ የማተሚያ ቤት ድርጅት ባለቤት እና ሁለት የኮምፒዩተር ቤት ባለቤቶች የሆኑ 10 ግለሰቦች ሰሞኑን በቁጥጥር ስር ውለው ክስ እንደተመሰረተባቸው አስታውቀዋል፡፡
ግለሰቦቹ በህገ-ወጥ መንገድ ያስተላለፉት 473 ሺ 504 ካሬ ሜትር ቦታ በአሁኑ ወቅት ወደ ህጋዊ የመሬት ባንክ መግባቱን አቶ ብርሃኑ ጠቅሰዋል፡፡
የምርመራ ቡድኑ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል የህዝብ እና የመንግስት ሃብት ለማስመለስ ያደረገው ጥረት እንዲሳካ የክልሉ መንግስት በቁርጠኝነት እየደገፈ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ያደረገውን እገዛ የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ አቃቢ ህጉ የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪ መረጃ በመስጠት ያሳየውን አጋርነት አድንቀዋል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ሃላፊ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ እዝ አባል ኮማንደር አምሳሉ ኢረና በበኩላቸው በግልገልበለስ ከተማ የተፈጸመው ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ የመተከል ዞንን ሠላም ሲያውክ ከነበረው አሸባሪው ህወሃት ጋር ግንኙነት እንዳለው አስረድተዋል፡፡
በግለሰቦቹ ላይ ምርመራ ከተጀመረ በኋላ የአካባቢው ጸጥታ እንዳይረጋጋ በማድረግ የምርመራውን ሂደት ለማደናቀፍ ተደጋጋሚ ሙከራ መደረጉን ሃላፊው ጠቅሰዋል፡፡
በ1990 ዓ.ም እንደተመሰረተች የሚነገርላት የግልገል በለስ ከተማ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በ150 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡
ወደ ህዳሴው ግድብ ዋነኛ መተላለፊያ የሆነችው ከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ የንግድ እንቅስቃሴዋ እና የከተማው ህዝብ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
The Ethiopian News Agency dispatches text news, and audio and video stories about local and international events to media enterprises and the public.