02/05/2020
ከኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው 2,516 ሰዎች ተለይተው
ክትትል እየተደረገላቸው ነው-የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
**************
ኮሮናቫይረስ በሀገራችን ከመጋቢት 03 ቀን 2012 ዓ.ም ይፋ ከተደረገበት ጀምሮ
እስከ ዛሬ ድረስ በኮሮና ቫይረስ መታመማቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር የቅርብ
ንክኪ የነበራቸው 2,516 ሰዎች ተለይተዋል ሲል የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና
ኢንስትቲዩት ገለጸ።
ከእነዚህ መካከል 1,953 ሰዎች ክትትላቸውን አጠናቅቀው ወደ ኅብረተሰቡ
እንዲቀላቀሉ የተደረጉ ሲሆን፣ 521 ሰዎች ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛሉ
ብሏል።
በሀገራችን እስካሁን በቫይረሱ መታመማቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ውስጥ 42ቱ
(31%) የቅርብ ንክኪ የነበራቸው ሰዎች መሆናቸው ተረጋግጧል ሲል ገልጿል።
በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ
ማስተባበሪያ ማእከል የኮቪድ-19 ቅድመ ዝግጅት እና ምላሽ የቅኝት ክፍል
አስተባባሪ አቶ መስፍን ወሰን፣ አንድ ሰው ከበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ
ንክኪ አለው ሲባል በኮሮናቫይረስ የታመመ ሰው ምልክቱን ማሳየት ከመጀመሩ
ሁለት ቀናት በፊት በአንድ ሜትር ርቀት ውስጥ ሆኖ ከ15 ደቂቃ በላይ ቆይታ
ሲኖራቸው ሲሆን፣ በተጨማሪም የግል የጤና መከላከያ መሣሪያዎችን
ሳይጠቀሙ በበሽታው የተያዘን ሰው እንክብካቤ ሲያደርጉ ነው ብለዋል።
በዚህም መሠረት በበሽታው መታመማቸው ከተረጋገጡ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ
የነበራቸውን ሰዎች በመለየት በጤና ባለሞያዎች ለ14 ቀናት ክትትል
እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል። በመሆኑም የቅርብ ንክኪ የነበራቸውን ሰዎችን
በመለየት ክትትል ማድረጉ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል እና ወረርሽኙም
እንዳይስፋፉ እገዛ አድርጓል ብለዋል።
በሀገራችን ማኅበራዊ ግንኙነታችንና የአኗኗር ባሕላችን የጠነከረ በመሆኑ፣ አንድ
በቫይረሱ የታመመ ሰው መታመሙ በሕክምና እስከሚረጋገጥ ድረስ ከሰዎች ጋር
ከሚኖረው ንክኪ በተጨማሪ የሚጠቀምባቸው መገልገያዎች ሌሎችም
ሊጠቀሙበት ስለሚችሉ ቫይረሱ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው እንዲተላለፍ
ያስችለዋል በማለት ተናግረዋል።
ኅብረተሰቡ በሽታው በቀላሉ የሚተላለፍ በመሆኑ ሳይዘናጋ የሚተላለፉ
መልእክቶችንና መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ የበሽታውን ምልክት
የሚሳዩ ሰዎች በሚያገኝበትም ወቅት በተዘረጉ የነፃ የስልክ መስመሮች
በመደወል እንዲያሳውቅ እና የበሽታውን ስርጭት በመቆጣጠር በኩል
የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
በተጨማሪም ለተለያዩ ጉዳዮች በአንድ ቦታ መሰባሰብን በማስወገድ፣ እጅን
አዘውትሮ በመታጠብ፣ በመተው፣ ሰዎች በሚሰበሰቡበት ቦታዎች ላይ የአፍንና
የአፍንጫ መሸፈኛ በማድረግ፣ በአካል ንክኪ የሚደረግ ሰላምታን በመተው እና
አካላዊ መራራቅን ተግባራዊ በማድረግ የበሽታውን ስርጭት እንዲከላከል ጥሪ
አቅርበዋል።
ለተጨማሪ መረጃ በስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 በመደወል ወይም
በኢ-ሜይል አድራሻችን [email protected] በመጠቀም ወይም ባሉበት
ክልል በተዘጋጁ ነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል ሪፖርት እንዲያደርጉ ወይም
በአካባቢው ለሚገኙ ጤና ተቋማት በስልክ እንዲያሳውቁ ኢንስቲትዩቱ ጠይቋል።