27/04/2023
የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል እና የፓርቲው የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ ተገደሉ።
እስካሁን ባለው መረጃ ሌሎች 4 ሰዎችም መገደላቸው ተሰምቷል።
በአቶ ግርማ የሺጥላ፣በቤተሰቦቻቸው እና ጠባቂዎቻቸው ላይ ጥቃት የተፈፀመው በዛሬው ዕለት ሚያዝያ 19፣2015 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ መሆኑን የአማራ ክልላዊ መንግስት ተናግሯል።
አቶ ግርማ የተገደሉት "የመንግሥትና የድርጅት ሥራዎችን በሰሜን ሸዋ ዞን ሠርተው ከመሀል ሜዳ ወደ ደብረ ብርሀን ሲመለሱ ልዩ ቦታው መንዝ ጓሳ አካባቢ በታጠቁ ፅንፈኛ ሃይሎች በደረሰባቸው ጥቃት "መሆኑን የክልሉ መንግስት መግለጫ አስረድቷል።
ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ በአቶ ግርማ የሺጥላ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ፅፈዋል።
"ሐሳብን በሐሳብ ማሸነፍ ያቃታቸው አካላት የወንድማችንን የግርማ የሺጥላን ነፍስ ነጥቀዋል"ብለዋል።
"ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ መፍታት ባህል በሆነበት ክፍለ ዘመን፣ በሐሳብ የተለየንን ሁሉ በጠመንጃ ለማሳመን መነሣት የጽንፈኝነት የመጨረሻው ጥግ ነው"ሲሉም አክለዋል።
አቶ ግርማ ተወልዶው ባደገበት አካባቢ መገደላቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገዳዮቹ " ከእኛ የተለየ ሐሳብ ማሰብ አልነበረበትም ብለው የሚያምኑ ነውጠኛ ጽንፈኞች "ናቸው ብለዋል።
ተግባሩንም "አስነዋሪና አሰቃቂ "ሲሉ ገልፀውታል።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም የተሰማውን ሀዘን ገልጿል።
ገዳዮቹን "ፅንፈኛ ሀይሎች" ሲል የገለፃቸው የክልሉ መግለጫ በሀሳብ ትግል ማሽነፍ ያልቻሉትን በኀይል ለማስፈፀም ያደረሱት ጥቃት ዓላማውን ማሳካት የማይችልና ጊዜው ያለፈበት፣ ዘመኑን ያልዋጀ የጥፋት መንገድ ስለሆነ አምርረን የምንታገለው ተግባር ነው" ሲል ተናግሯል።
መንግስት በክልሉ ውስጥ የሚፈጽሙትን ስርዓት አልበኝነትና የሽብር ድርጊት ለመከላከል፤ ለመቆጣጠርና ሕግ ለማስከበር እርምጃ ይወስዳል ብሏል።
የጥቃቱን አድራሾችም ለሕግ ያቀርባል ሲል መግለጫው አስረድቷል፡፡
የክልሉ ሕዝብ የተፈጠረውን የሽብር ድርጊት ከማውገዝ ጀምሮ ወንጀለኞች ለሕግ ቀርበው ፍትህ እንዲረጋገጥ፣ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግና እንዲረጋጋ የክልሉ መግንስት ጥሪ አቅርቧል ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግላጫ የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጸ/ቤት ኃላፊ እና የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ግርማ የሺጥላ" ባደገበት ቀዬ በጽንፈኞች በግፍ ተገድሏል"ብሏል።
ግድያውን "ነውረኛ እና ዘግናኝ ተግባር"ሲል የገለፀው የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ ፈፃሚዎቹ የትም ቢገቡ ለሕግ ይቀርባሉ ብሏል።
የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች በአቶ ግርማ የሺጥላ ህልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገልፀዋል።