23/09/2023
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
ወላይታ ሶዶ፦መስከረም 11/2016 ዓ.ም የመስቀል በአል ሀይማኖታዊ በዓል ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ይህን በዓል የባህላቸው፣ የትውፊታቸው፣ የማኅበራዊ ዕሴቶቻቸው አካል አድርገው ነው የሚያከብሩት፡፡
የህብረ ብሔራዊነት ተምሳሌት በሆነው ክልላችን በመስቀል ዋዜማ የሚከበረው የዘመን መለወጫ በዓል እንደየ አካባቢው ባህልና ወግ ሲከበር የተለየ ድባብ ይፈጥራል።
በሁሉም አካባቢዎች የሰላም፣ የአብሮነት፣ የመተሳሰብ እሴታችን የሚንጸባረቅበት አውድ ሲሆን በጋሞ፣ በወላይታ፣ በጎፋ እና በኦይዳ ብሔረሰቦች ደግሞ የዘመን መለወጫ በዓል በድምቀት ይከበራል።
በዘመን መለወጫ በአሉ የተራራቁ ወዳጅ ዘመዳሞች በናፍቆት የሚገናኙበት የቤተሰብ አባላት በአዲሱ ዓመት አዲስ እቅድ የሚያወጡበት እና ለላቀ ስኬታ የሚተጉበት ወቅት ነው።
በክልሉ የበዓሉ አከባበር ከመስከረም 12 ቀን ጀምሮ ሲሆን በጋሞ ዮ-ማስቃላ፣ በዎላይታ ዮዮ ጊፋታ፣ በጎፋ ጋዜ ማስቃላ እና በኦይዳ ዮኦ ማስቃላ እየተባለ በዓሉን በልዩ ልዩ ሁነቶች በማክበር የተለየ ስሜት እንዲፈጠር ይደረጋል ለዚህ ነው ተናፋቂ በዓል እንዲሆን ያደረገው።
በዓሉ አዲሱን አመት ተከትሎ የሚከበር በመሆኑ የክልሉ መንግሥት በአዲስ መንፈስ እና በአዲስ አስተሳሰብ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግቶ ይሰራል።
መንግስት የክልላችንን ህዝብ የአደረጃጀት ጥያቄ መልሶ በደማቅ ሁነታ የክልሉን መንግስት ምስረታ አካሂደን ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት በሙሉ አቅም ወደ ልማት ስራ በገባንበት ብሎም ለላቀ ውጤት እየተጋን ባለንበት ወቅት የበዓሉ መከበር ከወትሮው የተለየ ያደርገዋል።
የተጀመረው የእድገት እና የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን ያሉንን ጸጋዎች በመጠቀም መስራት አብይ ትኩረታችን ይሆናል።
በአልን ስናከብር በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያቶች የተጎዱ ወገኖቻችንን መደገፍ መንከባከብ እና ከጎናቸው መሆን ከበዓሉ ቱሩፋቶች ውስጥ አንዱ ሊሆን ይገባል።
ለመላው የሀገራችን እና የክልላችን ህዝብ በዓሉ የሰላም፣የፍቅር፣የአብሮነትና የመተሳሰብ እንዲሆን እመኛለሁ !!
ዩ-ማስቃላ!!
ዮዮ ጊፋታ!!
ጋዜ ማስቃላ!!
ዮኦ ማስቃላ!!