18/05/2023
"ዘላቂና አስተማማኝ ሠላምን ለማረጋገጥ የኃይማኖት ተቋማት ሚና የጎላ ነው!" የጠበላ ከተማ አስ/ር ከንቲባ አቶ ዮሐንስ ቡናሮ
የጠበላ ከተማ አስ/ር የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሠራርና አደረጃጀት እና የኃይማኖት ነክ መልካም አስተዳደር ጉዳዮች እንዲሁም የከተማ አስተዳደር ሠላምና ፀጥታ ጉዳይ ዙሪያ የጋራ የውይይትና የምክክር መድረክ አካሄዱ።
የጠበላ ከተማ አስ/ር ፀላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ወቅታዊ የፀጥታ ነባራዊ ሁኔታ፣ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሠራርና አደረጃጀት እና የኃይማኖት ነክ መልካም አስተዳደር ጉዳዮችም እና በቀጣይ በቅንጅት መስራት ስለሚገባቸው ስራዎችን በተመለከተ የፀጥታ ስራዎች ማስፈፀሚያ ሰነድ ቀርቦ ከተሳታፊዎች ጋር ዉይይት ተደርጓል።
የሀይማኖት ተቋማት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ፣ የመቻቻል እና የአብሮነት እሴቶች እንዲጎለብቱ በማድረግ የአከባቢያችን ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን የጠበላ ከተማ አስ/ር ከንቲባ አቶ ዮሐንስ ቡናሮ ገልፀዋል።
አያይዘውም ሀይማኖቶች የተመሰረቱበት ዋና ዓላማ ሰላም በመሆኑ ለሰላም መረጋገጥ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የማድረግ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባልም ብለዋል፡፡
አቶ ዮሐንስ ቡናሮ አክለው ከተማውን ማልማት እና ማሳደግ ለከተማ አስተዳደር ብቻ የሚተው አይደለም ቤተ-እምነቶች በሰብዓዊ ድጋፍን ጨምሮ በአረንጓዴ አሻራ እና በሌሎች የልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ የበኩላቸውን አስተውጾ ማበርከት አለባቸው።
ከተማ አስተዳደሩ የጀመራቸው የልማትና መልካም አስተዳደር ሥራዎች በአስተዳደሩ ጥረት ብቻ ማሳካት ስለማይቻል የኃይማኖት ተቋማት የድርሻቸውን እንዲወጡ ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል።
የጠበላ ከተማ አስ/ር ሠላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ ሻ/ም ለማ ቂልታ በበኩላቸው የከተማችንን ሰላም መጠበቅ ወሳኝ እንደሆነ በመገንዘብ ይህንን ሰላም በማስቀጠል ሁሉም ሃይማኖቶች በጋራ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ሻ/ም ለማ ቂልታ አክለው የከተማችንን ሰላም በዘላቂነት ከማስጠበቅ አንጻር ሁሉም የራሱን ድርሻ ሊወጣ ይገባል በማለት ሃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ሠላምን በመሰበክና ስነምግባርን በማስተማር ሁሉም ሚናውን በተገቢው መወጣት ይገባል ብለዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት በሚደረገው ርብርብ የሃይማኖት ተቋማት ሚና የጎላ በመሆኑ ይህ የሰላምና የጋራ የውይይት መድረክ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል በማለት የሃይማኖት ተቋማት የጋራ ፎረም ሰብሳቢ አቶ አክሊሉ ሳሙኤል ገልፀዋል ፡፡
አቶ አክሊሉ ሳሙኤል አክለው የሃይማኖት ተቋማት ትውልዱን ከማነፅ ባለፈ ማህበረሰባዊ ትስስራችንንና ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ለማጠናከር ስነምግባርንና ግብረ ገብነትን በማስተማር ረገድ ሰፊ ስራ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የኃይማኖት ተቋማት በቀጣይም ሀገራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩና ትውልድን በስነ-ምግባር በሚያንፁ ስራዎች ላይ አተኩረው እንደሚሰሩ ገልፀዋል።
በመድረኩ ከየሃይማኖት ተቋማት የመጡ የእምነት አባቶች፣ ከዞን ሃይማኖት ተቋመት ተወክለው የመጡ የሃይማኖት አባቶች፣ ከዞን ሠላሞና ፀጥታ መምሪያ የተወከሉ አካላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።